በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እንዴ! አሁንም ሊዘንብ ነው?

እንዴ! አሁንም ሊዘንብ ነው?

እንዴ! አሁንም ሊዘንብ ነው?

አየርላንድ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

“እንዴ! አሁንም ሊዘንብ ነው?”

እንዲህ ብለህ አማርረህ ታውቃለህ? ለምሳሌ ያህል የክረምቱ ወቅት ካለፈ በኋላ ለመዝናናትና መንፈስህን ለማደስ በአየርላንድ ወደሚገኘው የአትላንቲክ የባሕር ዳርቻ ሄደሃል እንበል። ቀኑ ሞቃታማና ፀሐያማ ይሆናል ብለህ ስትጠብቅ በድንገት አየሩ ተለዋውጦ ዐውሎ ነፋስ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ መጣል ይጀምራል። በዚህ ጊዜ ዝናብ የሚሰጠው ጥቅም ጨርሶ ላይታይህ ይችላል። ዝናብ ባይኖር አንተም ሆንክ የምትጎበኘው ውብ አካባቢ ሊኖር አይችልም!

ዝናብ አንዴ ብቻ ዘንቦ አያቆምም፤ በየጊዜው እየዘነበ ምድሪቱን ያጠጣል። ይህ ሂደት መቼም ቢሆን አያቋርጥም። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? አንድ እጅግ አስደናቂ የሆነ የማያቋርጥ ዑደት በመኖሩ ነው። ለሕይወት በጣም አስፈላጊ የሆነውን የዚህን ዑደት ሦስት ደረጃዎች በጥቂቱ መመርመራችን ብቻ እንኳ ይህ ዑደት እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ ነገር እንዳልሆነ እንድናስተውል ይረዳናል። በመጀመሪያ ውኃው ይተናል፣ ከዚያም ይጤዛል በመጨረሻም ወደ ርደተ ውኃ ወይም ዝናብ ይለወጣል። አንድ መጽሐፍ ይህ ዑደት “በማይለዋወጥና ቋሚ በሆነ ሕግ የሚመራ” የረቀቀና የተወሳሰበ ሂደት እንደሆነ ገልጿል።

ትነት

ዘጠና ሰባት በመቶ የሚሆነው የምድር ውኃ የሚገኘው በውቅያኖሶች ውስጥ ነው። የተቀረው ውኃ ደግሞ የሚገኘው በግግር በረዶ መልክ አሊያም በሐይቆችና በምድር ከርስ ውስጥ ነው። እርግጥ ነው፣ የውቅያኖስ ውኃ ለመጠጥ አይሆንም። “የጥንታዊው መርከበኛ ግጥም” * የተባለ ጽሑፍ ችግር ላይ የወደቀ አንድ መርከበኛ በውቅያኖሶች ውስጥ ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ “ውኃ፣ ሁሉ ውኃ ቢሆንም፣ ለመጠጥ የሚሆን አንዲት ጠብታ አይገኝም” ብሎ እንደተናገረ ይገልጻል።

የውቅያኖስ ውኃ ለመጠጥነት ሊያገለግል የሚችለው ውስብስብ የሆኑ በርካታ ሂደቶችን ካለፈ በኋላ ነው። በመጀመሪያ ይተንና ወደ ጋዝነት ይለወጣል። የፀሐይ ሙቀት በየዓመቱ 400,000 ኪዩቢክ ኪሎ ሜትር ውኃ ከየብስና ከባሕር ወደ ከባቢ አየር እንዲተን ያደርጋል። በጥንት ዘመን ይኖር የነበረ ኤሊሁ የተባለ አንድ ሰው ይህን የሚያደርገው አምላክ እንደሆነ ሲገልጽ “የውኃውን ነጠብጣብ ወደ ላይ ይስባል፣ ዝናብም ከጉም ይንጠባጠባል” ብሏል።—ኢዮብ 36:27 የ1954 ትርጉም

