በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕዝብ ነክ ጥናት፣ መጽሐፍ ቅዱስ እና መጪው ጊዜ

ሕዝብ ነክ ጥናት፣ መጽሐፍ ቅዱስ እና መጪው ጊዜ

ሕዝብ ነክ ጥናት፣ መጽሐፍ ቅዱስ እና መጪው ጊዜ

ስዊድን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ሰብዓዊው ቤተሰብ በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ከነበረው 1.65 ቢሊዮን ተነስቶ በአስደናቂ ፍጥነት በማደግ በምዕተ ዓመቱ ማብቂያ ላይ 6 ቢሊዮን ደርሷል። የምድር ሕዝብ ቁጥር በዚህ አስደንጋጭ ፍጥነት ማደጉን ይቀጥል ይሆን? በያዝነው ሺህ ዓመት ዓለማችን በሕዝብ ብዛት ትጥለቀለቅ ይሆን? እንዲህ ካሉት ውስብስብ ጥያቄዎች ጋር የተፋጠጡት ጠበብት የሕዝብ ነክ ጥናት ባለሙያዎች ተብለው የሚጠሩ ሲሆን የተሠማሩበት መስክ ደግሞ ሕዝብ ነክ ጥናት (ዲሞግራፊ) ተብሎ ይጠራል።

ዌብስተርስ ዲክሽነሪ ይህን ቃል ሲፈታው “ሰብዓዊውን ኅብረተሰብ [በተለይ] ከቁጥሩ፣ ከአሠፋፈሩ፣ ከሥርጭቱና በጣም አስፈላጊ ከሆኑት አኃዛዊ መረጃዎች አንፃር የሚያጠና ስታቲስቲካዊ ጥናት” ብሎታል። በመስኩ የተሰማሩ ባለሙያዎች በሕዝብ ቁጥር ላይ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱትን ሦስት ነገሮች ያጠናሉ። እነዚህም ወሊድ (የሚወለዱ ሕፃናት ቁጥር)፣ ሞት (የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር) እና ፍልሰት (አንድን አገር ለቅቀው ወደ ሌላ አገር የሚዛወሩ ሰዎች ቁጥር) ናቸው።

ታሪካዊ ዲሞግራፊ ባለፉት ዘመናት የነበረውን የሕዝብ ቁጥር እድገትና ተለዋዋጭነት የሚያጠና የጥናት ዘርፍ ነው። በዚህ መስክ የተሰማሩ ሰዎች በጽሑፍ የሰፈሩ መረጃዎችን፣ ፍርስራሾችን፣ አጽሞችን እና ዕደ ጥበባትን በጥንቃቄ በመመርመር ስለ ጥንቱ ሥልጣኔ የቻሉትን ያህል ያጠናሉ። ታሪካዊ ዲሞግራፊ በከፊል የተመሠረተው በግምት ላይ ሲሆን ከፊሉ ደግሞ በተገኘው ሳይንሳዊ እውቀት ላይ ነው። አትላስ ኦቭ ዎርልድ ፖፑሌሽን ሂስትሪ የተባለው ጽሑፍ ሳይደብቅ እንደተናገረው “በታሪካዊው ዲሞግራፊ ጥናት ላይ የተሰማራ ሰው የሚያቀርባቸው መላ ምቶች በአሁኑ ዘመን ባሉት የኪነ ጥበብ መሥፈርቶች ሊረጋገጡ የማይችሉና በስታቲስቲክስ አውጪው ዘንድ ሙሉ አመኔታ ሊጣልባቸው የማይችሉ ናቸው።” ያም ሆኖ በሕዝብ ነክ ጥናቶች ላይ የተመሠረቱ ግምታዊ ሐሳቦች ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጠቀሜታ አላቸው። እንዲያውም እነዚህ ግምቶች ብዙውን ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ጋር ይስማማሉ።

ከጥፋት ውኃ በኋላ የታየው የሕዝብ ቁጥር እድገት

በኖኅ ዘመን ከነበረው የጥፋት ውኃ በሕይወት የተረፉት ስምንት ሰዎች ብቻ እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። አንዳንድ የሕዝብ ነክ ጥናት ባለሙያዎች ከጥፋት ውኃ በኋላ 1,400 ዓመታት ቆይቶ የምድር ሕዝብ ብዛት 50 ሚሊዮን ሳይደርስ እንዳልቀረ ይገምታሉ። ስምንት ሰዎች በ1,400 ዓመታት ውስጥ ቁጥራቸው ወደ 50 ሚሊዮን ማደጉ አጠራጣሪ ይሆንብሃል?

