በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጦርነት ዘመን ያሳለፍኩት መከራ ለቀሪው ሕይወቴ አሠልጥኖኛል

በጦርነት ዘመን ያሳለፍኩት መከራ ለቀሪው ሕይወቴ አሠልጥኖኛል

በጦርነት ዘመን ያሳለፍኩት መከራ ለቀሪው ሕይወቴ አሠልጥኖኛል

ኧርንስት ክሮመር እንደተናገረው

“ክፍላችሁ ይኸውና።” እኔና የአገልግሎት ጓደኛዬ ምዕራብ አፍሪካ በምትገኘው ጋቦን ስንደርስ አቀባበል የተደረገልን በእነዚህ ቃላት ነበር። ክፍላችን ፍራሽ ለማንጠፍ ካልሆነ በስተቀር ተጨማሪ ነገር አትይዝም። እኔና ጓደኛዬ በዚያች ክፍል ውስጥ ስድስት ወር ኖረናል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በግብርና ያሳለፍኩት ሕይወት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ችሎ መኖር አስተምሮኛል። በ1939 ጦርነቱ በፈነዳበት ወቅት ናዚ ጀርመን ፖላንድን ለመቆጣጠር ጊዜ አልወሰደበትም። በዚያን ጊዜ እኔ ገና የአራት ዓመት ልጅ ነበርኩ። የምኖረው ከወላጆቼ፣ ከታናናሽ ወንድሜና እህቴ እንዲሁም ከሁለት ታላላቅ እህቶቼ ጋር ነበር። አባታችን ጀርመን በጦርነቱ ብትሸነፍ ለሚያጋጥመን አስቸጋሪ ጊዜ እንድንዘጋጅ ያስጠነቅቀን ነበር።

የምንኖረው አሁን የፖላንድ ግዛት በሆነችውና በታችኛው ሳይሊዣ በምትገኝ ሎቨንስቲን በምትባል አነስተኛ የጀርመን መንደር ውስጥ ነበር። ሃያ አምስት ሄክታር በሚያህል እርሻችን ላይ እህል በማምረትና ከብቶች በማርባት እንተዳደር የነበረ ሲሆን አባቴ በአካባቢው ላሉት ገበሬዎች አስተዳዳሪ ሆኖ ይሠራ ነበር። ናዚዎች ሳይሊዣን ሲቆጣጠሩ ገበሬዎቹ ለጦርነቱ ድጋፍ እንዲሰጡ ለማስተባበር አባቴን ተጠቅመውበታል።

አባቴ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በፈረሰኛ ሠራዊት ውስጥ አገልግሎ የነበረ ሲሆን በዚህ ጊዜ ደግሞ ከናዚዎች ጋር መሥራቱ እንደገና ለውትድርና ከመመልመል አዳነው። ወላጆቼ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ቀሳውስት የሠሩት ሥራ ስላበሳጫቸው ከቤተ ክርስቲያን ለቀው ወጥተው ነበር። በዚህም ምክንያት ለሃይማኖት ምንም ፍላጎት ሳይኖረኝ አደግሁ።

በ1941 ትምህርት ብጀምርም ትምህርት ቤት መዋሉን ጠልቼው ነበር። ጥቁር ሰሌዳ ላይ አፍጥጦ ከመዋል የበለጠ የሚያስደስቱ ብዙ ነገሮች እንዳሉ ተሰምቶኝ ነበር። ጦርነቱ ከማብቃቱ ጥቂት ወራት ቀደም ብሎ በ1945 መጀመሪያ ላይ አሁን ሮትስሎፍ ተብላ የምትጠራው የታችኛው ሳይሊዣ ዋና ከተማ ብሬስላው በሩሲያውያን ተከበበች። አንድ ቅዳሜ ምሽት 50 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኘው ይህች ከተማ በአዳፍኔ ተኩስና ከአውሮፕላን በተጣሉ የቦምብ ፍንዳታዎች በእሳት ስትጋይ አየን። ወዲያውኑ ወደ ተራራማ አካባቢዎች መሸሽ ነበረብን። ጦርነቱ ሲያበቃ በሎቨንስቲን ወዳለው ቤታችን ተመለስን።

