በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንድ ሰው ባሕርይ የሚወሰነው በደሙ ዓይነት ነው?

የአንድ ሰው ባሕርይ የሚወሰነው በደሙ ዓይነት ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

የአንድ ሰው ባሕርይ የሚወሰነው በደሙ ዓይነት ነው?

በአንዳንድ አገሮች የአንድን ሰው ባሕርይ ካለው የደም ዓይነት አንጻር ለመግለጽ መሞከር የተለመደ ነገር ነው። ለምሳሌ ያህል ጃፓን ውስጥ አንዳንዶች ከሰዎች ጋር ወሬ ለመጀመር “የደምህ ዓይነት ምንድን ነው?” ብለው የመጠየቅ ልማድ አላቸው። እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦች የደማቸው ዓይነት ኤ የሆነ ሰዎች ረጋ ያሉ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸውና ተጠራጣሪ እንደሆኑ፣ የደማቸው ዓይነት ቢ የሆነ ደግሞ ቅን፣ ስሜታቸው የሚለዋወጥና በቀላሉ የሚታለሉ እንደሆኑ ይናገራሉ። ከዚህ በተጨማሪ አንድ ዓይነት ደም ያለው ሰው ሌላ ዓይነት ደም ካለው ሰው ጋር ተግባብቶ መኖር ሊያስቸግረው ወይም ሊቀለው እንደሚችል ይነገራል።

ከዚህ አስተሳሰብ በመነሳት አንዳንዶች ተማሪዎችን በቡድን ለመከፋፈል፣ ሥራ አስኪያጆችን ለመሾም ብሎም የትዳር ጓደኛ ለመምረጥ የግለሰቦች የደም ዓይነት ወሳኝ ነገር እንደሆነ ያስባሉ። የደማችን ዓይነት ባሕርያችንን ይወስናል ብሎ በትክክል መናገር ይቻላል? ከዚህ ጉዳይ ጋር ዝምድና ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አሉ?

የደም ዓይነት ሲባል ምን ማለት ነው?

ዘ ዎርልድ ቡክ መልቲሚዲያ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል:- “የቀይ የደም ሕዋሳት ሽፋን አንቲጂንስ (እንግዳ አካል) የሚባሉ ፕሮቲኖች አሉት። እንደዚሁም ከ300 በላይ የቀይ ሕዋስ አንቲጂኖች እንዳሉ ማወቅ ተችሏል።” አንዳንድ ሰዎች የተወሰኑ ዓይነት አንቲጂኖች ያሏቸው ሲሆን ሌሎች ደግሞ እነዚያ አንቲጂኖች የሏቸውም። ከዚህም ሌላ አንድ ላይ መሆን የማይችሉ አንቲጂኖች አሉ። በመሆኑም ኢንሳይክሎፒዲያው በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “ሳይንቲስቶች የአንዳንድ አንቲጂኖችን መኖር ወይም አለመኖር መሠረት በማድረግ የሰዎችን ደም በተለያየ ቡድን መከፋፈል ችለዋል።”

ሰፊ ተቀባይነት ያገኘው ደምን በተለያዩ ቡድኖች የመከፋፈል ዘዴ ኤቢኦ የሚባለው ነው። በዚህ ዘዴ መሠረት የሰው ደም ኤ፣ ቢ፣ ኤቢ ወይም ኦ ተብሎ በአራት ቡድን ይከፈላል። ከዚህ በተጨማሪ አርኤች ፋክተር በሰፊው የሚሠራበት ሌላ ዘዴ ነው። እንዲያውም የደም ዓይነቶችን በቡድን ለመከፋፈል የሚያስችሉ ወደ 20 ገደማ ዘዴዎች አሉ። በመሆኑም ደም በጣም ውስብስብ ባሕርይ ያለው ነገር መሆኑ ግልጽ ነው። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል:- “በጣም ብዙ የቀይ ሕዋስ አንቲጂኖች ስላሉ ተመሳሳይ መንትያዎች ካልሆኑ በስተቀር ሰዎች አንድ ዓይነት የደም ንጥረ ነገሮች ቅንብር ይኖራቸዋል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው።”

ይህም እያንዳንዱ ሰው ከሌላው የተለየ “የደም ዓይነት” አለው ማለት ነው። በመሆኑም የተወሰነ የደም ዓይነት ያላቸው ሰዎች ተመሳሳይ ባሕርይ ይኖራቸዋል ብሎ ለመናገር የሚያስችል መሠረት የለም። እንደ እውነቱ ከሆነ ማንነታችንን የሚወስኑት በርካታ ነገሮች ናቸው።

ማንነታችን የሚወሰነው በምንድን ነው?

