በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛ ተስፋ ማግኘት የምትችለው ከየት ነው?

እውነተኛ ተስፋ ማግኘት የምትችለው ከየት ነው?

እውነተኛ ተስፋ ማግኘት የምትችለው ከየት ነው?

ሰዓትህ ተሰብሮ ሳይሆን አይቀርም፣ መሥራቱን አቁሟል። ለማሠራት ስትፈልግ ደግሞ ብዙ ምርጫዎች እንዳሉ ትገነዘባለህ። ሰዓት አዳሾችን የሚያስተዋውቁ ማስታወቂያዎች ሞልተዋል፤ ሁሉም ስለ ችሎታቸው በእርግጠኝነት የሚናገሩ ከመሆናቸውም በላይ አንዳንዶቹ የሚናገሩት ሐሳብ እርስ በርሱ ይጋጫል። ዳሩ ግን ይህን የተበላሸብህን ሰዓት ከዓመታት በፊት የሠራው በአካባቢህ የሚኖር የረቀቀ ችሎታ ያለው ጎረቤትህ መሆኑን ብትደርስበትስ? ከዚህም በላይ በነጻ ሊያድስልህ ፈቃደኛ እንደሆነ ቢነገርህ ምን ታደርጋለህ? ወደ ማን እንደምትሄድ ግልጽ ነው።

ይህን ሰዓት ተስፋ ከማድረግ ችሎታህ ጋር አወዳድረው። በዚህ በመከራ በተሞላ ዘመን አንተም እንደ ብዙዎች ሁሉ በምንም ነገር ላይ ተስፋ እንዳጣህ ከተሰማህ ለእርዳታ ወደ ማን ዞር ትላለህ? በርካታ ሰዎች ችግሩን ለመፍታት ችሎታ እንዳላቸው ቢናገሩም ማለቂያ የሌለው ምክራቸው አደናጋሪና እርስ በርሱ የሚጋጭ ሊሆን ይችላል። ታዲያ መጀመሪያውኑ የሰውን ልጅ ተስፋ የማድረግ ችሎታ እንዲኖረው አድርጎ ወደሠራው ፈጣሪ ለምን ዞር አትልም? መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪ “ከእያንዳንዳችን የራቀ . . . አይደለም” በማለት ይናገራል። እርሱ ሊረዳህ ፈቃደኛ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 17:27፤ 1 ጴጥሮስ 5:7

ጥልቀት ያለው የተስፋ ፍቺ

መጽሐፍ ቅዱስ ለተስፋ የሚሰጠው ፍቺ በዛሬው ጊዜ ያሉ ሐኪሞች፣ የሳይንስ ሊቃውንትና የሥነ ልቦና ጠበብቶች ከሚሰጡት ፍቺ ይበልጥ ሰፊና ጥልቀት ያለው ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ተስፋ” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት በጉጉት መጠበቅና መልካም ነገር እንደሚመጣ ማመን የሚል ፍቺ አላቸው። በመሠረቱ ተስፋ የሁለት ነገሮች ቅንጅት ውጤት ነው። ይኸውም አንድን ጥሩ ነገር የማግኘት ምኞት እና ያ ጥሩ ነገር እንደሚመጣ ለማመን የሚያስችለውን መሠረት አካትቶ የያዘ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሰጠው ተስፋ በእውነታ እና በማስረጃ ላይ ጽኑ ሆኑ የተመሠረተ እንጂ እንዲያው ምኞት ብቻ አይደለም።

በዚህ ረገድ ተስፋ በጭፍን ሳይሆን በማስረጃ ላይ ከተመሠረተ እምነት ጋር ተመሳሳይ ነው። (ዕብራውያን 11:1) ያም ሆኖ ግን መጽሐፍ ቅዱስ በእምነትና በተስፋ መካከል ልዩነት እንዳለ ይናገራል።—1 ቆሮንቶስ 13:13

ጉዳዩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድ የምትወደው ወዳጅህ አንድ ውለታ እንዲውልልህ ስትጠይቀው የምትፈልገውን እንደሚያደርግልህ ተስፋ አድርገህ ነው። በእርሱ የተማመንከውና ተስፋ ያደረግከው ወዳጅህን አሳምረህ ስለምታውቀውና ከዚያ በፊት ደግነቱንና ልግስናውን ስላየህ እንጂ እንዲያው በከንቱ አይደለም። እምነትህና ተስፋህ እርስ በርስ የተሳሰሩ ቢሆኑም የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ታዲያ በአምላክ ላይ እንዲህ ያለ እምነት ሊኖርህ የሚችለው እንዴት ነው?

