በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የቤት ሥራዬን ለመሥራት ጊዜ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?

የቤት ሥራዬን ለመሥራት ጊዜ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

የቤት ሥራዬን ለመሥራት ጊዜ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?

‘የአሥራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪ ስሆን በቃላት ልገልጸው ከምችለው በላይ ተወጥሬያለሁ። . . . ጥናት የማደርግባቸውና በንግግር መልክ የማቀርባቸው ብዙ የቤት ሥራዎች አሉኝ። ይህ ደግሞ ቀላል አይደለም። ለዚህ ሁሉ የሚበቃ ጊዜ የለኝም።’—የ18 ዓመት ልጃገረድ የተናገረችው

በየቀኑ ከትምህርት ቤት የሚሰጥህ የቤት ሥራ ተከምሮ ከአቅምህ በላይ እንደሆነብህ ይሰማሃል? ከሆነ እንደዚህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። ከዩናይትድ ስቴትስ የተገኘ አንድ ጋዜጣዊ መግለጫ “በመላው ዩናይትድ ስቴትስ ያሉ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራት ደረጃንና መመዘኛ ፈተናዎችን ከፍ ለማድረግ ስለሚጥሩ ለተማሪዎች የሚሰጣቸው የቤት ሥራ በጣም እየጨመረ ነው” ብሏል። “በአንዳንዶቹ ትምህርት ቤቶች የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በየምሽቱ ከሦስት ሰዓት በላይ የሚፈጅ የቤት ሥራ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል። በሚሽገን ዩኒቨርሲቲ የተደረገ አንድ ጥናት እንደገለጸው በአሁኑ ጊዜ ያሉ ልጆች ከ20 ዓመት በፊት ከነበሩት ልጆች ጋር ሲነጻጸር በሦስት እጥፍ የሚበልጥ የቤት ሥራ ይሠራሉ።”

ብዙ የቤት ሥራ የሚሰጣቸው በዩናይትድ ስቴትስ ያሉ ተማሪዎች ብቻ አይደሉም። ለምሳሌ ያህል በዚህች አገር ካሉት የ13 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ተማሪዎች መካከል የቤት ሥራ በመሥራት በየቀኑ ከሁለት ሰዓት የሚበልጥ ጊዜ የሚያሳልፉት 30 በመቶ የሚያህሉት ሲሆኑ በታይዋንና በኮሪያ 40 በመቶ፣ በፈረንሳይ ደግሞ ከ50 በመቶ የሚበልጡ ተማሪዎች ይህን ያህል ጊዜ የቤት ሥራ በመሥራት ያሳልፋሉ። “አንዳንድ ጊዜ የቤት ሥራ ሲበዛብኝ በጣም እጨነቃለሁ” በማለት በዩናይትድ ስቴትስ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነችው ካቲ ምሬቷን ገልጻለች። በማርሴይ፣ ፈረንሳይ በሚገኝ ትምህርት ቤት የሚማሩት ማርሊንና ቤሊንዳም የካቲን ስሜት ይጋራሉ። ማርሊን “አብዛኛውን ጊዜ የቤት ሥራ በመሥራት በየምሽቱ ሁለት ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ እናጠፋለን” በማለት ተናግራለች። “ቤት ውስጥ ሌላ ኃላፊነት ካለባችሁማ ጊዜ ማግኘት አስቸጋሪ ይሆንባችኋል።”

ጊዜ ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?

ብዙ የምትሠሩት ሥራ በሚኖራችሁ ጊዜ የቤት ሥራችሁን እንድትጨራርሱና ሌላ ሥራችሁንም እንድታከናውኑ በቀኑ ላይ ጥቂት ሰዓቶች መጨመር ብትችሉ ጥሩ አልነበረም? እንደ እውነቱ ከሆነ በኤፌሶን 5:15, 16 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ በማድረግ በቀኑ ላይ ከ24 ሰዓት በላይ የተጨመረላችሁ ያህል ብዙ ሥራ ማከናወን ትችላላችሁ። ጥቅሱ እንዲህ ይላል: “እንግዲህ ጥበብ እንደ ሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ። ቀኖቹ ክፉ ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ።” ምንም እንኳ ይህንን ሐሳብ ያሰፈረው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ በአእምሮው የያዘው የቤት ሥራን ባይሆንም መሠረታዊ ሥርዓቱ ለሁሉም የኑሮ ዘርፎች ያገለግላል። አንድ ነገር ስትገዙ በምትኩ የምትሰጡት ሌላ ነገር አለ። እዚህ ላይ ለመግለጽ የተፈለገው ነጥብ ለጥናት ጊዜ ለማግኘት መተው ያለባችሁ ነገር እንዳለ ነው። ይሁን እንጂ መተው ያለባችሁ ነገር ምንድን ነው?

