በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጓደኛዬ እንዲህ የሚያመናጭቀኝ ለምንድን ነው?

ጓደኛዬ እንዲህ የሚያመናጭቀኝ ለምንድን ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

ጓደኛዬ እንዲህ የሚያመናጭቀኝ ለምንድን ነው?

“ጓደኛዬ ብዙ ጊዜ በረባ ባልረባው ይነተርከኛል። ሆኖም እኔ ከእሱ መለየት አይሆንልኝም።”—ካትሪን *

“ከላይ ለሰው ስለማይታይ ነው እንጂ ውስጥ ውስጡን ቆስያለሁ።”—ጓደኛዋ በጥፊ የመታት አንድራ

ሁሌም የሚያጋጥም ነገር ነው። አንዲት ወጣት መልከ መልካም ከሆነና ሰው አክባሪ ከሚመስል ወጣት ጋር ተቀጣጥራ መጫወት ትጀምራለች። የልጁ ጠባይ ግን ቀስ በቀስ መለወጥ ይጀምራል። ለእሷ ያለውን ፍቅር ይገልጽበት በነበረው አንደበቱ አጥንት የሚሰብር አሽሙርና የሚያንቋሽሽ ትችት ይሰነዝራል። እሷም መጀመሪያ ላይ እነዚህ ነገሮች ቢያስቀይሟትም እንደፍቅር ቀልዶች ቆጥራ ታልፋቸዋለች። ይሁን እንጂ ስድቡ፣ በቁጣ መገንፈሉና በቁጭት መናገሩ ጭራሹኑ ተባብሶ ይቀጥላል። እሷም ለእሱ የባሕርይ መበላሸት ራሷን ተጠያቂ ታደርግና ሁኔታዎች ይለወጡ ይሆናል ብላ ተስፋ በማድረግ ውስጥ ውስጡን ትብሰለሰላለች። ነገር ግን ሁኔታው ምንም አይለወጥም። ጓደኛዋ ይባስ ብሎ ይጮኽባትና ያንባርቅባት ጀመር። እንዲያውም ግልፍ ሲለው በኃይል ይገፈትራታል! ቀጥሎ ደግሞ ይመታኛል ብላ ትሸማቀቃለች። *

ፍቅረኛሞች የሆኑ ወጣት ወንዶችና ሴቶች አብዛኛውን ጊዜ የሚጣሉና የሚሰዳደቡ ከሆነ ጠቅላላ ግንኙነታቸው ነጋ ጠባ ትችት፣ የሚያቆስል ንግግር፣ ቁጣና ንትርክ የበዛበት ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው። በአንቺም ላይ እየደረሰ ያለው ሁኔታ እንዲህ ነው? (“አንዳንድ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች” የሚለውን ሣጥን ተመልከቺ።) ከሆነ በጣም ከመቸገርሽና ከማፈርሽ የተነሳ የምታደርጊው ጠፍቶሽ ይሆናል።

እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች የሚደርሱት በአንቺ ላይ ብቻ አይምሰልሽ። እየተቀጣጠሩ አብረው ጊዜ ከሚያሳልፉ ፍቅረኛሞች መካከል ከአምስቱ አንዷ በሆነ መልኩ በፍቅረኛዋ እንደምትደበደብ አጥኚዎች ይገምታሉ። እንደ ስድብ፣ ማመናጨቅና ትችት የመሳሰሉት ነገሮችም እንደ ጥቃት ከተቆጠሩ ደግሞ ከአምስት ሰዎች መካከል አራቱ የዚህ ችግር ሰለባዎች እንደሚሆኑ ተገምቷል። አብዛኞቹ ሰዎች እንደሚያስቡት የዚህ ችግር ተጠቂዎች ሴቶች ብቻ አይደሉም። በብሪታንያ ተቀጣጥሮ በመጫወት ወቅት የሚፈጸም የኃይል ድርጊትን አስመልክቶ በተደረገ ጥናት መሠረት ጥቃት እንደተፈጸመባቸው የተናገሩት “ወንዶችና ሴቶች ቁጥራቸው እኩል ነው ለማለት ይቻላል።” *

ለጋብቻ በመጠናናት ላይ ባሉ ወንዶችና ሴቶች ላይ እንዲህ ያለ የባሕርይ ጉድለት የሚያጋጥመው ለምንድን ነው? አንቺስ እንዲህ ያለ ሁኔታ ቢያጋጥምሽ ምን ማድረግ ይኖርብሻል?