ከጦርነቱ በኋላ

ጦርነቱን ተከትሎ በጣም አሰቃቂ ጊዜ መጣ። ሴቶች ተገድደው ይደፈሩ ነበር። ዘረፋም የየዕለቱ ተግባር ሆነ። አብዛኞቹ ከብቶቻችን ተሰረቁብን።

አባቴ ሐምሌ 1945 ተይዞ ታሠረ። ሰባት ሌሊት ሙሉ ጭካኔ የተቀላቀለበት ምርመራ ከተካሄደበት በኋላ ተለቀቀ። ከሦስት ወራት በኋላ እንደገና ተይዞ ተወሰደ። ከዚያ በኋላ አላየነውም። ሁለት የፖላንድ ተወላጆች እርሻችንን ወስደው የግላቸው አደረጉት። ሚያዝያ 1946 በመንደሩ የነበሩት ሁሉም ጀርመናውያን ሊሸከሙ የሚችሉትን ዕቃ ብቻ ይዘው አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ ተነገራቸው።

እናቴ ይህ እንደሚመጣ ገብቷት አስቀድማ አዘጋጅታን ስለነበር አልተደናገጥንም። ጎማ ያለው አንድ ትልቅ ቅርጫት ላይ አንሶላዎቻችንንና ብርድ ልብሶቻችንን ጫነች። እኛም እያንዳንዳችን በባለማንገቻ ከረጢት ውስጥ የሚያስፈልገንን ሁሉ ሞልተን ያዝን። የፖላንድ ብሔራዊ ጦር እኛን ጀርመናውያንን በሙሉ ከብት በሚጫንበት በእያንዳንዱ ባቡር ውስጥ ሠላሳ ሠላሳ ሰው እያጎሩ ይዘውን ሄዱ። ከሁለት ሳምንታት በኋላ ከኔዘርላንድ ብዙም ሳይርቅ በሚገኘው በሰሜናዊ ምዕራብ ጀርመን ወዳለው የጉዟችን መጨረሻ ደረስን።

መንግሥት የእኛን ቤተሰብ ጨምሮ በጠቅላላው 19 የምናህል ዘመዳሞችን ከክቫከንብሩክ 8 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ እርሻ ላይ ባሉ ሁለት ክፍሎች እንድንኖር መደበን። የኋላ ኋላ አንዳንዶቹ ዘመዶቻችን ሌሎች ገበሬዎች ቤት ቦታ አግኝተው ስለወጡ ክፍሉ በመጠኑም ቢሆን ሰፋ አለልን።

እናቴ ብዙውን ጊዜ እኛ እንድንበላ ስትል እርሷ ፆሟን ተደፍታ እያደረች በርካታ መሥዋዕትነት ከፍላለች። በመጣንበት ዓመት ለክረምት የሚሆን የማገዶ እንጨት አልነበረንም። የቤታችን ግድግዳና ጣሪያው በወፍራም የበረዶ ግግር ተሸፍኖ ስለነበር ክፍሎቻችን የበረዶ ዋሻ መስለው ነበር። ደግነቱ መኝታችን ይሞቅ ስለነበር ልንተርፍ ችለናል።

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘት

በ1949 እናቴ ከወንድሟ ሚስት አንድ የመጠበቂያ ግንብ ቅጂ አገኘች። በመጽሔቱ ውስጥ ያነበበችው አንድ ርዕሰ ትምህርት በጦርነቱ ወቅት ሂትለር የተናገረውን ነገር አስታወሳት፤ ሂትለር በጀርመን ላይ የሚያሟርቱ ‘የሰው ጫጩቶች’ በማለት በሬዲዮ ተናግሮ ነበር። እናቴ እነዚህ ሰዎች እነማን ይሆኑ እያለች ታስብ ነበር። በመጠበቂያ ግንቡ ላይ እነዚህ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን ስታነብ ፍላጎቷ ተቀሰቀሰና ከእነሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ወሰነች።