ለተስፋ መሠረቱ

አምላክ የእውነተኛ ተስፋ ምንጭ ነው። እንዲያውም በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ይሖዋ “የእስራኤል ተስፋ” ተብሎ ተጠርቷል። (ኤርምያስ 14:8) የጥንት እስራኤላውያን የነበራቸው ማንኛውም አስተማማኝ ተስፋ ከእርሱ የመነጨ ስለሆነ እሱ ተስፋቸው ነበር። እንዲህ ዓይነቱ ተስፋ እንዲያው ምኞት ብቻ አልነበረም። አምላክ እስራኤላውያን ተስፋ እንዲያደርጉ የሚያስችል ጠንካራ መሠረት ሰጥቷቸው ነበር። በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት ከእነርሱ ጋር ባደረገው ግንኙነት ቃል የገባላቸውን ተስፋዎች በመፈጸም ረገድ መልካም ስም አትርፏል። የእስራኤላውያን መሪ የነበረው ኢያሱ “አምላካችሁ እግዚአብሔር ከሰጣችሁ መልካም ተስፋ ሁሉ አንዲቱን እንኳ እንዳላስቀረባችሁ . . . ታውቃላችሁ” በማለት ነግሯቸዋል።—ኢያሱ 23:14

በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላም አምላክ የሰጠውን ተስፋ በመፈጸም ረገድ ያተረፈውን ስም እንደያዘ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ቃል በገባቸው አስደናቂ ተስፋዎች እንዲሁም እነዚህ ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ በሚዘግቡ ትክክለኛ ታሪኮች የተሞላ ነው። ትንቢታዊ ተስፋዎቹ እጅግ አስተማማኝ ከመሆናቸው የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ተስፋዎቹ በተሰጡበት ወቅት ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ ተደርጎ ተገልጿል።

መጽሐፍ ቅዱስ የተስፋ መጽሐፍ እንደሆነ የምንናገረው ለዚህ ነው። አምላክ ከሰዎች ጋር ስላደረጋቸው ግንኙነቶች የሚናገሩ ታሪኮችን ስታጠና በእሱ ላይ ተስፋ እንድታደርግ የሚገፋፋህ ምክንያት እየተጠናከረ እንደሚሄድ የተረጋገጠ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “በጽናትና ቅዱሳት መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ እንዲኖረን፣ ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአል” ሲል አስፍሯል።—ሮሜ 15:4

አምላክ ምን ተስፋ ይሰጠናል?

ከማንኛውም ጊዜ በበለጠ ተስፋ የሚያስፈልገን መቼ ነው? ከሞት ጋር ስንፋጠጥ ነው ብለህ ትመልስ ይሆናል። ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች ተስፋ ፈጽሞ የማይጨበጥ መስሎ የሚታያቸው የሚወዱትን ሰው በሞት በሚነጠቁበት ጊዜ ነው። ደግሞስ ከሞት የበለጠ ተስፋ የሚያስቆርጥ ምን ይኖራል? ሞት እያንዳንዳችንን እግር በእግር ይከታተለናል። ልናመልጠው የማንችል ከመሆኑም በላይ በራሳችን ከሞት ለመነሳት ኃይል የለንም። መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን “የመጨረሻው ጠላት” ብሎ መጥራቱ የተገባ ነው።—1 ቆሮንቶስ 15:26