ጂልያን የተባለች ወጣት “ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን እንደየቅደም ተከተላቸው መዝግቡ” ብላለች። በሌላ አባባል ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን ለዩ። ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና መንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል። እርግጥ በቤት ውስጥ ያሏችሁን ኃላፊነቶችና የቤት ሥራችሁንም መሥራት አትርሱ።

በመቀጠልም ለአንድ ሳምንት ወይም ከዚያ ለሚበልጥ ጊዜ ያህል፣ ጊዜያችሁን እንዴት እንደምታሳልፉት ለማየት በየቀኑ ማስታወሻ ያዙ። ጊዜያችሁን እንዴት እንደምትጠቀሙበት ስትመለከቱ ትገረሙ ይሆናል። ቴሌቪዥን ወይም ፊልም በማየት፣ ኢንተርኔት በመመልከት፣ በስልክ በማውራትና ጓደኞቻችሁን በመጠየቅ ምን ያህል ጊዜ ታጠፋላችሁ? በእነዚህ ነገሮች ላይ ያጠፋችሁትን ጊዜ ቅድሚያ ልትሰጧቸው በምትፈልጓቸው ነገሮች ላይ ካጠፋችሁት ጊዜ ጋር ስታነጻጽሩት እንዴት ነው? ምናልባትም ቅድሚያ ልትሰጧቸው ለምትፈልጓቸው ነገሮች ተጨማሪ ጊዜ ለማግኘት ቴሌቪዥን በማየት፣ ስልክ በመደወል ወይም ኢንተርኔት በመመልከት ከምታሳልፉት ጊዜ ላይ መዋጀት ትችሉ ይሆናል!

መቅደም ያለባቸውን ነገሮች አስቀድሙ

ይህ ሲባል ግን ጨርሶ ቴሌቪዥን ማየት የለባችሁም ወይም የብሕትውና ኑሮ ኑሩ ማለት አይደለም። “መቅደም ያለባቸውን ነገሮች አስቀድሙ” የሚለውን ደንብ መተግበር ያስፈልጋችኋል ማለት ነው። እዚህ ላይ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ “ከሁሉ የሚሻለውን ለይታችሁ [እወቁ]” ይላል። (ፊልጵስዩስ 1:10) ለምሳሌ ያህል ትምህርታችሁ አስፈላጊ እንደመሆኑ መጠን የቤት ውስጥ ኃላፊነታችሁን እስክታጠናቅቁ፣ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እስክትዘጋጁ እንዲሁም የቤት ሥራችሁን ሠርታችሁ እስክትጨርሱ ድረስ ቴሌቪዥን ላለመክፈት ለራሳችሁ ሕግ ልታወጡ ትችላላችሁ። የምትወዱት የቴሌቪዥን ፕሮግራም ሲያመልጣችሁ ደስ እንደማይላችሁ አይካድም። ይሁን እንጂ ሐቁን ለመናገር የምትወዱትን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ብቻ ለማየት ብላችሁ ተቀምጣችሁ ምሽቱን ሙሉ በቴሌቪዥን ፊት ተጎልታችሁ በማሳለፍ ምንም ሳታከናውኑ የቀራችሁት ምን ያህል ጊዜ ነው?

በሌላ በኩል ደግሞ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎችም ቅድሚያ መስጠት ይገባችኋል። ለምሳሌ ያህል አንድ ፈተና ወይም የቤት ሥራ እንዳለባችሁ ካወቃችሁ ከስብሰባው እንዳያስተጓጉላችሁ አስቀድማችሁ ትዘጋጃላችሁ ወይም ትሠሩታላችሁ። የቤት ሥራችሁን የምታቀርቡበት ቀን ከስብሰባ ቀናችሁ ጋር በሚገጣጠምበት ጊዜ አስቀድመው ቢያሳውቋችሁ ምን ያህል አመስጋኞች እንደምትሆኑ ለአስተማሪዎቻችሁ ለመናገርም ልትሞክሩ ትችሉ ይሆናል። አንዳንድ መምህራን ለመተባበር ፈቃደኞች ሊሆኑ ይችላሉ።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ሌላው ጠቃሚ መሠረታዊ ሥርዓት የኢየሱስ ወዳጅ ስለነበረችው ስለማርታ በሚናገረው ታሪክ ላይ የተገለጸው ትምህርት ነው። ማርታ በጣም ሥራ የበዛባትና ታታሪ ሴት ብትሆንም ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡ ነገሮች ቅድሚያ አልሰጠችም ነበር። በአንድ ወቅት ለኢየሱስ ይህ ቀረው የማይባል ግብዣ ለማዘጋጀት ስትባክን እህቷ ማርያም ግን ማርታን በወጥ ቤት ሥራ በማገዝ ፈንታ ኢየሱስ ሲያስተምር ታዳምጥ ነበር። ማርታም ስለዚህ ጉዳይ ቅሬታዋን ስትገልጽ ኢየሱስ “ማርታ፣ ማርታ፤ ስለብዙ ነገር ትጨነቂያለሽ፤ ትዋከቢአለሽም፤ የሚያስፈልገው ግን አንድ ነገር ብቻ ነው፤ ማርያም እኮ የሚሻለውን ድርሻ መርጣለች፤ ይህም ከእርስዋ አይወሰድም” አላት።—ሉቃስ 10:41, 42

ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? ነገሮችን ቀላል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን እንማራለን። ታዲያ ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በቤት ሥራችሁ ረገድ ተግባራዊ ልታደርጉት የምትችሉት እንዴት ነው? የቤት ሥራንና የትርፍ ሰዓት ሥራን አንድ ላይ ለማስኬድ በመሞከር ‘በብዙ ነገር እየተጨነቃችሁና እየተዋከባችሁ’ ይሆን? ሥራ ካላችሁ የምትሠሩት በእርግጥ ገንዘቡ ለቤተሰቦቻችሁ ስለሚያስፈልጋቸው ነው? ወይስ መሠረታዊ ለሆኑት ነገሮች የማያስፈልጋችሁ ቢሆንም እንዲሁ ያማራችሁን ነገር ለመግዛት የሚያስችላችሁ ገንዘብ እንዲኖራችሁ ስለምትፈልጉ ነው?

ለምሳሌ ያህል፣ በአንዳንድ አገሮች ወጣቶች የራሳቸው መኪና ለመግዛት ይጓጓሉ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አማካሪ የሆኑት ካረን ተርነር የተባሉ ሴት “ባለ መኪና መሆን ብዙ ወጪ ስለሚጠይቅ በዛሬው ጊዜ ወጣቶች ገንዘብ እንዲኖራቸው ወይም ሠርተው እንዲያገኙ ከፍተኛ ግፊት ይደረግባቸዋል” ብለዋል። ሆኖም ተርነር ሲያጠቃልሉ “ከብዙ የቤት ሥራ ጋር ከትምህርት ሰዓት ውጪ የሆኑ እንቅስቃሴዎችንና የትርፍ ሰዓት ሥራ የመሳሰሉትን ነገሮች ደርባችሁ ማካሄድ በመንገዳችሁ ላይ ጋሬጣ ማኖር ነው” ብለዋል። “በዚህ ጊዜ ተማሪው ከባድ ጫና ያጋጥመዋል።” የግድ መሥራት የማያስፈልጋችሁ ከሆነ በራሳችሁ ላይ ለምን ከባድ ጫና ትጭናላችሁ? በዚህ የተነሳ የትምህርት ቤት ሥራችሁ እየተጎዳ ከሆነ ምናልባት በትርፍ ጊዜ የምትሠሩበትን ሰዓት መቀነስ አለዚያም ጨርሶ ማቆም ትችሉ ይሆናል።

በትምህርት ቤት ‘ጊዜ መዋጀት’

ከትምህርት ቤት ውጪ ካላችሁ ጊዜ ላይ ትርፍ ሰዓት ለማግኘት ከመጣር ባሻገር በትምህርት ቤት የምታሳልፉትን ጊዜ በተሻለ መንገድ እንዴት መጠቀም እንደምትችሉም አስቡበት። “ለጥናትና የቤት ሥራዎችን ለመሥራት በሚሰጠን ክፍለ ጊዜ የቻልኩትን ያህል የቤት ሥራዎቼን ለማጠናቀቅ እጥራለሁ” በማለት ሆስዌ ይናገራል። “እንደዚህ በማድረግ በዚያ ቀን ክፍል ውስጥ ያልገባኝ ነገር ካለ መምህሬን ለመጠየቅ አጋጣሚ አገኛለሁ።”

ሌላው ሊታሰብበት የሚገባ ነገር ደግሞ ከምትማሯቸው ትምህርቶች ውስጥ በምርጫችሁ የምትወስዷቸውን ትምህርቶች ቁጥር የመቀነሱ ጉዳይ ነው። በተጨማሪም ከትምህርት ሰዓት ውጪ የምትካፈሉባቸውን እንቅስቃሴዎች መተው ያስፈልጋችሁ ይሆናል። በእነዚህ መስኮች ማስተካከያዎች በማድረግ ተጨማሪ የጥናት ሰዓት ማግኘት ትችላላችሁ።