የአምላክን አመለካከት መረዳት

በመጀመሪያ እንዲህ ያለው ሁኔታ በአምላክ ፊት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ በትክክል መገንዘብ አለብሽ። ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ሌሎችን የሚጎዱ ነገሮች መናገርና ማድረግ የሚቀናቸው መሆኑ እውነት ነው። (ያዕቆብ 3:2) እርስ በርስ የሚዋደዱና የሚተማመኑ ሰዎችም እንኳን አልፎ አልፎ አለመግባባት የሚያጋጥማቸው መሆኑም እውነት ነው። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስና በርናባስ የጎለመሱ ክርስቲያኖች ነበሩ። ሆኖም በአንድ ወቅት “የከረረ አለመግባባት በመካከላቸው” ተፈጥሮ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 15:39) ስለዚህ ከአንድ ሰው ጋር ለጋብቻ በመጠናናት ላይ ከሆንሽ አልፎ አልፎ አለመግባባት ያጋጥምሽ ይሆናል።

ከዚህም በላይ ጓደኛሽ ፈጽሞ የትችት ቃል አይወጣውም ብሎ መጠበቅ ከእውነታው የራቀ ይሆናል። ደግሞም ልትጋቡ አስባችኋል። እሱ በአንቺ ላይ አንድ ደስ የማይለው ጠባይ ወይም ልማድ ቢያይና እንድታስተካክዪ ቢነግርሽ ፍቅር አይሆንም? እርግጥ ነው፣ ስህተታችን ሲነገረን ደስ ላይለን ይችላል። (ዕብራውያን 12:11) ሆኖም በፍቅር ከተነገረን እንደ ስድብ ወይም ትችት አንቆጥረውም።—ምሳሌ 27:6

መጮኸ፣ በጥፊና በቡጢ መምታት ወይም መሳደብ ግን ፈጽሞ ሌላ ነገር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ቁጣን፣ ንዴትን፣ ስድብን” ያወግዛል። (ቆላስይስ 3:8) አንድ ሰው ያለውን “ኀይል” ሌሎችን ለማዋረድ፣ ለማስፈራራት ወይም ለመጨቆን ሲጠቀምበት ይሖዋ ይቆጣል። (መክብብ 4:1፤ 8:9) እንዲያውም የአምላክ ቃል ባሎች “ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ ሥጋቸው መውደድ ይገባቸዋል። . . . የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ማንም የለም፤ ይመግበዋል፤ ይንከባከበዋል” በማለት ይገልጻል። (ኤፌሶን 5:28, 29) ሊያገባት ያሰባትን ሴት የሚሳደብ ወይም የሚያመናጭቅ ወንድ የትዳር ጓደኛ ለመሆን ብቃት የሌለው መሆኑን ያሳያል። እንዲሁም በዚህ አድራጎቱ ይሖዋ አምላክን ያሳዝናል።

ጥፋቱ የአንቺ አይደለም!

እርግጥ ነው፣ እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ያላቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ ለመጥፎ ድርጊታቸው ተወቃሽ የሚያደርጉት ሌላውን ወገን ነው። ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ ጓደኛሽ የተናደደው በአንቺ ጥፋት እንደሆነ ይሰማሽ ይሆናል። ይሁን እንጂ የእሱን ንዴት ከአንቺ ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር ላይኖር ይችላል። ብዙ ጊዜ መሳደብ፣ መቆጣት ወይም መጮኽ በተለመደበት ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ወንዶች ከጊዜ በኋላ እነሱም ያንኑ ባሕርይ ያንጸባርቃሉ። * ወንድ ልጅ ምንጊዜም የበላይ መሆን አለበት የሚል አስተሳሰብ በነገሠበት ኅብረተሰብ ውስጥ ያደጉ ወጣት ወንዶች በባሕርያቸው ላይ ይህ ዝንባሌ ሲንጸባረቅ ይታያል። ወንድ ልጅ ኮስታራ መሆን አለበት የሚለው የእኩዮች ተጽዕኖም ቀላል አይደለም። በራሱ የማይተማመን ከሆነ የምታደርጊውም ሆነ የምትናገሪው ነገር ሁሉ ወንድነቱን የሚጋፋ ሊመስለው ይችላል።

ሁኔታው ምንም ይሁን ምን ለአንድ ሰው ቁጡ መሆን ተጠያቂዋ አንቺ አይደለሽም። ተሳዳቢነትና ተደባዳቢነት በምንም ዓይነት ተቀባይነት የላቸውም።

