በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጋብቻ እንደ ቅዱስ ነገር መታየት ያለበት ለምንድን ነው?

ጋብቻ እንደ ቅዱስ ነገር መታየት ያለበት ለምንድን ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ጋብቻ እንደ ቅዱስ ነገር መታየት ያለበት ለምንድን ነው?

በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ጋብቻ ቅዱስ እንደሆነ እንደሚያምኑ ይናገሩ ይሆናል። ታዲያ ብዙ ጋብቻዎች በፍቺ የሚፈርሱት ለምንድን ነው? በአንዳንዶቹ ዘንድ ጋብቻ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ቃል ኪዳንና ሕጋዊ ውል ከመሆን አያልፍም። ቃል ኪዳን ደግሞ ሊፈርስ እንደሚችል ይሰማቸዋል። ጋብቻን በዚህ መንገድ የሚመለከቱት ሰዎች ከጋብቻ አገኛለሁ ብለው የጠበቁትን ነገር ሲያጡ ጋብቻውን ማፍረስ በጣም ቀላል ሆኖ ያገኙታል።

አምላክ የጋብቻ ጥምረትን የሚመለከተው እንዴት ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዕብራውያን 13:4 ላይ የሚገኝ ሲሆን እሱም “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር ይሁን” ይላል። “ክቡር” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ውድ የሆነና ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነገር የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። አንድን ነገር ከፍ ያለ ዋጋ የምንሰጠው ከሆነ አጥብቀን ለመያዝ እንጠነቀቃለን እንጂ በምንም ሁኔታ እንዲጠፋብን አንፈልግም። ጋብቻንም እንዲህ ልንመለከተው ይገባናል። ክርስቲያኖች ጋብቻን እንደ ክቡር ነገር ማለትም በጥንቃቄ ሊያዝ እንደሚገባው ውድ ነገር አድርገው መመልከት አለባቸው።

ይሖዋ አምላክ ጋብቻን ሲመሠርት ባልና ሚስትን የሚያጣምር ቅዱስ ዝግጅት እንዲሆን አስቦ እንደነበር ግልጽ ነው። ታዲያ እኛ አምላክ ለጋብቻ ያለው ዓይነት አመለካከት እንዳለን የምናሳየው እንዴት ነው?

ፍቅርና አክብሮት

ጋብቻ ክቡር እንዲሆን የትዳር ጓደኛሞች እርስ በርሳቸው መከባበር አለባቸው። (ሮሜ 12:10) ሐዋርያው ጳውሎስ ለመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች “ከእናንተ እያንዳንዱ ሚስቱን እንደ ራሱ አድርጎ ይውደድ፤ ሚስትም ባሏን ታክብር” በማለት ጽፎላቸው ነበር።—ኤፌሶን 5:33

እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ የትዳር ጓደኛ የሚያደርገው ነገር እምብዛም የሚያስወድድ ወይም የሚያስከብር ላይሆን ይችላል። ሆኖም ክርስቲያኖች ከላይ የተጠቀሰውን ዓይነት ፍቅርና አክብሮት ማሳየት አለባቸው። ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ሌላውን ይቅር በሉ” በማለት ጽፏል።—ቆላስይስ 3:13

ለትዳር ጓደኛ ጊዜና ትኩረት መስጠት

ጥምረታቸውን እንደ ቅዱስ የሚመለከቱ ባልና ሚስት አንዱ የሌላውን አካላዊና ስሜታዊ ፍላጎት ለማሟላት ጊዜ ይመድባሉ። ይህ ጉዳይ በወሲባዊ ግንኙነታቸው ረገድም ይሠራል። መጽሐፍ ቅዱስ “ባል ለሚስቱ የሚገባትን ሁሉ ያድርግላት፤ ሚስትም እንዲሁ ለባሏ የሚገባውን ሁሉ ታድርግለት” ይላል።—1 ቆሮንቶስ 7:3

ይሁን እንጂ አንዳንድ ባልና ሚስቶች ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ሲባል ባልየው ለጊዜው ራቅ ወዳለ ቦታ ሄዶ መሥራቱ አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል። አንዳንድ ጊዜም ባልና ሚስቱ ተራርቀው የሚቆዩበት ጊዜ ሳይታሰብ ሊረዝም ይችላል። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለው መራራቅ በጋብቻው ላይ ችግር የሚያስከትል ሲሆን አንዳንዴም ምንዝር እስከመፈጸምና እስከፍቺ ያደርሳል። (1 ቆሮንቶስ 7:2, 5) በዚህም ምክንያት ብዙ ክርስቲያን ባልና ሚስቶች እንደ ቅዱስ ነገር የሚቆጥሩት ጋብቻቸው አደጋ ላይ ከሚወድቅ ይልቅ ቁሳዊ ጥቅም እንዲቀርባቸው ወስነዋል።