ሚያዝያ 1954 አንድ ቀን የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ባልና ሚስት ከእናቴ ጋር ሲያጠኑ አገኘኋቸው። ከጥናቱ በኋላ በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ መኖር ትችላለህ? (እንግሊዝኛ) የተሰኘች አንዲት ቡክሌት የሰጡኝ ሲሆን መጠበቂያ ግንብ በየጊዜው እንዲደርሰኝም ኮንትራት ገባሁ። ቡክሌቷን ሳነብ እውነትን እንዳገኘሁ አመንኩ። ስለዚህ አሠሪዬ እንድታነበው ሰጠኋት። ስላነበበችው ነገር ምን እንደተሰማት ስጠይቃት “ሐሳቦቹ በጣም ግሩም ናቸው። ነገር ግን ይፈጸማል ብዬ ማመን ይቸግረኛል። እኔ አላምንበትም” አለችኝ።

“እንግዲያውስ እኔ ይህ እውነት እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ። በመሆኑም እከተለዋለሁ” አልኳት። ራሷን ነቀነቀችና “ይህ መልእክት የሚስማማው ለገራገር ሰው ነው። አንተ ደግሞ ዱርዬ ስለሆንክ የይሖዋ ምሥክር መሆን አትችልም” አለችኝ። ይሁን እንጂ በሕይወቴ ውስጥ ለውጥ ማድረግ ጀመርኩ።

በአካባቢው ሊያስጠኑኝ የሚችሉ የይሖዋ ምሥክሮች ስላልነበሩ እኔው ራሴ ያጠናሁ ሲሆን በስብሰባቸው ላይ ለመገኘት በየሳምንቱ 10 ኪሎ ሜትር ያህል በብስክሌት እጓዝ ነበር። በኋላም በርካታ ጉባኤዎች ለአምልኮ አንድ ላይ በሚሰባሰቡበት የወረዳ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። እዚያም ለመጀመሪያ ጊዜ ከሌሎች ጋር ሆኜ በስብከቱ ሥራ ተካፈልኩ። ብዙም ሳይቆይ በስብከቱ እንቅስቃሴ ላይ አዘውትሬ መካፈል ጀመርኩ። ሐምሌ 14, 1954 እኔና እናቴ ተጠመቅን። በኋላም በእናቴ በኩል የሴት አያቴ በ80 ዓመት ዕድሜዋ ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ሆነች።

በእርሻ ላይ የምሠራው ሥራ ብዙ ጊዜ የሚጠይቅ በመሆኑ ያንን ትቼ በደን ጥበቃ ውስጥ ሥራ አገኘሁ። ከዚያም ቤተሰባችን ሽቱትጋርት አቅራቢያ ወዳለችው ሩትሊንገን የምትባል አነስተኛ ከተማ ተዛወረ። ታናሽ እህቴ ኢንግሪት የተጠመቀችው እዚያ እያለን ነበር፤ ከወንድሜና ከእህቶቼ መካከል የይሖዋ ምሥክር የሆነችው እርሷ ብቻ ናት።

የሙሉ ጊዜ አገልግሎት

አባቴ ለመሞቱ ተጨባጭ ማስረጃ ባይገኝም በ1957 እናቴ ባል የሞተባት ለመሆኗ ሕጋዊ እውቅና አገኘች። በዚህም ምክንያት ከእኔ የገንዘብ እርዳታ ሳያስፈልጋት ለመኖር የሚያስችላትን የጡረታ አበል ማግኘት ጀመረች። እኔም ይህ የቤተሰብ ኃላፊነት ሲቀርልኝ በሚያዝያ 1957 የግማሽ ቀን ሥራ ያዝኩና በአቅኚነት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርኩ። ከጊዜ በኋላ ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ግብዣ ቀረበልኝ። አንድ ወንድም ይህን ሲሰማ ቢሮው ድረስ ጠርቶ “ትንሽ እርዳታ የሚያስፈልግህ ይመስለኛል” አለና 500 የጀርመን ፍራንክ ሰጠኝ። በዚያ ገንዘብ የሚያስፈልጉኝን ልብሶች ሁሉ ከገዛሁ በኋላ 200 ፍራንክ ተረፈኝ።