ከባቢ አየር ራሱ “እጅግ የረቀቀና ውስብስብ” ሲሆን ከምድር አንስቶ እስከ ጠፈር ድረስ 400 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ አለው። የውኃ ዑደት የሚካሄደው ግን ከምድር በላይ ከ10 እስከ 20 ኪሎ ሜትር ባለው ርቀት ውስጥ ነው። ይሄኛው የከባቢ አየር ክፍል ታህታይ ከባቢ አየር በመባል የሚታወቅ ሲሆን አወር ፍራጃይል ወተር ፕላኔት የተባለው መጽሐፍ “ይህን ክልል ለምድር ገጽ በጣም ቅርብ የሆነ የደመናት፣ የዝናብ፣ የበረዶ፣ የዐውሎ ነፋስና የነጎድጓዳማ ውሽንፍር ዓለም” ሲል ገልጾታል።

አየሩ ሞቃት ሲሆን ብዙ ውኃ መሰብሰብ ይችላል። ሞቃታማና ነፋሻማ በሆነ ቀን ያሰጣኸው ልብስ ቶሎ የሚደርቀው ለዚህ ነው። አብዛኛው ውኃ የሚገኘው በሐሩር ክልል ባለው ከባቢ አየር ውስጥ ነው። ‘ታዲያ ይህ ውኃ ወደሚፈለግበት አካባቢ ሄዶ የሚዘንበው እንዴት ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ምድርን ከብበው የሚገኙት ኃይለኛ ነፋሳት እየገፉ ይወስዱታል። ምድር በምሕዋሯ ላይ የምትዞርበት መንገድ ለእነዚህ ነፋሳት መፈጠር አንዱ ምክንያት ነው። ከዚህም በተጨማሪ የተወሰነው የምድር ክፍል ከሌላው ይበልጥ የሚሞቅ መሆኑ በከባቢ አየር ውስጥ ነውጥ እንዲፈጠር ስለሚያደርግ እንዲህ ያሉ ነፋሳት እንዲፈጠሩ ምክንያት ይሆናል።

በነውጥ በተሞላው ከባቢ አየር ውስጥ ተመሳሳይ የሙቀት መጠን ያላቸው የአየር ክምችቶች ይገኛሉ። እነዚህ የአየር ክምችቶች ምን ያህል ስፋት አላቸው? በሚሊዮን የሚቆጠሩ ካሬ ኪሎ ሜትሮችን ሊሸፍኑ ይችላሉ። ሞቃታማ የሆኑ የአየር ክምችቶች የሚፈጠሩት በሐሩር ክልል ሲሆን ቀዝቃዛ የአየር ክምችቶች ደግሞ የሚፈጠሩት በአርክቲክ ወይም በምድር ዋልታዎች አካባቢ ነው። እነዚህ የአየር ክምችቶች በከባቢ አየር ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ያጓጉዛሉ።

የውኃ ተን በከባቢ አየር ውስጥ በሚያደርገው እንቅስቃሴ አማካኝነት የሚከናወን ሌላም አስደናቂ ክስተት አለ። የውኃው ተን እንደ ሐሩር ክልል ባሉ ቦታዎች የሚገኘውን ከፍተኛ ሙቀት ቀዝቃዛ ወደሆኑ ሌሎች ቦታዎች ያጓጉዛል። ይህ ባይሆን ኖሮ በአንዳንድ የምድር ክፍሎች ያለው ሙቀት ያለማቋረጥ እየጨመረ ይሄድ ነበር።

ጥዜት

የውኃ ተን በከባቢ አየር ውስጥ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ተግባራትን የሚያከናውን ቢሆንም እንኳ በዚያው ተወስኖ የሚቀር ቢሆን ኖሮ ምድራችንን ሊያጠጣ አይችልም ነበር። ለምሳሌ ያህል በሰሃራ በረሃ የሚገኘው ከባቢ አየር ከፍተኛ መጠን ያለው እርጥበት ያዘለ ቢሆንም አካባቢው ዝናብ የማይዘንብበት ደረቅ ምድር ነው። በከባቢ አየር ውስጥ የሚገኘው እርጥበት ወደ ምድር ተመልሶ የሚመጣው እንዴት ነው? መጀመሪያ ይጤዝና ወደ ፈሳሽነት ይለወጣል።