የአንድ ሰው ማንነት፣ ተለይቶ የሚታወቅበት በተፈጥሮ ያገኛቸውም ሆኑ ያዳበራቸው የተለያዩ ጠባዮች ስብስብ ነው። አዎን፣ በተፈጥሮ ካገኘነው ባሕርይ በተጨማሪ ያደግንበት ቤተሰብ፣ የቀሰምነው ትምህርት፣ ጓደኞቻችን እንዲሁም በሕይወታችን ያጋጠሙን ጥሩም ሆኑ መጥፎ ነገሮች ማንነታችንን ይወስናሉ። በመሆኑም የተፈጥሮ ባሕርያችን ማንነታችንን የሚወስን ብቸኛው ነገር አይደለም። አንድ ዓይነት አፈጣጠር ያላቸው ተመሳሳይ መንትያዎች እንኳ አብዛኛውን ጊዜ በባሕርያቸው ይለያያሉ።

መዘንጋት የሌለብን ሌላው ነገር የአንድ ሰው ባሕርይ በጊዜ ሂደትም ሆነ በጥረት ሊለወጥ የሚችል መሆኑ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ሰዎችን የመለወጥ ኃይል እንዳለው አበክሮ ገልጿል። ‘አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር አውልቃችሁ ጥላችኋል። የፈጣሪውን መልክ እንዲመስል በዕውቀት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችኋል’ በማለት ጽፏል። (ቈላስይስ 3:9, 10) ክርስቲያኖች ኃጢአተኞችና ወደ ኃጢአት የሚገፋፋ ዝንባሌ የወረሱ መሆናቸውን ያውቃሉ። በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት እንዲችሉ አዲሱን ሰው መልበስ አለባቸው።

እንዲህ ዓይነት ለውጥ እንዲያደርጉ የሚያስችላቸው ምንድን ነው? የአምላክ ቃል ወይም ትምህርት ያለው ኃይል ነው። ጳውሎስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮ የሚገኘው የአምላክ ቃል ያለውን ኃይል በተመለከተ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነውና፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ ስለታም ነው፤ ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም ሐሳብና ምኞት ይመረምራል።” (ዕብራውያን 4:12) አንድ ሰው የአምላክ መንፈስ ለሚያሳድርበት ተጽዕኖ ሲገዛና መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሰፈረው የሥነ ምግባር መሥፈርት ጋር ተስማምቶ ለመኖር ሲጥር ባሕርይው ቀስ በቀስ ሊለወጥ ይችላል። በዚህ መንገድ ከሚያፈራቸው ክርስቲያናዊ ባሕርያት መካከል ‘ርኅራኄ፣ ቸርነት፣ ትሕትና፣ ጨዋነትና ትዕግሥት’ አንዳንዶቹ ናቸው።—ቈላስይስ 3:12

አንድ ክርስቲያን ምክንያታዊ መሆን አለበት

መጽሐፍ ቅዱስ የደም ዓይነቶችን ለማወቅ የሚደረግን ጥናት አያወግዝም። ሆኖም የደም ዓይነት ከሰው ባሕርይ ጋር ዝምድና አለው ማለት አይቻልም። በሕይወታችን ውስጥ በሌሎች ጉዳዮች እንደምናደርገው ሁሉ በዚህ ረገድም የአምላክ ቃል አካሄዳችንን እንዲመራልን መፍቀድ ይኖርብናል። (መዝሙር 119:105) ምክንያታዊ መሆንም በጣም አስፈላጊ ነው።—ፊልጵስዩስ 4:5

አንድ ሰው ባለው የደም ዓይነት አመካኝቶ የባሕርይ ድክመቱን ለማሸነፍ ጥረት የማያደርግ ከሆነ ምክንያታዊነት ይጎድለዋል ማለት ነው። ክርስቲያኖች በተፈጥሮ የወረሱት ባሕርይ ምንም ይሁን ምን አቅማቸው በፈቀደ መጠን ይሖዋንና ኢየሱስን መምሰል እንዲችሉ ባሕርያቸውን እያስተካከሉ መሄድ ይኖርባቸዋል።—ኤፌሶን 5:1

ከዚህ በተጨማሪ ክርስቲያኖች ሌሎችን በይሖዋ ዓይን ለማየት ጥረት ያደርጋሉ። ‘እግዚአብሔር ለማንም አያዳላም።’ (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) ይሖዋ ከተለያየ ዘር የመጡ ሰዎችን በደስታ ይቀበላል። በመሆኑም በደማቸው ዓይነት የተነሳ ሰዎችን መራቅ ወይም ማግለል ምክንያታዊነት የጎደለውና ከክርስቲያናዊ ባሕርይ የራቀ ድርጊት ነው። አንድ ክርስቲያን የደም ዓይነታችን “ይገጥማል” ከሚላቸው ሰዎች ጋር ብቻ የሚቀራረብ ከሆነም ድርጊቱ ከዚህ ተለይቶ አይታይም። መጽሐፍ ቅዱስ “አድልዎ ብታደርጉ ግን ኀጢአት መሥራታችሁ ነው” በማለት ያስጠነቅቃል።—ያዕቆብ 2:9

ሳይንስና ቴክኖሎጂ እያደገ በሄደ መጠን የሰውን አካል በተመለከተ ብዙ አዳዲስ ግኝቶችና ትምህርቶች ይፋ መሆናቸው አይቀርም። ስለ እነዚህ ግኝቶች ስንሰማ መደነቃችን ያለ ነገር ነው። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች ማሰብ ያለባቸው በሰብዓዊ ትምህርት ላይ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርተው መሆን አለበት። በማንኛውም የሕይወት ዘርፍ ክርስቲያኖች ‘ሁሉን ፈትነው መልካሙን መያዝ’ አለባቸው።—1 ተሰሎንቄ 5:21