በ1960 በኦስትሪያ ሺፕስ በምትባል አንዲት ትንሽ መንደር ከዚያም ለአጭር ጊዜ በሊንዝ ከተማ አስደሳች የአገልግሎት ጊዜ አሳለፍኩ። ይሁን እንጂ በዚያው ዓመት ማብቂያ ላይ ከባድ የሞተር ብስክሌት አደጋ ስለደረሰብኝ የቀኝ እግሬ ተሰበረ። ተከታታይ ቀዶ ሕክምና ከተደረገልኝ በኋላ በተመደብኩበት ቦታ ማገልገሌን ቀጠልኩ። ሆኖም በ1962 የኢሚግሬሽን ጉዳዮችን ለማስፈጸም ወደ ሩትሊንገን መመለስ ነበረብኝ። እዚያ ሳለሁ በእግሬ ውስጥ የገባልኝን የብረት ዘንግ ለማስወጣት ሌላ ቀዶ ሕክምና አደረግሁ። የሕክምና ወጪዎችን ለመሸፈን የሚያስችለኝ ገንዘብ ለማግኘት ስል አቅኚነቴን ለስድስት ወራት አቋርጬ ነበር።

አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ጉባኤያችንን ሲጎበኝ በወቅቱ በጀርመን ቪስባደን በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ለማገልገል ማመልከቻ እንዳስገባ ሐሳብ አቀረበልኝ። እኔም እንዳለኝ አደረግሁ፤ ከሁለት ሳምንት በኋላ፣ በተቻለ ፍጥነት ወደ ቤቴል እንድመጣ የሚገልጽ ቴሌግራም ደረሰኝ። ከአንድ ሳምንት በኋላ በግንቦት 1963 ቤቴል ተብሎ በሚጠራው የጀርመን ቅርንጫፍ ቢሮ የደረስኩ ሲሆን በመጽሔት ማተሚያ ማሽን ላይ እንድሠራ ተመደብኩ።

አዲስ ቋንቋ በትጋት ተማርኩ

ቤቴል ከዚያ በፊት ከኖርኩባቸው ቦታዎች ሁሉ የበለጠ ድንቅ ቦታ ስለነበር በዚያ ያለውን ከባድ ሥራ ለመላመድ ጊዜ አልወሰደብኝም። በዚያን ጊዜ በስፔይን የነበረው የስብከት ሥራ እገዳ ተጥሎበት ስለነበር በ1965 መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በድብቅ ለማድረስ ወደዚያ ሄጄ ነበር። ያ ጉብኝት ሌላ ቋንቋ የማወቅ ፍላጎት አሳድሮብኝ ስለነበር እንግሊዝኛ ለመማር ቆረጥኩ። ያገኘሁትን አጋጣሚ ሁሉ ለመማር እጠቀምበት ነበር። በዚህ ጊዜ በጀርመን የመጀመሪያው እንግሊዝኛ ተናጋሪ ቡድን ተቋቁሞ ስለነበር እኔም ከዚህ ቡድን ጋር መሰብሰብ ጀመርኩ። በእንግሊዝኛ በሚመራ የመጠበቂያ ግንብ ስብሰባ ላይ ለመገኘት የሚጠናውን ርዕስ ለመጀመሪያ ጊዜ ስዘጋጅ ሰባት ሰዓት ፈጅቶብኝ ነበር። ለሁለተኛ ጊዜ ስዘጋጅ አምስት ሰዓት ብቻ ሲፈጅብኝ እያሻሻልኩ መሆኑን ተረዳሁ።

