የላክቶስ አለመስማማት ምንድን ነው?
የላክቶስ አለመስማማት ምንድን ነው?
በጣም የምትወደውን አይስክሬም ወይም አይብ አጣጥመህ ከጨረስክ ከአንድ ሰዓት አይበልጥም። ሆድህ ተቆጥቶ ተወጥሯል፣ ተነፍቷል። አሁንም ከአጠገብህ የማይለየውን መድኃኒት ወስደህ እፎይታ ለማግኘት ትፈልጋለህ። ‘ሆዴ ይህን ያህል ታማሚ የሆነው ለምንድን ነው?’ ብለህ ማሰብ ትጀምራለህ።
ወተት ወይም የወተት ተዋጽኦ ከወሰድክ በኋላ ማቅለሽለሽ፣ ቁርጠት፣ የሆድ መነፋት፣ የጋዝ መብዛት ወይም ተቅማጥ የሚጀምርህ ከሆነ መንስኤው የላክቶስ አለመስማማት ይሆናል። የላክቶስ አለመስማማት የወተት ተዋጽኦዎች በመመገብ የሚነሳ የተለመደ ችግር ነው። የስኳር፣ የሆድ ዕቃና የኩላሊት በሽታዎች ብሔራዊ ተቋም “ከ30 እስከ 50 ሚሊዮን የሚደርሱ አሜሪካውያን ላክቶስ አይስማማቸውም” ሲል ዘግቧል። በሐርቫርድ የሕክምና ትምህርት ቤት የታተመው ዘ ሴንሲቲቭ ገት የተባለ መጽሐፍ እንደሚለው “ከዓለም ሕዝቦች መካከል እስከ 70 በመቶ የሚደርሱት ከላክቶስ ጋር የሚዛመድ አንድ ዓይነት ችግር እንደሚኖርባቸው” ይገመታል። ታዲያ የላክቶስ አለመስማማት ምንድን ነው?
ላክቶስ፣ በወተት ውስጥ የሚገኘው ስኳር ነው። ትንሹ አንጀት ላክተስ የሚባል ኢንዛይም ያመነጫል። የዚህ ኢንዛይም ተግባር ላክቶስን፣ ግሉኮስና ጋላክቶስ ወደሚባሉ ሁለት የስኳር ዓይነቶች መለወጥ ነው። ይህም ግሉኮስ በቀላሉ ከደም ጋር እንዲዋሃድ ያስችላል። ይህን ተግባር የሚያከናውን ላክተስ በበቂ መጠን ከሌለ ወደ ግሉኮስና ጋላክቶስ ያልተለወጠው ላክቶስ ወደ ትልቁ አንጀት ከገባ በኋላ ፈልቶ አሲድና ጋዝ እንዲፈጠር ያደርጋል።
ይህ የላክቶስ አለመስማማት ተብሎ የሚጠራው ሁኔታ ከላይ የተገለጹትን የሕመም ስሜቶች በሙሉ ወይም በከፊል ሊያስከትል ይችላል። ላክተስ በከፍተኛ መጠን የሚመነጨው እስከ ሁለት ዓመት ዕድሜ ባለው ጊዜ ውስጥ
ሲሆን ከዚያ በኋላ ግን በጣም እየቀነሰ ይሄዳል። በመሆኑም ብዙዎች ይህ የጤና ችግር ሊያጋጥማቸውና ሳያውቁት ሥር እየሰደደ ሊሄድ ይችላል።አለርጂ ነው?