አስተሳሰብሽን መለወጥ

ምንም እንኳ ጓደኛሽ ቁጡና ግልፍተኛ እንዲሆን ያደረግሽው አንቺ ባትሆኚም ለነገሮች ያለሽ አመለካከት መስተካከል ያስፈልገው ይሆናል። እንዴት? አንዲት ወጣት መጣላትና መሰዳደብ በተለመደበት ቤተሰብ ውስጥ ካደገች የጓደኛዋ ግልፍተኝነት ምንም ላይረብሻት ይችላል። እንዲህ ያለውን ክርስቲያናዊ ያልሆነ ጠባይ በመጥላት ፈንታ እንዲያውም ልትወደው ትችላለች። አዎን፣ በጩኸትና በማመናጨቅ ያደጉ አንዳንድ ሴቶች ጨዋና ሰው አክባሪ የሆኑ ወንዶች ብዙም እንደማይማርኳቸው ይናገራሉ። ሌሎች ወጣት ሴቶች ደግሞ የወንድ ጓደኞቻቸውን እንለውጣቸዋለን በሚል የተሳሳተ እምነት የተነሳ እየተሰቃዩ ይኖራሉ።

ከላይ የተጠቀሱት አመለካከቶች ካሉሽ ‘በአእምሮሽ መታደስ መለወጥ’ ያስፈልግሻል። (ሮሜ 12:2) ጸሎት፣ የግል ጥናትና ማሰላሰል ይሖዋ እንዲህ ዓይነቱን ጠባይ በተመለከተ ምን አመለካከት እንዳለው እንድትገነዘቢ የሚረዳሽ ከመሆኑም በላይ ይህን ጠባይ እንድትጠዪው ያደርግሻል። ጓደኛሽ እንዲህ ሊያመናጭቅሽ እንደማይገባ መረዳት ያስፈልግሻል። ትሑት መሆንሽ ግልፍተኛ የሆነ ጓደኛሽን በመለወጥ ረገድ አቅምሽ ውስን መሆኑን እንድትገነዘቢ ሊረዳሽ ይችላል። መለወጥ የራሱ ኃላፊነት ነው!—ገላትያ 6:5

አንዳንድ ጊዜ ወጣት ሴቶች እንዲህ ያለውን በደል ችለው የሚኖሩት ለራሳቸው ያላቸው ግምት ዝቅተኛ ሲሆን ነው። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ካትሬን “ከእሱ ተለይቼ መኖር አይታየኝም። ከእሱ የተሻለ ሰው አገኛለሁ ብዬ አላስብም” ትላለች። ሄልጋ የተባለች አንዲት ሴትም በተመሳሳይ ስለ ወንድ ጓደኛዋ ስትናገር “እንዲደበድበኝ የምፈቅድለት ጭራሽ ዞር ብሎ ሳያየኝ ከሚቀር ይሻላል ብዬ ነው” ትላለች።

እንዲህ ያሉ አመለካከቶች ዘላቂ ለሆነ ግንኙነት ጥሩ መሠረት የሚሆኑ ይመስልሻል? ደግሞስ አንቺ ራስሽን እንኳን ልትወጂ ካልቻልሽ እንዴት ሌላ ሰው ልትወጂ ትችያለሽ? (ማቴዎስ 19:19) ለራስሽ ሚዛናዊ የሆነ አክብሮት ለማዳበር ጥረት አድርጊ። * ችግሩን ችለሽ መኖርሽ መፍትሔ አይሆንም። ኤሬና የተባለች ወጣት እንዲህ ዓይነቱን ባሕርይ ችሎ ለመኖር ጥረት ማድረግ “ለራስሽ ያለሽን አክብሮት ጨርሶ ያሟጥጥብሻል” በማለት ከራሷ ተሞክሮ በመነሳት ተናግራለች።

እውነታውን መጋፈጥ

አንዳንዶች በተለይ በወንድ ጓደኞቻቸው ኃይለኛ ፍቅር ከተያዙ ያልሆነ ግንኙነት እንደጀመሩ አምነው መቀበል ሊከብዳቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ሐቁን ላለማየት ዓይንሽን አትጨፍኚ። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል፤ ብስለት የጎደለው ግን በዚያው ይቀጥላል፤ መከራም ያገኘዋል” ይላል። (ምሳሌ 22:3) ሃና የተባለች አንዲት ወጣት “ከአንድ ወጣት ጋር ፍቅር ሲይዛችሁ እንደታወራችሁ ያህል ነው። የሚታያችሁ ጥሩ ጥሩ ባሕርይው ብቻ ነው” ብላለች። ይሁን እንጂ እያመናጨቀሽ ከሆነ እውነተኛ ማንነቱን መረዳትሽ አስፈላጊ ነው። ጓደኛሽ የሚያስፈራራሽ ወይም የሚያመናጭቅሽ ከሆነ አንድ ትልቅ ችግር አለ ማለት ነው። ስሜትሽን ለማስተባበል፣ ማሳበቢያ ለማቅረብ ወይም ራስሽን ለመውቀስ አትሞክሪ። ከተሞክሮ እንደታየው እንዲህ ያለው ድርጊት ካልታረመ እየተባባሰ ይሄዳል። ደኅንነትሽ በከባድ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል!

