በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሥራ ቦታ ሰላም እንዲሰፍን መጣር

በሥራ ቦታ ሰላም እንዲሰፍን መጣር

በሥራ ቦታ ሰላም እንዲሰፍን መጣር

አንዳንድ ሰዎች ሌሎችን የሚተነኩሱት ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚሰጠን ማብራሪያ አለ። የምንኖረው ይህ ሥርዓት ሊያከትም በተቃረበበት “በመጨረሻው ዘመን” ስለሆነ ጊዜው “የሚያስጨንቅ” እንደሚሆን ተናግሯል። “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክሕተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ለዕርቅ የማይሸነፉ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በከንቱ በትዕቢት የተወጠሩ . . . ይሆናሉ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) በዚህ ሁከት በነገሰበት ዘመን እነዚህ ጠባዮች በሠፊው የሚታዩ ሲሆን ይህ ሁኔታ ካስከተላቸው ውጤቶች አንዱ በሥራ ባልደረቦች ላይ ጥቃት መሰንዘር ነው። ታዲያ በሥራ ቦታ ሰላማዊ ሆኖ መኖር የሚቻለው እንዴት ነው?

ግጭቶችን መፍታት

አብዛኛውን ጊዜ ጥቃት መሰንዘር የሚጀመረው በሥራ ባልደረቦች መካከል ያልተፈታ ግጭት ሲኖር ነው። ስለዚህ በሰዎች የግል ጉዳይ ሳትገባ አንተ ራስህ ያጋጠመህን አለመግባባት ወዲያውኑ ለመፍታት ሞክር። በዘዴና በአክብሮት ቅሬታዎችን አስወግድ። ይህን ስታደርግ የሥራ ባልደረቦችህን በቡድን ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ አነጋግራቸው። አንድ ሰው በአንተ ላይ ቅሬታ ያለው መስሎ ከተሰማህ ነገሩን ለማስተካከል ሞክር። ኢየሱስ “ከባላጋራህ ጋር ፈጥነህ ተስማማ” ሲል የሰጠውን ምክር አትርሳ።—ማቴዎስ 5:25

ከዚህም በላይ መኳረፍ ለማንም አይጠቅምም። ስለዚህ በቅርብ አለቃህ ዘንድ ተወዳጅነት ለማትረፍ የምታጎበድድ እንዳይመስልብህ በመጠንቀቅ ከእሱ ጋር ለመግባባትና ለመነጋገር ሞክር። በተጨማሪም አብረውህ ከሚሠሩትና በሥርህ ካሉት ሠራተኞች ጋር በጥሩ ሁኔታ ሐሳብ መለዋወጥ መቻል ውጥረትን ለማስወገድ ጥሩ መድኃኒት እንደሆነ አስታውስ። ንጉሥ ሰሎሞን “ምክር ሲጓደል ዕቅድ ይፋለሳል፤ በብዙ አማካሪዎች ግን ይሳካል” ሲል ጽፏል።—ምሳሌ 15:22

ስለዚህ ከሥራ ባልደረቦችህ ጋር ለመግባባት የተቻለህን ሁሉ አድርግ። እንዲህ ሲባል ግን “አድርባይ” ወይም ማንም ሰው የሚጠይቅህን እሺ የምትል ወይም ሰላም እንዳይደፈርስ ስትል ብቻ የምታምንበትን መመሪያ የምትጥስ ወላዋይ ሰው ትሆናለህ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ፍቅራዊና ወዳጃዊ ባሕርይ በማሳየት መጥፎ ሁኔታዎችን ማስወገድ ትችላለህ። ለሰዎች ምን እንደምትናገር ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደምትናገር ጭምር አስብ። መጽሐፍ ቅዱስ “የለዘበ መልስ ቁጣን ያበርዳል” በማለት ጥሩ ምክር ይሰጣል። (ምሳሌ 15:1) “ፈውስ የምታመጣ ምላስ የሕይወት ዛፍ ናት።” (ምሳሌ 15:4) “በትዕግሥት ገዥን ማግባባት ይቻላል።” (ምሳሌ 25:15) “ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ በጨው እንደ ተቀመመ ሁልጊዜ በጸጋ የተሞላ ይሁን።”—ቆላስይስ 4:6

‘ምክንያታዊነትህ ለሰው ሁሉ ይታወቅ’

