የርችቶች መስህብ
የርችቶች መስህብ
ርችቶች የክብረ በዓላትንም ሆነ የኦሎምፒክ ጨዋታዎችን መክፈቻ ማድመቃቸው የተለመደ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ የነፃነትን ቀን፣ በፈረንሳይ የባስቲል ወህኒ ቤት የወደቀበትን ቀን እንዲሁም በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በአብዛኞቹ ዋና ዋና ከተሞች አዲስ ዓመትን ለማክበር የሚተኮሱ ርችቶች ሰማዩን በብርሃን ያንቆጠቁጡታል።
ይሁንና የሰው ልጅ በርችቶች መማረክ የጀመረው መቼ ነበር? እነዚህን አስደናቂ ትርዒቶች ለመፍጠር የተቻለውስ እንዴት ነው?
የምሥራቃውያን ባሕል
ርችቶችን የፈለሰፉት ቻይናውያን እንደሆኑ አብዛኞቹ የታሪክ ምሑራን ይስማማሉ። ከክርስቶስ ልደት በኋላ በአሥረኛው መቶ ዘመን፣ ምሥራቃውያን የኬሚስትሪ ባለሞያዎች ሶልትፒተር (ፖታሲየም ናይትሬት) የሚባለውን ንጥረ ነገር ከድኝና ከከሰል ጋር በማቀላቀል የሚፈነዳ ውሕድ መፍጠር እንደሚቻል አወቁ። ይህን የሚፈነዳ ንጥረ ነገር ወደ አውሮፓ ያመጡት እንደ ማርኮ ፖሎ ያሉት ምዕራባውያን አሳሾች ወይም የአረብ ነጋዴዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። በ14ኛው መቶ ዘመን በአውሮፓ በርችቶች አስደናቂ ትርዒት ይታይ ነበር።
ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቶቹን ውብ ትርዒቶች ያስገኘው ዱቄት የአውሮፓን ታሪክም ለውጦታል። የኋላ ኋላ ባሩድ ተብሎ የተጠራውን ይህን ንጥረ ነገር ወታደሮች ጥይቶችን ለማስፈንጠር፣ የግንብ ግድግዳዎችን ለማፍረስና የፖለቲካ ኃይሎችን ለማውደም ተጠቀሙበት። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል:- “በአውሮፓውያን መካከለኛ ዘመን፣ በምዕራቡ ዓለም ፈንጂዎች በስፋት ለጦርነት መዋላቸውን ተከትሎ ርችቶችም ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር። በአውሮፓ ለጦርነት የሚውል ፈንጂ የሚሠራው ባለሞያ የድልና የሰላም በዓላትን ለማክበር ርችቶች እንዲያዘጋጅ ግፊት ይደረግበት ነበር።”
እስከዚያ ጊዜ ድረስ ቻይናውያን ባሩድ ለጥፋት መሣሪያነት ሊውል መቻሉን እምብዛም ትኩረት የሰጡት አይመስልም። በ16ኛው መቶ ዘመን በቻይና የነበረው ማቴኦ ሪትቺ የሚባል ጣሊያናዊ ሚስዮናዊ እንደሚከተለው በማለት ጽፎ ነበር:- “ቻይናውያን ጠመንጃና መድፍ መጠቀም ስለማያውቁ ባሩድን ለጦርነት እምብዛም አይጠቀሙበትም። ይሁን እንጂ በሕዝብ ፊት በሚቀርቡ ግጥሚያዎች ላይ እንዲሁም በበዓላት ቀን የሚያሳዩትን ርችት ለመሥራት ሶልትፒተር የሚባለውን ንጥረ ነገር በብዛት ይጠቀሙበት ነበር። ቻይናውያን እንዲህ ያለው ትርዒት እጅግ ያስደስታቸዋል። . . . ርችቶችን በመሥራት ረገድ ያላቸው ችሎታ በእርግጥም የሚደነቅ ነው።”
ርችቶችን የሚሠሩት እንዴት ነው?
