በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የብቸኝነትን ስሜት መቋቋም

የብቸኝነትን ስሜት መቋቋም

የብቸኝነትን ስሜት መቋቋም

ብቸኝነትን ስሜት መቋቋም ቀላል ነገር አይደለም። የሚያስከትለው የስሜት መረበሽ በጣም ከባድ ነው። አንድ ሰው የብቸኝነትን ስሜት እንዴት መቋቋም ይችላል? አንዳንዶች ይህን ከባድ ስሜት ለመቋቋም ምን አድርገዋል?

ብቸኝነትን መቋቋም

ሄለን * አንዳንድ ውሳኔዎችን በምታደርግበት ጊዜ ብቻዋን መሆን የምትፈልግ ቢሆንም ብቸኝነት አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ይሰማታል። ልጅ ሳለች ከወላጆቿ ጋር እምብዛም አትግባባም ነበር። የእነርሱን ትኩረት ማግኘት ስላልቻለች በሯን ዘግታ ክፍሏ ውስጥ ብቻዋን ትቀመጥ ነበር። እንዲህ በማለት ትናገራለች:- “ምግብ አልበላ አለኝ። ከባድ ጭንቀት አደረብኝ። ‘ወላጆቼ ስለእኔ ችግር ደንታ እስከሌላቸው ድረስ እኔስ ስለ እነርሱ ችግር ምን አሳሰበኝ?’ ማለት ጀመርