በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

በአራዊት መጠበቂያ የሚኖሩ እንስሳትን ብዛት መቆጣጠር መላ ያጣ ችግር ሆኗል

በሚዩኒክ የሄላብሩን አራዊት መጠበቂያ ዋና የስነ እንስሳት ተመራማሪ የሆኑት ሄኒንግ ቪስነር “ዛሬ የወሊድ መቆጣጠሪያ ሳይጠቀም ሊቀጥል የሚችል የአራዊት መጠበቂያ ተቋም የለም” ይላሉ። በአራዊት መጠበቂያ ውስጥ የሚኖሩ እንስሳት በፍጥነት ይራባሉ፣ ልጆቻቸውም ቶሎ ያድጋሉ እንዲሁም በዱር ከሚኖሩ ወገኖቻቸው የበለጠ ዕድሜ አላቸው። ይሁን እንጂ የአራዊት መጠበቂያ ቦታዎች ያላቸው ቦታ በጣም ውስን ነው። በዚህ ምክንያት የወሊድ መቆጣጠሪያ መጠቀም የግድ አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ “በአራዊት መጠበቂያዎች የወሊድ ቁጥጥር ማድረግ ቀላል አይደለም። እንስሳቱ መድኃኒቱን መውሰድ አይፈልጉም” ይላል ፎከስ የተባለው የጀርመን መጽሔት። ለምሳሌ ድቦች ከምግባቸው ጋር ተደባልቆ የተሰጣቸውን የወሊድ መከላከያ አነፍንፈው ያወጣሉ። በተጨማሪም በአፍ የሚወሰድ የወሊድ መቆጣጠሪያ በአንዳንድ እንስሳት ላይ እንደ ጡት ካንሰር ያለ የጤና ችግር ያስከትላል። ሌላው አማራጭ እንስሳቱን ማኮላሸት ወይም ማምከን ሲሆን ይህ ደግሞ አዳዲስ ችግሮች አስከትሏል። አንደኛ ነገር የተኮላሹትን ወይም የመከኑትን እንስሳት እንደገና እንዲወልዱ ማድረግ አይቻልም። ደግሞም መውለዳቸው አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል። ሁለተኛ ደግሞ እነዚህ እንስሳት የጾታ ሆርሞን ማመንጨት ስለሚያቆሙ በመሰሎቻቸው ዘንድ የተጠሉ ወይም የተናቁ ይሆናሉ። ግልገሎችን መግደል ደግሞ ሌላው አማራጭ ሲሆን ይህ ድርጊት ግን በርካታ የእንስሳት አፍቃሪዎችንና የአራዊት ጥበቃ ተሟጋቾችን በእጅጉ ያስቆጣል። ስለዚህ የአራዊት መጠበቂያዎች መላ የሌለው ችግር ገጥሟቸዋል።

ጥራጊ የኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች

የካናዳው ናሽናል ፖስት ጋዜጣ ካናዳውያን በ2002 155,000 ቶን የሚመዝን የማይፈለግ የኤሌክትሮኒክ ዕቃ አውጥተው መጣላቸውን ገልጿል። ኢንቫይረመንት ካናዳ የተባለው ድርጅት ያወጣው ዘገባ ካናዳውያን “ሁለት ሚሊዮን ቴሌቪዥኖችን፣ 1.1 ሚሊዮን የቪዲዮ ካሴት ማጫወቻዎችንና 348,000 የሲዲ ማጫወቻዎችን አውጥተው እንደጣሉና አብዛኞቹ ከጥቂት ዓመታት ግልጋሎት በኋላ ጊዜ ያለፈባቸው ናቸው ተብለው የተጣሉ እንደሆኑ” ገልጿል። የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች “አብዛኛውን ጊዜ የሚጣሉት ስለተበላሹ ሳይሆን የተገልጋዩን ፍላጎት የማያሟሉ ሆነው በመገኘታቸው ነው” ሲል ዘገባው ይገልጻል። ከእነዚህ ጥራጊዎች መካከል አብዛኞቹ አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ በአንድ ቴሌቪዥን ውስጥ “ሁለት ኪሎ ግራም የሚመዝን ሊድ (እርሳስ) ሊኖር ይችላል” በማለት ጋዜጣው ዘግቧል። እንዲሁም በአንዳንድ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ውስጥ የሚገኘው ሜርኩሪ ባሁኑ ጊዜ ጥራጊ በሚቀበርባቸው ቦታዎች ብክለት እያስከተለ ነው። ሁኔታው በዚህ መልኩ ከቀጠለ የኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች ጥራጊ እስከ 2010 ድረስ በእጥፍ እንደሚጨምር ኢንቫይረመንት ካናዳ አስጠንቅቋል።