ቀደም ባሉት ዘመናት ርችቶችን ይሠሩ የነበሩ ሰዎች የተለያዩ ዓይነት ትርዒቶችን ለማዘጋጀት ጥሩ ችሎታና ድፍረት እንደጠየቀባቸው ጥርጥር የለውም። ከፍ ከፍ ያሉት የባሩድ ቅንጣቶች ቀስ ብለው የሚቀጣጠሉ ሲሆን ደቃቆቹ ቅንጣቶች ግን ሲነድዱ እንደሚፈነዱ ተገነዘቡ። ርችቶችን ለመሥራት በአንድ ወገን ቀዳዳው የተደፈነ ረዥም የቀርከሃ ዘንግ ወይም የወረቀት ቱቦ ከተዘጋጀ በኋላ በታችኛው ጫፍ በኩል እምብዛም ደቃቅ ያልሆኑ የባሩድ ቅንጣቶች ይጨመሩበታል። ባሩዱ ሲለኮስ ክፍት ከሆነው የቱቦው ጫፍ በኩል በፍጥነት የሚወጣው ጋዝ ቀርከሃው ወደ ሰማይ እንዲወነጨፍ ያደርገዋል። (በዛሬው ጊዜ ጠፈርተኞችን ወደ ሕዋ ለመላክ የሚሠራበት መሠረታዊ ደንብ ይኸው ነው።) ሁሉም ነገር እንደታሰበው ከተከናወነ ቀርከሃው የመጨረሻው ከፍታ ድረስ ከተስፈነጠረ በኋላ እንዲፈነዳ ሲባል በላይኛው ጫፍ ላይ ደቃቅ ባሩድ ይጨመርበታል።
ርችቶች ከተፈበረኩበት ጊዜ አንስቶ ባለፉት መቶ ዘመናት እምብዛም ለውጥ አላሳዩም። ቢሆንም አንዳንድ መሻሻሎች ተደርገዋል። መጀመሪያ ላይ የሩቅ ምሥራቅ ሰዎች የሚያውቁት ነጭ ወይም ወርቅማ ቀለም ያላቸውን ርችቶች
መሥራት ብቻ ነበር። ጣሊያናውያን ለርችቶች ህብረ ቀለማት ጨመሩላቸው። በ19ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ጣሊያናውያን ባሩድና ፖታሲየም ክሎሬት ሲደባለቁ የሚፈጠረው ውሕድ በከፍተኛ ሙቀት ስለሚቃጠል ነበልባሉን እንደሚያቀልመው ደረሱበት። በዛሬው ጊዜ ቀይ የብርሃን ብልጭታ ለመፍጠር በባሩዱ ላይ ስቶሮንቲየም ካርቦኔት ይጨመራል። ብሩሕ ነጭ ቀለም የሚፈጠረው ታይታኒየም፣ አሉሚኒየምና ማግኒዚየም በመጨመር ሲሆን ሰማያዊ ቀለም ያለው ርችት የሚፈጠረው የመዳብ ውሕዶችን በመቀላቀል፣ አረንጓዴ ቀለም ለመፍጠር ባሪየም ናይትሬት በመጨመር እና ቢጫ ቀለም ያለው የብርሃን ብልጭታ ለመፍጠር ደግሞ ሶዲየም ኦክሳሌት ያለበት ቅልቅል በመጠቀም ነው።ኮምፒውተሮችም ለርችቶች ድምቀት ተጨማሪ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ዛሬ ርችቶችን በእጅ በመለኮስ ፈንታ አንድ ዓይነት የሙዚቃ ድምፅ ሲሰማ ርችቶቹም አብረው እንዲተኮሱ ለማድረግ በኮምፒውተር አማካኝነት ማስተካከል ተችሏል።
ከሃይማኖት ጋር ያለው ግንኙነት