ሐዋርያው ጳውሎስ የፊልጵስዮስ ክርስቲያኖችን “ምክንያታዊነታችሁ ለሰው ሁሉ ይታወቅ” ሲል መክሯቸዋል። (ፊልጵስዮስ 4:5 NW) ይህን ምክር በመከተል ምክንያታዊ አቋም እንዲኖርህ ጣር። ከልክ በላይ በራስህ አትመካ ወይም በጣም ዓይናፋር አትሁን። ባልደረቦችህ ቢያሾፉብህ አንተም በእነርሱ ላይ በማሾፍ ብድር ለመመለስ አትሞክር። በጥሩና በመጥፎ ጠባይ መካከል ያለው ልዩነት እንዲሸፈን በማድረግ የምታገኘው ጥቅም አይኖርም። ሌሎችን በአክብሮትና በጨዋነት ከያዝክ አንተም ተመሳሳይ ነገር ማግኘትህ አይቀርም።

ስለ ጠባይህ ብቻ ሳይሆን ስለ አለባበስህ ጭምር አስብ። ‘አለባበሴ በሌሎች ላይ ምን ዓይነት ስሜት ያሳድራል? ቁመናዬ ወሲባዊ ስሜት ይቀሰቅሳል? በሌሎች ዓይን ስታይ ዝርክርክ እመስላለሁ? በሥራ ቦታ ጨዋነት የሚንጸባረቅበት አለባበስ ብከተል የተሻለ ይሆን?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።

በብዙ አገሮች ውስጥ ጠንቃቃና ትጉህ የሆኑ ሠራተኞች የሚከበሩ ከመሆኑም በላይ በጣም ተፈላጊ ናቸው። ስለዚህ ጥራት ያለው ሥራ በመሥራት አክብሮት ለማትረፍ ሞክር። እምነት የሚጣልብህና ታማኝ ሰው ሁን። እንዲህ ሲባል በጥቃቅኑ ነገር ሁሉ እንከን የለሽ ለመሆን መጣር ማለት አይደለም። ከሥራ ባልደረቦቿ ጥቃት የደረሰባት አንዲት ሴት የራሷን ጉድጓድ የቆፈረችው ራሷ እንደሆነች ተናግራለች። “የምሠራው ሥራ ሁሉ ፍጹም እንዲሆን እፈልግ ነበር” ብላለች። ይህች ሴት ፍጽምና ሊደረስበት የማይችል ግብ እንደሆነ ከጊዜ በኋላ ተገንዝባለች። “ጥሩ ሠራተኛ ነኝ፣ ሆኖም ሁሉንም ነገር ፍጹም አድርጌ መሥራት አለብኝ ማለት አይደለም።”

ሰዎች በሚናገሩት አሉታዊ ነገር ሁሉ መከፋት የለብህም። ስለ አንተ የተነገረውን በጎ ያልሆነ ነገር ሁሉ እንደ ጥቃት መቁጠር አይኖርብህም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ንጉሥ ሰሎሞን “በመንፈስህ ለቁጣ አትቸኩል። የሚነገረውን ቃል ሁሉ ለማዳመጥ አትሞክር፤ . . . ብዙ ጊዜ አንተ ራስህ፣ ሌሎችን እንደረገምህ ልብህ ያውቃልና” ሲል ጽፏል።—መክብብ 7:9, 21, 22

እነዚህን የመሰሉ ጥሩ መሠረታዊ ሥርዓቶችን መከተልህ ምንም ዓይነት ጥቃት እንዳይደርስብህ ዋስትና ይሆናል ማለት አይደለም። ምንም ያህል ጥረት ብታደርግ አንዳንድ የሥራ ባልደረቦችህ መተናኮላቸውን አይተዉ ይሆናል። ታዲያ ምን ብታደርግ ይሻላል?

የሌሎችን እርዳታ መጠየቅ

ግሪጎሪ “የሥራ ባልደረቦቼ ለበርካታ ወራት ባገለሉኝ ጊዜ ከፍተኛ የስሜት መረበሽ ደርሶብኝ ነበር” ብሏል። የደረሰበት ሥቃይ ከሌሎች ተጠቂዎች የተለየ አልነበረም። ብስጭት፣ የጥፋተኝነት ስሜት፣ እፍረት፣ ግራ መጋባትና የዋጋቢስነት ስሜት አደረበት። የሥራ ባልደረቦች የሰው ስሜት ለመንካት የሚያደርጉት ጥረት መንፈሰ ጠንካራ የሆነን ሰው ሳይቀር ቅስሙ እንዲሰበር ያደርጋል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ግፍ ጠቢቡን ያሳብደዋል” ይላል። (መክብብ 7:7 የ1954 ትርጉም) ታዲያ ምን ማድረግ ይቻላል?

