በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጎማዎች ለሕይወትህ ዋስትና ሊሆኑ ይችላሉ!

ጎማዎች ለሕይወትህ ዋስትና ሊሆኑ ይችላሉ!

ጎማዎች ለሕይወትህ ዋስትና ሊሆኑ ይችላሉ!

ከብረትና ከመስተዋት በተሠራ መለስተኛ ሣጥን ውስጥ ተዘግተሃል እንበል። በአጠገብህ ደግሞ ተቀጣጣይና መርዛማ የሆነ ፈሳሽ ያለበት ዕቃ ተቀምጧል። አሁን ደግሞ ይህን ሣጥን ከመሬት ጥቂት ሴንቲ ሜትሮች ብቻ ከፍ አድርገን በሚሽከረከር ነገር ላይ በማስቀመጥ በሴኮንድ 30 ሜትር እንዲጓዝ እናድርግ። በመጨረሻ ደግሞ ይህን ማሽን ተመሳሳይ ከሆኑ ሌሎች ማሽኖች ጋር እንዲሽከረከር እናድርግ።

መኪናህ ውስጥ ገብተህ በአውራ መንገድ ላይ በምታሽከረክርበት ጊዜ የምታደርገው ይህንኑ ነው። በምታሽከረክርበት ጊዜ መኪናህን እንድትቆጣጠርና ራስህን ጠብቀህ ካሰብክበት እንድትደርስ የሚያስችልህ ምንድን ነው? በአብዛኛው ጎማህ ነው።

የጎማዎች ተግባር

ጎማዎች ለተለያዩ ዓላማዎች ያገለግላሉ። የመኪናህ ክብደት የሚያርፈው በጎማዎች ላይ ከመሆኑም በላይ በመንገድ ላይ የሚያጋጥሙህ ጉብታዎች፣ ጉድጓዶችና ሌሎች እንቅፋቶች እንዳያንገጫግጩህ እንደ ትራስ ሆነው ያገለግላሉ። በይበልጥ ደግሞ በተለያዩ ዓይነት መንገዶች ላይ በፍጥነት ስትነዳ፣ ስታጠመዝዝና ፍሬን ስትይዝ መኪናህ አቅጣጫውን ሳይለቅና ሳይንሸራተት እንዲጓዝ የሚያስችሉት ጎማዎቹ ናቸው። ሆኖም በማንኛውም ጊዜ ከመንገዱ ጋር ሙሉ ንክኪ የሚኖረው የጎማው ክፍል በጣም አነስተኛ ነው።

ጎማዎች ካላቸው ጠቀሜታ አንጻር ደኅንነታቸውን ለመጠበቅና ተግባራቸውን በሚገባ እንዲያከናውኑ ለማስቻል ምን ማድረግ ትችላለህ? ጎማ መለወጥ በሚያስፈልግህ ጊዜስ ለመኪናህ የሚስማማውን ጎማ የምትመርጠው እንዴት ነው? እነዚህን ጥያቄዎች ከመመለሳችን በፊት የጎማን ታሪክ በአጭሩ እንመልከት።

የመጀመሪያዎቹ የጎማ ፈልሳፊዎች

ከእንጨት ወይም ከብረት የተሠሩ ሽክርክሪቶች አገልግሎት ላይ ከዋሉ በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ያለፉ ቢሆንም በእነዚህ ሽክርክሪቶች ላይ ጎማ መለጠፍ የተጀመረው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው ማለት ይቻላል። ከእንጨት ወይም ከብረት የተሠሩ ሽክርክሪቶችን የተፈጥሮ ጎማ ማልበስ የተጀመረው በ1800ዎቹ ዓመታት ነው። ይሁን እንጂ ጎማው ብዙም ስለማይበረክት በሽክርክሪቶች ላይ ጎማ መለጠፍ የሚያዛልቅ ዘዴ ሆኖ አልተገኘም። ቻርልስ ጉድይር የተባለ በከኔቲከት፣ ዩ ኤስ ኤ ይኖር የነበረ አንድ ሰው የተሻለ ዘዴ ፈለሰፈ። ጉድይር በ1839 ቅርጽ የሌለው ጎማ በከፍተኛ ሙቀትና ግፊት ታምቆ ከድኝ ጋር እንዲዋሃድ የሚደረግበትን ቨልካናይዜሽን የተባለ ዘዴ አገኘ። ይህ ዘዴ ጎማን በተፈለገው ቅርጽ ለማውጣት ያስቻለ ከመሆኑም በላይ ቶሎ እንዳያልቅና ረዥም ዕድሜ እንዲኖረው አስችሏል። ድፍን የላስቲክ ጎማዎች ይበልጥ ተወዳጅ እየሆኑ ቢመጡም ለማሽከርከር ምቹ ሆነው አልተገኙም።

