በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መሥሪያ ቤት ወይስ የውጊያ ቀጠና?

መሥሪያ ቤት ወይስ የውጊያ ቀጠና?

መሥሪያ ቤት ወይስ የውጊያ ቀጠና?

ጀርመን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

“አሁንስ፣ አንገሸገሸኝ። በዚህ ኩባንያ ውስጥ ከ30 ዓመት በላይ ሠርቻለሁ። እድገት አድርጌ የኃላፊነት ቦታ ተሰጥቶኛል። ድንገት አንድ አዲስ አለቃ ተመደበ። ገና ወጣት ሲሆን ደከመኝ የማያውቅ፣ አዳዲስ ሐሳቦች የሚያመነጭ ሰው ነው። ለሥራው እድገት እንቅፋት የሆንኩት እኔ እንደሆንኩ ስላሰበ ያጠቃኝ ጀመር። ከበርካታ ወራት ስድብ፣ ውርደትና የሐሰት ክስ በኋላ ስሜቴ ተነካ። ኩባንያው ጡረታ እንድወጣ ሲጠይቀኝ እሺ ብዬ ወጣሁ።”—ፒተር *

ፒተር በሥራ ቦታ ስሜታዊ ጥቃት ከደረሰባቸው በርካታ ሰዎች አንዱ ነው። እርሱ በሚኖርበት በጀርመን 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ተቀጥረው በሚሠሩበት ቦታ ስሜታቸውን ለመንካት ጥቃት እንደሚሰነዘርባቸው ይገመታል። በኔዘርላንድ ደግሞ ከአራት ሰዎች አንዱ በሥራ ዓለም በሚቆይበት ዘመን እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ያጋጥመዋል። በተጨማሪም በሥራ ቦታ የሰው ስሜት ለመንካት የሚሰነዘር ጥቃት በአውስትራሊያ፣ በኦስትሪያ፣ በብሪታንያ፣ በዴንማርክ፣ በስዊድንና በዩናይትድ ስቴትስ በጣም በመስፋፋት ላይ እንደሆነ የዓለም ሥራ ድርጅት ሪፖርት ያመለክታል። ይሁን እንጂ በሥራ ቦታ አንድን ሰው ማጥቃት ሲባል ምን ማለት ነው?

“የሰው ስሜት ለመንካት የሚሰነዘር ጥቃት”

ፎከስ የተባለው በጀርመንኛ የሚዘጋጅ ዜና መጽሔት እንደሚለው የሰው ስሜት መንካት “ተደጋጋሚና ታስቦ የሚሰነዘር ጥቃት ነው።” በሽሙጥ፣ በትችት፣ በማሾፍና በተረብ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን የሥነ ልቦና ሽብር ለመንዛት የሚደረግ ጥቃት ነው። የጥቃቱም ዓላማ አንድ ሰው የእንግድነትና የባይተዋርነት ስሜት እንዲሰማው ማድረግ ነው። *

ስሜት ለመጉዳት ተብሎ የሚደረጉ ነገሮች እንደ ልጅ ከማኩረፍ አንስቶ ወንጀል ተደርጎ የሚታይ ጥቃት እስከመፈጸም ሊደርሱ ይችላሉ። የጥቃት ዒላማ የሆነው ሰው ለስም ማጥፋት፣ ለስድብና ለጠብ ይዳረጋል እንዲሁም ፊት ይነሱታል። አንዳንዶቹ ሆን ተብሎ ሥራ እንዲበዛባቸው ወይም ማንም ሊሠራው የማይፈልገውን ሥራ ሁልጊዜ እንዲሠሩ ይደረጋል። የሥራ ባልደረቦቹ አንዳንድ መረጃዎችን እንዳያገኝ እንቅፋት በመፍጠርም ሆነ በሌሎች ዘዴዎች ሥራውን ያስተጓጉሉበታል። በሥራ ባልደረባቸው ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩ ሰዎች የግለሰቡን የመኪና ጎማ እስከማፈንዳትና ያለ ፈቃድ በኮምፒውተሩ ውስጥ ያለውን መረጃ እስከማየት የደረሱበት ሁኔታም አለ።

አንዳንድ ሠራተኞች ጥቃት የሚሰነዘርባቸው ከአንድ ሰው ብቻ ሊሆን ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ግን ጥቃት የሚደርስባቸው በቡድን በተቀናጁ ሰዎች ነው።

