በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከልክ በላይ መጠጣት በእርግጥ ስህተት ነው?

ከልክ በላይ መጠጣት በእርግጥ ስህተት ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ከልክ በላይ መጠጣት በእርግጥ ስህተት ነው?

ቲያትረኞች በመድረክ ላይ እንደ ሰካራም ሆነው በመቅረብ ለዓመታት አስቂኝ ትርዒት ለሕዝብ ሲያሳዩ ኖረዋል። ቲያትረኞች ሰካራም መስለው የሚታዩት ሰዎችን ለማሳቅ ብለው እንደሆነ የታወቀ ነው። ይሁንና እነሱ የሚያሳዩት ትርዒት ከልክ በላይ መጠጣት ‘ደካማነት ቢሆንም ምንም ጉዳት የለውም’ የሚለውን የብዙዎች አመለካከት የሚያንጸባርቅ ነው።

በገሐዱ ዓለም ግን ስካር ሊሳቅበት የሚገባ ጉዳይ አይደለም። የዓለም ጤና ድርጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የጤና ጠንቅ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ከልክ በላይ መጠጣት እንደሆነ ይፋ አድርጓል። ከትንባሆ ሱስ ቀጥሎ ከማናቸውም ሱስ የሚያስይዙ ንጥረ ነገሮች ይበልጥ ብዙ ሞትና ሕመም የሚያስከትለው ከልክ በላይ መጠጣት እንደሆነና በየዓመቱ በዩናይትድ ስቴትስ ኢኮኖሚ ላይ ብቻ እንኳ ከ184 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኪሳራ እንደሚያደርስ ተነግሯል።

ሐቁ ይህ ቢሆንም ብዙ ሰዎች እስካሁንም ድረስ ከልክ በላይ መጠጣት አሳሳቢነቱ አይታያቸውም። ቀጣይ የሆነ ከልክ በላይ የመጠጣት ልማድ የኋላ ኋላ ጎጂ ውጤቶች እንደሚያስከትል ባይክዱም አልፎ አልፎ በስካር መፈንጠዝ ያለው ጉዳት አይታያቸውም። በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ባሉት ወጣቶች ዘንድ መስከር ከልጅነት ወደ አዋቂነት መሸጋገራቸውን የሚያሳዩበት ሥነ ሥርዓት እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። የጤና ድርጅቶች ከባድ ማስጠንቀቂያ ቢሰጡም እስኪሰክሩ ድረስ መጠጣት በሁሉም የዕድሜ ክልል ባሉ ሰዎች ዘንድ በእጅጉ እየተለመደ መጥቷል። እንግዲያው ብዙ ግለሰቦች ከልክ በላይ መጠጣት በእርግጥ ያን ያህል መጥፎ ሆኖ ባይታያቸው ሊያስደንቀን አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?

ወይን ጠጅና ሌሎች የአልኮል መጠጦች የአምላክ ስጦታዎች ናቸው

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወይን ጠጅም ሆነ ስለ ሌሎች የአልኮል መጠጦች የሚናገሩ ብዙ ጥቅሶች ይዟል። ንጉሥ ሰሎሞን “ሂድ፤ ምግብህን በደስታ ብላ፤ ወይንህንም ልብህ ደስ ብሎት ጠጣ፤ ባደረግኸው ነገር እግዚአብሔር ደስ ብሎታልና” በማለት ጽፏል። (መክብብ 9:7) መዝሙራዊውም ይሖዋ አምላክ ‘የሰውን ልብ ደስ የሚያሰኘውን ወይን’ እንደሰጠን ገልጿል። (መዝሙር 104:14, 15) ወይን ጠጅ ይሖዋ ለሰው ልጆች ከሰጣቸው በረከቶች እንደ አንዱ የሚቆጠር መሆኑ ግልጽ ነው።

ወይን ጠጅ መጠጣት በኢየሱስ ዘንድም ተቀባይነት እንደነበረው ግልጽ ነው። እንዲያውም የመጀመሪያውን ተአምር ያከናወነው ውኃውን ምርጥ ወደሆነ የወይን ጠጅ በመለወጥ ነው። (ዮሐንስ 2:3-10) በተጨማሪም የጌታን ራት ሲያቋቁም ወይን ጠጅን ለደሙ ተስማሚ ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሞበታል። (ማቴዎስ 26:27-29) ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን “ለሆድህ . . . ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣበት” በማለት ስላበረታታው ወይን ጠጅ በመድኃኒትነት ሊያገለግል እንደሚችል ጭምር መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቅሳል።—1 ጢሞቴዎስ 5:23፤ ሉቃስ 10:34

