በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለምግብ የሚሆኑ አትክልቶች በጓሮህ አልማ

ለምግብ የሚሆኑ አትክልቶች በጓሮህ አልማ

ለምግብ የሚሆኑ አትክልቶች በጓሮህ አልማ

ማዕከላዊ አፍሪካ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

በብዙ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች ቤተሰቦቻቸውን እንዴት መመገብ እንደሚችሉ በየዕለቱ ይጨነቃሉ። ተራ የሆኑት አትክልቶች እንኳ ዋጋቸው እያሻቀበ በመምጣቱ ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ምግብ ማቅረብ በጣም ተፈታታኝ ሆኖባቸዋል። ሆኖም አንዳንዶች በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ ቀላል የሚባል መፍትሔ አግኝተዋል። ለራሳቸው ቀለብ የሚሆን አትክልት በማብቀል ችግራቸውን መቅረፍ ችለዋል።

አንተም በጓሮህ አትክልት በማብቀል ይህን መሞከር ትፈልግ ይሆናል። የመኖሪያህ ቅጥር ግቢ ያን ያህል ሰፊ ላይሆን ይችላል። ሆኖም በሠፈርህ ልታለማው የምትችለው መሬት ማግኘት ትችል ይሆናል። ጣፋጭና ለጤና ተስማሚ የሆነ አትክልት ራስህ ብታመርት ምን ያህል ገንዘብ መቆጠብ እንደምትችል አስብ። እንዲያውም አትክልተኛ መሆንህ ሰውነትህ የሚያስፈልገውን እንቅስቃሴ እንዲያገኝ ሊረዳው ይችላል። መላው ቤተሰብህም በሥራው ላይ የሚካፈል ከሆነ ልጆችህ የሚውሉበት አስደሳች ቦታ አገኙ ማለት ነው። አትክልት ከማልማት ትምህርት መቅሰምም ይቻላል። እንደ ትዕግሥት ያሉ ባሕርያትን እንድታዳብር ይረዳሃል። (ያዕቆብ 5:7) በተጨማሪም አትክልቶች ሲያድጉ መመልከት የመልካም ነገሮች ሁሉ ፈጣሪ ወደሆነው አምላክ እንድትቀርብ ሊያደርግህ ይችላል።—መዝሙር 104:14

የጓሮ አትክልት ማልማት ምንም ጥረት የማይጠይቅ ወይም ወዲያው ምርት የሚያስገኝ መስክ እንደሆነ አድርገህም ማሰብ አይኖርብህም። ቢሆንም ቆራጥ በመሆንና መጠነኛ እውቀት በማዳበር ጥረትህ ሊሳካልህ ይችላል!

ኑሮውን ያሸነፈ ቤተሰብ

ለአብነት ያህል ከሁለት ልጆቻቸው ጋር የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክ ዋና ከተማ በሆነችው በባንጉዊ የሚኖሩትን ቲሞቴ እና ሉሲ የተባሉ ክርስቲያን ባልና ሚስት እንውሰድ። በሚያገኟት አነስተኛ ገቢ ላይ የጓሮ አትክልት ቢኖራቸው ቤተሰባቸውን ጥሩ አድርገው መመገብ እንደሚችሉ ተገነዘቡ።

ሉሲ የ13 ዓመት ልጅ ሳለች አንዲት ትንሽ የአትክልት ቦታ ነበራት። ከትምህርት ቤት ስትመለስ እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ አትክልቷን ትንከባከብ ነበር። አትክልቱ ሲያድግላት በጣም ትደሰት ነበር። ትዳር ከያዘች በኋላ የጓሮ አትክልት ማልማት እንደምትችል ትዝ ያላት ግን ብዙ ዓመታት ካለፉ በኋላ ነበር። በሚኖሩበት አካባቢ ቆሻሻ የሚጣልበት መሬት ስለነበር ይህን ቦታ ለመጠቀም ዝግጅት አደረገች። ሉሲ መሬቱ ለአትክልት ምቹ ሊሆን እንደሚችል ተገነዘበች። በዚህ ቦታ ላይ ይጣል የነበረው ቆሻሻ መሬቱን ከማበላሸት ይልቅ ለዓመታት ተብላልቶ አትክልት ለማልማት የሚያስችል ለም አፈር እንዲኖረው አድርጓል። ሉሲ እና ቲሞቴ ያንን መሬት ውብ የአትክልት ቦታ ሊያደርጉት ወሰኑ።

ሥራውን መጀመር

በመጀመሪያ ግን ጥቂት ምርምር ማድረግ ፈለጉ። ስለ አትክልት የሚያውቁ ሰዎችን አነጋገሩና ምክራቸውን በጥሞና አዳመጡ። መሬቱን ለማልማት የመስኖ ውኃ የግድ መጠቀም እንዳለባቸው ስለተገነዘቡ ጉድጓድ ቆፍረው ውኃ እንዴት ማግኘት እንደሚችሉም ተማሩ። ስለ አትክልተኝነት የተጻፉ መጻሕፍትን ማንበባቸውም ጥቅም አስገኝቶላቸዋል።