ሪትቺ የተባለው ሚስዮናዊ እንደገለጸው ርችቶች ከቻይና ሃይማኖታዊ በዓል አከባበር ተነጥለው የማይታዩ ነገሮች ነበሩ። ፖፑላር ሜካኒክስ (እውቅ ሜካኒኮች) የተሰኘው መጽሔት እንደሚገልጸው “ቻይናውያን ርችቶችን የፈለሰፉት በአዲስ ዓመትና በሌሎች ክብረ በዓላት ላይ አጋንንትን ለማባረር” ነበር። ሃወርድ ሃርፐር ዴይስ ኤንድ ከስተምስ ኦቭ ኦል ፌዝስ (የሁሉም ሃይማኖቶች በዓላትና ባሕሎች) በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንደሚከተለው ብለዋል:- “ከጥንቶቹ የአረማውያን ዘመን አንስቶ ሰዎች ታላላቅ ሃይማኖታዊ ወቅቶችን በሚያከብሩበት ጊዜ ችቦና ደመራ ያበሩ ነበር። ስለዚህ በሃይማኖታዊ በዓላቸው ወቅት ድንቅ ቀለማት ያላቸውና በሰማይ ላይ ራሳቸው የሚንቀሳቀሱ የሚመስሉ ርችቶችን ቢጠቀሙ ምንም አያስደንቅም።”
ርችቶች በስመ ክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት ካገኙ በኋላ የርችት ሠሪዎች የቅዱሳን ጠባቂ እንዳላቸው ይታመን ጀመር። ዘ ኮሎምቢያ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል:- “[ቅድስት ባርባራ] ክርስቲያን በመሆኗ ምክንያት አባቷ በግንብ ውስጥ እንደዘጋባትና እንደገደላት ይነገራል። ከዚያም አባትየው በመብረቅ ተመትቶ ሞተ። ቅድስት ባርባራም አባቷ በተመሳሳይ ነገር ስለተገደለ የጠመንጃና የርችት ሠሪዎች እንዲሁም የተጠቃሚዎች ጠባቂ እንደሆነች ተደርጋ ተቆጠረች።”
ብዙ ገንዘብ የሚፈስበት
ሃይማኖታዊም ሆነ ዓለማዊ ክብረ በዓላት ላይ ሕዝቡ ሰፊና የተሻለ የርችቶች ትርዒት ለመመልከት በጣም ይፈልጋል። ሪትቺ በ16ኛው መቶ ዘመን በቻይና የተደረገ አንድ የርችቶች ትርዒትን በሚመለከት እንዲህ በማለት ጽፏል:- “በናንጂንግ ሳለሁ፣ የዓመቱን የመጀመሪያ ወር በሚያከብሩበት በዓል ላይ የርችቶች ትርዒት ተመልክቼ ነበር፤ ከፍተኛ ግምት ለሚሰጡት ለዚህ በዓል በተዘጋጀው ትርዒት ላይ ያዋሉት ባሩድ ለበርካታ ዓመታት ትልቅ ጦርነት ለማካሄድ የሚበቃ ነው።” ይህ ትርዒት የጠየቀውን ወጪ በሚመለከትም “ለርችት ሲባል የፈለገውን ያህል ቢወጣ ደንታ ያላቸው አይመስልም” ብሏል።
በእነዚህ መቶ ዘመናት ሁሉ ሰዎች ለርችቶች ባላቸው አመለካከት ረገድ ምንም የታየ ለውጥ የለም። በ2000፣ በሲድኒ ሃርበር ብሪጅ በተደረገ አንድ በዓል ላይ ብቻ በዚህ የባሕር ዳርቻ ላይ የተሰበሰቡ አንድ ሚሊዮን ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ ተመልካቾችን ለማዝናናት 20 ቶን ርችቶች ተተኩሰዋል። በዚያው ዓመት በዩናይትድ ስቴትስ 70,000,000 ኪሎ ግራም ለሚሆኑ ርችቶች 625 ሚሊዮን ዶላር ወጥቷል። እውነትም የተለያየ ባሕል ያላቸው ሰዎች አሁንም በርችቶች የሚማረኩ ሲሆን ዛሬም ቢሆን “ለርችት ሲባል የፈለገውን ያህል ቢወጣ ደንታ ያላቸው አይመስልም” ሊባል ይችላል።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]