እርግጥ መጀመሪያውኑ እንዲህ ካለው ራሱን የማይገዛ ሰው ጋር ግንኙነት አለመፍጠሩ ከሁሉ የተሻለ ነው። (ምሳሌ 22:24) ስለዚህ በደንብ የማታውቂው ሰው ከእሱ ጋር ለመጠናናት ተቀጣጥራችሁ እንድትጫወቱ ሐሳብ ቢያቀርብልሽ መጀመሪያ ስለእሱ ለማወቅ ጥረት ማድረግሽ ጥበብ ነው። ታዲያ ከእሱ ጋር መጫወት የምትፈልጊው ለብቻችሁ ሳይሆን ሌሎችም ባሉበት እንደሆነ ለምን ሐሳብ አታቀርቢም? ይህም ቶሎ በፍቅር ከመያዝሽ በፊት እንድታውቂው ያስችልሻል። ጓደኞቹ እነማን ናቸው? የሚወደው ምን ዓይነት ሙዚቃ፣ ፊልም፣ የቪዲዮ ጨዋታ ወይም ስፖርት ነው? ጭውውቱ ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍቅር እንዳለው ያሳያል? እንደሚሉት ያሉ ወሳኝ ጥያቄዎችን ራስሽን ጠይቂ። ስለእሱ በደንብ የሚያውቁ ሌሎች ሰዎችን ጠይቂ። ለምሳሌ ያህል የጉባኤውን ሽማግሌዎች መጠየቅ ትችያለሽ። በጉልምስናውና በአምላካዊ ጠባዩ ‘የተመሰከረለት’ ከሆነ እነሱ ይነግሩሻል።—የሐዋርያት ሥራ 16:2

ሆኖም ቀድሞውኑ እንዲህ ያለ ግንኙነት ጀምረሽ ከሆነ ምን ልታደርጊ ትችያለሽ? ወደፊት የሚወጣው ርዕስ የዚህን ጥያቄ መልስ ይሰጠናል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.5 ይህ ርዕስ የስድብ፣ የትችትና የአካላዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑትን ሁሉ ይመለከታል። በሚያዚያ-ሰኔ 1997 እና መጋቢት 22, 1997 (እንግሊዝኛ) እትሞች ላይ በወጡት “በሚያቆስሉ ቃላት ፈንታ የሚፈውሱ ቃላት መናገር” እና “ጉልበተኝነት ጉዳቱ ምንድን ነው?” በሚሉት ርዕሶች ላይ ጥቃት ፈጻሚዎቹን የሚረዳ ምክር ተሰጥቷል።

^ አን.7 ይሁን እንጂ ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል የጥቃቱን ሰለባዎች በአንስታይ ጾታ መግለጹን መርጠናል። እዚህ ላይ የቀረበው መሠረታዊ ሥርዓት ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች ይሠራል።

^ አን.14 በሚያዚያ-ሰኔ 1997 እትማችን ላይ የወጣውን “የስድብን ምንጭ ለይቶ ማወቅ” የሚለውን ርዕስ ተመልከቺ።

^ አን.20 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተሰኘውን መጽሐፍ ምዕራፍ 12 ተመልከቺ።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አንዳንድ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች

▪ ለብቻችሁ ስትሆኑም ሆነ ከሌሎች ጋር በምትሆኑበት ጊዜ ስለ አንቺ፣ ስለ ቤተሰቦችሽ ወይም ስለ ጓደኞችሽ የንቀት አስተያየት ይሰነዝራል።

▪ አብዛኛውን ጊዜ ፈቃድሽን ወይም ስሜትሽን ችላ ይላል።

▪ ሁልጊዜ የት እንደምትውዪ ለማወቅ በመጣርና አንቺ ማድረግ ያለብሽን ውሳኔ ሁሉ ራሱ በመወሰን መላ ሕይወትሽን ለመቆጣጠር ይሞክራል።

▪ ይጮኽብሻል፣ ይገፈትርሻል ወይም ያስፈራራሻል።

▪ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ፍቅርሽን እንድትገልጪለት ሊያሳምንሽ ይሞክራል።

▪ ሁሌ የማደርገው ነገር ያበሳጨው ይሆን እያልሽ ትጨነቂያለሽ?

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሁልጊዜ መተቸትና መንቀፍ ወይም መሳደብ ካለ ግንኙነቱ ጥሩ እንዳልሆነ ሊጠቁም ይችላል