መጀመሪያ ነገር ቁጥራቸው 50 ሚሊዮን ደርሶ ሊሆን ይችላል የሚለው አስተያየት ግምታዊ ነው። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዘፍጥረት 9:1 ላይ የተገለጸውን የሚከተለውን ቃል ልብ ማለት ያሻል:- “እግዚአብሔር ኖኅንና ልጆቹን እንዲህ ሲል ባረካቸው፤ ‘ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት።’” ከዚያም በዘፍጥረት ምዕራፍ 10 እና 11 ላይ የኖኅ ልጆች የሆኑት የሴም፣ የካምና የያፌት ዝርያዎች ስለሆኑ 70 ቤተሰቦች የሚገልጽ ዘገባ እናነባለን። ቀጥለን ከሴም እስከ አብርሃም ባለው የዘር ሐረግ ውስጥ የተጠቀሱትን ሰዎች ዝርዝር እናገኛለን። እነሱም ‘ወንዶችንና ሴቶችን ወለዱ’ የሚል እናነባለን። ይህ ጊዜ አምላክ “ምድርንም ሙሏት” በማለት ከሰጠው ትእዛዝ ጋር በሚስማማ መልኩ ሰዎች ከወትሮው በላቀ ደረጃ በብዛት የተዋለዱበት ዘመን ሊሆን ይችላል።

ስለሚሞቱት ሰዎች ቁጥርስ ምን ሊባል ይችላል? ከላይ ያየናቸው የዘፍጥረት መጽሐፍ ምዕራፎች ከጥፋት ውኃ በኋላ በነበሩት የመጀመሪያዎቹ መቶ ዘመናት የሰው ዕድሜ በጣም ረዥም እንደነበረ ይገልጻሉ። * የሚወለዱ ሕፃናት ቁጥር ከፍተኛ ሆኖ የሟቾች ቁጥር ዝቅተኛ ሲሆን የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት ያድጋል።

እስራኤላውያን በግብጽ የተቀመጡበት ዘመን

እስራኤላውያን በግብጽ ሳሉ ቁጥራቸው በከፍተኛ ፍጥነት ያድግ እንደነበር የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ አንዳንድ ተመራማሪዎች በጥርጣሬ ይመለከቱታል። መጽሐፍ ቅዱስ የልጆቹን ሚስቶች ሳይጨምር “ወደ ግብፅ የወረደው የያዕቆብ ቤተሰብ ቁጥር ሰባ ነበር” ይላል። (ዘፍጥረት 46:26, 27) ሆኖም እስራኤላውያን ከ215 ዓመታት በኋላ ከግብጽ ሲወጡ “ከልጆቹ ሌላ፣ ስድስት መቶ ሺህ እግረኛ ወንዶች ነበሩ።” (ዘፀአት 12:37) ሴቶቹንና ሕፃናቱን ጨምረን ስንቆጥር ከግብጽ የወጡት እስራኤላውያን ጠቅላላ ቁጥር ሦስት ሚሊዮን ሳይደርስ አይቀርም። እንዲህ ያለ የሕዝብ ቁጥር እድገት ሊከሰት ይችላል?

ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስ በግብጽ የነበሩትን እሥራኤላውያን ቁጥር መጨመር አስመልክቶ ምን እንደሚል እንመልከት:- “እስራኤላውያን እየተዋለዱ በዙ፤ ቁጥራቸው እጅግ ከመጨመሩም የተነሣ የግብፅን ምድር ሞሏት።” በዚያን ጊዜ በእስራኤል ሕዝብ ቁጥር ላይ የታየው ጭማሪ ከተለመደው የተለየ ነበር።—ዘፀአት 1:7

በአሁኑ ዘመን ባሉት አገሮችም ተመሳሳይ የሆነ የሕዝብ ብዛት ጭማሪ መታየቱ ትኩረት የሚስብ ነው። በ1980ዎቹ ዓመታት በኬንያ የተከሰተውን ሁኔታ ለዚህ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። የሆነ ሆኖ የእስራኤልን ሕዝብ ቁጥር ጭማሪ የተለየ የሚያደርገው ለረዥም ጊዜ የቀጠለ መሆኑ ነው።

