በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ግብር “የሠለጠነ ኅብረተሰብ” እንዲኖር ሲባል የሚከፈል ነው?

ግብር “የሠለጠነ ኅብረተሰብ” እንዲኖር ሲባል የሚከፈል ነው?

ግብር “የሠለጠነ ኅብረተሰብ” እንዲኖር ሲባል የሚከፈል ነው?

“ግብር የምንከፍለው የሠለጠነ ኀብረተሰብ እንዲኖር ስንል ነው።”ዋሽንግተን ዲ.ሲ. በሚገኝ የአገር ውስጥ ገቢ አገልግሎት ሕንፃ ላይ የተቀረጸ ጽሑፍ

መንግሥታት ግብር መክፈል ደስ የማይል ነገር ቢሆንም “የሠለጠነ ኅብረተሰብ” እንዲኖር ከተፈለገ የግድ መከፈል አለበት የሚል አቋም አላቸው። ከዚህ አስተያየት ጋር የምትስማማ ሆንክም አልሆንክ፣ ግብር መክፈል የሚጠይቀው ዋጋ በአብዛኛው ከፍተኛ መሆኑ አሌ የሚባል አይደለም።

የግብር ዓይነቶች በሁለት ሊከፈሉ ይችላሉ። እነሱም ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ የግብር ዓይነቶች ናቸው። ቀጥተኛ ግብር ከሚሰበሰብባቸው ዘርፎች ውስጥ ከገቢ ግብር፣ ማለትም ከሥራ፣ ከንግድ፣ ከተቀማጭ ገንዘብ እንዲሁም በሕግ ከተቋቋሙ ማኅበራትና እንደ ቤት ካሉት ንብረቶች ላይ የሚቀረጥ ቀረጥ ይገኝበታል። ከእነዚህም ብዙ ቅሬታ የሚያሳድረው የገቢ ግብር ሳይሆን አይቀርም። በተለይም የምትከፍለው ግብር በምታገኘው ገቢ ልክ ከፍ እያለ እንዲሄድ የሚያደርግ የግብር አሰባሰብ ሥርዓት ተግባራዊ በሆነባቸው አገሮች ቅሬታው በዚያው ልክ ከፍተኛ ነው። አንዳንድ የግብር ሥርዓቶችን የሚተቹ ሰዎች አዳጊ የገቢ ግብር ታታሪነትንና ስኬትን ዋጋ የሚያሳጣ ነው ብለው ይከራከራሉ።

ኦኢሲዲ ኦብዘርቨር የተሰኘው የኢኮኖሚያዊ ትብብርና ልማት ድርጅት ጽሑፍ እንደሚያሳስበን ለማዕከላዊ መንግሥት ከሚከፈለው የገቢ ግብር በተጨማሪ “ገቢ የሚያገኙ ሰዎች ለወረዳ፣ ለዞንና ለአውራጃ ወይም ለክፍለ ሀገር ግብር እንዲያስገቡ ሊጠየቁ ይችላሉ። በቤልጅየም፣ በካናዳ፣ በአይስላንድ፣ በኮሪያ፣ በኖርዲክ አገሮች፣ በስፔይን፣ በስዊዘርላንድና በዩናይትድ ስቴትስ ያለው አሠራር ይኸው ነው።”

ተዘዋዋሪ ግብር የሚባለው የሽያጭ ግብር፣ የመጠጥና የሲጋራ እንዲሁም የጉምሩክ ግብር የመሳሰሉትን ይጨምራል። በእነዚህ ነገሮች ላይ የሚጫነው ግብር እንደ ቀጥተኛው ግብር በግልጽ የሚታይ ባይሆንም በተለይ ለድሃው የኅብረተሰብ ክፍል ከባድ ሸክም ነው። ጃያሊ ጎሽ የተባሉት ጸሐፊ በሕንድ ውስጥ አብዛኛውን ግብር የሚከፍሉት ንዑስ ከበርቴዎችና ሀብታሞች ናቸው የሚባለው ነገር መሠረት የሌለው መሆኑን በሕንድ በሚታተመው ፍሮንትላይን በተሰኘው መጽሔት ላይ ባወጡት ጽሑፍ ገልጸዋል። ጎሽ ሲናገሩ “የሕንድ መንግሥት ከሚሰበስበው ግብር ውስጥ ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው ተዘዋዋሪ ግብር ነው። . . . ከሀብታሞቹ ይልቅ አብዛኛውን ገቢያቸውን ለግብር የሚያወጡት ድሆች ናቸው።” ይህን ያህል ልዩነት ሊፈጠር የቻለው እንደ ሣሙናና ምግብ በመሳሰሉ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ ከፍተኛ ቀረጥ በመጣሉ እንደሆነ ግልጽ ነው።

