በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሠራተኞች የጥቃት ዒላማ የሚሆኑት እንዴት ነው?

ሠራተኞች የጥቃት ዒላማ የሚሆኑት እንዴት ነው?

ሠራተኞች የጥቃት ዒላማ የሚሆኑት እንዴት ነው?

ሞኒካ በሕግ ሞያ ተለማማጅ ጸሐፊ ሆና የተቀጠረችው ገና ትምህርቷን እንደጨረሰች ነበር። ከትምህርት ዓለም ወደ ሥራ ዓለም ስትሸጋገር ምንም ዓይነት ችግር ያጋጥመኛል ብላ አላሰበችም።

ሆርስት ደግሞ በሠላሳዎቹ አጋማሽ ላይ የሚገኝ የሕክምና ዶክተር ነበር። ሚስትና ልጆች ያሉት ሲሆን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከመድረስና ከፍተኛ ገቢ ከማግኘት የሚያግደው ነገር ያለ አይመስልም ነበር።

ሆኖም ሞኒካም ሆነች ሆርስት በሥራ ቦታቸው ጥቃት ይሰነዘርባቸው ጀመር።

በሞኒካም ሆነ በሆርስት ላይ ከደረሰው ነገር አንድ ጥሩ ትምህርት እናገኛለን። በሥራ ቦታ የሰው ስሜት ለመጉዳት ተብሎ ለሚሰነዘር ጥቃት የሚጋለጡት እንዲህ፣ እንዲህ ዓይነት ሠራተኞች ናቸው ብሎ መገመት አይቻልም። እንዲያውም በማንኛውም ዓይነት ሞያ የተሰማራ የትኛውም ሰው የሥራ ባልደረቦቹ ለሚሰነዝሩበት ጥቃት ሊጋለጥ ይችላል። ታዲያ ራስህን ከጥቃት መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው? አንደኛው መንገድ አስቸጋሪ ከሆኑ የሥራ ባልደረቦች ጋር ሳይቀር በሰላም ለመኖር ጥረት ማድረግ ነው።

ከሥራ ባልደረቦች ጋር መላመድና መግባባት

ለብዙ ሰዎች ሥራ መቀጠር ከአንድ የሠራተኞች ቡድን ጋር መግባባትንና ቡድኑ የሚጠበቅበትን ሥራ በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲያከናውን መርዳትን ይጠይቃል። የሥራ ባልደረቦች እርስ በርሳቸው የሚግባቡ ከሆነ አመርቂ ሥራ ማከናወን ይቻላል። ካልተግባቡ ደግሞ ሥራው ይጎዳል፤ በሥራ ባልደረቦች የመጠቃት አጋጣሚውም ከፍተኛ ይሆናል።

አንድ የሠራተኞች ቡድን ሥራውን በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዳያከናውን እንቅፋት የሚሆንበት ነገር ምን ሊሆን ይችላል? አንደኛው የሠራተኞች ቶሎ ቶሎ መለዋወጥ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ባለው ሁኔታ በሠራተኞች መካከል ጠንካራ የሆነ ትስስር መፍጠር አስቸጋሪ ይሆናል። በተጨማሪም አዳዲስ ሠራተኞች ከሥራው ባሕርይና እንቅስቃሴ ጋር ቶሎ ስለማይላመዱ የሌሎቹም ምርታማነት ይጓተታል። ሥራው እየተከመረ ከሄደ በቡድኑ ውስጥ የተካተቱት ሠራተኞች በሙሉ ለጭንቀት ይዳረጋሉ።

ከዚህም በላይ አንድ የሠራተኞች ቡድን ግልጽ የሆነ ግብ ከሌለው በሠራተኞቹ መካከል የአንድነት ስሜት አይኖርም። ለምሳሌ አንድ በራሱ የማይተማመን አለቃ ሠራተኞቹን ከመምራት ይልቅ አብዛኛው ጊዜውን የሚያጠፋው የራሱን ሥልጣንና ቦታ ለማስጠበቅ ከሆነ እንዲህ ያለ ሁኔታ መፈጠሩ አይቀርም። እንዲያውም ሠራተኞቹን እርስ በርሳቸው በማናቆር የበላይነቱን ለማስጠበቅ ይሞክር ይሆናል። ይባስ ብሎ ደግሞ የእያንዳንዱ ሰው የሥራ ድርሻና ኃላፊነት በግልጽ ያልተቀመጠ ይሆንና አንዳንዶቹ ሠራተኞች ኃላፊነታቸው የት ጀምሮ የት እንደሚያቆም ሳይረዱ ይቀራሉ። ለምሳሌ ሁለት ሠራተኞች በአንድ ሰነድ ላይ ሁለቱም መፈረም እንዳለባቸው ሲያስቡ ግጭት ሊፈጠር ይችላል።