ጊዜያችሁን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም

እንግዲህ አንዳንድ መሥዋዕቶችንና ማስተካከያዎችን አድርጋችሁ ለቤት ሥራ የሚሆን ተጨማሪ ጊዜ አገኛችሁ እንበል። ታዲያ ይህን ጊዜ ውጤታማ በሆነ መንገድ ልትጠቀሙበት የምትችሉት እንዴት ነው? በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ድሮ ከምትሠሩት በላይ 50 በመቶ የሚሆን ተጨማሪ የቤት ሥራ መሥራት ከቻላችሁ 50 በመቶ የሚሆን ተጨማሪ ጊዜ አገኛችሁ ማለት እይደለም? በዚህ መንገድ ውጤታማነታችሁን የምታሻሽሉባቸው አንዳንድ ሐሳቦች እነሆ።

እቅድ አውጡ። የቤት ሥራችሁን መሥራት ከመጀመራችሁ በፊት እንደሚከተሉት ያሉትን ነገሮች አስቡባቸው:- በመጀመሪያ መሥራት ያለብኝ የትኛውን ትምህርት ነው? የቤት ሥራው ምን ያህል ጊዜ ሊወስድ ይገባል? ይህን የቤት ሥራ ለመሥራት የትኞቹ የትምህርት መሣሪያዎች ማለትም መጻሕፍት፣ ወረቀት፣ ብዕር፣ የሒሳብ ስሌት ማሽንና የመሳሰሉት ያስፈልጉኛል?

የጥናት ቦታ ይኑራችሁ። የጥናት ቦታው ሐሳብ የሚበታትኑ ነገሮች የሌሉበት መሆን ይኖርበታል። ‘ዴስክ ካላችሁ ተጠቀሙበት’ ትላለች ኤሊስ የምትባል ወጣት። ‘በአልጋችሁ ላይ ጋደም ብላችሁ ከመሥራት ይልቅ ቀጥ ብላችሁ ስትቀመጡ ሐሳባችሁን ሰብሰብ አድርጋችሁ ለማጥናት ይረዳችኋል።’ የራሳችሁ ክፍል ከሌላችሁ በጥናት ሰዓታችሁ ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ጸጥታ እንድታገኙ ይተባበሯችሁ ይሆናል። ወይም ደግሞ በመናፈሻ ቦታ ወይም በሕዝብ ቤተ መጻሕፍት መጠቀም ትችሉ ይሆናል። የራሳችሁ ክፍል ካላችሁ ደግሞ በምታጠኑበት ጊዜ ቴሌቪዥን በመክፈት ወይም ሙዚቃ በማዳመጥ ጥረታችሁን መና አታስቀሩት።

በየመሃሉ እረፍት ውሰዱ። ለተወሰነ ጊዜ ያህል ካጠናችሁ በኋላ ትኩረታችሁን መሰብሰብ እንዳቃታችሁ ከተሰማችሁ ትንሽ እረፍት መውሰድ እንደገና ለመቀጠል ይረዳችኋል።

ዛሬ ነገ አትበሉ! “ዛሬ ነገ ማለት ለምዶብኛል” ትላለች ቀደም ሲል የጠቀስናት ካቲ። “በመጨረሻዋ ደቂቃ አጣብቂኝ ውስጥ እስክገባ ድረስ የቤት ሥራዬን መሥራት አልጀምርም።” የቤት ሥራችሁን የምትሠሩበት የተወሰነ ፕሮግራም አውጥታችሁ ከፕሮግራማችሁ ውልፍት ባለማለት ዛሬ ነገ እያላችሁ የማዘግየትን ልማድ አስወግዱ።

የትምህርት ቤት ሥራ አስፈላጊ ቢሆንም ኢየሱስ ለማርታ እንደነገራት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ነገር ‘የሚሻለው ድርሻ’ የተባለው መንፈሳዊ ግብ ነው። የቤት ሥራችሁ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ማንበብ፣ በአገልግሎት እንደ መሳተፍና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እንደ መገኘት ለመሳሰሉት አስፈላጊ ነገሮች ጊዜ እንዳያሳጣችሁ ተጠንቀቁ። ሕይወታችሁን ለዘላለሙ የሚያበለጽጉላችሁ እነዚህ ነገሮች ናቸው!—መዝሙር 1:1, 2፤ ዕብራውያን 10:24, 25

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙ ተግባሮችን ለማከናወን መሞከር የቤት ሥራችሁን የምትሠሩበት ጊዜ ማግኘት አዳጋች እንዲሆንባችሁ ሊያደርግ ይችላል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሚገባ መደራጀት የቤት ሥራችሁን ለመሥራት ተጨማሪ ጊዜ እንድታገኙ ሊረዳችሁ ይችላል