በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ግብርን በተመለከተ የሚሰማው ቅሬታ እየጨመረ መጥቷል

ግብርን በተመለከተ የሚሰማው ቅሬታ እየጨመረ መጥቷል

ግብርን በተመለከተ የሚሰማው ቅሬታ እየጨመረ መጥቷል

“የለፋሁበትንና የደከምኩበትን እነጠቃለሁ።”—በ2300 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ የተነገረ የባቢሎን ምሳሌ

“በዚህ ዓለም የሞትንና የግብርን ያህል አይቀሬ የሆነ ነገር የለም።”—የዩናይትድ ስቴትስ መሪ የነበሩት ቤንጃሚን ፍራንክሊን የተናገሩት፣ 1789

ሩበን አሻሻጭ ሆኖ ይሠራል። በየዓመቱ ለፍቶ ካገኘው ገቢ ውስጥ ሢሶ የሚሆነው በግብር ስም ይጠፋበታል። “ይህ ሁሉ ገንዘብ ምን እንደሚደረግበት አይገባኝም” በማለት ምሬቱን ይገልጻል። “መንግሥት ይህን ሁሉ ገንዘብ ከደመወዛችን ላይ እየቆረጠ ለእኛ የሚሰጠን ግልጋሎት ግን ከምንጊዜውም ይበልጥ እየቀነሰ መጥቷል።”

ወደድንም ጠላን፣ ግብር መክፈል የሕይወታችን ክፍል ነው። ቻርልዝ አዳምስ የተባሉት ጸሐፊ “የሠለጠነ ማኅበራዊ ኑሮ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ መንግሥታት በተለያዩ መንገዶች ግብር ሲያስከፍሉ ኖረዋል” ብለዋል። ግብር መክፈል ብዙ ጊዜ ቅሬታ የቀሰቀሰ ሲሆን አንዳንድ ጊዜም ዓመጽ አስነስቷል። የጥንቶቹ ብሪታንያውያን ከሮማውያን ጋር የተዋጉት “ግብር በራሳችን ላይ ተጭኖብን ከምንኖር ብንሞት ይሻለናል!” በሚል መርሕ ነበር። በፈረንሳይ ግብር ሰብሳቢዎች የተሠየፉበትን የፈረንሳይ አብዮት የቀሰቀሰው ሕዝቡ ለጨው ግብር ያደረበት ጥላቻ ነበር። በግብር ላይ ማመጽ ዩናይትድ ስቴትስ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛትነት ነፃ ለመውጣት ባደረገችው ጦርነትም ሚና ተጫውቷል።

እንግዲያውስ በግብር ላይ ማመጽ እስካሁንም ድረስ ያልበረደ ችግር ሆኖ መቀጠሉ አያስደንቅም። በታዳጊ አገሮች ያሉት የግብር ሥርዓቶች “ቅልጥፍና የጎደላቸው” እና “ፍትሐዊም ያልሆኑ” እንደሆኑ ጠበብት ይናገራሉ። በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ አንድ ሰው እንደተናገሩት “ጥሩ ችሎታ ላላቸው ያስተዳደር ሠራተኞች እንኳን ሳይቀር ላያያዝ አስቸጋሪ የሆኑ ከ300 በላይ ያገር ውስጥ ግብር ማስገቢያዎች” ያሉት አንድ ድሃ አፍሪካዊ አገር አለ። “ተገቢ የግብር አሰባሰብና ቁጥጥር ዘዴዎች አንድም ባለመኖራቸው አለዚያም በሥራ ላይ ባለመዋላቸው . . . በሚሰበሰበው ግብር አላግባብ የመጠቀም አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ።” በአንድ የእስያ አገር ‘የአካባቢው ባለ ሥልጣናት ለአገሩ መንግሥት ገቢ ለማስገኘት ወይም የራሳቸውን ኪስ ለማደለብ ሲሉ ሙዝ ከሚያበቅሉና አሳማ ከሚያርዱ ሰዎች ሳይቀር ብዙ ሕገወጥ ክፍያዎችን ከሕዝብ እንደሚቀበሉ’ የቢቢሲ ዜና ዘግቧል።