እንዲህ ባለው ሁኔታ ሠራተኞች እርስ በርሳቸው መነጋገርና መግባባት ያቅታቸዋል፤ ቅሬታዎችም መፍትሔ ሳያገኙ ይቆያሉ። በመካከላቸው በሚፈጠረው መቀናናት ምክንያት የሥራው መንፈስ ይበላሻል። ሠራተኞቹ በአለቃቸው ለመወደድ ሲሉ እርስ በርሳቸው ይፎካከራሉ። አነስተኛ የሆነ አለመግባባት እንደ ትልቅ በደል ይቆጠራል። በሌላ አባባል ትንሹ ኩይሳ ትልቅ ጋራ ያክላል። በዚህ መንገድ እርስ በርስ ለመጠቃቃት አመቺ የሆነ ሁኔታ ይፈጠራል።

ለሚሠራው ጥፋት ሁሉ ማሳበቢያ መፈለግ

ውሎ አድሮ፣ ለሚሠራው ጥፋት ሁሉ ማሳበቢያ የሚሆን አንድ ሠራተኛ ተነጥሎ ይወጣል። በአመዛኙ እንዲህ ዓይነት ችግር የሚያጋጥመው ምን ዓይነት ሠራተኛ ነው? ለየት ብሎ የሚታይ ሠራተኛ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ብዙ ሴቶች ባሉበት የሥራ ክፍል ውስጥ የሚሠራ ብቸኛ ወንድ ወይም ብዙ ወንዶች በሚሠሩበት ክፍል የተመደበች ብቸኛ ሴት ልትሆን ትችላለች። በራሱ የሚተማመን ሠራተኛ እንደ ጠበኛ፣ ዝምተኛ የሆነ ሠራተኛ ደግሞ እንደ ተንኮለኛና መሠሪ ተደርጎ ይታይ ይሆናል። በተጨማሪም ጥቃት የሚሰነዘርበት ሠራተኛ ከሌሎቹ ሠራተኞች በዕድሜ ያነሰ ወይም የበለጠ ስለሆነ አሊያም ለሥራው ከሌሎቹ የበለጠ ብቃት ስላለው የተለየ ሆኖ ሊታይ ይችላል።

የጥቃት ዒላማ የሆነው ሰው ማንም ይሁን ማን የሥራ ባልደረቦቹ “እሱን በማናደድና በማበሳጨት የየራሳቸውን የውጥረት ጫና እርሱ ላይ በማራገፍ እፎይታ እንዳገኙ ይሰማቸዋል” በማለት ኤምቲኤ የተባለው የጀርመን የሕክምና መጽሔት ዘግቧል። ለጥቃት የተጋለጠው ሠራተኛ ሁኔታውን ለማስተካከል የሚወስደው እርምጃ ችግሩን ከማቃለል ይልቅ ሊያባብስበት ይችላል። ዛቻውና ማስፈራሪያው እየከረረና እየተደጋገመ በሄደ መጠን ለሚሠራው ጥፋት ሁሉ ማሳበቢያ የሚሆነው ሠራተኛ ይበልጥ እየተገለለ ይሄዳል። በዚህ ጊዜ ሁኔታውን መቋቋም ከአቅሙ በላይ ይሆንበታል።

መቼም በሥራ ቦታ መበደል አዲስ ነገር አይደለም። ቢሆንም የሥራ ባልደረቦች ይበልጥ ይግባቡና ይረዳዱ የነበረበት ጊዜ እንደነበረ ብዙዎች ያስታውሳሉ። ግንባር ፈጥሮ አንድን ሠራተኛ ማጥቃት እምብዛም አይታወቅም ነበር። አንድ ዶክተር እንዳሉት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን “የመረዳዳት መንፈስ እየተመናመነና እፍረተቢስነት እየተስፋፋ መጥቷል።” በአሁኑ ጊዜ በሥራ ቦታ ግብ ግብ ቢፈጥሩ እፍረት የማይሰማቸው ሰዎች በዝተዋል።

ስለዚህ ተቀጥረው የሚሠሩ ሰዎች ሁሉ የሚከተሉት ጥያቄዎች ያሳስቧቸዋል:- በሥራ ባልደረቦች የሚሰነዘር ጥቃት ሊወገድ ይችላል? በሥራ ቦታ ሰላማዊ ግንኙነት መፍጠር የሚቻለው እንዴት ነው?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሰው ስሜት ለመንካት ተብሎ ጥቃት የሚሰነዘረው ሠራተኛውን ባይተዋር ለማድረግ ነው