ታዲያ መንግሥታት የሚሰበስቡትን ይህን ሁሉ ገንዘብ ምን ያደርጉበታል?

ገንዘቡ ምን ላይ ይውላል?

እርግጥ ነው፣ መንግሥታት አስፈላጊ የሆኑ ግልጋሎቶችን ለማንቀሳቀስና ለማቅረብ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ይጠይቅባቸዋል። ለምሳሌ ያህል በፈረንሳይ ከአራት ሰዎች ውስጥ አንዱ በመንግሥት መሥሪያ ቤት ይሠራል። ይህም መምህራንን፣ የፖስታ ሠራተኞችን፣ የሙዚየምና የሆስፒታል አስተዳደሮችን፣ ፖሊስንና ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞችን ይጨምራል። ለእነዚህ ሁሉ ደመወዝ ለመክፈል ግብር መሰብሰብ ያስፈልጋል። በተጨማሪም የሚሰበሰበው ግብር ለመንገድ፣ ለትምህርት ቤቶች፣ ለሆስፒታሎች፣ ለቆሻሻ ማስወገጃ፣ ለፖስታ አገልግሎትና ለመሳሰሉት ይውላል።

ለጦር ሠራዊት የሚያስፈልገው ወጪም ግብር እንዲሰበሰብ የሚያስገድድ ሌላው ምክንያት ነው። ሀብታም በነበሩ ብሪታንያውያን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የገቢ ግብር የተጣለባቸው በ1799 ከፈረንሳይ ጋር የተደረገውን ውጊያ በገንዘብ እንዲደግፉ ነበር። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ግን የብሪታንያ መንግሥት የሚደርስባቸውን የገቢ ግብር እንዲከፍሉ ሠራተኛውን ክፍል መጠየቅ ጀመረ። በአሁኑ ወቅት በሰላሙም ጊዜ እንኳን ሳይቀር የአገሩን ወታደራዊ ተቋም በገንዘብ መደገፍ በጣም ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል። የስቶክሆልሙ ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ተቋም እንደገመተው በ2000 የዓለም ወታደራዊ ወጪ 798 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል።

ማኅበራዊ ችግሮችን ለማረቅ ሲባል የሚጣሉ ግብሮች

በተጨማሪም ግብሮች “ማኅበራዊ ችግሮችን ለማረቅ” ማለትም አንዳንድ አድራጎቶችን ለማበረታታት ወይም ለማስተው እንደመሣሪያ ሆነው ያገለግላሉ። ለምሳሌ ያህል የአልኮል መጠጦችን መቅረጥ ከልክ በላይ መጠጣትን ለመግታት ይረዳል ተብሎ ይታመናል። በመሆኑም በብዙ አገሮች ከቢራ ሽያጭ 35 በመቶው ይቀረጣል።

በትንባሆ ላይም ከፍተኛ ቀረጥ ተጥሏል። በደቡብ አፍሪካ ከአንድ ፓኬት ሲጋራ ዋጋ ከ45 እስከ 50 በመቶ የሚሆነው ይቀረጣል። ይሁን እንጂ አንድ መንግሥት እንዲህ ዓይነት ቀረጥ የሚጥለው ለዜጎች ደኅንነት በማሰብ ብቻ ላይሆን ይችላል። ኬነት ዋርነት ፎረይን ፖሊሲ በተባለው መጽሔት ላይ እንደጻፉት ትንባሆ “ከሽያጩ በመቶ ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር፣ በቀረጥ መልክ ደግሞ በየዓመቱ በርካታ ቢሊዮን ዶላር የሚያስገኝ ጠንካራ የኢኮኖሚ ኃይል ነው።”