በ1845 ሮበርት ደብልዩ ቶምሰን የተባለ ስኮትላንዳዊ መሐንዲስ ለመጀመሪያ ጊዜ በአየር የሚሞላ ጎማ በመፈልሰፍ የፈጠራ ሥራ ባለቤትነት ማረጋገጫ አገኘ። ይሁን እንጂ በአየር የተሞላ ጎማ ገበያ ላይ ተቀባይነት ያገኘው ጆን ቦይድ ዳንሎፕ የተባለ ሌላ ስኮትላንዳዊ የልጁን ብስክሌት ግልቢያ ለማሻሻል በተነሳ ጊዜ ነበር። ዳንሎፕ የአዲሱን ጎማውን የፈጠራ መብት በ1888 ካስመዘገበ በኋላ የራሱን ኩባንያ አቋቋመ። ይሁን እንጂ በአየር የሚሞላው ጎማ ገና ሊወጣቸው የሚገቡ ትላልቅ እንቅፋቶች ነበሩ።

ከዕለታት አንድ ቀን በ1891 አንድ ፈረንሳዊ ብስክሌተኛ ጎማው ይተነፍስበታል። ጎማው ከብስክሌቱ ተሽከርካሪ ጋር የተጣበቀ ስለሆነ ሊጠግነው ሞክሮ ሳይሆንለት ቀረ። በመሆኑም ለቨልካናይዝድ ጎማ እድገት ባበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እውቅና ያተረፈውን ኤድዋር ሚሽላን የተባለ ፈረንሣዊ እንዲረዳው ጠየቀው። ሚሽላን ጎማውን ለመጠገን ዘጠኝ ሰዓት የፈጀበት ሲሆን በዚህ ተነሳስቶ በቀላሉ ተለይቶ ሊወጣና ሊጠገን የሚችል በነፋስ የሚሞላ ጎማ ፈለሰፈ።

የሚሽላን ጎማዎች ከፍተኛ ተወዳጅነት በማትረፋቸው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የእነዚህ ጎማዎች ተጠቃሚ ብስክሌተኞች ቁጥር 10,000 ደረሰ። ብዙም ሳይቆይ እነዚህ ነፋስ የተሞሉ ጎማዎች በፓሪስ ሠረገላዎች ላይ በመገጠማቸው ተሳፋሪዎቻቸው በጣም ተደሰቱ። ነፋስ የተሞሉ ጎማዎች በመኪናዎች ላይም ሊገጠሙ እንደሚችሉ ለማሳየት በ1895 ኤድዋርና ወንድሙ አንድሬ በአንድ የውድድር መኪና ላይ እንዲገጠሙ አደረጉ። መኪናው ግን በውድድሩ ላይ መጨረሻ ወጣ። ቢሆንም ሰዎች በእነዚህ እንግዳ የሆኑ ጎማዎች እጅግ በመደነቃቸው እነኤድዋር ጎማው ውስጥ ምን እንደደበቁ ለማየት ጎማዎቹን እስከመሰንጠቅ ደርሰው ነበር።

በ1930ዎቹና 40ዎቹ ዓመታት እንደ ሬዮን፣ ናይለንና ፖሊስተር የመሳሰሉ ጠንካራና አዳዲስ ማቴሪያሎች በመገኘታቸው ከጥጥና ከተፈጥሮ ላስቲክ ይሠሩ የነበሩት የጎማ ክፍሎች እየቀሩ መጡ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አየሩን የሚይዝ የውስጥ ላስቲክ ሳያስፈልግ ከመኪናው ቸርኬ ጋር ተጣብቆ አየር ሳያስወጣ ሊይዝ የሚችል ጎማ ለመሥራት መሠረት ተጣለ። ቆየት ብሎ ደግሞ ሌሎች መሻሻሎች ተደርገዋል።

ዛሬ አንድ ጎማ ለመሥራት ከ200 የሚበልጡ ጥሬ ዕቃዎች ያስፈልጋሉ። በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጋዥነት እስከ 130,000 ኪሎ ሜትር ሊጓዙ የሚችሉ ጎማዎች መሥራት የተቻለ ከመሆኑም በላይ በውድድር መኪናዎች ላይ ተገጥመው በሰዓት በመቶዎች በሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች የሚለካ ፍጥነት መቋቋም የሚችሉ ጎማዎች አሉ። በዚህ ላይ ደግሞ የጎማዎች ዋጋ እየቀነሰ መጥቶ ማንኛውም ተራ ሸማች ሊገዛ የሚችልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።