እንፋሎት መስተዋት ላይ በሚያርፍበት ጊዜ መስተዋቱ ላይ የውኃ ተን እንደሚከማች ሳታስተውል አልቀረህም። ይህ እንዲፈጠር የሚያደርገው የመስተዋቱ ቅዝቃዜ ነው። ልክ እንደዚሁም ሞቃት የሆነ አየር ቀዝቃዛ ወደሆኑ ከፍታ ቦታዎች በሚወጣበትና የሙቀት መጠኑ በሚቀንስበት ጊዜ ተመሳሳይ ሁኔታ ይፈጠራል። አየሩ ወደ ላይ የሚወጣው ለምንድን ነው? ቀዝቃዛ የሆነውና የበለጠ ክብደት ያለው አየር ሞቃቱን አየር ወደ ላይ ስለሚገፋው ነው። ተራሮችም አየሩን ወደ ላይ የሚገፉበት ጊዜ አለ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ፣ በተለይ በሐሩር ክልሎች በከባቢ አየር ውስጥ የሚፈጠረው ሞገድ ሞቃታማውን አየር ወደ ላይ ይገፋዋል።

‘ይሁን እንጂ በከባቢ አየር ውስጥ የውኃው ተን ሊጤዝበት የሚችል ምን ነገር አለ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ከባቢ አየር እንደ ጭስ፣ አቧራና የባሕር ጨው ባሉ ጥቃቅን ቅንጣቶች የተሞላ ነው። ሞቃታማው አየር ሲቀዘቅዝ የውኃው ተን በእነዚህ ጥቃቅን ቅንጣቶች ላይ ይጤዛል። ከዚያም የጤዙት የውኃ ጠብታዎች ተከማችተው ደመና ይፈጥራሉ።

ይሁን እንጂ ይህ ውኃ ወዲያው ወደ ምድር አይወርድም። ለምን? ውኃ ከአየር ይበልጥ 800 ጊዜ እጥፍ የታመቀ በመሆኑ ብዙ ቦታ እንደማይወስድ መዘንጋት የለበትም። እያንዳንዷ የደመና ብናኝ በጣም ትንሽና ቀላል በመሆኗ በአየር ሞገድ ውስጥ መንሳፈፍ ትችላለች። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ኤሊሁ በዚህ አስገራሚ የውኃ ዑደት በመደነቅ “ደመናት ሚዛን ጠብቀው እንዴት እንደሚንሳፈፉ፣ በዕውቀቱ ፍጹም የሆነውን፣ የእርሱን [የፈጣሪን] ድንቅ ሥራ ታውቃለህን?” ሲል ተናግሯል። (ኢዮብ 37:16) በአየር ላይ የሚንሳፈፈው አነስተኛና ስስ ደመና ከ100 እስከ 1,000 ቶን እርጥበት ሊይዝ መቻሉ የሚያስደንቅ አይደለም?

ርደተ ውኃ

አብዛኞቹ ደመናዎች ርደተ ውኃ ወይም ዝናብ አያስገኙም። ደመናት ዝናብ እንዲሰጡ የሚያደርጋቸው ነገር ምን እንደሆነ ከማብራራት ይልቅ ውኃ እንዴት ወደ ከባቢ አየር እንደሚገባና ደመናት እንዴት በሰማይ ላይ እንደሚንሳፈፉ ማስረዳት ይቀላል። አንድ ጸሐፊ “ከሁሉ በላይ አስቸጋሪ የሚሆነው ውኃው እንዴት ተመልሶ ወደ ምድር እንደሚመጣ ማስረዳት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።—ዘ ቻሌንጅ ኦቭ ዚ አትሞስፌር

