በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክን በስም ልታውቀው የምትችለው እንዴት ነው?

አምላክን በስም ልታውቀው የምትችለው እንዴት ነው?

አምላክን በስም ልታውቀው የምትችለው እንዴት ነው?

አንዲት የጋዜጣ አምድ አዘጋጅ ከአንድ አንባቢ የሚከተለው ደብዳቤ ደረሳት:- “ሕይወቴን በሙሉ ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ስጥር ኖሬያለሁ። እናንተ መልስ እንደምትሰጡኝ ተስፋ አደርጋለሁ። የአምላክ ስም ማነው? አይሁዳውያን ትክክለኛው ስም በዘመናት ሂደት ውስጥ ጠፍቶ ቀርቷል ይላሉ። ክርስቲያኖች ኢየሱስ ይሉታል። ሙስሊሞች አላህ ብለው ይጠሩታል። . . . ታዲያ ትክክለኛ ስሙ ማነው?” ጋዜጣው ጥያቄውን ከነመልሱ አትሞ አውጥቷል። እንዲህ ይላል:- “በጥንታዊው የዕብራውያን ትምህርት መሠረት አምላክ ሁሉን ቻይ ነው። ስለሆነም በማንኛውም አንድ ስም ሊወሰን አይችልም። ይሁን እንጂ እርሱ (ወይም እርሷ) በማንኛውም ስም በአክብሮት እስከጠራኸው/ሃት ድረስ ይመልስልሃል (ወይም ትመልስልሃለች።)”

ዛሬ በአምላክ ስም ረገድ ይህን የመሰለ የግድየለሽነትና የደንታቢስነት ዝንባሌ መስማት ያልተለመደ ነገር አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ከሚያምኑ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ሃይማኖታዊ ዝንባሌ ቢኖራቸውም ለአምላክ ስም ትልቅ ቦታ አይሰጡም። ይሁን እንጂ አምላክ ምን ይሰማዋል? ለእርሱ የስሙ ጉዳይ ከዚህ ግባ የማይባል ቀላል ነገር ነው?

ተራ ነገር አይደለም

መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ የሚለውን የአምላክ የግል ስም በሺህ ለሚቆጠሩ ጊዜያት እንደሚጠቅስ ልብ በል። በአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ውስጥ መለኮታዊው ስም 7,210 ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። * የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ስሙን ይህን ያህል ጊዜ እንዲጠቀሙና ጎላ ያለ ቦታ እንዲሰጡት በመንፈሱ የገፋፋቸው አምላክ ራሱ ነው። ከእነዚህ ጸሐፊዎች አንዱ የሆነው መዝሙራዊው አሳፍ “ስምህ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] የሆነው አንተ ብቻ፣ በምድር ሁሉ ላይ ልዑል እንደ ሆንህ ይወቁ” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 83:18) በተጨማሪም ዳዊት ከመዝሙሮቹ በአንዱ ላይ “ትምክህታችን የአምላካችን የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ስም ነው” ሲል ጽፏል።—መዝሙር 20:7

ይሖዋ አምላክ ስለ ስሙ ምን እንደሚሰማን ለማወቅ ልባችንን እንደሚመረምር መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክታል። መዝሙራዊው “የአምላካችንን ስም ረስተን . . . ቢሆን ኖሮ፣ እግዚአብሔር ይህን ማወቅ ይሳነዋልን? እርሱ ልብ የሰወረውን የሚረዳ ነውና” ብሏል። (መዝሙር 44:20, 21) ነቢዩ ኢሳይያስ “እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ስሙንም ጥሩ፤ ያደረገውንም በአሕዛብ መካከል አስታውቁ፤ ስሙ ከፍ ከፍ ማለቱንም ዐውጁ” ሲል ጽፏል።—ኢሳይያስ 12:4

አምላክ ራሱ “ስሜ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW]፣ እንደ ሆነ ያውቃሉ” ብሏል። (ኤርምያስ 16:21) በሌላ ጊዜ ደግሞ “በአሕዛብ መካከል የረከሰውን . . . የታላቁን ስሜን ቅድስና አሳያለሁ፤ . . . አሕዛብ እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] እንደ ሆንሁ ያውቃሉ” ብሏል። (ሕዝቅኤል 36:23) ከእነዚህ መግለጫዎች አንዳንዶቹ የሚጠቁሙት ይሖዋ ስሙን በሚያቃልሉ ላይ የቁጣ እርምጃ የሚወስድበት ጊዜ እንዳለ ነው። ለአምላክ የግል ስሙ ጉዳይ ተራ ነገር አይደለም።

ይሖዋ አምላክ ከአንተ የራቀ አይደለም

አምላክን በስም ልታውቅ የምትችለው እንዴት ነው? አምላክን በስም ማወቅ ማለት ምን ማለት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ስምህን የሚያውቁ ይታመኑብሃል” በማለት መልሱን ይሰጠናል። (መዝሙር 9:10) አምላክን በስም ማወቅ ስሙ ማን እንደሆነ በማወቅ ብቻ የሚያቆም ነገር እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በእርሱ መታመን ይገባሃል። እንዴት ያለ አምላክ እንደሆነ ማወቅ፣ ስለ ባሕርያቱና ስለ ሐሳቦቹ መማር ማለት ነው። ይህን ማድረግህ በእርሱ እንድትታመን ያስገድድሃል።