የጎማ አመራረጥ

መኪና ካለህ አዲስ ጎማ የመምረጥ ችግር ውስጥ ልትገባ ትችላለህ። ጎማህ የሚቀየርበት ጊዜ መድረሱን እንዴት ታውቃለህ? ጎማህ ግልጽ የሆነ ጉዳት ወይም የማለቅ ምልክት እንዳለበት በመመልከት ነው። * የጎማ አምራቾች የጎማህ ዕድሜ ማለቁን የሚያሳዩ ምልክቶች ያደርጋሉ። እነዚህ ምልክቶች ጎማህ ጥርስ ላይ አግድም የተሰመሩ መስመሮች ሆነው ይታያሉ። በተጨማሪም ጥርሱ ከጎማው ተለያይቶ እንደሆነ፣ የወጣ ሽቦ መኖሩን፣ ከጎን በኩል ወጣ ያለ እብጠት ወይም ሌላ ዓይነት ምልክት መኖሩን መፈተሽ ተገቢ ነው። ከእነዚህ ምልክቶች አንዱን ብትመለከት ጎማህ እስኪቀየር ወይም እስኪጠገን ድረስ መኪናህን መንዳት የለብህም። ጎማህን የገዛኸው በአዲስነቱ ከሆነና ዋስትና ካለው የሸጠልህ ድርጅት የተጎዳውን ጎማ በቅናሽ ሊቀይርልህ ይችል ይሆናል።

ከፊት ወይም ከኋላ ያሉት ጎማዎች አንድ ላይ ቢቀየሩ ጥሩ ይሆናል። አንድ አዲስ ጎማ ብቻ የምትቀይር ከሆነ ፍሬን በምትይዝበት ጊዜ ወደ አንድ ወገን እንዳይንሸራተት የተሻለ ጥርስ ካለው ጎማ ጋር እንዲቀናጅ አድርግ።

የተለያየ ዓይነት፣ መጠንና ሞዴል ካላቸው በርካታ ጎማዎች መካከል ለአንተ መኪና የሚስማማውን ጎማ መምረጥ ሊያስቸግርህ ይችላል። ይሁን እንጂ ቁልፍ የሆኑ ጥቂት ጥያቄዎችን ከጠየቅክ ብዙ ላይከብድህ ይችላል። በመጀመሪያ መኪናውን ያመረተው ፋብሪካ ምን ዓይነት ጎማ እንደሚያዝ ተመልከት። መኪናህ ሊሟላለት የሚገባ የጎማና የቸርኬ መጠን እንዲሁም የጭነት ልክ አለ። በተጨማሪም መኪናህ ከመሬት ሊኖረው የሚገባውን ከፍታ በተመለከተ የተሠጠ መመሪያ ይኖራል። የመኪናህም አሠራር ግምት ውስጥ ሊገባ ይገባል። ፍሬን እንዳይቆለፍና መኪናው እንዳይንሸራተት የሚከላከል መሣሪያ የተገጠመላቸውና ባለ ሁለት ዲፈረንሻል የሆኑ ዘመናዊ መኪናዎች የተወሰነ የአሠራር ባሕርይ ያላቸው ጎማዎች እንዲገጠሙላቸው ሆነው የተሠሩ ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ ምን ዓይነት ጎማ መገጠም እንደሚገባው የሚገልጽ መመሪያ በተሽከርካሪው የአጠቃቀም መመሪያ መጽሐፍ ውስጥ ይገኛል።

ሌላው ሊታሰብበት የሚገባ ነገር የመንገዱ ሁኔታ ነው። መኪናህ በአብዛኛው የሚነዳው በጠጠር መንገድ ላይ ነው ወይስ በአስፋልት? በዝናባማ ወራት ነው ወይስ በደረቅ? የምትነዳበት ሁኔታ በጣም የተለያየ ሊሆን ይችላል። እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ ለሁሉም ዓይነት መንገዶችና ወቅቶች የሚያገለግል ጎማ መግዛት ይኖርብህ ይሆናል።