ታዲያ ከሞት ጋር ስንፋጠጥ ተስፋ ልናገኝ የምንችለው እንዴት ነው? ሞትን የመጨረሻው ጠላት ብሎ የጠራው መጽሐፍ ቅዱስ በዚያው ጥቅስ ላይ ይህ ጠላት ‘እንደሚደመሰስ’ ይናገራል። ይሖዋ አምላክ ከሞት ይበልጥ ኃይለኛ ነው። ይህንንም በበርካታ አጋጣሚዎች አረጋግጧል። እንዴት? ሙታንን በማስነሣት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በዘጠኝ የተለያዩ አጋጣሚዎች ኃይሉን ተጠቅሞ የሞቱ ሰዎችን እንደገና እንዳስነሳ የሚዘግቡ ታሪኮችን ይዟል።

ከእነዚህ መካከል አንዱ ይሖዋ ለልጁ ለኢየሱስ ኃይል ሰጥቶ ለአራት ቀናት ሞቶ የቆየውን ወዳጁን አልዓዛርን እንዲያስነሣ ያደረገበት አጋጣሚ ነው። ኢየሱስ ይህን ያደረገው በምስጢር ሳይሆን በግልጽ ብዙ ሰዎች በተሰበሰቡበት ነው።—ዮሐንስ 11:38-48, 53፤ 12:9, 10

‘እነዚያ ሰዎች የተነሡት ለምን ነበር? አርጅተው እንደገና ሞተው የለም?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። አዎን ሞተዋል። ሆኖም ከላይ እንደተገለጹት ያሉ ስለ ትንሣኤ የሚናገሩ እምነት የሚጣልባቸው ታሪኮች በመኖራቸው የሞቱብን የምንወዳቸው ሰዎች እንደገና እንዲነሱ ከመመኘት ያለፈ ነገር ሊኖረን ችሏል። ይኸውም እንደገና እንደሚነሱ ለማመን የሚያስችል መሠረት ወይም ማስረጃ አለን። በሌላ አነጋገር እውነተኛ ተስፋ አለን።

ኢየሱስ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” ብሏል። (ዮሐንስ 11:25) በዓለም አቀፍ ደረጃ ሙታንን እንዲያስነሣ ይሖዋ የሚጠቀምበት እሱን ነው። ኢየሱስ “መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን [የክርስቶስን] የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 5:28, 29) አዎን፣ በመቃብር የሚገኙ አንቀላፍተው ያሉት ሁሉ በገነት ምድር ላይ እንደገና ሕይወት የማግኘት ተስፋ አላቸው።

ነቢዩ ኢሳይያስ ይህን ልብ የሚነካ የትንሣኤ ትዕይንት እንዲህ በማለት ገልጾታል:- “ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፤ በድናቸውም ይነሣል። እናንት በዐፈር ውስጥ የምትኖሩ፣ ተነሡ፤ በደስታም ዘምሩ። ጠልህ እንደ ንጋት ጠል ነው፤ ምድር ሙታንን ትወልዳለች።”—ኢሳይያስ 26:19

ይህ ተስፋ የሚያጽናና አይደለም? አንድ ሕፃን ጥበቃ በሚያገኝበት በእናቱ ማህፀን ውስጥ እንደሚቆይ ሁሉ ሙታንም ማንም ሊያስበው ከሚችለው በላይ አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ሥር ይገኛሉ። በእርግጥም በመቃብር ያረፉ ሁሉ ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ወሰን የለሽ የማስታወስ ችሎታ ውስጥ ፍጹም በሆነ ሁኔታ ተጠብቀው ይገኛሉ። (ሉቃስ 20:37, 38) አዲስ የተወለደ ሕፃን አፍቃሪ ከሆነና በጉጉት ሲጠባበቀው ከቆየው ቤተሰብ ጋር እንደሚቀላቀል ሁሉ ሙታንም በቅርቡ ተነስተው አስደሳች ወደሆነና በደስታ ወደሚቀበላቸው ዓለም ይገባሉ! ስለዚህ ከሞት ጋር በምንጋፈጥበት ጊዜም ተስፋ አለን።

ተስፋ ምን ጥቅም ሊያስገኝልህ ይችላል?

