በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አደገኛ—ነፍሰ ገዳይ ተክሎች!

አደገኛ—ነፍሰ ገዳይ ተክሎች!

አደገኛ—ነፍሰ ገዳይ ተክሎች!

ብሪታንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

እንስሳት ተክሎችን እንደሚመገቡ ሁሉም ሰው ያውቃል። ነገር ግን አንዳንድ ተክሎች እንስሳትን እንደሚመገቡ ታውቅ ነበር? እስከ አሁን ድረስ 550 የሚያህሉ ሥጋ በል ወይም ነፍሳት ተመጋቢ ተክሎች እንዳሉ የታወቀ ሲሆን ገና ሌሎችም እየተገኙ ነው። እነዚህ አስደናቂ ተክሎች የፀሐይን ብርሃን በመጠቀም ካርቦሃይድሬት መሥራት ይችላሉ፤ ለምነቱን ባጣ አፈር ላይ ከበቀሉ ግን እንደ ናይትሬትስ ያሉ አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን ማግኘት ይቸግራቸዋል። ለእነዚህ የተራቡ ተክሎች አስፈላጊ የምግብ ምንጭ የሚሆኑላቸው ነፍሳት ናቸው።

እያንዳንዱ ተክል ነፍሳትን የሚያጠምድበት የራሱ ዘዴ አለው። አንዳንዶቹ ወጥመድ ወይም ነፍሳቱ ከገቡ በኋላ የሚዘጋ በር ያላቸው ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ሰለባዎቻቸውን የሚማርክና ካረፉበት በኋላ ሙጭጭ አድርጎ የሚይዝ ወጥመድ አላቸው። እስቲ እነዚህን ሥጋ በል ተክሎች ቀረብ ብለን እንመርምራቸው።

ወጥመዶችና የወጥመድ በሮች

በጣም የታወቀው ሥጋ በል ተክል እስከ 30 ሴንቲ ሜትር የሚደርስ ቁመት ያለው ቬነስ ፍላይትራፕ የሚባለው ሳይሆን አይቀርም። በሰሜን አሜሪካ የካሮላይና ግዛቶች ረግረጋማ ቦታዎች የሚበቅለው ይህ ተክል የሚያብረቀርቁና ደማቅ ቀለም ያላቸው ቅጠሎች ያሉት ሲሆን በእነዚህ ቅጠሎች ዳር ዳር ላይ ነፍሳትን በእጅጉ የሚማርክ የአበባ ማር የሚያመነጩ ዕጢዎች አሉት። ቬነስ ፍላይትራፕ በእያንዳንዱ ቅጠል አጋማሽ ላይ ሦስት ተስፈንጣሪ ፀጉሮች ስላሉት ለነፍሳት አደገኛ የሚሆነው በዚሁ ምክንያት ነው። አንድ ያልጠረጠረ ፍጡር ፀጉሮቹን ሲነካቸው ቅጠሎቹ ይዘጋሉ። አንድ የብረት ወጥመድ ያጠመደውን አይጥ አንቆ እንደሚይዝ ሁሉ በዚህ ተክል ቅጠሎች ጠርዝ ላይ የሚገኙ እሾህ መሰል ጉጦች የተጠመደው ፍጡር እንዳያመልጥ እርስ በርሳቸው ይቆላለፋሉ።

ንፋስ ያመጣው ጭራሮ መሳይ ነገር ወጥመዱ ላይ ሲያርፍበት ቅጠሉ ቢዘጋም ተክሉ በጥቂት ቀናት ውስጥ ይለቀዋል። ነገር ግን በቅጠሉ ላይ ያሉት ነርቮች አስፈላጊ የሆነ ናይትሮጂንነት ያለው ነገር መያዛቸውን ከተገነዘቡ፣ ተክሉ ከተጠመደው ነፍስ የሚገኙትን ንጥረ ነገሮች እንዲያዋህድ የነፍሳቱን ገላ የሚያፈራርሱ ኢንዛይሞች ይመነጫሉ። ይህም እንደተገደለው ነፍስ መጠን ከ10 እስከ 35 ቀናት ይፈጃል።