በ1966፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘውና የይሖዋ ምሥክሮችን ለሚስዮናዊ አገልግሎት በሚያሰለጥነው በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 43ኛ ክፍል ገብቼ እንድማር ተጋበዝኩ። ከምረቃው በኋላ በሚያዝያ 1967 እኔና ጉንተር ሬሽከ በምዕራብ አፍሪካ በምትገኘው ጋቦን እንድናገለግል ተመደብን። የጋቦን ዋና ከተማ ሊብረቪል ደርሰን በመግቢያው ላይ በገለጽኳት ትንሽ ክፍል ውስጥ ስንኖር ልብሶቻችንን የምንሰቅለው በመመገቢያ ክፍላችን ነበር። ከስድስት ወር በኋላ ወደ ሌላ የሚስዮናውያን ቤት ተዛወርን።

በጋቦን የገጠመኝ ትልቁ ችግር ፈረንሳይኛ ቋንቋን መማር ነበር። በመጨረሻም ከፍተኛ ጥረት አድርጌ በመጠኑም ቢሆን ቋንቋውን ቻልኩ። ከዚያም በ1970 በጋቦን የስብከቱ ሥራችን በድንገት ታገደና ሚስዮናውያን በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ አገሪቱን ለቀን እንድንወጣ ተነገረን።

ወደ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክ ተዛወርን

ከሌሎች ሚስዮናውያን ጋር በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክ እንዳገለግል ተመደብኩ። የአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ፈረንሳይኛ ነበር። ነገር ግን ለአብዛኞቹ ዜጎች ለመስበክ ሳንጎ የሚባለውን ቋንቋ መማር ነበረብን። ከዋና ከተማዋ ከባንግዊ 300 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኘው በባምባሪ ከተማ የሚስዮናውያን ቤት እንድናቋቁም ተልከን ነበር። ባምባሪ ኤሌክትሪክም ሆነ የቧንቧ ውኃ ያልነበራት ቢሆንም በዚያ የነበሩት ሁለት ጉባኤዎች የእኛ እርዳታ ያስፈልጋቸው ነበር። በአውሮፓ ሳለሁ በጦርነቱ ዘመን ያሳለፍኩት ተሞክሮ በባምባሪና ከዚያ በኋላ በተመደብኩባቸው ሌሎች ቦታዎች ያጋጠመኝን አስቸጋሪ ሁኔታ በተሳካ መንገድ እንድወጣው አስችሎኛል።

በባምባሪ ለሁለት ዓመታት ካገለገልኩ በኋላ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ ጉባኤዎችን እንድጎበኝ ተመደብኩ። በመላ አገሪቱ 40 የሚያህሉ ጉባኤዎች የነበሩ ሲሆን በተመደብኩበት በእያንዳንዱ ጉባኤ አንድ ሳምንት አሳልፍ ነበር። አንዲት ትንሽ መኪና የነበረችኝ ቢሆንም ኮረኮንች መንገዶቹ በጣም የተበላሹ በሚሆኑበት ጊዜ በሕዝብ መጓጓዣዎች እጠቀም ነበር።

በመላ አገሪቱ ውስጥ ተሽከርካሪዎች የሚጠገኑበት ጋራዥ ያለው በባንግዊ ብቻ ነበር። አገልግሎቴ ብዙ መጓዝ የሚጠይቅ በመሆኑ የተሽከርካሪ ጥገና የሚያስተምሩ ጥቂት መጻሕፍት ገዝቼ አንዳንድ መሣሪያዎችንም አሟላሁና መኪናዬን በአብዛኛው እኔው ራሴ መጠገን ጀመርኩ። አንድ ጊዜ ሺሚያስ በሚባለው ዘንግ ላይ የሚገኘው የክሮቼራ ማቀፊያ ስለተሰበረ መኪናው ሊንቀሳቀስ አልቻለም። ሰው ከሚኖርበት አካባቢ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ስለነበርኩ ከጫካ አንድ ጠንካራ እንጨት ቆረጥኩና ማቀፊያውን አስመስዬ ሠራሁት። ግራሶ በደንብ አጠጥቼው ከዘንጉ ጋር በሽቦ ግጥም አድርጌ አሰርኩትና ጉዞዬን ቀጠልኩ።