በሀብታሞችና በድሆች መካከል ያለው ልዩነትም ግብር መክፈልን በተመለከተ ያለውን ቅሬታ ያባብሰዋል። አፍሪካ ሪካቨሪ የተሰኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣው ጽሑፍ ሲናገር “ባደጉትና በማደግ ላይ ባሉት አገሮች መካከል ካሉት ብዙ ኢኮኖሚያዊ ልዩነቶች ውስጥ አንዱ ያደጉት አገሮች ለገበሬዎቻቸው የገንዘብ ድጎማ የሚያደርጉ ሲሆን በማደግ ላይ ያሉት አገሮች ግን ከገበሬዎቻቸው ግብር ይሰበስባሉ። . . . የዓለም ባንክ ያደረገው ጥናት የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ለገበሬዎቹ ያደረገው የገንዘብ ድጎማ ብቻ ምዕራብ አፍሪካ ጥጥ ወደ ውጭ በመላክ ከምታገኘው ዓመታዊ ገቢ ላይ 250,000,000 ዶላር ቀንሶባታል” ብሏል። በዚህም ምክንያት በማደግ ላይ ባሉት አገሮች ያሉ ገበሬዎች መንግሥታቸው ከዚያችው አነስተኛ ገቢ ላይ ግብር ሲወስድ ቅሬታ ያድርባቸዋል። በአንድ የእስያ አገር የሚገኝ ገበሬ “የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ወደ እኛ የሚመጡት ገንዘብ አምጡ ሊሉ መሆኑን እናውቃለን” ብሏል።

በደቡብ አፍሪካም በቅርቡ መንግሥት በገበሬዎች ላይ የመሬት ግብር ሲጥል በተመሳሳይ ቅር ተሰኝተዋል። ገበሬዎቹ መንግሥትን በሕግ እንፋረዳለን ሲሉ ዝተዋል። ግብሩ “በገበሬዎች ላይ ኪሣራና ተጨማሪ ሥራ አጥነት ያስከትላል” በማለት የገበሬዎቹ ቃል አቀባይ ተናግሯል። ግብር እስከዛሬም ድረስ አልፎ አልፎ ዓመጽ መቀስቀሱ አልቀረም። የቢቢሲ ዘገባ እንደሚገልጸው “ባለፈው ዓመት በእስያ ከመጠን በላይ የሆነ ግብር አንከፍልም ብለው ያመጹ ገበሬዎች ያሉባትን መንደር ፖሊሶች በከበቡ ጊዜ ሁለት ገበሬዎች ተገድለዋል።”

ይሁንና ግብር መክፈል የሚጠሉት ድሆች ብቻ አይደሉም። በደቡብ አፍሪካ በተደረገ ጥናት እንደተደረሰበት ባለጠጋ የሆኑ ብዙ ግብር ከፋዮች “ተጨማሪ ግብር ባለመክፈላቸው ምክንያት መንግሥት የሚሰጣቸውን አስፈላጊ ግልጋሎቶች ለማሻሻል እንደሚያዳግተው ቢገነዘቡም እንኳን ተጨማሪ ግብር ለመክፈል ፈቃደኞች አይደሉም።” በሙዚቃው፣ በፊልሙ፣ በስፖርቱና በፖለቲካው መስክ ስመ ጥር የሆኑ ሰዎች ግብር ከመክፈል ለመሸሽ በመሞከራቸው ምክንያት የዜና ርዕስ ሆነዋል። ዘ ዲክላይን ኤንድ ፎል ኦቭ ዚ ኢንካም ታክስ (የገቢ ግብር ማሽቆልቆልና መውደቅ) የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚናገረው “የሚያሳዝነው ነገር ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ሥልጣኖቻችን፣ ፕሬዚዳንቶቻችንም ጭምር ተራ ዜጎች የግብር ሕጉን እንዲታዘዙ የሚያበረታታ ጥሩ ምሳሌነት አላሳዩም።”

ምናልባት አንተም ግብር ፍትሐዊነት የጎደለውና ከአቅም በላይ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ታዲያ ግብር መክፈልን እንዴት ልትመለከተው ይገባል? ለመሆኑ የሚሰበሰበው ግብር የሚሰጠው ግልጋሎት ይኖራል? የግብር አከፋፈል ሥርዓቶች ይህን ያህል ውስብስብ የሆኑትና ፍትሐዊነትም የጎደላቸው የሚመስሉት ለምንድን ነው? የሚቀጥሉት ርዕሶች እነዚህን ጥያቄዎች አንድ በአንድ ይመረምራሉ።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የግብር ጫናው የሚወድቀው በድሆች ላይ ሊሆን ይችላል

[ምንጭ]

Godo-Foto