የሚገርመው ነገር አንድ የዝናብ ጠብታ በአንዱ ተስፈንጣሪ ፀጉር ላይ ቢያርፍ ወጥመዱ አይዘጋም። ተክሉ ምላሽ የሚሰጠው በሃያ ሴኮንድ ጊዜ ውስጥ ሁለቱ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ፀጉሮች ከተነኩ ብቻ ነው። ወጥመዱ የሚዘጋበት ፍጥነት በአየሩ ሙቀትና በፀሐይ ብርሃን ላይ የተመካ ነው። በአንዳንድ ሁኔታዎች ወጥመዱ በአንድ ሠላሳኛ ሴኮንድ ቅፅበት ይዘጋል።

የአንዳንድ ተክሎች ወጥመዶች ከዚህም በበለጠ ፍጥነት ይዘጋሉ። በውኃ ውስጥ የሚያድጉ ቅጠሎች ያሉት በዋነኝነት የውኃ ተክል የሆነውን ብላደርዎርትን ተመልከት። ቅጠሎቹ እያንዳንዳቸው የሚዘጋ ወጥመድና የተገጠገጡ አያሌ ረዣዥም ፀጉሮች ያላቸው በርካታ ፊኛዎች ይዘዋል። የውኃ ቁንጫ የመሰለ አንድ ትንሽ ነፍሳት በተክሉ ፀጉሮች ላይ ሲያርፍ ፊኛው ይሰረጉዳል። በፊኛው ውስጥ ያለው የውኃ ግፊት በውጭ ካለው ስለሚያንስ ደቃቃው ፍጡር ወደ ውስጥ ተስቦ ይገባና የወጥመዱ በር ይዘጋበታል። ይህ ሂደት የሚከናወነው በአንድ ሠላሳ አምስተኛ የሴኮንድ ጊዜ ውስጥ ሊሆን ይችላል!

የሚያጣብቁ ወጥመዶች

ከትልልቆቹ ሥጋ በል ተክሎች መካከል ሃንጊንግ ፒቸር ፕላንትስ የሚባሉት ይገኙበታል። በደቡባዊ ምሥራቅ እስያ እንደሚገኙት ያሉ አንዳንድ የፒቸር ተክል ዝርያዎች እስከ ዛፎች ጫፍ ድረስ የሚያድጉ ሐረጎች ናቸው። እነዚህም እንቁራሪት የሚያህሉ ፍጥረታትን የሚያጠምዱበት እስከ ሁለት ሊትር ፈሳሽ የሚይዝ ወጥመድ አላቸው። እንዲያውም አንዳንዶቹ አይጥም እንኳን ሳይቀር እንደሚይዙ ይታመናል። ይሁን እንጂ ወጥመዱ የሚሠራው እንዴት ነው?

እያንዳንዱ የፒቸር ተክል ቅጠል ጆግ ወይም ደንበጃን የሚመስል ቅርጽ ያለው ሲሆን የዝናብ ውኃ እንዳይገባ የሚከለክል ክዳን አለው። የተክሉ ደማቅ ቀለምና ብዛት ያለው የአበባ ማር ለነፍሳት ማራኪ ቢሆንም የቅጠሉ ጠርዝ የሚያሙለጨልጭ ነገር አለው። ነፍሳቱ የአበባውን ማር ለመቅሰም ሲሞክር ተንሸራቶ ከሥር ወዳለው ፈሳሽ ውስጥ ይወድቃል። በቅጠሉ ውስጥ ያሉ ቁልቁል ያዘቀዘቁ ፀጉሮች የተጠመደው ነፍስ እንዳያመልጥ ያግዱታል። በተጨማሪም አንዳንዶቹ ፒቸር ተክሎች የሚያዘጋጁት የአበባ ማር የሚጠመደውን ነፍስ የሚያፈዝ ዕፅ አለው።