ጳውሎስ ስለ ተስፋ ጠቃሚነት ብዙ ያስተምረናል። ተስፋን ከራስ ቁር ጋር በማመሳሰል የመንፈሳዊ ትጥቅ አንዱ አቢይ ክፍል እንደሆነ ተናግሯል። (1 ተሰሎንቄ 5:8) ተስፋን ከራስ ቁር ጋር ያመሳሰለው ለምን ነበር? በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንድ ወታደር ወደ ጦርነት በሚዘምትበት ጊዜ በአብዛኛው ከሱፍ ወይም ከቆዳ በሚሠራ ቆብ ላይ የብረት ቁር ይለብስ ነበር። የብረት ቁሩ በወታደሩ ራስ ላይ የሚሰነዘሩት አብዛኞቹ ምቶች የሞት አደጋ ሳያስከትሉ ነጥረው እንዲመለሱ ያደርጋል። ጳውሎስ ሊያስተላልፍ የፈለገው ቁም ነገር ምንድን ነው? ቁር በራስ ላይ ከሚሰነዘር ምት እንደሚከላከል ሁሉ ተስፋም አእምሮን ይጠብቃል። ከአምላክ ዓላማ ጋር የሚስማማ ጠንካራ ተስፋ ካለህ መከራ በሚደርስብህ ጊዜ የአእምሮህ ሰላም በድንጋጤ አይናጋም ወይም ተስፋ አትቆርጥም። ታዲያ ከመካከላችን እንዲህ ዓይነቱ ቁር የማያስፈልገው ማን ነው?

ጳውሎስ ከአምላክ ፈቃድ ጋር ተዛማጅ የሆነ ተስፋን ለመግለጽ ሌላም ጉልህ ምሳሌ ተጠቅሟል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እኛም የነፍስ መልሕቅ የሆነ ጽኑና አስተማማኝ ተስፋ አለን።” (ዕብራውያን 6:19) ከአንድ ጊዜ በላይ የመርከብ አደጋ ደርሶበት በሕይወት የተረፈው ጳውሎስ የመልሕቅን ጥቅም አሳምሮ ያውቃል። መርከበኞች ማዕበል ሲያንገላታቸው የመርከቡን መልሕቅ ወደ ባሕሩ ይጥሉታል። መልሕቁ የባሕሩ ወለል ላይ አርፎ እንደማይነቃነቅ ሆኖ ከተያዘ መርከቡ ወደ ባሕሩ ዳር ተገፍቶ ከዓለት ጋር በመላተም ፋንታ ማዕበሉ ከሚያስከትለው አደጋ ለመትረፍና በሰላም ለመሄድ አጋጣሚ ይኖረዋል።

በተመሳሳይም አምላክ ቃል የገባልን ነገሮች በሙሉ “ጽኑና አስተማማኝ” ከሆኑልን ይህን በመከራ የተሞላ ዘመን በሰላም እንድናልፈው ይረዱናል። የሰው ልጅ ከእንግዲህ በጦርነት፣ በወንጀል፣ በኀዘን አልፎ ተርፎም በሞት ፍዳውን የማያይበት ዘመን በቅርቡ እንደሚመጣ ይሖዋ ቃል ገብቷል። (በገጽ 20 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት) ይህን ተስፋ የሙጥኝ ብለን ብንይዝ በዚህ ዓለም ተስፋፍቶ በሚገኘው ምስቅልቅሉ የወጣ የብልግና መንፈስ ሳንሸነፍ ከአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን ለመኖር የሚያስፈልገንን ማበረታቻ ስለሚሰጠን ከጥፋት ለመዳን ይረዳናል።

ይሖዋ የሚሰጠው ተስፋ አንተንም በግል ይጨምራል። እሱ ያዘጋጀልህን ሕይወት እንድታጣጥም ይፈልጋል። የእሱ ፍላጎት “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ” ነው። ታዲያ ልንድን የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ እያንዳንዳችን ‘ትክክለኛውን እውነት ወደ ማወቅ መድረስ’ አለብን። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) የዚህ መጽሔት አዘጋጆች የአምላክን ቃል እውነት አስመልክቶ ይህን ሕይወት ሰጪ እውቀት እንድትቀስም ያበረታቱሃል። በዚህም አማካኝነት አምላክ የሚሰጥህ ተስፋ በዚህ ዓለም ልታገኝ ከምትችለው ከማንኛውም ተስፋ እጅግ የላቀ ነው።

