ብቸኝነት የሚሰማቸው ሰዎች ይህን ያህል የበዙት ለምንድን ነው?
ብቸኝነት የሚሰማቸው ሰዎች ይህን ያህል የበዙት ለምንድን ነው?
ዛሬ ባለው ማኅበረሰብ ውስጥ ብቸኝነት የሚሰማቸው ሰዎች በጣም ብዙ ናቸው። ብቸኝነት ዕድሜና ዘር፣ የኑሮ ደረጃና ሃይማኖት የማይለይ የሰው ልጅ የጋራ ችግር ሆኗል። አንተስ ብቸኝነት ተሰምቶህ ያውቃል? አሁን ብቸኝነት ይሰማሃል? እንደ እውነቱ ከሆነ ሁላችንም በአንድ ወቅት ጆሮውን ሰጥቶ የሚያዳምጠን፣ አይዞህ የሚለን ወይም ውስጣዊ ስሜታችንንና ማንነታችንን የሚረዳልን ባልንጀራ የፈለግንበት ጊዜ አለ። ስሜታችንን የሚያውቅልን ሰው እንፈልጋለን።
ይሁን እንጂ ብቻችንን መሆናችን በራሱ ብቸኝነት እንዲሰማን ምክንያት አይሆንም። አንድ ሰው ደስ የሚለውን ነገር እያደረገ ምንም የብቸኝነት ስሜት ሳይሰማው ረዥም ጊዜ ብቻውን ሊያሳልፍ ይችላል። በአንጻሩ ደግሞ ብቻቸውን መሆንን ፈጽሞ ሊቋቋሙ የማይችሉ ሰዎች አሉ።
ብቸኝነት በጣም ከባድና የሚያሰቃይ ሊሆን ይችላል። የባዶነት ስሜት እንዲሰማ ያደርጋል። ከሌሎች ሰዎች የመነጠልና የመገለል ስሜት ያሳድራል። አቅመ ደካማና ፈሪ እንድንሆን ሊያደርገን ይችላል። ጁዲት ቪዮረስት የተባሉ ደራሲ ብቸኝነትን እንደሚከተለው ሲሉ ጥሩ አድርገው ገልጸውታል:- “የብቸኝነት ስሜት እንደ ድንጋይ ይከብዳል። . . . የብቸኝነት ስሜት ባዶና ተስፋ ቢስ ያደርገናል። የብቸኝነት ስሜት እናት እንደሌለው ልጅ፣ እንደ ባዘነች የበግ ግልገል፣ ምንም እንደማንረባ እንዲሁም ለሌላው ደንታ ቢስ በሆነ ሰፊ ዓለም ውስጥ መውጫ መግቢያው እንደጠፋብን እንዲሰማን ያደርጋል።” እንዲህ ተሰምቶህ ያውቃል? ብቸኝነት ምክንያቱ ምንድን ነው?
የተለያዩ ችግሮች፣ ሁኔታዎችና ክስተቶች በሰዎች ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ የተለያየ
ነው። ምናልባት በቁመናህ፣ በዘርህ ወይም በሃይማኖትህ ምክንያት እኩዮችህ እንደሚያገልሉህ ሊሰማህ ይችላል። አዲስ ትምህርት ቤት እንደመግባት፣ አዲስ ሥራ እንደመጀመር ወይም አገር፣ ከተማ ወይም የመኖሪያ ሠፈር እንደመለወጥ ያለ የአካባቢ ለውጥ ከቀድሞ ጓደኞችህ እንድትለያይ ስለሚያደርግህ የብቸኝነት ስሜት ሊያሳድርብህ ይችላል። ወላጅን ወይም የትዳር ጓደኛን በሞት ማጣት ምናልባትም ለበርካታ ዓመታት ለብቸኝነት ስሜት ሊዳርግ ይችላል። በተጨማሪም ዕድሜያችን እየገፋ ሲሄድ ከቀድሞ ወዳጆቻችንና እናውቃቸው ከነበሩ ሰዎች ልንራራቅ ወይም ጭራሽ ከአንዳቸውም ጋር ላንገናኝ እንችላለን።ትዳርም ቢሆን ሁልጊዜ የብቸኝነትን ስሜት ለማስወገድ ዋስትና አይሆንም። አለመግባባት ወይም አለመጣጣም ያልተረጋጋ ኑሮ ከማስከተሉም በላይ ባለትዳሮችና ልጆች ራሳቸውን እንዲያገልሉ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ የዘመድ ወይም የወዳጅ ሞት፣ ፍቺ እንዲሁም አካላዊ ወይም ስሜታዊ መገለል ከሚያስከትለው የብቸኝነት ስሜት ሌላ የከፋ ውጤት ሊያስከትል የሚችል የብቸኝነት ዓይነት አለ። እንዲህ ያለው ሁኔታ የሚፈጠረው ከአምላካችን ጋር ያለን ዝምድና ሲበላሽና ከእርሱ እንደተቆራረጥን ሆኖ ሲሰማን ነው።
ከላይ ከተጠቀሱት ሁኔታዎች አንዱ አጋጥሞህ ያውቃል? የብቸኝነት ስሜትንስ መቋቋም ይቻላል?
[በገጽ 4 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
አዲስ ትምህርት ቤት እንደመግባትም ሆነ የትዳር ጓደኛን እንደማጣት የመሳሰሉ በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ለውጦች ለብቸኝነት ስሜት ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