በጣም የሚያምር መልክ ያለው ሌላው የፒቸር ተክል ዝርያ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚገኙት የካሊፎርኒያ ተራሮችና በኦሪገን የሚበቅለው ኮብራ ፕላንት የተሰኘው ነው። ይህ ተክል ሊናደፍ ፈልጎ ራሱን ቀና ካደረገ ኮብራ ከተሰኘ እባብ ጋር በእጅጉ ይመሳሰላል። አንዲት ነፍሳት ወደ ተክሉ አፍ ስትገባ በትናንሽ መስኮቶች ሾልኮ የሚገባ በሚመስል ብርሃን ግራ ትጋባለች። ከዚያም ባይሳካላትም ብርሃኑ ባለበት በኩል ለማምለጥ ትሞክራለች። በመጨረሻም ደክሟት በተክሉ ግንድ ውስጥ ወዳለው ፈሳሽ ወድቃ ትሰጥማለች።

ሥጋ በል ተክሎች ለቤት ውስጥና ለንግድ የሚሰጡት ጥቅም

በተርዎርት የተባሉት ሥጋ በል ተክሎች ሲያሪድ ፍላይ እና ዋይት ፍላይ የሚባሉ የዝንብ ዓይነቶችን የሚማርኩና አጣብቀው የሚይዙ ቅጠሎች አሏቸው። እነዚህ ዝንቦች ለንግድ ሲባል በመስታወት ቤት ለሚተከሉና ለቤት ውስጥ ተክሎች ፀር ናቸው። ሰው ሠራሽ የዝንብ ወጥመዶች እነዚህን ዝንቦች ለማጥፋት ውጤታማ ቢሆኑም እንደ ንብ ያሉ ጠቃሚ ነፍሳትንም አይምሩም። በበተርዎርት ላይ ያለው ማጣበቂያ ግን ጥቃቅን ነፍሳትን ብቻ ስለሚይዝ ከሰው ሠራሽ የዝንብ ወጥመድ የላቀ ነው።

የሰሜን አሜሪካዎቹ የፒቸር ተክሎች ዛሬ ዛሬ በአትክልተኞች ዘንድ ተወዳጅነት እያተረፉ ነው። የእነዚህ ተክሎች ውብ አበቦችና ማራኪ የሆነው የቅጠሎቻቸው ቅርጽ በውበት ከሌሎች ተክሎች ጋር የሚተካከሉ ሲሆን ለማልማትም ቀላል ናቸው። የሚበሉት የዝንብ መጠንም ከፍተኛ ነው። በእርግጥም እያንዳንዱ ቅጠል በአንድ ወቅት በሺህ የሚቆጠሩ ዝንቦችን ሊይዝ ይችላል። ንቦች በፒቸር ተክሎች የአበባ ማር ስለማይማረኩ ለእነርሱ የሚያሰጋ አይደለም። ታዲያ አበቦቹ ለመራባት የሚያስፈልጓቸውን ነፍሳት የሚይዙ ከሆነ የሴቴው አበባ እንቁላል የሚዳብረው እንዴት ነው? አበቦቹ የሚያብቡት ቅጠሎቹ ገና በማደግ ላይ ባሉበት ጊዜ ነው። ቅጠሎቹ የተሟላ ዕድገት ላይ ሲደርሱ አበቦቹ ስለሚረግፉ የአበባ ዱቄት የሚቀስሙት ነፍሳትም ሥራቸውን ጨርሰው ሄደዋል ማለት ነው።