በተክሎች መካከል ስላለው ዝምድና የሚገልጹ ጽሑፎችን በማንበባቸው አንዳንድ ተክሎች ለማደግ የሌላ ተክል እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው አወቁ። አንዳንድ ተክሎች ደግሞ ለሌሎች ተክሎች እድገት ፀር ናቸው። ካሮትና ቲማቲም በአንድ እርሻ ላይ አብረው ቢተከሉ ጥሩ እንደሚሆን አንዳንድ ሰዎች ይናገራሉ። እንደዚሁም የሾርባ ቅጠልና የአበባ ጎመን አንድ ላይ ቢተከሉ ለሁለቱም ጠቃሚ ነው። ድንብላልም የአተር፣ የኩከምበር፣ የሰላጣና የሽንኩርት “ወዳጅ” ነው። ይሁን እንጂ ሰላጣና የስጎ ቅጠል አብረው አይሄዱም። ሽንኩርትም ባቄላንና አተርን ይጎዳል። ተክሎች እርስ በርሳቸው የሚጎዳዱ ከሆነ ይዳከሙና በበሽታና በጎጂ ነፍሳት በቀላሉ ይጠቃሉ።

ቲሞቴ እና ሉሲ በትንሽ መሬታቸው ላይ አንድ ዓይነት ተክል ብቻ መትከል ጥሩ እንዳልሆነም ተገነዘቡ። ተክላቸው በነፍሳት ወይም በበሽታ ከተጠቃ ሁሉንም ነገር አጡ ማለት ነው። በደንብ የተመረጡ የተለያዩ ተክሎችን መትከል ግን እንዲህ ዓይነቱን ችግር በእጅጉ ለመቀነስ ይረዳል። ቅጠላ ቅጠሎችና አበቦች ለጓሮ አትክልታቸው ቀለምና ውበት ስለሚጨምሩ ንቦችንና ለተክሎቹ ጤንነት የሚረዱ ሌሎች ጠቃሚ ነፍሳትን ይስባሉ።

በተጨማሪም ባልና ሚስቱ መርዛማ ኬሚካሎችን በሰብሎቻቸው ላይ ከመርጨት የሚቆጠቡበትን መንገድ አወቁ። ነጭ ሽንኩርት መትከል አትክልታቸውን ከአንዳንድ በሽታዎች ሊጠብቅ እንደሚችል ተማሩ። *

ቲሞቴ እና ሉሲ ጥረትና ትዕግሥት ቢጠይቅባቸውም ዛሬ ያማረ አትክልት ሊኖራቸው ችሏል። በመሬታቸው ላይ ጥቅል ጎመን፣ ፐርሰሜሎ፣ ካሮት፣ ኩከምበርና ደበርጃን የሚያበቅሉ ሲሆን አንዳንድ ጊዜም ከቤተሰባቸው ፍጆታ በላይ ያመርታሉ።

አንተም በጓሮህ አትክልት አልማ!

በጓሮ አትክልት ማልማት ጠቃሚ መሆኑን የተገነዘቡት አፍሪካውያን ብቻ አይደሉም። ለምሳሌ ያህል በጀርመን በከተሞች ጫፍ የሚለሙ ከሚሊዮን የሚበልጡ የአትክልት ቦታዎች አሉ። በጀርመኑ የተክሎች ተመራማሪ በዳንኤል ቮን ሽሬበር ስም የተሰየሙት ሽሬበርጋርተን እየተባሉ የሚጠሩት እነዚህ የአትክልት ቦታዎች እያንዳንዳቸው ከ200 እስከ 400 ካሬ ሜትር የሚደርስ ስፋት ያላቸው ሲሆን ለከተማው ነዋሪዎች ይከራያሉ። አንድ ተመራማሪ እንዳሉት እነዚህ ትናንሽ የአትክልት ቦታዎች “የተፈጥሮ ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን ለማምረት ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።” የአትክልት ቦታዎቹ የምግብ ምንጭ ከመሆናቸውም በላይ ለባለቤቶቻቸው እንደ “ገነት” ያለ የመዝናኛ ሥፍራ ሆነው ያገለግላሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ በቅርቡ መላዋ ምድር ቃል በቃል የአትክልት ስፍራ ወይም ገነት እንደምትሆን ተስፋ ይሰጣል። (ሉቃስ 23:43) እስከዚያው ድረስ ግን አንተም ጓሮህን በማልማት ለምግብ የሚሆንህን አትክልት ማብቀል ትችል ይሆናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.13 በተክሎች ላይ በሽታ ማጥፊያ ኬሚካል መርጨት ሳያስፈልግ አትክልትን ከበሽታ እንዴት መጠበቅ እንደሚቻል ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት “በተፈጥሯዊ ዘዴዎች አትክልት ማልማት” የሚለውን በሰኔ 2002 የወጣውን የንቁ! እትም ተመልከት።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቲሞቴ እና ሉሲ ለአትክልታቸው ውኃ ሲቀዱ

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጀርመን፣ ሙኒክ ለሕዝብ የተከፋፈለው የአትክልት ሥፍራ