በጣም የሚያስደንቀው ግን በአንድ ሠራተኛ ላይ ጥቃት የሚሰነዘረው በአለቅየው ፈቃድና ስምምነት መሆኑ ነው። በአውሮፓ በተደረጉ አንዳንድ ጥናቶች 50 በመቶ በሚሆኑት ሁኔታዎች ኃላፊው ጥቃት በመሰንዘሩ ድርጊት ሙሉ ተሳታፊ ሆኖ እንደሚገኝ፤ አብዛኛውን ጊዜም የድርጊቱ ብቸኛው ቆስቋሽ እንደሆነ ተደርሶበታል። በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የተነሣ የሥራ ቦታ “የሰው ስሜት ለመንካት የሚደረግ ረዥምና ፈታኝ የሆነ ጦርነት” የሚካሄድበት ቀጠና እንደሆነ ፍራንክፈርተር አልጌማይነ ጻይቱንግ የተባለው የጀርመን ዕለታዊ ጋዜጣ ገልጿል።

መዘዙ በሥራ ቦታ ብቻ ተወስኖ አይቀርም

አብዛኛውን ጊዜ ጥቃቱ የሚያስከትለው ውጤት በሥራ ቦታ ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም። አብዛኞቹ ተጠቂዎች ስሜታቸው በጣም ስለሚጎዳ ከባድ የጤና ችግር ያጋጥማቸዋል። ጭንቀት፣ እንቅልፍ ማጣትና ድንጉጥ መሆን ከሚያጋጥሙት ችግሮች መካከል ይጠቀሳሉ። በመግቢያው ላይ የጠቀስነው ፒተር ምን ደረሰበት? ለራሱ የነበረውን ጥሩ ግምት ሙሉ በሙሉ አጣ። ጀርመናዊቷ ማርጋሬት የአእምሮ ሕክምና መከታተል እንደሚያስፈልጋት የግል ሐኪምዋ መክሯታል። ለዚህ ያበቃት ምንድን ነው? በሥራ ቦታ ያጋጠማት ጥቃት ነው። በመሥሪያ ቤት የሰው ስሜት ለመንካት የሚሰነዘር ጥቃት በትዳር ወይም በቤተሰብ ሕይወት ላይ ጉዳት የሚያስከትልበት ጊዜም አለ።

በጀርመን በሥራ ቦታ የሚሰነዘር ጥቃት በጣም እየተስፋፋ በመምጣቱ አንድ የጤና መድን ድርጅት በዚህ ረገድ ችግር የሚያጋጥማቸው ሰዎች እርዳታና ምክር የሚያገኙበት የስልክ መስመር ከፍቷል። ወደዚህ ኩባንያ ስልክ ከደወሉት ሰዎች መካከል ከግማሽ የሚበልጡት ለስድስት ሳምንት ያህል፣ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ለሦስት ወራት፣ ከአሥር በመቶ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከሦስት ወር በላይ ለሚሆን ጊዜ ሥራ መሥራት እንዳቃታቸው ሪፖርት አድርገዋል። አንድ የጀርመን የሕክምና መጽሔት “ራሳቸውን ከሚገድሉ ሰዎች መካከል እስከ 20 በመቶ የሚደርሱት ለዚህ እርምጃ የተገፋፉት በሥራ ቦታቸው ስሜት የሚነካ ጥቃት ስለሚደርስባቸው እንደሆነ” ገምቷል።

በሥራ ቦታ በሚሰነዘር ጥቃት ሳቢያ አንድ ሰው መሥሪያ ቤት መሄድ ሊያስጠላው እንደሚችል ግልጽ ነው። ይህን ሁኔታ ማስወገድ የሚቻልበት መንገድ ይኖር ይሆን? በሥራ ቦታ ሰላማዊ ሆኖ መኖር የሚቻለው እንዴት ነው?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.6 በሥራ ቦታ ስሜት ለመንካት የሚሰነዘር ጥቃት ሰለባዎች በአብዛኛው ከወንዶች ይልቅ ሴቶች እንደሆኑ የሚያመለክቱ አሐዛዊ መረጃዎች ቢኖሩም ይህ የሆነው ስላጋጠማቸው ችግር ለመናገርና መፍትሔ ለመፈለግ ፈቃደኛ የሚሆኑት ከወንዶቹ ይልቅ ሴቶቹ ስለሆኑ ሳይሆን አይቀርም።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የሰው ስሜት ለመንካት የሚሰነዘር ጥቃት የሥራ ገበታን የጦርነት ቀጠና አድርጎታል