ግብር ማኅበራዊ ችግሮችን ለማረቅ እንደሚሰራበት የሚያሳይ በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ የተከናወነ አንድ ሁኔታ እናገኛለን። የዩናይትድ ስቴትስ ሕግ አውጪዎች እጅግ የናጠጡ ባለጠጋዎች ሀብት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሻገረ እንዳይቀጥል ለማድረግ ፈለጉ። እንዴት? በርስት ላይ የሚጣል ግብር ደነገጉ። አንድ ባለጠጋ ሰው ሲሞት አብዛኛው ያካበተው ሀብት በግብር ይወሰዳል። የዚህ ዓይነቱ ግብር ደጋፊዎች “ይህ ዓይነቱ ግብር ሀብት ከጥቂት ባላባታዊ ቤተሰቦች እጅ ወጥቶ ወደ ብዙኃኑ እንዲከፋፈል ያስችላል” ይላሉ። ይህ እውነት ሊሆን ቢችልም ባለጠጋ ግብር ከፋዮች ግን ከዚህ ዓይነቱ ግብር ለማምለጥ የሚጠቀሙባቸው በርካታ ዘዴዎች አሏቸው።

ዛሬም ቢሆን ግብር እንደ አካባቢ ደኅንነት የመሰሉትን ማኅበራዊ ጉዳዮች ለማራመድ ያገለግላል። ዚ ኢንቫይረመንታል ማጋዚን “በቅርቡ ዘጠኝ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች በአብዛኛው የአየር ብክለትን ለመቀነስ ሲሉ የአካባቢ ደኅንነት ግብር ጥለዋል” ሲል ዘግቧል። ከፍ ሲል የተጠቀሰው አዳጊ የገቢ ግብርም ማኅበራዊ ችግሮችን ለመፍታት ሲባል ከሚጣሉ የግብር ዓይነቶች አንዱ ነው። ይህ ዓይነቱ ግብር የሚጣለው በሀብታሞችና በድሆች መካከል ያለውን የኑሮ መራራቅ ለማጥበብ ሲባል ነው። አንዳንድ መንግሥታት ደግሞ ገንዘባቸውን ለበጎ አድራጎት ለሚያውሉ ወይም ልጆች ላሏቸው ወላጆች የግብር ቅነሳ ያደርጋሉ።

የግብር ሕግ ይህን ያህል ውስብስብ የሆነው ለምንድን ነው?

ሕግ አውጪዎች አዲስ ዓይነት ግብር በሚያጸድቁበት ጊዜ ምንም ዓይነት የማጭበርበሪያ ክፍተት ላለመተው ይጠነቀቃሉ። ለጥፋት ሊዳረግ የሚችለው ገንዘብ ቀላል እንዳልሆነ አትዘንጋ። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? የግብር ሕጎች በጣም የተወሳሰቡና ለተራ ሰው የማይገቡ ሆነዋል። ታይም መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ የዩናይትድ ስቴትስ የግብር ሕግ ይህን ያህል ውስብስብ የሆነው ግብር የሚከፈልበት ገቢ ምን እንደሆነ ሠፊ ትርጉምና ማብራሪያ መስጠት በማስፈለጉ እንደሆነ ገልጿል። “ከግብር ነጻ የሚያስደርጉና ግብር የሚያስቀንሱ በጣም ብዙ ምክንያቶች መኖራቸውም” ለሕጉ መወሳሰብ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ በጣም የተወሳሰበ የግብር ሕግ ያላት አገር ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ አይደለችም። በቅርቡ አንድ ላይ ተጠቃልሎ የወጣ የብሪታንያ የግብር ሕግ አሥር ጥራዞችና 9,521 ገጾች አሉት።

በሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ የግብር ፖሊሲ ምርምር ቢሮ የሚከተለውን ዘግቧል:- “በየዓመቱ የዩናይትድ ስቴትስ ግብር ከፋዮች የገቢ ግብር መክፈያ ቅጾችን ለመሙላት ብቻ ሦስት ቢሊዮን ሰዓት ያጠፋሉ። . . . በአጠቃላይ የዩናይትድ ስቴትስ ግብር ከፋዮች የግብር መክፈያ ቅጾችን በመሙላት የሚያጠፉት ጊዜና ገንዘብ በዓመት 100 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ሲሆን ይህም ከሚሰበሰበው ጠቅላላ ግብር 10 በመቶ ይሆናል። ግብር ለመክፈል ሲባል ይህን የሚያክል ከፍተኛ ኪሣራ የሚደርሰው የገቢ ግብር ሕጉ በጣም ውስብስብ በመሆኑ ነው።” በመጀመሪያው ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሰው ሩበን እንዲህ ብሏል:- “የግብር ጉዳዮቼን ራሴው ለማከናወን እሞክር ነበር። ይሁን እንጂ ብዙ ጊዜ የሚፈጅ ከመሆኑም በላይ ሁልጊዜ መክፈል ከሚገባኝ በላይ ግብር እየከፈልኩ እንዳለሁ ይሰማኝ ነበር። ስለዚህም አሁን የግብር ጉዳዮቼን እንዲከታተልልኝ የሂሣብ ሠራተኛ ቀጥሬያለሁ።”—በገጽ 18 ላይ የሚገኘውን “የግብር ሕጎችን ማክበር” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ግብር ከፋዮች፣ ግብር አምታቾችና ከግብር የሚያመልጡ

አብዛኞቹ ሰዎች ቢያንስ ቅር እያላቸውም ቢሆን ግብር መክፈል ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ መሆኑን ይቀበላሉ። በአንድ ወቅት የብሪታንያ የአገር ውስጥ ገቢ መሥሪያ ቤት ኃላፊ “ግብር መክፈል የሚያስደስተው ሰው አለ ለማለት ባይቻልም ግብር ባይኖር ይሻለን ነበር ብሎ ለመከራከር የሚደፍርም ሰው አይኖርም” ብለዋል። በአንዳንዶች ግምት መሠረት በዩናይትድ ስቴትስ 90 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች የግብር ሕጉን ያከብራሉ። አንድ ባለ ሥልጣን “ብዙውን ጊዜ የግብር ሕግ የሚጣሰው በሕጉ ላይ ለማመጽ በመፈለግ ሳይሆን ከሕጉና ከሕጉ አፈጻጸም በሚመነጩ ችግሮች ምክንያት ነው” በማለት አምነዋል።

ቢሆንም ብዙዎች አንዳንድ የግብር ዓይነቶችን ከመክፈል የሚያመልጡበት መንገድ ማግኘታቸው አልቀረም። ለምሳሌ በዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ ያለውን ተመልከት:- “ብዙ የንግድ ድርጅቶች በቀረጥ ማስቀነሻ ሕጎችና በረቀቁ የሂሣብ አያያዝ ዘዴዎች በመጠቀም መክፈል የሚገባቸውን ብዙ ገንዘብ ለራሳቸው ያስቀራሉ።” ጽሑፉ አንድ በጣም የረቀቀ ዘዴ በምሳሌነት በመጥቀስ ይቀጥላል:- “በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ አንድ ድርጅት በጣም አነስተኛ ግብር በሚከፈልበት አገር ዋና መሥሪያ ቤቱን ያቋቁማል። ከዚያም በዩናይትድ ስቴትስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በውጭ አገር የተቋቋመው ኩባንያ ቅርንጫፍ ያደርጋል።” በዚህ መንገድ ኩባንያው “በዋና መሥሪያ ቤቱ ያለው ንብረት ከጠረጴዛና ወንበር ያላለፈ እንኳን ቢሆንም” እስከ 35 በመቶ የሚደርሰውን የዩናይትድ ስቴትስ ቀረጥ ከመክፈል ያመልጣል።

ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ግብር ከመክፈል የሚያመልጡ አሉ። በአንድ የአውሮፓ አገር ከግብር ማምለጥ “እንደ ብሔራዊ ስፖርት” እንደሚታይ ተገልጿል። በዩናይትድ ስቴትስ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከ25 እስከ 29 ዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ወንዶች መካከል ሙሉ ገቢን አስታውቆ ግብር አለመክፈል ስህተት ነው ብለው የሚያምኑት 58 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። የጥናቱ አጠናቃሪዎች “ሪፖርቱ ማኅበረሰባችን ሊኩራራበት የሚችል የሥነ ምግባርና የሞራል አቋም እንደሌለው ያመለክታል” ብለዋል። በሜክሲኮ ከግብር የሚሸሹ ግብር ከፋዮች 35 በመቶ ደርሰዋል።

ይሁን እንጂ ሰዎች በአብዛኛው ግብር መክፈል አስፈላጊ መሆኑን ይቀበላሉ እንዲሁም ያለ ቅሬታ የድርሻቸውን ይከፍላሉ። ቢሆንም ጢባርዮስ ቄሣር ተናግሮታል የሚባለው ዝነኛ አባባል ትልቅ እውነተኝነት አለው። “ጥሩ እረኛ የመንጋውን ፀጉር ይሸልታል እንጂ ቆዳቸውን አይገፍም።” የግብር ሥርዓቱ ከልክ በላይ እንደተጫነህ፣ ፍትሕ የጎደለው እንደሆነና በጣም የተወሳሰበ እንደሆነ የሚሰማህ ከሆነ ግብር መክፈልን እንዴት ልትመለከተው ይገባል?

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ወደ ሌላ አገር ከመሄድህ በፊት ቆም ብለህ አስብ!

የግብር ሥርዓቶች ከአገር ወደ አገር ይለያያሉ። እንዲያውም በአንድ አገር ውስጥ እንኳን በአንድ አካባቢ ያለው የገቢ ግብር ሥርዓት ከሌላው አካባቢ የተለየ ሊሆን ይችላል። ታዲያ የግብሩ ምጣኔ አነስተኛ ወደሆነ አካባቢ ሄዶ መኖር የተሻለ ይሆናል? ሊሆን ይችላል። ግን ከመሄድህ በፊት ቆም ብለህ አስብ።

ለምሳሌ በኦኢሲዲ ኦብዘርቨር ላይ የወጣ ጽሑፍ ችግሩ በመሠረታዊ የገቢ ግብር ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቀር እንዳልሆነ አንባቢዎቹን ያሳስባል። እንዲህ ይላል:- “አንድ ግብር ከፋይ የሚከፍለው ጠቅላላ መጠን በተለያዩ ተቀናሽ ሂሣቦች ምክንያት ሊቀንስ ወይም ሊጨምር ይችላል።” ለምሳሌ አንዳንድ አገሮች “በጣም ዝቅተኛ የሆነ የገቢ ግብር ምጣኔ አላቸው። ይሁን እንጂ ምንም ዓይነት የግብር ቅናሽ ሕግ አይኖራቸው ይሆናል።” በዚህ የተነሣ ግብር ከፋዩ ከፍተኛ የግብር ምጣኔ ቢኖረውም ከግብር ነጻ የሚያደርጉና የግብር ቅናሽ የሚያስገኙ ሕጎች ባሉት አገር ይከፍል ከነበረው ግብር በላይ ሊከፍል ይችላል።

በዩናይትድ ስቴትስ አንዳንዶች የገቢ ግብር ወደማይከፈልበት ግዛት ለመዛወር ያስባሉ። ይሁን እንጂ ይህን ማድረጋቸው ገንዘባቸውን ያድንላቸው ይሆን? ኪፕሊንገርስ ፐርሰናል ፋይናንስ እንደሚለው ከሆነ አያድንላቸውም። “አብዛኛውን ጊዜ የገቢ ግብር የማያስከፍሉ ግዛቶች ከፍ ያለ የንብረት ግብር፣ የሽያጭ ቀረጥና ሌላ ዓይነት ቀረጥ በማስከፈል የገቢ ግብሩን እንደሚያካክሱ በጥናታችን ማወቅ ችለናል” ብሏል።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የግብር ሕጎችን ማክበር