ጉንዳኖችና አንቲባዮቲኮች

ዘ ማያሚ ሄራልድ የተባለው ጋዜጣ በዓለም አቀፍ እትሙ ላይ “አንዳንድ የጉንዳን ዝርያዎች እንጉዳይ አብቅለው ልጆቻቸውን እንደሚመግቡና ይህንኑ ሰብላቸውን ለመጠበቅ አንቲባዮቲኮችን ‘ፀረ ተባይ መድኃኒት’ አድርገው እንደሚጠቀሙ ሳይንቲስቶች ደርሰውበታል” ይላል። ሊፍ ከተርስ የሚባሉት እነዚህ ጉንዳኖች ልክ እንደ ገበሬ ሰብላቸውን ያርማሉ፣ ይከረክማሉ እንዲሁም ችግኝ ይተክላሉ። የጉንዳኖቹን ሰብል ከተላላፊ ሻጋታ የሚከላከለው አንቲባዮቲክ የሚሠራው የስትሬፕቶማይሲን ቤተሰብ ከሆነ ባክቴሪያ ሲሆን የሚኖረው ደግሞ በጉንዳኖቹ ቆዳ ላይ ነው። በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የተፈጥሮ ታሪክ ብሔራዊ ሙዚየም የሦስት አጽቄዎች ስፔሻሊስት የሆኑት ቴድ ሹልዝ የሰው ልጆች መድኃኒት የመቋቋም ችሎታ ያላቸውን ጀርሞች ለማሸነፍ ሁልጊዜ አዳዲስ አንቲባዮቲኮችን ለመፈልሰፍ ሲገደዱ ሊፍ ከተርስ ግን በተመሳሳይ አንቲባዮቲክ አላንዳች ችግር ለዘመናት ሲጠቀሙ እንደኖሩ ገልጸዋል። ጉንዳኖች በዚህ ረገድ ያገኙትን ስኬት መረዳት መቻል “ለሰው ልጅ ሕልውና በጣም ጠቃሚ ነገር ሳይሆን አይቀርም” ብለዋል ሹልዝ።

በመላው ምድር ላይ የመጣ መቅሰፍት

ዓለም አቀፍ የስኳር ሕመም ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት የብሪታንያው ፕሮፌሰር ሰር ጆርጅ አልበርቲ የስኳር በሽታ በሚያስደነግጥ ሁኔታ እየተስፋፋ በመምጣቱ ምክንያት ዓለማችን “ከዚህ በፊት አጋጥሟት የማያውቅ ታላቅ መቅሰፍት” ተደቅኖባታል ሲሉ አስጠንቅቀዋል። በመላው ዓለም ከ300 ሚሊዮን በላይ የሚያክሉ ሰዎች ግሉኮስ የማዋሀድ ችግር እንዳለባቸውና ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ውሎ አድሮ የስኳር ሕሙማን መሆናቸው እንደማይቀር የብሪታንያው ጋርዲያን ጋዜጣ ዓለም አቀፍ የስኳር ሕመም ፌዴሬሽንን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል። አንድ ወቅት በአመዛኙ አረጋውያንን ያጠቃ የነበረው ታይፕ 2 የስኳር በሽታ፣ መናኛ ምግቦችን በማዘውተራቸውና በቂ የአካል እንቅስቃሴ ባለማድረጋቸው ምክንያት እየወፈሩ የሄዱትን የብሪታንያ ወጣቶች ጭምር ማጥቃት ጀምሯል። “ይህ በሽታና በሽታው የሚያስከትለው መዘዝ የአኗኗር ለውጥ በማድረግ ብቻ ሊወገድ የሚችል ሆኖ ሳለ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ በጣም ያሳዝናል” ይላሉ አልበርቲ። በማደግ ላይ ያሉ አገሮችም “የበለጸገውን ዓለም ጎጂ የአመጋገብ ልማድና የከተማ የአኗኗር ዘይቤ እየለመዱ በሄዱ መጠን የስኳር ሕመምተኞቻቸው ቁጥር በፍጥነት እያሻቀበ ሲሄድ መመልከታቸው አይቀርም” ይላል ዘ ጋርዲያን።

እየተለወጠ የመጣው የጣልያናውያን ቤተሰብ

ከ1995 እስከ 2001 ባለው ጊዜ በጣልያን በጋብቻ ሳይተሳሰሩ አብረው የሚኖሩ ጥንዶች ቁጥር በእጥፍ ሲያድግ የሚጋቡ ሰዎች ቁጥር ግን ቀንሷል። በሌላ በኩል ብቻቸውን የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል። ላ ሪፑብሊካ በተባለው ጋዜጣ ላይ የወጣው ይህ ግኝት የተመሠረተው የጣልያን ብሔራዊ ስታትስቲክስ ተቋም ባሰባሰበው መረጃ ላይ ነው። በዚሁ ጊዜ ውስጥ የቤተሰብ አባላት አማካይ ቁጥር ወደ 2.6 አሽቆልቁሏል። የጣልያን ብሔራዊ ስታትስቲክስ ተቋም እንዳለው ከሆነ ብዙ ጥንዶች የመጋባት ሐሳብ ቢኖራቸውም ከዚያ በፊት የተወሰነ “የሙከራ ጊዜ” አብረው ለማሳለፍ ይመርጣሉ።