የተለያየ የአየር ሙቀት ለመቋቋም የሚችልና ለማሳደግ ቀላል የሆነ ሌላው ተክል ደግሞ የአውስትራሊያው ፎርክ ሊፍ ሰንዲው ነው። ለንደን ውስጥ በዎልወርዝ የአካባቢ ጥበቃና የተክሎች ልማት ትምህርት ማዕከል የሥጋ በል ተክሎችን የሚያጠኑ ክሪስ ሄዝ የተባሉ ምሑር “ቢንቢዎች ማታ ማታ ደጅ አላስቀምጥ ብለው ካስቸገሯችሁ ይህ ተክል ፍቱን መፍትሔ ይሆንላችኋል” ይላሉ። “ከተክሉ የሚንጠባጠበው ሙጫነት ያለው የሚያብረቀርቅ ፈሳሽ ትንኞችን ስለሚስብ በቅርጫት ተክላችሁ ደጅ አንጠልጥሉት።” የዚህን ተክል ቅጠል የሚነካ ማንኛውም ትንኝ ወደ ውስጥ በተቆለመሙት የሚያጣብቁ ፀጉሮች ስለሚያዝ ከቅጠሉ ጋር ተጣብቆ ይቀራል።

አዳኝ ተክሎችን ከጥፋት መታደግ

የሚያሳዝነው ግን ብዙ ሥጋ በል ተክሎች የሚበቅሉት የሰው ልጅ በአካባቢ ላይ ውድመት እያስከተለ ባለበት ቦታ ነው። ለምሳሌ ያህል የደቡብ ምሥራቅ እስያው ሐረግማ የፒቸር ተክል የአካባቢው ደን የእርሻ መሬት ለማግኘት ሲባል ስለሚመነጠርና ስለሚቃጠል ጨርሶ ለመጥፋት ተቃርቧል። በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ረግረግ የሆኑ ቦታዎች ለልማት ጉዳይ እንዲደርቁ በመደረጉ የዚህ ተክል አንዳንድ ዝርያዎች ቀደም ሲል ጠፍተዋል። *

ሥጋ በል ተክል እንዲኖርህ ትፈልጋለህን? እነርሱን ፍለጋ ወደ ዱር መሄድ ሳያስፈልግህ ችግኝ አፍልተው ወይም ግንጣዩን አባዝተው ከሚያቀርቡ ነጋዴዎች በቀላሉ ማግኘት ትችላለህ። ተክሎቹን ለማሳደግ የሚያስፈልገው መመሪያ ቀላል ነው። የሚፈለገው ምንጊዜም የዝናብ ውኃ ማጠጣት ነው። በተጨማሪም ሥጋ በል ተክሎች ፀሐይ ሲያገኙ የሚመቻቸው ቢሆንም ከመካከለኛው ሞቃት ክልል የመጡ ዝርያዎች ከሆኑ በክረምት ወራት በቀዝቃዛ ሥፍራ እንዲቀመጡ ቢደረግ በጣም የተሻለ ነው። አንዳንዶቹ ተክሎች እስኪደርሱ ሦስት ዓመት ሊፈጅ ስለሚችል ትዕግሥት ያስፈልጋል። ሌላው ቢቀር ለእነዚህ ተክሎች ምግብ ማቅረብ አያስፈልግም፣ ምክንያቱም የራሳቸውን ምግብ ራሳቸው ያሰናዳሉና!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.19 አንዳንድ ነፍሳት በል ተክሎች ለመጥፋት የተቃረቡ ዝርያዎችን ለመጠበቅ በወጣው ዓለም አቀፍ ድንጋጌ አማካኝነት ጥበቃ እየተደረገላቸው ነው።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የሻጋታዎች ቀለብ

በጣም ጥቃቅን የሆኑት ሥጋ በል ተክሎች በአፈርና በውኃ ውስጥ የሚኖሩና በዓይን የማይታዩ ትላትሎችን አጥምደው የሚይዙት ሻጋታዎች (fungi) ናቸው። ከእነዚህ ሻጋታዎች መካከል አንዳንዶቹ በአገዳቸው ላይ የሚያጣብቅ ነገር ያላቸው ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ውፍረቱ 0.03 ሚሊ ሜትር ብቻ የሆነ ሦስት ሴሎችን አጣምሮ የያዘ ወጥመድ ስላላቸው አገር ሰላም ብሎ ለማለፍ የሚሞክረውን ማንኛውንም ትል አንቀው ይይዛሉ። ትሉ በወጥመዱ እንደተያዘ ሻጋታው ላይ በሚገኙ ክር መሳይ ነገሮች ይወጋጋና ወዲያው ይሞታል። ትላትሎቹ በየዓመቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የገንዘብ ኪሳራ ለሚያስከትል የሰብል ጥፋት ስለሚዳርጉ እነዚህ ሻጋታዎች ያላቸው ተባይን የመከላከል ብቃት እየተጠና ነው።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ነፍሳት ራሳቸውን ይከላከላሉ!