አንዲት አነስተኛ የዝናብ ጠብታ ለማግኘት “አንድ ሚሊዮን ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ የደመና ብናኞች” ያስፈልጋሉ። በአየር ውስጥ የሚንሳፈፉት እነዚህ ትናንሽ የደመና ብናኞች በየቀኑ በእያንዳንዷ ደቂቃ ወደ ምድር የሚወርደውን አንድ ቢሊዮን ቶን ወይም ከዚያ በላይ የሚገመት ውኃ የሚያስገኙት እንዴት እንደሆነ ሙሉ በሙሉ አጥጋቢ ማብራሪያ መስጠት የሚችል ሰው የለም። የዝናብ ጠብታዎች የሚፈጠሩት አነስተኛ የደመና ብናኞች አንድ ላይ ሲዋሃዱ ነው? እንደ ሐሩር ክልል ባሉ አንዳንድ ቦታዎች የዝናብ ጠብታዎች የሚፈጠሩት በዚህ መንገድ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ በአየርላንድ እንደሚገኘው የአትላንቲክ የባሕር ዳርቻ ባሉ ቦታዎች “የዝናብ ጠብታዎች የሚፈጠሩት እንዴት ነው ለሚለው ጥያቄ” ይህ መልስ ሊሆን አይችልም።

በአየርላንድ የአትላንቲክ የባሕር ዳርቻ አነስተኛ የደመና ብናኞች አንድ ላይ በመዋሃድ የዝናብ ጠብታዎችን አያስገኙም። ከዚህ ይልቅ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባይታወቅም በዚህ ቦታ የሚገኙት የደመና ብናኞች አንድ ላይ ተዋህደው የበረዶ ብናኞችን ይፈጥራሉ። እነዚህ የበረዶ ብናኞች ደግሞ አንድ ላይ በመዋሃድ “ድንቅ የተፈጥሮ ሥራ” የሆነውን የበረዶ ቅንጣት ያስገኛሉ። እነዚህ የበረዶ ቅንጣቶች መጠናቸውና ክብደታቸው እየጨመረ ሲሄድ ወደ ላይ የሚወጣውን የአየር ሞገድ በማሸነፍ ወደ ምድር ይወርዳሉ። አየሩ ቀዝቃዛ ከሆነ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ቅንጣቶች በረዶ እንደሆኑ ወደ ምድር ይዘንባሉ። አየሩ ሞቃት ከሆነ ግን ይቀልጡና በዝናብ መልክ ይወርዳሉ። ስለዚህ በረዶ የቀዘቀዘ ዝናብ ማለት አይደለም። እንዲያውም መካከለኛ የሙቀት መጠን ባላቸው የምድር ክፍሎች መጀመሪያ ላይ የሚፈጠረው ዝናብ ሳይሆን በረዶ ነው። በረዶው ወደ ዝናብነት የሚለወጠው ወደ ምድር በሚወርድበት ጊዜ የአየሩ ሙቀት ስለሚያቀልጠው ነው።

ስለዚህ ውኃ እስካሁን ሳይንስ ሙሉ በሙሉ ያልደረሰባቸውን ውስብስብ ሂደቶች አልፎና በሺህ የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዞ በዝናብ መልክ ወደ ምድር ይመለሳል። ዝናብ አንዳንድ ጊዜ ፕሮግራምህንና እቅድህን ሊያስተጓጉልብህ እንደሚችል የታወቀ ነው። ሆኖም ያለማቋረጥ ውኃ እንድናገኝ የሚያስችለን ይህ ዑደት መሆኑን መዘንጋት የለብህም። አዎን፣ ዝናብ ትልቅ በረከት ነው። እንግዲያው ወደፊት ዝናብ ሲመታህ ከማማረር ይልቅ ይህን የአምላክ ስጦታ እንደምታደንቅ ተስፋ እናደርጋለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 ሳሙኤል ቴይለር ኮልሪጅ የተባለ እንግሊዛዊ ገጣሚ የጻፈው።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕላዊ መግለጫ]

ድቡልቡል በረዶ የሚፈጠረው እንዴት ነው?

