በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አውሮፕላኑን በድንገት ማሳረፍ

አውሮፕላኑን በድንገት ማሳረፍ

አውሮፕላኑን በድንገት ማሳረፍ

ሴዛር ሙኖዝ እንደተናገረው

በሜክሲኮ ሞንቴሪ ከተማ ቤተሰቦቼን ለመጠየቅ ሄጄ አስደሳች ጊዜ ካሰለፍኩ በኋላ የማገልገል መብት ባገኘሁበት በሜክሲኮ ከተማ ወዳለው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ለመመለስ ተነሳሁ። ዕለቱ እሁድ፣ ታኅሣሥ 1, 2002 ነበር። በበረራ ቁጥር 190 ተሳፈርኩና አውሮፕላኑ ከምሽቱ በ1 ሰዓት ተነሳ።

ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል ሰላማዊ በረራ ካደረግን በኋላ አውሮፕላኑ ወደ ታች መውረድ ጀመረ። ከዚያም በድንገት ሽቅብ ሲፈተለክ ከታች በሚያሰማው በጣም አሰቃቂ ድምፅ የተነሳ ሁላችንም በጣም ደነገጥን። ቀጥሎም አብራሪው የአውሮፕላኑ ጎማዎች አልዘረጋ እንዳሉት ነገረን። ከመንገደኞቹ አንዳንዶቹ በጣም ስለፈሩ ያለቅሳሉ፤ ሌሎች ደግሞ ጮክ ብለው ይጸልያሉ። እኔም ምን ሊደርስብን ነው ብዬ ተጨነቅኩ።

አብራሪው የአውሮፕላኑ ጎማዎች እንዲዘረጉ ለማድረግ አንዳንድ እርምጃዎችን እንደሚወስድ ነገረን። ስለዚህ በሜክሲኮ ከተማ ሰማይ ላይ አውሮፕላኑን ከላይ ታች እንዲሁም ከአንዱ ጎን ወደሌላው እያንገጫገጨ ለአንድ ሰዓት ያህል አበረረ። በአንዳንድ መናፈሻዎች ሰዎችን ለማዝናናት ሲባል የሚዘጋጁ አስፈሪ በሆነ ፍጥነት በሐዲድ ላይ ሽቅብና ቁልቁል የሚምዘገዘጉ ተሽከርካሪዎች አሉ። እርግጥ ሰዎች በእነዚህ ተሽከርካሪዎች የሚሳፈሩት ለመዝናናት ነው። ይህ ግን ከዚያ ፈጽሞ የተለየ ነው! ከዚያም አብራሪው “እንግዲህ የአውሮፕላኑ ጎማዎች አልዘረጋ እንዳሉ ስንነግራችሁ በጣም እያዘንን ነው። ስለዚህ አሁን ያለን አማራጭ አውሮፕላኑ ያለ ጎማ እንዲያርፍ ማድረግ ብቻ ነው” በማለት አስታወቀን። በቃ ማለቃችን ነው ብለን በመጨነቅ እርስ በርሳችን ተያየን።

ከዚያም ልንወስዳቸው የሚገቡንን እርምጃዎች በተመለከተ አንዳንድ መመሪያዎች ተሰጡን። ጫማችንን አወለቅን፣ ሊያቆስለን የሚችል ማንኛውንም ነገር አስወገድን እንዲሁም በተነገረን መመሪያ መሠረት ተቀመጥን። ከማኮብኮቢያው መንገድ ጋር እንደምንላተም እርግጥኛ ነበርኩ! በዚሁ ወቅት ወደ ይሖዋ ጸለይኩ፤ ከዚያም ጥልቅ የሆነ የመረጋጋት ስሜት ተሰማኝ።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