በተለይ ተፈታታኝ የነበረው ነገር ጥቂት ሰዎች ብቻ ተበታትነው በሚኖሩባቸውና ዱር በሚበዛባቸው ገጠራማ ቦታዎች ማገልገል ነበር፤ ምክንያቱም ማንበብና መጻፍ የሚችሉት በጣም ጥቂት ሰዎች ብቻ ነበሩ። በአንድ ጉባኤ ማንበብ የሚችለው አንድ ሰው ብቻ ሲሆን እሱም የመናገር ችግር ነበረበት። የመጠበቂያ ግንብ ጥናት በጣም ይከብድ የነበረ ቢሆንም ጉባኤው ውይይት እየተደረገበት ያለውን ነጥብ ለመረዳት ልባዊ ጥረት ሲያደርግ ማየት እምነት የሚያጠነክር ነበር።

ከዚያ በኋላ አንድ ቀን ወንድሞችና እህቶችን ጥናቱን ሙሉ በሙሉ ካልተረዱት እንዴት እንደሚጠቀሙ ጠይቄያቸው ነበር። “እርስ በርሳችን ማበረታቻ እናገኛለን” በማለት የሰጡኝ መልስ በጣም የሚያበረታታ ነበር።—ዕብራውያን 10:23-25

ምንም እንኳን ብዙዎቹ ክርስቲያን ወንድሞቼ ፊደል ያልቆጠሩ ቢሆኑም ስለ ሕይወትና እንዴት መኖር እንዳለብኝ ብዙ ነገር አስተምረውኛል። “ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ በትሕትና ቁጠሩ” የሚለው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ያለውን ጠቀሜታ መገንዘብ ችያለሁ። (ፊልጵስዩስ 2:3) አፍሪካውያን ወንድሞቼ ስለ ፍቅር፣ ስለ ደግነት እንዲሁም ስለ እንግዳ ተቀባይነት ብዙ አስተምረውኛል። የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ፕሬዚዳንት የነበረው ወንድም ናታን ኖር የተናገራቸው የመሰነባበቻ ቃላት ከፍተኛ ትርጉም ያዘሉ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። እንዲህ ብሎ ነበር:- “ትሑታን ሁኑ። ሁሉንም ነገር እናውቃለን ብላችሁ አታስቡ። ሁሉን ነገር አናውቅም። ገና የምንማራቸው ብዙ ነገሮች አሉ።”

ኑሮ በአፍሪካ ገጠራማ አካባቢ

ጉባኤዎችን ስጎበኝ በአካባቢው ወንድሞች ቤት አርፍ ነበር። የጉብኝቱ ሳምንት አብዛኛውን ጊዜ ድግስ ይመስል ነበር፤ በተለይም ለልጆች። ምክንያቱም የምጎበኘው ጉባኤ ወንድሞች ለሁሉም የሚበቃ የተትረፈረፈ ምግብ ለማዘጋጀት ወደ አደን ወይም ዓሣ ለማጥመድ ይወጡ ስለነበር ነው።