ጥናቶች እንዳመለከቱት ችግሩን ለብቻህ ለመቋቋም ባትሞክር ይሻላል። ታዲያ እርዳታ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው? አንዳንድ ትላልቅ ድርጅቶች ከሥራ ባልደረቦቻቸው ችግር እያጋጠማቸው እንዳለ ለሚሰማቸው ሠራተኞች እርዳታ የሚሰጡበት ዝግጅት አቋቁመዋል። እንደነዚህ ያሉት ድርጅቶች ሠራተኞች በደል እንዳይፈጸምባቸው ጣልቃ ቢገቡ የሚጠቀሙት እነርሱ ጭምር እንደሆኑ ያውቃሉ። አንድ ጥናት እንዳመለከተው የሥራ ባልደረቦቻቸውን የሚያስቸግሩ ሠራተኞች ከሥራ ጊዜያቸው 10 በመቶ የሚሆነውን በከንቱ ያባክናሉ። እንዲህ ዓይነት ዝግጅት ካለ ጥቃት የሚሰነዘርበት ሠራተኛ እርዳታ ሊጠይቅ ይችላል። በመሥሪያ ቤቱ ውስጥም ሆነ ከመሥሪያ ቤቱ ውጭ የሚገኝ ገለልተኛ የሆነ አማካሪ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ ችግራቸውን ተወያይተው መፍትሔ የሚያገኙበትን መንገድ ሊያመቻች ይችላል።

መቶ በመቶ ይሠራል የሚባል መፍትሔ የለም

እርግጥ፣ በሥራ ቦታ ለሚፈጸም ጥቃት መቶ በመቶ ይሠራል የሚባል መፍትሔ እንደሌለ መካድ አይቻልም። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የተዘረዘሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ የሚያውሉ ሰዎች እንኳን በመሥሪያ ቤት ከሚያጋጥማቸው ጥቃት ሙሉ በሙሉ ሊላቀቁ እንዳልቻሉ ይገነዘቡ ይሆናል። እንደነዚህ ያሉት ሰዎች ብዙ ችግር እየደረሰባቸውም የሚያሳዩት ጥረትና ጽናት ከይሖዋ አምላክ ዓይን የተሰወረ እንዳልሆነ እርግጠኛ መሆን ይችላሉ።—2 ዜና መዋዕል 16:9፤ ኤርምያስ 17:10

አንዳንዶች የሚደርስባቸው ግፍ እየተባባሰና እየተደጋገመ ሲሄድ ሌላ ሥራ ማፈላለግ ይጀምራሉ። ሌሎች ደግሞ ሌላ ሥራ በቀላሉ ስለማይገኝና ሊረዳቸው የሚችል አካል ስለሌለ ችግራቸውን እንደተሸከሙ ለመኖር ይገደዳሉ። ከዚህ በፊት በነበረው ርዕስ የተጠቀሰችው ሞኒካ ያስቸግሯት ከነበሩት ሠራተኞች መካከል ቀንደኛ የሆነው ሥራውን ለቅቆ ሲወጣ ችግሯ መፍትሔ አግኝቷል። ከዚህም የተነሣ በምትሠራበት ቦታ አንጻራዊ ሰላም በመስፈኑ ሌላ ሥራ ከመቀጠሯ በፊት ሥልጠናውን ማጠናቀቅ ችላለች።

በመጀመሪያው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ፒተር ዕድሜው ሳይደርስ ጡረታ በመውጣቱ ከችግሩ ሊገላገል ችሏል። ይሁን እንጂ ፒተር ችግር ላይ በነበረበት ወቅት ሚስቱ ትሰጠው የነበረ ድጋፍ በጣም ጠቅሞታል። “ችግሬ ይገባት ስለነበረ አለኝታ ሆናልኝ ነበር” ይላል። የይሖዋ ምሥክር የሆኑት ሞኒካና ፒተር ግፍ ይፈጸምባቸው በነበረ ጊዜ ሁሉ እምነታቸው ከፍተኛ መጽናኛ አስገኝቶላቸዋል። በአገልግሎት መሳተፋቸው ለራሳቸው ያላቸውን ግምት ያሳደገላቸው ሲሆን ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ደግሞ ወዳጅነታቸውን እንዲያጠናክሩ አስችሏቸዋል።

በምንም ዓይነት ሁኔታ ብትገኝ በሥራ ቦታህ ከሌሎች ጋር ተግባብተህ ለመሥራት የተቻለህን ሁሉ አድርግ። ጥቃት ከተሰነዘረብህ “ለማንም ክፉን በክፉ አትመልሱ፤ . . . ቢቻላችሁስ በበኩላችሁ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። . . . ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ” የሚለውን የሐዋርያው ጳውሎስ ምክር ሥራ ላይ ለማዋል ጥረት አድርግ።—ሮሜ 12:17-21

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ወዳጃዊ ጠባይ ማሳየት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ሊያስወግድ ይችላል

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ቢቻላችሁስ በበኩላችሁ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።”—ሮሜ 12:18

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አለመግባባት ሲፈጠር ወዲያው ቅሬታውን ለማስወገድ ጥረት አድርግ