የነፍሳት በል ተክሎች የጥቃት ሰለባ የሚሆኑት ሁሉም ነፍሳት አይደሉም። ለምሳሌ ያህል፣ የሥጋ ትሎችን የሚፈለፍሉት የዝንብ ዝርያዎች በእያንዳንዱ እግራቸው ላይ ቅጥል አካል አላቸው። ተራራ የሚወጣ ሰው መሬቱን የሚቆነጥጥ ብረት እንደሚያደርግ ሁሉ የእነዚህ ዝንቦች ቅጥል አካልም በፒቸር ተክል ታንቆ ቢያዝ ታግሎ እንዲወጣ ያስችለዋል። የዝንቦቹ እንቁላሎች ሲቀፈቀፉ ዕጮቹ ፒቸር ተክሉ ቀደም ሲል ያጠመዳቸውን በመበስበስ ላይ ያሉ ነፍሳት ይመገባሉ። ከዚያም ዕጮቹ ወደ ኩብኩባነት ደረጃ ሲያድጉ የተክሉን ቅጠል ይበሱትና ሾልከው ያመልጣሉ። የአንዲት ትንሽ የእሳት እራት አባጨጓሬም በአጸፋው አጥረው የያዙትን የፒቸር ተክል ፀጉሮች በድሮቹ ከሸፈነ በኋላ ያመልጣል። አንዳንድ ሸረሪቶችም በፒቸር ተክል ውስጥ የሚገቡ ነፍሳትን ቀድሞ ለመያዝ በተክሉ አፍ ላይ በዘዴ ድራቸውን የሚያደሩ ሲሆን ቢያንስ ቢያንስ ከተለያዩ የሸረሪት ዓይነቶች መካከል አንዷ አደገኛ ሁኔታ ቢያጋጥማት የተክሉ ምግብ መፍጫ ፈሳሽ እንዳይጎዳት የሚያስችላት ልዩ ቆዳ አላት።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሃንጊንግ ፒቸር ኘላንት ቅጠል

[በገጽ 20, 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቬነስ ፍላይትራፕ

በስተ ግራ ያለው ቅጠል የተጠመደ ዝንብ አለበት፤ በስተ ቀኝ ያለው ደግሞ ተስፈንጣሪ ፀጉሮችን ያሳያል

[ምንጭ]

ተክሎች:- Copyright Chris Heath, Kentish Town City Farm, London

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኮብራ ኘላንት አበባ እና ለጋ ቅጠል

[ምንጭ]

Copyright Chris Heath, Kentish Town City Farm, London

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሰሜን አሜሪካው ፒቸር ተክል

አበባው ብርቱካን ያክላል

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በተርዎርት

ሲያሪድ ፍላይና ዋይት ፍላይ የሚባሉ የዝንብ ዝርያዎች በቅጠሎቹ ላይ ተጣብቀዋል

[በገጽ 22 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የሰሜን አሜሪካው ፒቸር ተክል ቅጠሎች

ከመሃል ያለው ሥዕል:- አንዲት ዝንብ የሚያፈዝ የአበባ ማር ስትቀስም

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፎርክ ሊፍ ሰንዲው

አንዲት ነፍሳት በተክሉ የሚያጣብቁ ፀጉሮች ተይዛለች

[ምንጭ]

ተክሎች:- Copyright Chris Heath, Kentish Town City Farm, London