የጉጉቶች ልዩ የሆነ የማየትና የማዳመጥ ችሎታ

ጉጉቶች ትላልቅ ዓይኖችና በሁለቱም ዓይኖች አነጣጥሮ የመመልከት ችሎታ ስላላቸው “የእነርሱን ያህል በጨለማ አጥርቶ የማየት ችሎታ ያለው እንስሳ የለም” ሲል አውስትራሊያን ጂኦግራፊክ መጽሔት ዘግቧል። ብዙዎቹ ደግሞ “ሰው ሊያዳምጥ ከሚችለው የድምፅ መጠን በ10 እጥፍ የሚያንስ ድምፅ የመስማት ችሎታ አላቸው።” ይህን የመሰለ የጠራ የመስማት ችሎታ ሊኖራቸው የቻለው እንዴት ነው? ጽሑፉ እንደሚለው “በተወሰነ መጠን ልዩነት ቢኖራቸውም የጉጉት ዝርያዎች በሙሉ ልዩ የሆነ የጆሮ አፈጣጠር አላቸው። የአንደኛው ጆሮ ቀዳዳ ከሌላኛው ጆሮ ቀዳዳ ከፍ ያለ ነው።” ከዚህ አፈጣጠር የተነሳ ጉጉቶች ለምግብነት የሚፈልጓቸው ፍጥረታት ሲንቀሳቀሱ ሰምተው ያሉበትን ቦታ በቀላሉ ማግኘት ይችላሉ። ታይቶ የሚባሉት የጉጉት ዘሮች ደግሞ የድምፅ ሞገዶችን ሰብስቦ ወደ ጆሯቸው የሚያስገባና እንደ ድምፁ አቅጣጫ ሊስተካከል የሚችል ክብ ሳህን የመሰለ ቅርጽ ያለው ላባ ፊታቸው ላይ አለ። ከዚህም በላይ ከመስማት ጋር የቅርብ ትስስር ያለው ሜዱላ የሚባለው የአንጎል ክፍል ከሌሎች አእዋፍ ይበልጥ በጉጉቶች ላይ አፈጣጠሩ እጅግ የተወሳሰበ ነው።

ሊወገዱ የሚችሉ የሄፐታይተስ ኢንፌክሽኖች

በፖላንድ በየሳምንቱ የሚታተመው ፖሊቲካ የተባለው መጽሔት አብዛኛው “የሄፐታይተስ ኢንፌክሽን በሕክምና ሠራተኞች የንጽሕና ጉድለት ሳቢያ የሚከሰት ነው” ብሏል። የፖላንድ ብሔራዊ የንጽሕና ተቋም በ1997 ባወጣው ሪፖርት መሠረት በሄፐታይተስ ሲ ኢንፌክሽን የተያዙ ሰዎች ብዛት 992 የነበረ ሲሆን ከአምስት ዓመት በኋላ ግን 1,892 ደርሷል። የጽሑፉ አዘጋጅ ባሁኑ ጊዜ ሄፐታይተስ ሲን የሚከላከል በሕግ የተፈቀደ ክትባት አለመኖሩ በጣም እንደሚያሳዝን ገልጿል። የተዛማች በሽታዎች ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አንጄ ግዋዲሽ “በፖላንድ ከ500 ሺህ እስከ 600 ሺህ የሚደርሱ በሄፐታይተስ ሲ ቫይረስ የተለከፉ ሰዎች ይኖራሉ ብንል ማጋነን አይሆንም” ብለዋል። በፖዝናን የሕክምና ዩኒቨርሲቲ የተዛማጅ በሽታዎች ሆስፒታል ባልደረባ የሆኑት ያትሴክ ዩሽቺክ ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ በበሽታው የሚያዙት ለሕክምና “ዶክተሮች ወይም የጥርስ ሐኪሞች ዘንድ በቀረቡበት ወቅት ነው” ብለዋል። መጽሔቱ ሲደመድም “ዶክተሮች እጅ ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ እጆቻቸው በጣም ንጹሕ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንፈልጋለን” ብሏል።

የጎስቋላ መንደሮች መበራከት

የሜክሲኮ ሲቲው ኤል ኡኒቨርሳል የተባለ ጋዜጣ “በጎስቋላ የከተማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ብዛት አንድ ቢሊዮን ወይም ደግሞ በዓለም ዙሪያ በከተሞች ከሚኖሩ ሕዝቦች መካከል 32 በመቶ ይሆናል” ብሏል። አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥናት፣ ጎስቋላ መንደሮች እየተበራከቱ ከመጡባቸው ከተሞች መካከል ቦጎታን፣ ሃቫናን፣ ሜክሲኮ ሲቲን፣ ኩዌቶንና ሪዮ ዴ ጄኔሮን ለአብነት ያህል ይጠቅሳል። መንስኤው ምንድን ነው? የቦጎታን ሁኔታ ከተመለከትን ጎስቋላ መንደሮች በጣም የተበራከቱበት ምክንያት “የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት ማደግ፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሱ ሰዎች መብዛትና ለማኅበረሰቦች መፈናቀል ምክንያት የሆኑ የዓመጽ ድርጊቶች መስፋፋት” እንደሆነ የተመድ ሪፖርት ይገልጻል። በተጨማሪም በዚያች ከተማ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ሰዎች ብዛት በ1994 ከነበረበት 19.4 በመቶ ተነስቶ በ2000 23 በመቶ ደርሷል።