በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከበሽታ የጸዳ ዓለም

ከበሽታ የጸዳ ዓለም

ከበሽታ የጸዳ ዓለም

የማንኛውም አገር ሰዎች ጤነኛ መሆን ሌሎቹን አገሮች በቀጥታ መጥቀሙና ማሳሰቡ ስለማይቀር ሁሉም አገሮች በተባባሪነትና አንዱ ሌላውን ለማገልገል በመፈለግ መንፈስ ተነሳስተው ሁሉም ሰው መሠረታዊ የሆነ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ የጋራ ጥረት ማድረግ አለባቸው።”የአልማ አታ መግለጫ፣ መስከረም 12, 1978

ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት ለእያንዳንዱ የምድር ነዋሪ መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ማዳረስ የሚቻል ነገር መስሎ ታይቶ ነበር። በአሁኑ ጊዜ በካዛክስታን በምትገኘው በአልማ አታ የተደረገው የመሠረተ ጤና አገልግሎት ጉባኤ ዓለም አቀፍ ተወካዮች እስከ 2000 ዓመት ድረስ የዋና ዋናዎቹን ተላላፊ በሽታዎች ክትባቶች ለሁሉም የሰው ልጅ ለማዳረስ ውሳኔ አስተላልፈው ነበር። በተጨማሪም በዚሁ ዓመት መሠረታዊ የፍሳሽ ማስወገጃና ንጹሕ ውኃ ለዓለም ሕዝብ በሙሉ ለማዳረስ እንደሚቻል ተስፋ አድርገው ነበር። ሁሉም የዓለም ጤና ድርጅት አባል አገሮች ይህን ውሳኔ በፊርማቸው አጽድቀዋል።

ሕልማቸው በጣም የሚደነቅ ይሁን እንጂ ያሰቡትን እውን ለማድረግ የተደረገው ክትትል በጣም ደካማ ነው። መሠረታዊ የጤና አጠባበቅ አገልግሎት ለሁሉም የሰው ዘር ማዳረስ ካለመቻሉም በላይ አሁንም ድረስ በቢሊዮን የሚቆጠሩ የሰው ልጆች ለተላላፊ በሽታዎች የተጋለጡ ናቸው። እነዚህ ገዳይ በሽታዎች ደግሞ በአብዛኛው የሕፃናትንና በአፍላ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ጎልማሶችን ሕይወት በአጭር በመቅጨት ላይ ይገኛሉ።

ሦስቱ ተጣማሪ በሽታዎች ማለትም ኤድስ፣ ሳንባ ነቀርሳና ወባ የፈጠሩት አስጊ ሁኔታ እንኳን አገሮች ‘የጋራ ጥረት እንዲያደርጉ’ አላንቀሳቀሳቸውም። ኤድስን፣ ሳንባ ነቀርሳንና ወባን ለመዋጋት የተቋቋመው ዓለም አቀፍ ድርጅት የእነዚህን በሽታዎች ወረርሽኝ ለመግታት መንግሥታት 13 ቢሊዮን ዶላር እንዲያዋጡ ጠይቆ ነበር። ይሁን እንጂ እስከ 2002 አጋማሽ ድረስ የተገኘው ገንዘብ ከ2 ቢሊዮን ዶላር ብዙም ያልበለጠ ሲሆን በዚሁ ዓመት ለወታደራዊ ወጪ የዋለው ገንዘብ 700 ቢሊዮን ዶላር ደርሶ ነበር። በዚህ የተከፋፈለ ዓለም ውስጥ እየተከሰቱ ያሉት አስጊ ሁኔታዎች የዓለምን ብሔራት ለጋራ ጥቅም በአንድ ልብ እንዲቆሙ ሊያነሳሷቸው አለመቻላቸው በጣም ያሳዝናል።