ችግር ሲያጋጥም

ጋብቻቸውን የሚያከብሩ ክርስቲያኖች ችግር ሲያጋጥም በችኮላ አይለያዩም ወይም አይፋቱም። (ሚልክያስ 2:16፤ 1 ቆሮንቶስ 7:10, 11) ኢየሱስ እንደሚከተለው ሲል ተናግሯል:- “በላዩ ላይ ስታመነዝር ካላገኛት በስተቀር፣ ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ እንድታመነዝር ያደርጋታል፤ በዚህ ሁኔታ የተፈታችውን ሴት ያገባም እንዳመነዘረ ይቆጠራል።” (ማቴዎስ 5:32) ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት ሳይኖር መፋታትን ወይም መለያየትን መምረጥ ጋብቻን ማርከስ ነው።

ለጋብቻ ያለን አመለካከት በትዳራቸው ችግር ለገጠማቸው ሰዎች በምንሰጠው ምክር ላይም ይንፀባረቃል። እንዲለያዩ ወይም እንዲፋቱ ለመምከር እንቸኩላለን? እርግጥ ነው፣ ከፍተኛ የሆነ አካላዊ ድብደባና ሆን ብሎ መተዳደሪያ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆንን የመሳሰሉ ለመለያየት የሚያበቁ ሕጋዊ ምክንያቶች የሚኖሩበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። * በተጨማሪም ከላይ እንደተጠቀሰው መጽሐፍ ቅዱስ ፍቺ የሚፈቅደው አንዱ የትዳር ጓደኛ ምንዝር ሲፈጽም ነው። ያም ሆኖ ክርስቲያኖች እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎች በሚያደርጉት ውሳኔ ላይ ጫና ማድረግ አይኖርባቸውም። ደግሞም የውሳኔውን መዘዝ የሚጋፈጠው ባለ ችግሩ ነው እንጂ ምክር ሰጪው አይደለም።—ገላትያ 6:5, 7

ጋብቻን እንደ ቀላል ነገር አትቁጠሩ

በአንዳንድ አካባቢዎች ግለሰቦች በሌላ አገር ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ሲሉ በጋብቻ መጠቀማቸው የተለመደ ነገር ሆኗል። ይህም አብዛኛውን ጊዜ የፈለጉትን አገር ዜጋ በገንዘብ ገዝቶ ማግባትን ይጨምራል። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ባልና ሚስቶች ቢጋቡም አብረው የማይኖሩ ከመሆኑም በላይ በወዳጅነት እንኳ የማይቀራረቡ ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚያም የተፈለገውን ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ካገኙ በኋላ ይፋታሉ። ጋብቻቸውን የሚመለከቱት እንደ ንግድ ስምምነት ብቻ አድርገው ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ግን እንዲህ ዓይነቱን የግዴለሽነት አመለካከት አይደግፍም። የልባቸው ግፊት ምንም ይሁን ምን ያገቡ ሰዎች አምላክ የዕድሜ ልክ ትስስር እንደሆነ በሚቆጥረው ቅዱስ ዝግጅት ውስጥ ገብተዋል። እንደዚህ ባለው ስምምነት ውስጥ የሚገቡ ሁሉ በአምላክ ፊት አሁንም እንደ ባልና ሚስት ስለሚቆጠሩ ለመፋታት የሚያበቃ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት እስከሌላቸው ድረስ እንደገና ማግባት አይችሉም።—ማቴዎስ 19:5, 6, 9

ማንኛውንም ጠቃሚ ነገር ለማግኘት ልፋት እንደሚጠይቅ ሁሉ ጥሩ ጋብቻም ጥረትና ብዙ ልፋት ይጠይቃል። የጋብቻን ቅዱስነት የማይገነዘቡ ሰዎች በቀላሉ ጋብቻቸውን ለማፍረስ ይወስናሉ። ወይም ደግሞ ሳይወዱ በግድ ደስታ በሌለው ጋብቻ ውስጥ እንደሚኖሩ ይናገራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የጋብቻን ቅዱስነት አምነው የሚቀበሉ ሰዎች አምላክ አብረው እንዲኖሩ እንደሚጠብቅባቸው ያውቃሉ። (ዘፍጥረት 2:24) በተጨማሪም ጋብቻቸው ያላንዳች እንከን እንዲቀጥል በማድረግ ጋብቻን ያቋቋመውን አምላክ ያስከብራሉ። (1 ቆሮንቶስ 10:31) ይህን አመለካከት መያዛቸው ጋብቻቸው እንዲሰምር ያላሰለሰ ጥረት እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.14 መጠበቂያ ግንብ 21-109 ገጽ 16-17 (በእንግሊዝኛ ኅዳር 1, 1988 ገጽ 22-3) ተመልከቱ።