ዌዘር የተባለው መጽሐፍ “ድቡልቡል በረዶ የሚፈጠረው በነጎድጓዳማ ደመናዎች ነውጥ ሳቢያ ነው” ሲል ይገልጻል። የደመና ብናኞች ጥቃቅን በሆኑ ብናኞች ላይ ሲጤዙ አንዳንድ ጊዜ ኃይለኛ ግፊት ባለው አየር ወደ ላይ ተገፍተው ከፍተኛ ቅዝቃዜ ወዳለበት የደመናው ክፍል ይወሰዳሉ። ከፍተኛ ቅዝቃዜ ባለበት በዚህ የደመናው ክፍል ሌሎች ጠብታዎች ቀደም ሲል በተፈጠሩት ጠብታዎች ላይ በመከማቸት በረዶ ይሠራሉ። ወደ በረዶነት የተለወጠው የዝናብ ጠብታ ወዲያና ወዲህ በመንቀሳቀስ ከቀዝቃዛው የደመና ክፍል ስለሚወጣና ስለሚገባ ይህ ሂደት በተደጋጋሚ ይከናወናል። በዚህ ጊዜ ወደ በረዶነት የተለወጠው የዝናብ ጠብታ ሌሎች የበረዶ ብናኞች ስለሚያርፉበት ልክ እንደ ሽንኩርት በርካታ ንብሮች በመፍጠር ክብደቱ እየጨመረ ይሄዳል። በመጨረሻም ክብደት ስለሚኖረው በደመናው ውስጥ ያለውን የአየር ግፊት በመጣስ ጠጣር በረዶ ሆኖ ወደ ምድር ይወርዳል። አትሞስፌር፣ ዌዘር ኤንድ ክላይሜት የተባለው መጽሐፍ “አንዳንድ ጊዜ እስከ 0.76 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ትልልቅ ድቡልቡል በረዶዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ” ሲል ገልጿል።

[ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ድቡልቡል በረዶ

↑ ወደ ላይ የሚወጣ አየር

በረዶ የሚፈጠርበት የደመና ክፍል .........................

↓ ወደ ታች የሚወርድ አየር

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ይህን ታውቅ ኖሯል?

በዓለም ዙሪያ በከባቢ አየር ውስጥ የሚገኘው ውኃ ሊሰጥ የሚችለው የዝናብ መጠን በአማካይ ለአሥር ቀን ብቻ የሚበቃ ነው።

አንድ ነጎድጓዳማ ዝናብ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሂሮሽማ ላይ የተጣለውን ቦምብ አሥራ ሁለት ጊዜ እጥፍ የሚሆን ኃይል አለው። በየቀኑ በዓለም ዙሪያ 45,000 ነጎድጓዳማ ዝናብ ይከሰታል።

ከባቢ አየር የሚሞቀው በቀጥታ ከፀሐይ በሚመጣው ሙቀት አይደለም። ከፀሐይ የሚመጣው ሙቀት በከባቢ አየር ውስጥ ያልፍና ምድርን ያሞቃል። ከዚያም ከምድር ገጽ ላይ የሚነሳው ሙቀት ከባቢ አየሩን ያሞቀዋል።

በምድር ላይ በአንድ አካባቢ በጠጣር፣ በፈሳሽና በጋዝ መልክ በገፍ ሊገኝ የሚችል ብቸኛው ንጥረ ነገር ውኃ ነው።

ጉም ወደ ምድር ቀረብ ብሎ የሚታይ የደመና ዓይነት ነው።

[በገጽ 20, 21 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ሥዕሎች]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ዘጠና ሰባት በመቶ የሚሆነው የምድር ውኃ የሚገኘው በውቅያኖሶች ውስጥ ነው

ከፀሐይ የሚመጣው ሙቀት ውኃውን ያተነዋል

የውኃ ተን ይጤዝና ደመና ይፈጥራል

ደመናዎች በርደተ ውኃ አማካኝነት ለምድር ዝናብ ይሰጣሉ

የዝናብ ጠብታዎችና የበረዶ ቅንጣቶች