የጤና ድርጅቶች ምንም ያህል ታላቅ ዓላማ ይዘው ቢነሱ አቅማቸው ውስን መሆኑ ከተላላፊ በሽታዎች ጋር የሚያደርጉትን ውጊያ በብቃት እንዳይወጡ እንቅፋት ፈጥሮባቸዋል። መንግሥታት የሚያስፈልገውን ያህል ገንዘብ ላያቀርቡ ይችላሉ። ረቂቅ ተሕዋስያን ብዙዎቹን መድኃኒቶች የመቋቋም አቅም አዳብረዋል፣ ሰዎች ደግሞ ለአደጋ እንዳይጋለጡ የሚያስችላቸውን የባሕርይ ለውጥ አያደርጉም። ከዚህም በላይ በአንዳንድ የዓለም አካባቢዎች በተደጋጋሚ ጊዜያት የሚከሰት ጦርነት፣ ረሃብና ድህነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በበሽታዎች እንዲለከፉ ያደርጋል።

አምላክ ስለ ጤንነታችን ያስባል

ይሁንና ይህ ችግር ምንም መፍትሔ የለውም ማለት አይደለም። ይሖዋ አምላክ ስለ ሰው ልጆች ጤና በጥብቅ እንደሚያስብ የሚያረጋግጥ ማስረጃ አለን። የገዛ ሰውነታችን ያለው በሽታ የመከላከል ኃይል ለዚህ አሳቢነቱ ግሩም ማስረጃ ነው። ይሖዋ ለጥንት ሕዝቦቹ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው በርካታ ሕጎች ሕዝቡን ከተላላፊ በሽታዎች የመጠበቅ ፍላጎት እንደነበረው ያሳያሉ። *

የሰማይ አባቱን ባሕርይ የሚያንጸባርቀው ኢየሱስ ክርስቶስም በተመሳሳይ ለሕሙማን ይራራል። የማርቆስ ወንጌል ኢየሱስ አንድ ሥጋ ደዌ የያዘው ሰው ባገኘ ጊዜ ያደረገውን ይነግረናል። ሕመምተኛው “ብትፈቅድ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” ብሎ ለመነው። ኢየሱስ የሰውየውን ሕመምና ሥቃይ ሲመለከት በጣም አዘነለት። “እፈቅዳለሁ፣ ንጻ” አለው።—ማርቆስ 1:40, 41

የኢየሱስ ተአምራዊ ፈውስ በጥቂት ግለሰቦች ብቻ ተወስኖ የቀረ አልነበረም። ማቴዎስ የተባለው የወንጌል ጸሐፊ እንደዘገበው ኢየሱስ “እያስተማረ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል እየሰበከ፣ በሕዝቡ መካከል ማንኛውንም ደዌና ሕመም እየፈወሰ በመላው ገሊላ ይዘዋወር ነበር።” (ማቴዎስ 4:23) ኢየሱስ የፈጸመው ተአምራዊ ፈውስ የይሁዳንና የገሊላን ሕሙማን ከመጥቀሙ በተጨማሪ ሌላም ዓላማ ነበረው። ኢየሱስ የሰበከው የአምላክ መንግሥት አለማንም ተቃዋሚ መላውን የሰው ዘር በሚገዛበት ጊዜ ሁሉም ዓይነት በሽታዎች እንዴት ፈጽመው እንደሚወገዱ ከወዲሁ ያመላክታል።

ሁሉም ሰው ጤናማ ይሆናል የሚለው ተስፋ የማይሆን ሕልም አይደለም

በመላው ምድር ላይ ፍጹም ጤና ይሰፍናል ብሎ ተስፋ ማድረግ ሊሆን የማይችል ሕልም አይደለም። ሐዋርያው ዮሐንስ “የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል” የሚሆንበትን ጊዜ አስቀድሞ ተመልክቶ ነበር። አምላክ በሚወስደው በዚህ እርምጃ ምክንያት “ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም። የቀድሞው ሥርዓት ዐልፎአልና።” አይሆንም እንጂ ቢሆንማ በጣም ጥሩ ነበር ብለህ ታስባለህ? አምላክ ራሱ “ይህ ቃል የታመነና እውነት” እንደሆነ አረጋግጦልናል።—ራእይ 21:3-5