በተጨማሪም የጎማው ዕድሜ ምን ያህል እንደሚሆንና ምን ያህል መሬት የመቆንጠጥ ባሕርይ እንዳለው መመርመር ይኖርብሃል። በአጠቃላይ የጎማው ጥርስ ለስላሳ በሆነ መጠን የበለጠ መሬት የመቆንጠጥ ችሎታ ይኖረዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ጎማ ቶሎ ያልቃል። በአንጻሩ ደግሞ ጥርሱ ጠንካራ ከሆነ የጎማው መሬት የመቆንጠጥ ባሕርይ አነስተኛ ይሆናል፣ ዕድሜው ግን ረዥም ነው። የእነዚህ ሁኔታዎች መመዘኛ አብዛኛውን ጊዜ ጎማ ሻጮች በሚሰጡት ጽሑፍ ላይ ይገኛል። መመዘኛውና የደረጃ ምደባው እንደየአምራች ኩባንያው ሊለያይ እንደሚችል መርሳት የለብህም።

የሚያስፈልግህን የጎማ ዓይነት ከመረጥክ በኋላ የመጨረሻ ምርጫህን የሚወስነው ዋጋ ሊሆን ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ እውቅ የሆኑ አምራቾች ጥሩ የጥራት ማረጋገጫና ዋስትና ይሰጣሉ።

ለጎማ አስፈላጊ እንክብካቤ ማድረግ

ተገቢ የሆነ የጎማ አያያዝ ሦስት ነገሮችን ያጠቃልላል። ትክክለኛ የነፋስ ግፊት እንዲኖር ማድረግ፣ ጎማዎችን በየጊዜው ማዘዋወር እንዲሁም እንዳይንቀጠቀጡና ወደ አንድ ወገን እንዳያጋድሉ መጠበቅ። ትክክለኛውን የነፋስ ግፊት መጠን መጠበቅ በጣም አስፈላጊ ነው። ነፋሱ ከበዛ ጎማው መሃሉ ላይ ያልቃል። በሌላ በኩል ደግሞ ነፋሱ ካነሰ የጎማው ዳርና ዳር ከመበላቱም በላይ ነዳጅ ይባክናል።

ጎማዎች በአንድ ወር ውስጥ እስከ ግማሽ ኪሎ የሚደርስ ግፊት ያለው አየር ሊቀንሱ ይችላሉ። ስለዚህ የጎማህን ቅርጽ ብቻ በመመልከት ጎማዬ በትክክል ተነፍቷል ብለህ አታስብ። የላስቲክ አምራቾች ማኅበር እንደሚለው ከሆነ “አንድ ጎማ የመተንፈስ ምልክት ሳይታይበት ከነበረው ትክክለኛ የነፋስ ግፊት ግማሽ ያህሉን ሊያጣ ይችላል።” ስለዚህ ቢያንስ በወር አንድ ጊዜ የጎማህን ነፋስ ማስለካት ያስፈልግሃል። ብዙ የተሽከርካሪ ባለቤቶች የነፋስ መለኪያ መሣሪያ መኪናቸው ውስጥ ያስቀምጣሉ። ሁልጊዜ የሞተር ዘይት ስትቀይር ጎማህንም አስለካ። ማስለካት የሚኖርብህ መኪናህ ቢያንስ ለሦስት ሰዓታት ያህል ቆሞ ከቀዘቀዘ በኋላ ወይም ከአንድ ኪሎ ሜትር ተኩል የማይበልጥ ርቀት ከተጓዘ በኋላ ነው። የነፋሱ ልክ ምን ያህል መሆን እንደሚገባው አብዛኛውን ጊዜ በተሽከርካሪ አጠቃቀም መመሪያ መጽሐፍ ውስጥ ወይም በተሽከርካሪው አካል ላይ ተጽፎ ይገኛል። መኪናህ በጣም እንዳያንገጫግጭህ ከፈለግክ ጎማውን ከልክ በላይ ማስነፋት የለብህም።

የመኪናህን ጎማዎች በተወሰነ ጊዜ የምታቀያይራቸው ከሆነ ይበልጥ ከመበርከታቸውም በላይ እኩል ተስተካክለው ሊያልቁ ይችላሉ። የመኪናህ አምራች ኩባንያ የተለየ መመሪያ ካልሰጠ በቀር ጎማዎችህን ከ10,000 እስከ 13,000 ኪሎ ሜትር ከነዳህ በኋላ ብታቀያይር ጥሩ ይሆናል። አሁንም እንዴት መቀያየር እንደሚኖርባቸው የፋብሪካውን መመሪያ ተመልከት።

