በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያህል የሚለፉት መልካቸውን ለማሳመር ብቻ ነው?

ይህን ያህል የሚለፉት መልካቸውን ለማሳመር ብቻ ነው?

ይህን ያህል የሚለፉት መልካቸውን ለማሳመር ብቻ ነው?

ስፔይን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

ፎች በአፋቸው ላባቸውን በማጽዳትና በመንቀስ ብዙ ሰዓት እንደሚያጠፉ ልብ ብለህ ታውቃለህ? በየቀኑ ብዙ ሰዓት የሚያጠፉት ላባቸውን በመንቀስና በማርገፍገፍ እንጂ ሌላ ነገር ሲሰሩ አይደለም። በቀቀኖችም ይሁኑ ጰልቃኖች፣ ድንቢጦችም ይሁኑ ጅንጅላቴዎች ሁሉም ወፎች በየቀኑ በተደጋጋሚ ይህን ያደርጋሉ። ለምን? ይህ ሁሉ ልፋት መልካቸውን ለማሳመር ብቻ ነው?

ይህን የሚያደርጉበት ዋነኛ ምክንያት መልክን ከማሳመር የበለጠ ቁም ነገር አለው። አንድ አውሮፕላን ከበረራ በፊት ሙሉ ምርመራና ጥገና እንደሚያስፈልገው ሁሉ ወፎችም ጊዜ ወስደው ላባቸውን መንቀስና ማስተካከል ያስፈልጋቸዋል። እንዲያውም እንዲህ ያለው ላባን የማበጃጀት ሥራ ለወፎች የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው። በሚበርሩበት ጊዜ ላባቸው ብዙ ብልሽት ይደርስበታል። ስለዚህ መንቀሱ ላባቸውን ለማጽዳትና ከተባይ ለማንጻት ብቻ ሳይሆን ያለ ችግር እንዲበርሩም ያስችላቸዋል።

ነጋ ጠባ የማበጣጠሩና የመንቀሱ ተግባር ሊነቃቀሉ የሚችሉ የተንጨባረሩ ላባዎችን “አንድ ላይ ማያያዝን” ይጨምራል። የተንጨባረሩት ላባዎች መስተካከላቸውና ስክትክት ማለታቸው ወፉ ያለ ችግር

በቅልጥፍና እንዲበር ያስችለዋል። ቡክ ኦቭ ብሪቲሽ በርድስ የተባለው መጽሐፍ “በተለይ ለመብረር የሚያገለግሉት የክንፍ ላባዎችና አቅጣጫ ለማስተካከል የሚረዱት የጅራት ላባዎች ልዩ ትኩረት ያሻቸዋል” በማለት ይገልጻል።

ወፎች ከተባዮች ራሳቸውን ለመከላከልም የማያቋርጥ ትግል ያደርጋሉ። ጥቃቅን ተባዮች ለወፉ ጤና ጠንቅ ከመሆንም አልፈው ላባዎቹን ይበሉበታል። የተጎዳ መንቆር ያላቸው ወፎች ላባቸውን በአግባቡ ማበጣጠርና መንቀስ ስለማይችሉ ከጤነኞቹ ወፎች ይበልጥ በላባዎቻቸው ላይ ብዙ ተባዮች እንደሚሰፍሩባቸው የሥነ ተፈጥሮ ተመራማሪዎች አስተውለዋል። ከጉንዳኖች የሚመነጨው ፎርሚክ አሲድ የሚባል ኬሚካል ተባዮችን በመግደል በኩል ውጤታማ ስለሆነ አንዳንድ የወፍ ዝርያዎች ሆን ብለው በጉንዳኖች ይወረራሉ።

በመጨረሻም ላባዎቹ ዘይት መቀባት ያስፈልጋቸዋል። ይህም በውኃ ላይ ለሚኖሩ አእዋፍ ላባቸው ውኃ የማይዘልቀው እንዲሆን የሚረዳ ሲሆን ሌሎቹ ወፎች ደግሞ መጥፎ የአየር ሁኔታን በቀላሉ መቋቋም እንዲችሉ ያግዛል። ዘይቱ ግን የሚመጣው ከየት ነው? ይህን ዘይት ወይም ቅባት የሚያመነጨው ከጅራት በላይ የሚገኘው ፕሪን ግላንድ የተባለው ዕጢ ነው። ወፉ ይህ ዕጢ የሚያመነጨውን ቅባት በብዙ ልፋት ለላባዎቹ በሙሉ ያዳርሳል። የበረራ ላባዎች በዚህ ሂደትም ልዩ ትኩረት ያገኛሉ።

ስለዚህ አንድ ወፍ ላባዎቹን በማበጃጀትና በመንቀስ ብዙ ሰዓት ሲያሳልፍ ብናይ ሥራ ፈትቶ ነው ብለን ማሰብ የለብንም። እርግጥ ነው፣ ይህ ሂደት ወፉ ውበቱን እንዲጠብቅ የሚረዳው ቢሆንም ጤንነቱንም ይጠብቅለታል። ላባን ማበጃጀትና መንቀስ ለወፎች የሕልውና ጉዳይ ነው።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ሥዕሎች]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ዘንግ

ላባ ፀጉር

ላባ ጭረት

ቅርንጫፍ

[ሥዕል]

ወፎች ትንንሾቹን ላባዎች ከትልልቆቹ ጋር በማሰካካት የተንጨባረሩት ላባዎች አንድ ላይ እንዲያያዙ ያደርጋሉ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Cortesía del Zoo de la Casa de Campo, Madrid

[በገጽ 24 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

ጰልቃን:- Foto: Loro Parque, Puerto de la Cruz, Tenerife; በቀቀን:- Cortesía del Zoo de la Casa de Campo, Madrid