አንዳንዶች የወተት ተዋጽኦ የሆነ ምግብ ከተመገቡ በኋላ በሚሰማቸው የሕመም ስሜት ምክንያት ለወተት አለርጂክ ነኝ ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። ስለዚህ ችግሩ የምግብ አለርጂ * ነው ወይስ አለመስማማት? አንዳንድ ስለ አለርጂ የሚያጠኑ ባለሞያዎች እንደሚሉት እውነተኛ የምግብ አለርጂ እምብዛም ያልተለመደ ከመሆኑም ሌላ የላክቶስ አለመስማማት ከሚያጠቃቸው ሰዎች መካከል 1 ወይም 2 በመቶ ብቻ ቢያህሉ ነው። የምግብ አለርጂ በሕፃናት ላይ ይበልጥ የተለመደ ቢሆንም ከ8 በመቶ አያልፍም። የአለርጂና የላክቶስ አለመስማማት ምልክቶች ተመሳሳይ ሊሆኑ ቢችሉም እንኳ የሚለያዩባቸው ነገሮች አሉ።
የምግብ አለርጂ በሚኖርበት ጊዜ የሰውነት የበሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ሂስተሚን የተባለ ቅመም ስለሚያመነጩ የሕመም ስሜት ይኖራል። ከአለርጂ ምልክቶቹ መካከል የከንፈርና የምላስ እብጠት፣ ሽፍታና አስም ይገኛሉ። የላክቶስ አለመስማማት ግን የበሽታ ተከላካይ ሕዋሳትን ስለማይነካ እነዚህ የሕመም ምልክቶች አይታዩም። የላክቶስ አለመስማማት የሚፈጠረው ምግብ በሚገባ መዋሃድ ሳይችል ሲቀር ነው፤ ይህም የሕመም ስሜቶች ያስከትላል።
በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት እንዴት ማወቅ ይቻላል? ዘ ሴንሲቲቭ ገት የተባለው መጽሐፍ ይህን መልስ ይሰጣል:- “ትክክለኛው የአለርጂ ሕመም ምልክቶች . . . መታየት የሚጀምሩት ሰውነት የማይቀበለው ምግብ በተበላ በደቂቃዎች ውስጥ ነው። ከአንድ ሰዓት ከሚበልጥ ጊዜ በኋላ የሚታዩ የሕመም ምልክቶች አብዛኛውን ጊዜ የሚያመለክቱት የምግብ አለመስማማትን ነው።”
በልጆች ላይ የሚያስከትለው ውጤት
አንድ ሕፃን ወይም ትንሽ ልጅ የጠጣው ወተት ሳይስማማው ሲቀር የሚያስከትለው ሕመም ሕፃኑንም ሆነ ወላጆቹን
ሊያስጨንቅ ይችላል። የሚያስቀምጠው ከሆነ ደግሞ በሰውነቱ ውስጥ ያለው ፈሳሽ ሊሟጠጥ ይችላል። በዚህ ጊዜ ወላጆች የሕፃናት ሐኪም ቢያማክሩ ጥሩ ነው። የላክቶስ አለመስማማት ችግር እንዳለው ከታወቀ አንዳንድ ሐኪሞች ወተትን የሚተካ ሌላ ዓይነት ምግብ መስጠት እንደሚሻል ይመክራሉ። ይህን በማድረግ ያስጨንቃቸው ከነበረ ሕመም የተገላገሉ ብዙዎች ናቸው።አለርጂ በሚሆንበት ጊዜ ግን ጉዳዩ ይበልጥ አሳሳቢ ይሆናል። አንዳንድ ዶክተሮች አንታይሂስተሚን የተባለ መድኃኒት ያዛሉ። ይሁን እንጂ የመተንፈስ ችግር ካጋጠመ ሕመሙን ለማስወገድ ተጨማሪ ሕክምና ሊያስፈልግ ይችላል። አልፎ አልፎ ደግሞ አናፍላክሲስ የተባለ ለሞት የሚዳርግ የትንፋሽ መዘጋት ችግር ያጋጥማል።
አንድ ሕፃን ማስመለስ ከጀመረ ጋላክቶሴሚያ የተባለ ብዙ ጊዜ የማያጋጥም አሳሳቢ የጤና መታወክ ደርሶበት ይሆናል። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ጋላክቶስ ከላክቶስ ተለይቶ የሚወጣው ላክተስ በተባለው ኢንዛይም አማካኝነት ቢሆንም ጋላክቶስ የግድ ወደ ግሉኮስ መቀየር ይኖርበታል። የጋላክቶስ ክምችት ከተፈጠረ ከባድ የጉበት መጎዳት፣ የኩላሊት ቅርጽ መበላሸት፣ የአእምሮ ዝግመት፣ የስኳር እጥረትና ዓይን በሞራ መሸፈን ሊያጋጥም ይችላል። ስለዚህ ችግሩ ሳይባባስ ሕፃኑን ፈጽሞ ላክቶስ ያለው ምግብ አለመመገብ በጣም አስፈላጊ ነው።
የላክቶስ አለመስማማት ለሕይወት አስጊ ነው?
አንዲት ወጣት ሥር የሰደደ የጋዝ መብዛትና ሆድ ቁርጠት ያሰቃያት ነበር። ሕመሟ እየተባባሰ በመምጣቱ ሕክምና መከታተል ጀመረች። በርካታ ምርመራዎች ከተደረጉላት በኋላ ኢንፍላማቶሪ ባወል ዲዚዝ የተባለ የአንጀት በሽታ እንዳለባት ተነገራት። * በሽታውን ለማዳን የሚያስችል መድኃኒት ታዘዘላት። ይሁን እንጂ በየቀኑ የምትመገባቸውን የወተት ተዋጽኦዎች ስላላቆመች በሽታው ሊወገድላት አልቻለም። የችግሩን መንስኤ ለማወቅ በግሏ ጥረት ካደረገች በኋላ ችግሯ ከምትመገባቸው ምግቦች የመነጨ ሊሆን እንደሚችል ተገነዘበች። በመሆኑም የትኛው እንደሆነ ለማወቅ አንዳንድ ምግቦችን መመገብ አቆመች። በመጨረሻም የወተት ተዋጽኦዎችን መመገብ ተወች፤ በሽታውም ቀስ በቀስ እየለቀቃት መጣ። አንድ ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ተጨማሪ ምርመራዎች ካደረገች በኋላ ሐኪምዋ በሽታው እንደለቀቃት ነገራት። ችግሯ የላክቶስ አለመስማማት ነበር። ምን ያህል እፎይ እንዳለች ልትገምት ትችላለህ!