እንዲህ ያለ ተስፋ እስካለህ ድረስ አምላክ ከፈቃዱ ጋር ተስማምተህ የምታወጣቸውን ግቦች ሁሉ እንድትደርስባቸው የሚያስፈልግህን ጥንካሬ ሊሰጥህ ስለሚችል ፈጽሞ ተስፋ አትቆርጥም። (2 ቆሮንቶስ 4:7፤ ፊልጵስዩስ 4:13) የሚያስፈልግህ ይህ ዓይነቱ ተስፋ አይደለም? ስለዚህ ተስፋ የሚያስፈልግህ ከሆነ፣ ስትፈልገው የቆየኸው ይህን ከነበረ፣ አይዞህ። ተስፋው በእጅህ ነው። ልታገኘው ትችላለህ!

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ተስፋ እንድናደርግ ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች

የሚከተሉት ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች ተስፋህን እንድታለመልም ሊረዱህ ይችላሉ።

አምላክ ወደፊት አስደሳች ጊዜ እንደሚያመጣ ቃል ገብቷል።

የአምላክ ቃል መላዋ ምድር ገነት እንደምትሆንና አንድነት ባላቸው ደስተኛ ቤተሰቦች እንደምትሞላ ይናገራል።—መዝሙር 37:11, 29፤ ኢሳይያስ 25:8፤ ራእይ 21:3, 4

አምላክ ሊዋሽ አይችልም።

እርሱ ማንኛውንም ዓይነት ውሸት ይጠላል። ይሖዋ ከማንኛውም ዓይነት ነውር የጸዳና ቅዱስ ስለሆነ ከቶ ሊዋሽ አይችልም።—ምሳሌ 6:16-19፤ ኢሳይያስ 6:2, 3፤ ቲቶ 1:2፤ ዕብራውያን 6:18

አምላክ ገደብ የለሽ ኃይል አለው።

ይሖዋ ብቻ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ቃል የገባቸውን ነገሮች ከመፈጸም ሊያግደው የሚችል አንዳችም ነገር የለም።—ዘፀአት 15:11፤ ኢሳይያስ 40:25, 26

አምላክ ለዘላለም እንድትኖር ይፈልጋል።

ዮሐንስ 3:16፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4

አምላክ በእኛ ላይ ተስፋ አለው።

በስህተታችንና በጉድለታችን ላይ ሳይሆን በጥሩ ባሕርይዎቻችንና በምናደርጋቸው ጥረቶች ላይ ማተኮር ይመርጣል። (መዝሙር 103:12-14፤ 130:3፤ ዕብራውያን 6:10) ትክክል የሆነውን እንደምናደርግ ተስፋ የሚያደርግ ሲሆን እንዲህ ማድረጋችን ያስደስተዋል።—ምሳሌ 27:11

አምላክ ከዓላማው ጋር የሚስማሙ ግቦች ላይ እንድትደርስ እንደሚረዳህ ቃል ገብቷል።

አገልጋዮቹ ተስፋ እንደሌላቸው እንዲሰማቸው አይፈልግም። አምላክ እኛን ለመርዳት ከምንም በላይ ብርቱ የሆነውን ቅዱስ መንፈሱን በልግስና ይሰጠናል።—ፊልጵስዩስ 4:13

በአምላክ ተስፋ ማድረግ ፈጽሞ አያስቆጭም።

እጅግ አስተማማኝና እምነት የሚጣልበት ስለሆነ አያሳፍራችሁም።—መዝሙር 25:3

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቁር ራስን ከጉዳት እንደሚጠብቅ ሁሉ ተስፋም አእምሮን ይጠብቃል

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንደ መልሕቅ ሁሉ ጽኑ መሠረት ያለው ተስፋም መረጋጋት ያስገኛል

[ምንጭ]

Courtesy René Seindal/Su concessione del Museo Archeologico Regionale A. Salinas di Palermo