እርግጥ፣ በሽታ እንዲጠፋ ከተፈለገ ድህነት፣ ረሃብና ጦርነትም መጥፋት ይኖርበታል። ምክንያቱም እነዚህ ችግሮች ተላላፊ በሽታ ለሚያመጡ ረቂቅ ተሕዋስያን እገዛ ያደርጋሉ። በመሆኑም ይሖዋ ይህን ታላቅ ሥራ በክርስቶስ ለሚተዳደረው ሰማያዊ መንግሥቱ ሰጥቷል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከልባቸው ለሚያቀርቡለት ጸሎት መልስ በመስጠት ይህን መንግሥት ያመጣል። መንግሥቱ ደግሞ የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲሆን ያደርጋል።—ማቴዎስ 6:9, 10

የአምላክ መንግሥት መቼ ይመጣል ብለን መጠበቅ እንችላለን? ኢየሱስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ የአምላክ መንግሥት እርምጃ ሊወስድ መቃረቡን የሚያመለክቱ ተከታታይ ክስተቶች እንደሚኖሩ ተንብዮአል። ከእነዚህ ምልክቶች አንዱ ምን እንደሆነ ሲገልጽ “ቸነፈር በተለያየ ስፍራ ይከሠታል” ብሏል። (ሉቃስ 21:10, 11፤ ማቴዎስ 24:3, 7) “ቸነፈር” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ማንኛውንም ለሞት የሚያደርስ ተላላፊ በሽታ” ያመለክታል። በ20ኛው መቶ ዘመን በሕክምና ሳይንስ ረገድ ከፍተኛ የሆነ እድገት ቢታይም በጣም አስከፊ የሆኑ ቸነፈሮች ተከስተዋል።—“ከ1914 ወዲህ በተከሰቱ ቸነፈሮች የሞቱ ሰዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ኢየሱስ በወንጌሎች ውስጥ ከተናገረው ቃል ጋር የሚመሳሰለው የራእይ መጽሐፍ ትንቢት ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይ ሥልጣኑን በሚይዝበት ጊዜ አጅበው የሚከተሉት ፈረሰኞች እንደሚኖሩ ይገልጻል። አራተኛው ፈረሰኛ ‘በግራጫ ፈረስ’ ላይ ተቀምጦ “መቅሠፍት” እያስከተለ ያልፍ ነበር። (ራእይ 6:2, 4, 5, 8) ከ1914 ወዲህ በተከሰቱት ዋና ዋና ተላላፊ በሽታዎች ምክንያት የሞቱት ሰዎች ብዛት በእርግጥም ይህ ምሳሌያዊ ፈረሰኛ በመጋለብ ላይ መሆኑን ያረጋግጥልናል። በዚህ “መቅሠፍት” ሳቢያ በመላው ዓለም የደረሰው መከራ የአምላክ መንግሥት የሚመጣበት ጊዜ በጣም ቅርብ ለመሆኑ ተጨማሪ ማረጋገጫ ይሰጠናል። *ማርቆስ 13:29

የሕክምናው ሳይንስ የአንዱን ተላላፊ በሽታ ግስጋሴ ለጥቂት ዓመታት ጋብ ሲያደርግልን ሌላ አዲስ ቸነፈር ይከሰታል። ይህን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊያስወግድልን የሚችለው ከሰው የበለጠ ኃይል ያለው አካል እንደሆነ ግልጽ ነው። ፈጣሪያችንም ይህን እንደሚያደርግ ቃል ገብቶልናል። ነቢዩ ኢሳይያስ በአምላክ መንግሥት ውስጥ “‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም” በማለት ዋስትና ይሰጠናል። ከዚህም በተጨማሪ “[አምላክ] ሞትንም ለዘላለም ይውጣል። ጌታ እግዚአብሔር ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል።” (ኢሳይያስ 25:8፤ 33:22, 24) ይህ ቀን ሲጠባ በሽታ ከናካቴው ድል ይደረጋል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.8 በሙሴ ሕግ ውስጥ ቆሻሻ ስለ ማስወገድ፣ ስለ አካባቢ ንጽሕና፣ ስለ ጤና አጠባበቅና የታመመ ሰው ከሌሎች ተገልሎ ስለሚቆይበት ሁኔታ የተሰጡ መመሪያዎች ይገኛሉ። ዶክተር ኤች ኦ ፊሊፕስ “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ሥነ ተዋልዶ፣ በሽታዎችን ስለ መመርመር፣ ስለ ማከምና ስለ መከላከል የተሰጡት መግለጫዎችና መመሪያዎች ከሂፖክራተስ መላ ምቶች የበለጠ ዘመናዊና አስተማማኝ ናቸው” ብለዋል።