በመጨረሻም በየዓመቱ ወይም የመኪናህ መሪ እንግዳ የሆነ የመንቀጥቀጥ ጠባይ ካመጣ የጎማዎቹ አቋቋም ትክክል መሆን አለመሆኑ እንዲመረመርልህ አድርግ። ሰስፔንሽኑ በተለያየ ጭነት ወቅት የጓማዎቹ አቋቋም እንዳይዛነፍ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ቢሆንም ጎማዎቹ እያለቁ ሲሄዱ አቋቋማቸው ትክክል መሆን አለመሆኑን አይቶ ማስተካከል አስፈላጊ ይሆናል። በዚህ ሙያ በቂ ችሎታ ያለው መካኒክ አስፈላጊውን ማስተካከያ ሊያደርግልህ ይችላል፤ ይህ ደግሞ የጎማዎቹ ዕድሜ እንዲረዝምና አነዳድህም ምቹ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል።

ራሳቸውን በራሳቸው የማስተካከል ችሎታ ያላቸው ጎማዎች

አንዳንድ መኪናዎች የጎማቸው ነፋስ መጠን ከሚገባው በላይ ሲያንስ በኮምፒውተር እርዳታ ለአሽከርካሪው ማስጠንቀቂያ ይሰጣሉ። አንዳንድ ጎማዎች ቢተነፍሱም የተወሰነ ርቀት አለችግር መጓዝ ሲችሉ ሌሎች ደግሞ ቀዳዳቸውን በራሳቸው የማሸግ ችሎታ አላቸው። በእርግጥም መሐንዲሶች ለተለያዩ የአነዳድ ሁኔታዎች የሚያገለግሉ አዳዲስ የጎማ ዓይነቶችን በመፈልሰፍ ላይ ናቸው።

ጎማዎች የሚሠሩበት ጥሬ ዕቃና የጥርሳቸው ዲዛይን እንዲሁም የሰስፔንሽን፣ የመሪና የፍሬን አሠራር እየተሻሻለ በሄደ መጠን ጎማዎች ይበልጥ ለመንዳት አመቺ እየሆኑ ከመሄዳቸውም በላይ ለአደጋ የማያጋልጡ እየሆኑ ይመጣሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.15 የጎማህን ደኅንነት ለመመርመር የሚረዳህን በገጽ 23 ላይ የሚገኘውን ዝርዝር ተመልከት።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/ሥዕሎች]

የጎማን ደኅንነት ለመመርመር የሚረዳ ዝርዝር

በማየት የሚደረግ ምርመራ:-

□ ከጎን በኩል ወጣ ያለ እብጠት ይታያል?

□ ጥርሱ ላይ ወጣ ያሉ ሽቦዎች ይታያሉ?

□ ጥርሱ የመበላትና የማለቅ ምልክት ይታይበታል?

የሚከተሉትንም ነገሮች መርምር:-

□ የነፋሱ መጠን የተሽከርካሪውን አጠቃቀም በሚገልጸው መጽሐፍ ላይ የተሰጠውን መመሪያ የተከተለ ነው?

□ ጎማዎቹን ማቀያየር የሚያስፈልግበት ጊዜ ደርሷል? (ጎማዎቹን በየስንት ኪሎ ሜትር ማቀያየር እንደሚያስፈልግና እንዴት ማቀያየር እንደሚገባ በመጽሐፉ ላይ የተሰጠውን መመሪያ ተከተል።)

□ ወቅቶች ሲለወጡ የጎማውን ዓይነት መለወጥ ያስፈልግ ይሆን?

[ሥዕል]

የማለቅ ምልክት

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የጎማ ክፍሎች

ጥርስ:- መኪና ሲጠመዘዝና ፍሬን ሲይዝ እንዳይንሸራተት ያደርጋል

ቤልት:- ጥርሶቹን ያጠናክራል፣ ቦታቸውንም እንዲጠብቁ ያደርጋል

ግድግዳ:- የጎማው ጎን መኪናው በሚጠመዘዝበትና ከመንገድ ጠርዝ ጋር በሚፋተግበት ጊዜ እንዳይጎዳ ይከላከላል

ነጠላ ሽፋን:- ጎማው ጠንካራና የሚተጣጠፍ እንዲሆን ይረዳል

የውስጥ ልጥፍ:- የጎማው ነፋስ እንዳይወጣ ይከላከላል

እጥፋት:- ጎማው ከቸርኬው ጋር በሚገባ እንዲጋጠም ያስችላል

[በገጽ 21 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የሚነፋ ጎማ የተገጠመላቸው የቀድሞ ብስክሌትና መኪና፤ በድሮ የጎማ ፋብሪካ ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞች

[ምንጭ]

The Goodyear Tire & Rubber Company