መፍትሔው ልከኝነት ነው

ጳውሎስ የመከረው “ጥቂት የወይን ጠጅ” እንዲጠጣ መሆኑን አስተውል። መጽሐፍ ቅዱስ በማንኛውም መልኩ የአልኮል መጠጥን ከልክ በላይ መጠጣትን በግልጽ ያወግዛል። አይሁዳውያን ካህናት ሥራ ላይ በማይሆኑበት ጊዜ በልከኝነት መጠጣት ይፈቀድላቸው ነበር። ይሁን እንጂ በክህነት ሥራቸው ላይ እያሉ ምንም ዓይነት የአልኮል መጠጥ እንዳይጠጡ ይከለከሉ ነበር። (ዘሌዋውያን 10:8-11) ከብዙ ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችም ሰካራሞች ‘የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ’ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10

ከዚህም በላይ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በሰጠው መመሪያ መሠረት በጉባኤ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው የሚያገለግሉ ወንድሞች ‘የማይሰክሩ’ ወይም “ለብዙ ወይን ጠጅ የማይጐመጁ” መሆን ይጠበቅባቸው ነበር። * (1 ጢሞቴዎስ 3:3, 8) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ንስሐ የማይገቡ ሰካራሞች ከክርስቲያን ጉባኤ እንዲወገዱ ያዛል። (1 ቆሮንቶስ 5:11-13) ቅዱሳን ጽሑፎች በትክክል እንዳስቀመጡት “የወይን ጠጅ ፌዘኛ” ያደርጋል። (ምሳሌ 20:1) የአልኮል መጠጦችን ከልክ በላይ መጠጣት የጠጪውን ራስን የመግዛት አቅም ያዳክማል እንዲሁም የማመዛዘን ችሎታውን ያዛባል።

የአምላክ ቃል ከልክ በላይ መጠጣትን የሚያወግዘው ለምንድን ነው?

‘የሚበጀን ምን እንደ ሆነ የሚያስተምረን’ አምላካችን ይሖዋ አንድን ነገር አላግባብ ስንጠቀምበት ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን መጉዳታችን እንደማይቀር ያውቃል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) የአልኮል መጠጦችን ከልክ በላይ መጠጣትን በተመለከተም ሁኔታው ያው ነው። የአምላክ ቃል “ዋይታ የማን ነው? ሐዘንስ የማን ነው? ጠብ የማን ነው? ብሶትስ የማን ነው? በከንቱ መቁሰል የማን ነው? የዐይን ቅላትስ የማን ነው?” በማለት ይጠይቅና “የወይን ጠጅ በመጠጣት ጊዜያቸውን ለሚያባክኑ ነው፤ እየዞሩ ድብልቅ የወይን ጠጅ ለሚቀማምሱ ሰዎች ነው” ሲል መልስ ይሰጣል።—ምሳሌ 23:29, 30

ሰዎች ከልክ በላይ በመጠጣታቸው ምክንያት አሳቢነት የጎደላቸውና አደገኛ የሆኑ በርካታ ድርጊቶች ፈጽመዋል። ለምሳሌ ያህል ጠጥተው ሲያሽከረክሩ ራሳቸውንና ሌሎችን አደጋ ላይ ጥለዋል፣ ለሌላ ሰው የትዳር ጓደኛ አግባብ ያልሆነ የፍቅር ስሜት በማሳየት ትዳሮችን አበላሽተዋል እንዲሁም ማስተዋል የጎደለው አልፎ ተርፎም ብልሹ የሆነ ንግግር ከመናገራቸውም በላይ ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ ድርጊት ፈጽመዋል። (ምሳሌ 23:33) የአልኮል መጠጦችን ከልክ በላይ መጠጣት በዛሬው ጊዜ የሰውን ልጅ ከለከፉት ጎጂ ማህበራዊ በሽታዎች ሁሉ የከፋው ነው መባሉ ተገቢ ነው። እንግዲያውስ አምላክ “ብዙ የወይን ጠጅ ከሚጠጡ . . . ጋር አትወዳጅ” ብሎ መምከሩ አያስደንቅም!—ምሳሌ 23:20

በገላትያ 5:19-21 ላይ ጳውሎስ ስካርንና ፈንጠዝያን የአምላክ መንፈስ ፍሬ ተቃራኒ ከሆኑት ‘የሥጋ ሥራዎች’ መካከል ጠቅሷቸዋል። የአልኮል መጠጦችን ከልክ በላይ መጠጣት አንድ ሰው ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና ያበላሽበታል። እንግዲያው ክርስቲያኖች በማንኛውም መልኩ የአልኮል መጠጦችን ከልክ በላይ ከመጠጣት መቆጠብ እንዳለባቸው ግልጽ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.11 የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ አገልጋዮች አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ከፍ ያሉትን የይሖዋ የአቋም ደረጃዎች በማክበር በማመዛዘን ችሎታቸውና በጠባያቸው ለመንጋው ምሳሌ መሆን ስለሚጠበቅባቸው ይህን መሥፈርት ሌሎች ክርስቲያኖችም በሥራ ሊያውሉት ይገባል።