ይሖዋ እንዴት ያለ አምላክ እንደሆነ በጥልቅ ልታስተውል የምትችለው መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ካነበብክና ካጠናህ ብቻ ነው። እርሱንና ስሙን የሚወዱ ሰዎችን እንደሚጠብቃቸው ቃል ገብቷል። አምላክ ስሙን ስለሚወድ ሰው የሚከተለውን ብሏል:- “ወዶኛልና እታደገዋለሁ፤ ስሜንም አውቆአልና እከልለዋለሁ። ይጠራኛል፤ እመልስለታለሁ፤ በመከራው ጊዜ ከእርሱ ጋር እሆናለሁ፤ አድነዋለሁ፤ አከብረዋለሁ። ረጅም ዕድሜን አጠግበዋለሁ፤ ማዳኔንም አሳየዋለሁ።”—መዝሙር 91:14-16

ይሖዋ አምላክ በስም ከሚያውቁት ጋር ያለው ዝምድና ምንኛ አስደናቂ ነው! አንተም እንዲህ ያለውን ዝምድና ማግኘት ትችላለህ። ከልብህ በምታቀርበው ጸሎት እርሱን በስም ከመጥራት ወደኋላ አትበል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም’ ስለሚል ለጸሎትህ መልስ ይሰጥሃል።—የሐዋርያት ሥራ 17:27

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም የጥንታዊ ትርጉሞችን ዘመን ያለፈበት ቋንቋ በዘመናዊ አነጋገር የተካ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ነው። የዚህ ትርጉም ዋነኛ ገጽታ መለኮታዊው ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትክክለኛ ቦታውን እንዲያገኝ ማድረጉ ነው። እስከዛሬ ድረስ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ወይም በከፊል በ45 ቋንቋዎች ተተርጉሞ ከ122 ሚሊዮን በላይ በሚሆኑ ቅጂዎች ታትሟል።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አምላክ በስም ያውቅሃል

አምላክ ሙሴን “በስም አውቅሃለሁ” ብሎታል። (ዘፀአት 33:12) ይህ እውነት መሆኑ በሠፊው በሚታወቀው የሚቃጠል ቁጥቋጦ ታሪክ ተረጋግጧል። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ‘ከቁጥቋጦው ውስጥ ሙሴ፣ ሙሴ ብሎ ጠራው’ በማለት ይናገራል። (ዘፀአት 3:4) ይህ አምላክ ሰዎችን በግል ስማቸው ከጠራባቸው በጣም ብዙ ጊዜያት አንዱ ብቻ ነው። የጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ በየግላችን እንደሚያስብልን ግልጽ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠሩትን ከዋክብት እያንዳንዳቸውን በስም እንደሚያውቅ ይናገራል። (ኢሳይያስ 40:26) ታዲያ እርሱን ለሚያመልኩ ሰዎች ከዚህ የበለጠ አያስብላቸውም? ሐዋርያው ጳውሎስ ይሖዋ “የእርሱ የሆኑትን ያውቃል” ብሏል። (2 ጢሞቴዎስ 2:19) ይህ ማለት እንዲሁ ስማቸውን ከማስታወስ የበለጠ ነገር ያካትታል። አምላክ አገልጋዮቹን በቅርብ ያውቃቸዋል። እኛም በበኩላችን አምላክን በስም ማወቅና ከባሕርያቱ ጋር በቅርብ መተዋወቅ ይኖርብናል።

የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ አምላክ በታሪክ ዘመናት በሙሉ ያመለኩትን ሰዎች ስም ስለጻፈበት ምሳሌያዊ መጽሐፍ ይገልጻል። ይሖዋ በዚህ መጽሐፍ ለተጻፉ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ስለሚሰጥ መጽሐፉ ‘የሕይወት መጽሐፍ’ ተብሏል። (ራእይ 17:8) አምላክን በስም ለሚያውቁ ሁሉ ይህ በጣም ብሩሕ የሆነ ተስፋ ነው።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የአምላክን ስም አውጀዋል

● እስራኤል ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊገባ ሲል የተዘመረ የሙሴ መዝሙር:- “የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ስም ዐውጃለሁ።”—ዘዳግም 32:3

● ዳዊት ለግዙፉ ጎልያድ የተናገረው ቃል:- “እኔ . . . የእስራኤል ሰራዊት አምላክ በሆነው . . . በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ።”—1 ሳሙኤል 17:45

● ኢዮብ ንብረቱ በሙሉ ከጠፋና ልጆቹ በሙሉ በድንገት ከሞቱበት በኋላ የተናገራቸው ቃላት:- “የእግዚአብሔር ስም ቡሩክ ይሁን።”—ኢዮብ 1:21

● ሐዋርያው ጴጥሮስ ባደረገው ንግግር የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ሲጠቅስ:- “የጌታን [“የይሖዋን፣” NW] ስም፣ የሚጠራ ሁሉ ይድናል።”—የሐዋርያት ሥራ 2:21

● ነቢዩ ኢሳይያስ:- “እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] አመስግኑ፤ ስሙንም ጥሩ፤ . . . ስሙ ከፍ ከፍ ማለቱንም ዐውጁ።”—ኢሳይያስ 12:4

● ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ጸሎት ሲያስተምር:- “እናንተ ግን እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፤ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ።’”—ማቴዎስ 6:9, 10

● ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አምላክ ሲጸልይ:- “ስምህን ገልጬላቸዋለሁ።”—ዮሐንስ 17:6

● አምላክ ለሕዝቦቹ ሲናገር:- “እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ነኝ፤ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ . . . አልሰጥም።”—ኢሳይያስ 42:8