እስከዛሬ ድረስ ሰውነት ብዙ ላክተስ እንዲያመነጭ የሚያደርግ ሕክምና አልተገኘም። ይሁን እንጂ የላክቶስ አለመስማማት ለሞት እንደማያደርስ በጥናት ተረጋግጧል። ታዲያ የላክቶስ አለመስማማት ችግሮችን ለመቋቋም ምን ማድረግ ይቻላል?
አንዳንዶች በራሳቸው ላይ ተደጋጋሚ ሙከራ በማድረግ ሰውነታቸው ሊቀበል የሚችለውን የወተት ተዋጽኦ መጠን ማወቅ ችለዋል። የተመገብከውን የወተት ተዋጽኦ መጠንና ሰውነትህ የሚሰጠውን ምላሽ በጥንቃቄ በመከታተል ሰውነትህ ሊያዋህደው የሚችለው የወተት ተዋጽኦ መጠን ምን ያህል እንደሆነ ማወቅ ትችላለህ።
አንዳንዶች የወተት ተዋጽኦዎችን ሙሉ በሙሉ መተው እንደሚሻላቸው ወስነዋል። አንዳንዶች ሰውነታቸውን በማዳመጥ ወይም የሥነ ምግብ ባለሞያ በማማከር ለሰውነታችን የሚያስፈልገው የካልስየም ፍጆታ ሊሟላ የሚችልባቸውን ሌሎች መንገዶች አግኝተዋል። አንዳንድ አረንጓዴ አትክልቶችና የዓሣ ዝርያዎች እንዲሁም የቅባት እህሎች ከፍተኛ የካልስየም መጠን አላቸው።
የወተት ተዋጽኦዎችን ጨርሶ መተው ለማይሆንላቸው ደግሞ በእንክብል ወይም በፈሳሽ መልክ የሚወሰዱ መድኃኒቶች ማግኘት ይችላሉ። እነዚህ መድኃኒቶች አንጀት ላክቶስን ወደ ስኳር እንዲቀይር የሚረዳው ላክተስ የተባለ ኢንዛይም አላቸው። እነዚህን መድኃኒቶች መውሰድ የላክቶስ አለመስማማት የሚያስከትለውን ችግር ሊያስወግድ ይችላል።
በዚህ ዓለም ጤንነትን ጠብቆ መኖር ከባድ ችግር ሆኗል። ይሁን እንጂ “‘ታምሜአለሁ’ የሚል” ሰው የማይኖርበት ጊዜ እስከሚመጣ ድረስ በሕክምና እርዳታና ሰውነታችን ባለው በሽታ የመቋቋም ችሎታ እየታገዝን እነዚህን የጤና እክሎች ተቋቁመን መኖር እንችላለን።—ኢሳይያስ 33:24፤ መዝሙር 139:14
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.7 የሰውነት መቆጣት ማለት ነው።
^ አን.15 ሁለት ዓይነት የኢንፍላማቶሪ ባወል ዲዚዝ ችግሮች አሉ። ክሮንስ ዲዚዝ እና አልሰረቲቭ ከላይተስ ይባላሉ። አንድ ሰው በእነዚህ ከባድ የበሽታ ዓይነቶች የሚጠቃ ከሆነ የተወሰነ የአንጀት ክፍል ቆርጦ ማውጣት ሊያስፈልግ ይችላል። ኢንፍላማቶሪ ባወል ዲዚዝ ሥር ሰድዶ ሌላ ችግር ካስከተለ ለሞት ሊዳርግ ይችላል።
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
እነዚህም ላክቶስ ሊኖርባቸው ይችላል:-
▪ ዳቦና የዳቦ ተዋጽኦዎች
▪ ኬክና ብስኩት
▪ ከረሜላዎች
▪ ተዘጋጅቶ የሚሸጥ የድንች ዱቄት
▪ ማርጋሪን
▪ በሐኪም ትእዛዝ የሚወሰዱ መድኃኒቶች
▪ አለሐኪም ትእዛዝ የሚወሰዱ መድኃኒቶች
▪ ብስኩትና ኬክ ለመጋገር የተዘጋጁ የተቀመሙ ዱቄቶች
▪ በማሽን የተዘጋጁ ለቁርስ የሚቀርቡ የእህል ዘሮች
▪ የሰላጣ ማጣፈጫዎች
▪ የሥጋ ውጤቶች
▪ ሾርባዎች