አንድ ሰው ሊሞት ሲል ሕይወቱን መለስ ብሎ እንደሚቃኝና ይህን ወይም ያን አድርጌ ቢሆን ኖሮ እያለ እንደሚቆጭ በተደጋጋሚ ሰምቼ ነበር። ከጎኔ ለተቀመጠችው ልጅ ስለ አምላክ መንግሥት ሳልነግራት በመቅረቴ አዘንኩኝ፤ ከዚህ አደጋ በሕይወት ከተረፍኩ ያገኘሁትን እያንዳንዱን አጋጣሚ ለመመስከር እንደምጠቀምበት ለራሴ ቃል ገባሁ። ለይሖዋ ሳቀርብ የነበረውን አገልግሎትም ለአንድ አፍታ መለስ ብዬ ለመገምገም ሞከርኩ።

አውሮፕላኑ ወደ ታች መውረድ ሲጀምር የእሳት አደጋ መከላከያ መኪናዎች፣ አምቡላንሶችና ብዙ ሰዎች በአካባቢው ቆመው ተመለከትኩ። ከዚያም አውሮፕላኑ በሆዱ የማኮብኮቢያ መንገዱን ሲነካ ከፍተኛ መንገጫገጭ ተሰማን። አውሮፕላኑ በደረቱ እየተንፏቀቀ ሲሄድ የሚፈጠረው እሳት ሲፈነጣጠር ይታያል። ከማኮብኮቢያው መንገድ ግራና ቀኝ ቆመው የነበሩት የእሳት አደጋ መኪናዎች አውሮፕላኑን ለማብረድ ወዲያውኑ ብዙ ውኃ መርጨት ጀመሩ።

በመጨረሻም በብዙ ጭንቅ ለጥቂት ጊዜ ከቆየን በኋላ አውሮፕላኑ ቆመ። የአውሮፕላኑ አብራሪ ይህን ድንገተኛ ሁኔታ በተሳካ መንገድ ለመቆጣጠር በመቻሉ በጣም በመደሰት ጭብጨባችንን አቀለጥነው። ከዚያም አውሮፕላኑን ቶሎ ለቀን እንድንወጣ ተነገረን። በፍጥነት ወደ መውጫ በሮቹ ሄደን ቀጥ ብለው በሚያወርዱት ማንሸራተቻዎች ላይ ተንሸራትተን በማኮብኮቢያዎቹ መሃል ባለው ሣር ላይ በደህና ወረድን።

ተንኮታኩቶ ከአገልግሎት ውጭ የሆነውን አውሮፕላን ራቅ ብዬ ቆሜ በድንጋጤ እየተንቀጠቀትኩ ተመለከትኩት። ደግነቱ የተጎዱት ጥቂት መንገደኞች ሲሆኑ የደረሰባቸው ጉዳትም ቢሆን በጣም ቀላል ነበር። በድንጋጤ የተዝለፈለፉትም እዚያው በአምቡላንሶች ውስጥ የሕክምና እርዳታ ተደረገላቸው።

ጉዞ ስንጀምር ከምሽቱ በ3 ሰዓት ቤቴ ደርሳለሁ ብዬ አስቤ የነበርኩት ሰው ካሰብኩበት 4 ሰዓት ዘግይቼ ደረስኩ። ሊደርስ ይችል የነበረውንና የደረሰውን ሁሉ ሳስብ በሕይወት በመትረፌ በጣም አመስጋኝ ነኝ! ይህ ገጠመኝ ሕይወቴን መለስ ብዬ እንድቃኝ አድርጎኛል። ሕይወት አስተማማኝ ያለመሆኑን ሐቅ እንድቀበል አድርጎኛል። ሁሉም ነገር በቅጽበት እንዳልነበረ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ አስፈላጊ ነው። አንድ ሰው በሕይወት የመቀጠሉ ጉዳይ አጠራጣሪ ሲሆን ሕይወቱን ለማስተካከልም ሆነ በአምላክ ዘንድ ጥሩ ስም ለማትረፍ የሚያበቃ ጥሩ ተግባር ለማከናወን የሚያስችል ጊዜ አይኖረውም። አሁን ሕይወቴን በጥበብ ለመምራትና እያንዳንዱን ቀን አምላኬን ይሖዋን በማገልገል ለማሳለፍ ያገኘሁትን አጋጣሚ ከምን ጊዜውም ይበልጥ አደንቃለሁ።—መዝሙር 90:12