ለእስራኤል ሕዝብ ቁጥር መጨመር ምክንያት የሆነውን ሌላ ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ይነግረናል። እስራኤላውያን በግብጽ ሳሉ የምግብ እጥረት የሚባል ነገር አልነበረም። ረሃብ ሲመጣ ብዙ ሰዎች በለጋ ዕድሜያቸው እንደሚቀጩ የታወቀ ነው። በዚህም ምክንያት በረሃብ ወቅት ብዙ ልጆች አይወለዱም። እስራኤላውያን ግን የተትረፈረፈ ምግብ እንደነበራቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቁማል። የዮሴፍ ቤተሰብ ወደ ግብጽ ሲገቡ ፈርዖን ለዮሴፍ “አባትህንና ወንድሞችህን ምርጥ በሆነው ምድር አስፍራቸው፤ በጌሤም ይኑሩ” ብሎት ነበር። (ዘፍጥረት 47:6) እስራኤላውያን የግብጻውያን ባሮች በነበሩበት ጊዜም እንኳ ሳይቀር በቂ ምግብ ያገኙ የነበረ ይመስላል። እንዲያውም ከግብጽ ባርነት ነፃ ከወጡ በኋላ በባርነት ሳሉ ይበሉ የነበሩትን እንጀራ፣ ዓሣ፣ ዱባ፣ በጢኽ፣ ኩራት፣ ቀይና ነጭ ሽንኩርት እንዲሁም የሥጋውን ምንቸት በናፍቆት አስታውሰዋል።—ዘፀአት 16:3፤ ዘኁልቁ 11:5

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ

ሕዝብ ነክ ጥናት በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከሠፈረው ሐሳብ ጋር በተያያዘ ያለንን ግንዛቤ ሊያሰፋልን ይችላል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ለተከታዮቹ “ሕዝቦችን ሁሉ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ሲል የሰጣቸውን ትእዛዝ ስናነብ ‘ያ የስብከት ሥራ ምን ያህል ሰፊ ነበር?’ ብለን እናስብ ይሆናል። (ማቴዎስ 28:19) በመጀመሪያው መቶ ዘመን በሮማ ግዛት ምን ያህል ሕዝቦች ይኖሩ ነበር? አንዳንዶች በዚያ ጊዜ በሮማ ግዛት የነበረው ሕዝብ ብዛት ከ50 እስከ 60 ሚሊዮን እንደሚደርስ ይገምታሉ። ይህ ግምት ትክክል ከሆነ እነዚያ የጥንት ክርስቲያኖች ከባድ ሥራ ይጠብቃቸው ነበር ማለት ነው!

ክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን ማንበባችንን ስንቀጥል ሐዋርያው ጴጥሮስ ምሥራቹን ለመስበክ ራቅ ብላ ወደምትገኘው ወደ ባቢሎን ተጉዞ እንደነበረ እንረዳለን። (1 ጴጥሮስ 5:13) ወደ ባቢሎን ለመሄድ የመረጠው ለምንድን ነው? ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ላይ የተሰጠው የሚከተለው አስተያየት ፍንጭ ይሰጠናል:- “ከጳለስጢና ምድር ውጪ የነበሩት አይሁዳውያን በሶርያ፣ በትንሹ እስያ፣ በባቢሎኒያና በግብጽ ዋና ዋና ማዕከላት የነበሯቸው ሲሆን በእነዚህ ማዕከሎች በእያንዳንዳቸው ቢያንስ ቢያንስ 1,000,000 አይሁዳውያን ይኖሩ ነበር።” ጴጥሮስ በዋነኝነት ለአይሁድ የመስበክ ኃላፊነት ተጥሎበት ስለነበረ በባቢሎን ላሉት የአይሁድ ማኅበረሰብ ሊሰብክ መሄዱ ተገቢ ነበር። (ገላትያ 2:9) እዚያም ብዙ አይሁድ ይኖሩ ስለነበር የጴጥሮስ ክልል ሰፊ እንደነበረ መገመት አያዳግትም።

ወደፊትስ ምን ሁኔታ ይከሰት ይሆን?