^ አን.15 የአምላክ መንግሥት የሚመጣበት ጊዜ መቅረቡን የሚጠቁሙ ተጨማሪ ማስረጃዎች ማግኘት ከፈለግክ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 11ን ተመልከት።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ከ1914 ወዲህ በተከሰቱ ቸነፈሮች የሞቱ ሰዎች

እነዚህ አሐዛዊ መረጃዎች ግምታዊ ናቸው። ቢሆንም የሰው ልጅ ከ1914 ወዲህ በቸነፈሮች ምን ያህል እንደተጠቃ ያሳያሉ።

ፈንጣጣ (ከ300 ሚሊዮን እስከ 500 ሚሊዮን) ለፈንጣጣ አስተማማኝ የሆነ መድኃኒት አልተገኘም። ዓለም አቀፋዊ በሆነ የክትባት ፕሮግራም አማካኝነት በመጨረሻ በ1980 ሊወገድ ችሏል።

ሳንባ ነቀርሳ (ከ100 ሚሊዮን እስከ 150 ሚሊዮን) በአሁኑ ጊዜ ሳንባ ነቀርሳ በግምት በየዓመቱ ሁለት ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎችን ይገድላል። በተጨማሪም በምድር ላይ ከሚኖሩ 3 ሰዎች መካከል አንዱ በደሙ ውስጥ የሳንባ ነቀርሳ ባክቴሪያ ይገኝበታል።

ወባ (ከ80 ሚሊዮን እስከ 120 ሚሊዮን) በ20ኛው መቶ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ በየዓመቱ በወባ የሚሞቱ ሰዎች ብዛት ሁለት ሚሊዮን ያህል ነበር። በአሁኑ ጊዜ ሰዎች በብዛት በወባ የሚሞቱት ከሰሐራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ሲሆን አሁንም በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎችን ይገድላል።

የኅዳር በሽታ (ከ20 ሚሊዮን እስከ 30 ሚሊዮን) አንዳንድ ታሪክ ጸሐፊዎች በዚህ በሽታ ያለቁት ሰዎች ቁጥር ከዚህ በእጅጉ እንደሚበልጥ ይናገራሉ። ይህ ቀሳፊ በሽታ የመጣው የመጀመሪያውን ዓለም ጦርነት እግር ተከትሎ ሲሆን በ1918 እና 1919 መላውን ምድር አዳርሷል። ማን ኤንድ ማይክሮብስ የተባለው መጽሐፍ “ቡቦኒክ ቸነፈር እንኳን ይህን በሚያክል ፍጥነት ይህን የሚያክሉ ሰዎችን አልገደለም” ይላል።

ተስቦ (20 ሚሊዮን ገደማ) አብዛኛውን ጊዜ ጦርነት ሲነሳ የተስቦ ወረርሽኝ አብሮ ይከሰታል። አንደኛው የዓለም ጦርነትም የምሥራቅ አውሮፓ አገሮችን ያጨደ የተስቦ ወረርሽኝ እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል።

ኤድስ (ከ20 ሚሊዮን በላይ) ይህ ዘመናዊ መቅሠፍት በየዓመቱ ሦስት ሚሊዮን የሚያክሉ ሰዎችን ይገድላል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤድስ ፕሮግራም በሰጠው ግምታዊ አሐዝ መሠረት “በሽታውን ለመከላከልና ለማከም ከፍተኛ ጥረት ካልተደረገ . . . ከ2000 እስከ 2020 ባሉት ዓመታት 68 ሚሊዮን ሰዎች ይሞታሉ።”

[በገጽ 11 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በአምላክ መንግሥት ውስጥ እንደነዚህ ያሉ በሽታዎች ጨርሶ አይኖሩም

ኤድስ

ወባ

ሳንባ ነቀርሳ

[ምንጮች]

ኤድስ:- CDC; ወባ:- CDC/Dr. Melvin; ሳንባ ነቀርሳ:- © 2003 Dennis Kunkel Microscopy, Inc.

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ሁሉንም ዓይነት በሽታና የአካል ጉዳት ፈውሷል