ከወንድሞች ጋር በጎጆዎቻቸው ውስጥ አርፌ ከጉንዳን ጀምሮ እስከ ዝሆን ሥጋ ድረስ እነሱ የሚበሉትን ሁሉ እበላ ነበር። በየዕለቱ የዝንጀሮ ሥጋ መብላት የተለመደ ነበር። በተለይ ከዱር ዓሣማና ከጃርት ሥጋ የሚዘጋጁ ምግቦች በጣም ጣፋጭ ነበሩ። እርግጥ እያንዳንዱ ቀን ድግስ ነበር ማለት አይደለም። መጀመሪያ ላይ ሰውነቴ ምግቡን እስኪለምደው ድረስ ትንሽ ጊዜ ወስዶብኛል። ከለመድኩት በኋላ ግን ጨጓራዬ የበላሁትን ሁሉ መፍጨት ችሎ ነበር ለማለት እችላለሁ። ፓፓያን ከነፍሬው መብላት ለጨጓራ ጥሩ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ።

ገጠር ውስጥ ብዙ ዓይነት ያልተጠበቀ ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል። በአንድ ወቅት ወንዝ ውስጥ ገላዬን ስታጠብ ያዩኝ ሰዎች በውኃ ውስጥ ይኖራል ተብሎ የሚታሰብ ነጭ ጋኔን መስያቸው ነበር። የአካባቢው ሰዎች ነጭ ጋኔን ሰውን ጎትቶ ውኃ ውስጥ ያሰጥማል ብለው ያምኑ ነበር። ስለዚህ ታጥቤ ከውኃ ስወጣ ውኃ ልትቀዳ የመጣች አንዲት ልጃገረድ አየችኝና እየጮኸች ሩጫዋን ቀጠለች። አብሮኝ የነበረው ወንድም ለስብከት የመጣ እንግዳ እንጂ ጋኔን አይደለም ብሎ ለማስረዳት ቢሞክርም ሰዎቹ አላመኑትም ነበር። “ነጭ ሰው ይህን ሁሉ አገር አቋርጦ እዚህ ድረስ አይመጣም” ብለው ተከራከሩ።

የሌሊቱ አየር ነፋሻ ስለሆነ ብዙ ጊዜ እደጅ ተኝቼ አድር ነበር። ከወባ ትንኝ ብቻ ሳይሆን ከእባብ፣ ከጊንጥ፣ ከአይጥና ከሌሎችም ነገሮች መከላከያ እንዲሆንልኝ ሁልጊዜ አጎበር ይዤ እሄድ ነበር። ብዙ ጊዜ የጉንዳን ሠራዊት ወረራ ያጋጠመኝ ሲሆን የተከላከለልኝ አጎበሩ ነበር። አንድ ቀን ማታ የእጅ ባትሪዬን በአጎበሩ ላይ ሳበራ በጉንዳን ተሸፍኖ አየሁት። ከዚያም እግሬ አውጭኝ ብዬ ሸሸሁ፤ ምክንያቱም ጉንዳኖች ምንም ጥቃቅን ቢሆኑ አንበሳንም እንኳን መግደል ይችላሉ።

በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክ ሰሜናዊ ክፍል በኮንጎ ወንዝ አቅራቢያ ሳለሁ አካባቢው ያፈራውን በመጠቀም ለሚተዳደሩ ፒግሚ ተብለው ለሚጠሩት ጎሳዎች እሰብክ ነበር። የተዋጣላቸው አዳኞች ስለሆኑ መበላት ያለበትንና የሌለበትን የሚያውቁ ነበሩ። አንዳንዶቹ ሳንጎ የሚባለውን ቋንቋ ስለሚያውቁ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ማዳመጥ ደስ ይላቸው ነበር። ተመልሰን እንድናነጋግራቸው የሚስማሙ ቢሆኑም ተመልሰን ስንሄድ ግን ወደ ሌላ ቦታ ስለሚፈልሱ አናገኛቸውም። በዚያን ጊዜ ከፒግሚዎች መካከል አንድም የይሖዋ ምሥክር አልነበረም፤ በኋላ ግን በኮንጎ ሪፑብሊክ አንዳንዶቹ እውነትን እንደተቀበሉ ሰምቻለሁ።

በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት አምስት ዓመታት አገለገልኩ። በመላ አገሪቱ የተጓዝኩ ሲሆን አብዛኛውን ጉዞ ያደረግሁበት ምክንያትም በገጠራማ አካባቢዎች ያሉ ጉባኤዎችን ለመጎብኘት ነበር።

በናይጄሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ ማገልገል

በግንቦት 1977 በናይጄሪያ፣ ሌጎስ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እንዳገለግል ተጋበዝኩ። በአፍሪካ ካሉት አገሮች በሕዝብ ብዛት አንደኛ በሆነው በዚህ አገር በወቅቱ ወደ 100,000 የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች የነበሩ ሲሆን በቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚያገለግሉ 80 ያህል ሰዎች ነበሩ። ተሽከርካሪዎችን መጠገን ጨምሮ ሌሎች ሥራዎች በሚሠሩበት ጋራዥ ውስጥ እንድሠራ ተመደብኩ።

በ1979 በአውሮፓ በወጣትነቴ እሠራው ወደነበረው ግብርና ተመለስኩ። በቅርንጫፍ ቢሮው ለሚያገለግሉ ሠራተኞች ቀለብ የሚመረትበት ይህ እርሻ የሚገኘው ከሌጎስ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኤላሮ ነበር። እዚያም በዝናባማው የሐሩር ክልል የሚከናወነው ግብርና በአውሮፓ ካለው በጣም የተለየ መሆኑን ተረዳሁ። በዚህ ቦታ ለሦስት ዓመት ተኩል ከሠራሁ በኋላ ወደ ሌጎስ ተመለስኩና እንደገና ጋራዥ ውስጥ መሥራት ጀመርኩ።

በ1986 ከሌጎስ 360 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትልቅ የቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ እየተካሄደ ወደ ነበረባት ኢጌዱማ የሚባል ሥፍራ ተዛወርኩ። ይህ ሕንፃ ለይሖዋ አገልግሎት የተወሰነው በጥር 1990 ነበር። በውስጡም ማተሚያ፣ አነስተኛ የእርሻ ቦታና ከ500 የሚበልጡ ሰዎች የሚይዝ የመኖሪያ ሕንፃን ያካተተ ነበር። ይህ ትልቅ የቅርንጫፍ ቢሮ የሚገኘው ዙሪያውን ሁለት ሜትር ከፍታ ባለው አጥር በታጠረ 60 ሄክታር መሬት ላይ ነበር። በአሁኑ ጊዜ 35 ሠራተኞችን ያቀፈውን እርሻውንና የጥገናውን ክፍል በበላይነት እከታተላለሁ።

በናይጄሪያ 27 ዓመታት ገደማ የኖርኩ ሲሆን በተሰጡኝ የተለያዩ የሥራ ምድቦች በጣም ተደስቻለሁ። እናቴ ለይሖዋ ታማኝ ሆና በመኖሯና ለ14 ዓመታት በልዩ አቅኚነት ያገለገለችው ታናሽ እህቴ ኢንግሬትም እስከ አሁን ከባለቤቷ ጋር ይሖዋን በማገልገል ላይ በመሆኗ ደስ ይለኛል።

ብዙ ተፈታታኝ ሁኔታዎች የገጠሙኝ ቢሆንም ይሖዋንና በምዕራብ አፍሪካ ያሉ መንፈሳዊ ወንድሞቼን ለማገልገል በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ። እስካሁን ድረስ ላገኘሁት ጥሩ ጤንነት እያመሰገንኩ ታላቁን አምላካችንን ይሖዋን በንቃት ማገልገሌን እንድቀጥል ጤንነቴን ጠብቄ ለመኖር እንድችል እጸልያለሁ።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ናይጄሪያ

ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክ

ጋቦን

[ምንጭ]

Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከእናቴ ከጌርትሩድና ከእህቴ ከኢንግሬት ጋር በ1939

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጋቦን ሚስዮናዊ ሆኜ ሳገለግል

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክ እንደዚህ ባሉ መንደሮች ውስጥ ኖሬአለሁ