ቀደም ብለን እንዳየነው የሕዝብ ነክ ጥናት ባለሙያዎች ከሰው ልጅ ያለፈ ታሪክ ውስጥ ጥናት የሚያካሂዱት በተወሰኑ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ብቻ ነው። ታዲያ ስለወደፊቱ ጊዜ ምን ይላሉ? በአእምሯቸው ውስጥ የሚውጠነጠኑ አበይት ጥያቄዎች አሉ። በያዝነው ሺህ ዓመት ዓለማችን በሕዝብ ብዛት ትጥለቀለቅ ይሆን? የዚህን ጥያቄ መልስ በእርግጠኝነት የሚያውቅ የለም። በበርካታ አገሮች የወሊድ መጠን እየቀነሰ በመሆኑ አንዳንዶቹ ተመራማሪዎች የዓለም ሕዝብ ቁጥር ጭማሪ ሳያሳይ ባለበት ይቀጥላል ብለው ይተነብያሉ።

ይሁን እንጂ በዚህ ትንበያ የሚስማሙት ሁሉም ባለሙያዎች አይደሉም። ፖፑሌሽን ቱዴይ የተሰኘው ጽሑፍ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ ያሉ አገሮች በሕዝብ ቁጥር ጭማሪ ረገድ በሁለት የተለያዩ ክፍሎች ይመደባሉ። እነርሱም፣ ባልና ሚስት ሁለት ወይም ከዚያ በታች ልጆች የሚወልዱባቸውና ብዙ ልጆች የሚወልዱባቸው አገሮች ናቸው። ወላጆች ሁለት ወይም ከዚያ በታች ልጆች የሚወልዱባቸው አገሮች አውሮፓን፣ ዩናይትድ ስቴትስን፣ ካናዳንና በኢንዱስትሪ በፍጥነት በማደግ ላይ ያሉ ጥቂት አገሮችን ይጨምራሉ። . . . በአንፃሩ ደግሞ በሕዝብ ብዛት ፈጣን እድገት በማሳየት ላይ ካሉት አገሮች መካከል ባልና ሚስት ከሁለት ልጆች በላይ የሚወልዱባቸው አብዛኞቹ የአፍሪካ፣ የእስያና የላቲን አሜሪካ አገሮች ይገኙበታል። ከዓለም ጠቅላላ ሕዝብ ውስጥ ከግማሽ የሚበልጠው በሚኖርባቸው በእነዚህ አገሮች ሴቶች እያንዳንዳቸው በአማካይ አራት ልጆች ይወልዳሉ።”

ስለዚህ በአንዳንድ አገሮች ያለው የሕዝብ ብዛት እየቀነሰ ሲሆን በሌሎች አገሮች ግን ጨምሯል ወይም ባለበት ቀጥሏል። ፖፑሌሽን ቱዴይ መጪው ጊዜ በሕዝብ ብዛት ረገድ ምን መልክ ሊኖረው እንደሚችል እንደሚከተለው በማለት ጠቅለል አድርጎ ገልጿል:- “በብዙዎቹ ታዳጊ አገሮች የሚታየው ፈጣን የሕዝብ ቁጥር እድገት ገና አልተገታም። በዓለም አቀፍ ደረጃ ‘በከፍተኛ ፍጥነት እያሻቀበ ያለውን የሕዝብ ቁጥር’ እንዲሁ በሐሳብ ደረጃ ሳይሆን በተግባር መግታት ይቻላል አይቻልም የሚለውን ጉዳይ የሚወስነው አገሮች የሕፃናትን ሞት ለመቀነስ፣ ሴቶችን ለማስተማርና የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ለመስጠት የሚንቀሳቀሱበት ፍጥነትና ለዚህ ዓላማ የሚያውሉት የገንዘብ መጠን ነው።”

በአሁኑ ጊዜ ከስድስት ቢሊዮን በላይ የሆነው የምድር ሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ይሄድ ይሆን? ጊዜ ያሳየናል። ይሁን እንጂ በእርግጠኝነት የምናውቀው ነገር ቢኖር የአምላክ ዓላማ ምድር እንድትሞላ እንጂ በሕዝብ ብዛት እንድትጥለቀለቅ አለመሆኑን ነው። (ዘፍጥረት 1:28) በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ይህ እንደሚከናወን እርግጠኞች እንድንሆን የሚያስችለን በቂ ምክንያት አለን።—ኢሳይያስ 55:10, 11

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.9 ከጊዜ በኋላ ግን በ1500 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ ሙሴ እንዳመለከተው የሰው አማካይ ዕድሜ ወደ 70 እና 80 ዝቅ ብሏል።—መዝሙር 90:10

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዛሬ ከስድስት ቢሊዮን በላይ የሆነው የዓለም ሕዝብ የተገኘው ከጥፋት ውኃ ከተረፉ ጥቂት ሰዎች ነው

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወደ ግብጽ ሲገቡ ጥቂት የነበሩት እስራኤላውያን ቁጥር በ215 ዓመታት ውስጥ ወደ ሦስት ሚሊዮን አድጓል