ለብዙዎቻችን ግብር መክፈል ብዙ ውጥረት የሚፈጥርና ከባድ ነገር ነው። ስለሆነም ንቁ! አንድ የግብር ባለሞያ ተግባራዊ ምክሮች እንዲሰጠን ጠይቋል።

“ጥሩ ምክር አግኝ። የግብር ሕግ በጣም ውስብስብ ሊሆን ስለሚችልና ሕጉን ባለማወቄ ነው የሚለው ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ ተቀባይነት ስለማያገኝ ይህን ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። አንድ ግብር ከፋይ ግብር ሰብሳቢ ሠራተኞችን እንደ ጠላት ሊያይ ቢችልም አብዛኛውን ጊዜ የግብር ጉዳዮችን እንዴት መያዝ እንደሚኖርብን ቀላልና ትክክል የሆነ መመሪያ ይሰጣሉ። የግብር ባለ ሥልጣናት ፍላጎት ግብር አልከፈልክም ብሎ መክሰስ ሳይሆን ከመጀመሪያው ጀምሮ ትክክለኛውን መስመር እንድትከተል ነው።

“ገቢህና ወጪህ በጣም የተወሳሰበ ከሆነ ባለሞያ የሆነ ሰው ምክር እንዲሰጥህ አድርግ። ይሁን እንጂ እዚህ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል! ለደኅንነትህ የሚያስቡ በርካታ የግብር ባለሞያዎች የመኖራቸውን ያህል አሳቢ ያልሆኑ ባለሞያዎችም አሉ። የምታምነው ወዳጅህ ወይም የምታውቀው ሰው የሚታመን ባለሞያ እንዲጠቁምህ አድርግ። ያለው የሞያ ብቃት ምን ያህል እንደሆነም አረጋግጥ።

“ዛሬ ነገ አትበል። በጊዜው አስፈላጊውን መረጃ አለመስጠት ከባድ ቅጣት ሊያስከትል ይችላል።

“በጥሩ ሁኔታ የተዘጋጀ መዝገብ ይኑርህ። ማንኛውንም ዓይነት የሂሣብ አያያዝ ሥርዓት ብትከተል በሚገባ የተያዘና ወቅታዊ እንዲሆን አድርግ። በዚህ መንገድ ግብር በምትከፍልበት ጊዜ ማከናወን የሚኖርብህ ሥራ አነስተኛ ይሆናል። በተጨማሪም መዝገብህ መመርመር ቢያስፈልገው ምንም ችግር አይገጥምህም።

“ሐቀኛ ሁን። ለማምታታት ወይም ሕጉን ትንሽ ጠመም ለማድረግ ትፈተን ይሆናል። ይሁን እንጂ የግብር ባለ ሥልጣናት የሐሰት መረጃዎችን ለይተው የሚያውቁባቸው በርካታ ዘዴዎች አሏቸው። ምንጊዜም ቢሆን ሐቀኛ ሆኖ መገኘት የተሻለ ይሆናል።

“የቅርብ ክትትል አድርግ። የቀጠርከው የሂሣብ ሠራተኛ ትክክል ያልሆነ መረጃ ቢያቀርብ በኃላፊነት መጠየቅህ አይቀርም። ስለዚህ የወከልከው ሰው ከፈቃድህ የወጣ ነገር እንዳያደርግ ክትትል አድርግ።”

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በብዙ አገሮች በትንባሆ ውጤቶችና በአልኮል መጠጦች ላይ ከፍተኛ ቀረጥ ይጣላል

[በገጽ 18, 19 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ግብር ባይከፈል ኖሮ፣ እንደተራ ነገር የምንቆጥራቸውን በርካታ አገልግሎቶች ማግኘት አንችልም ነበር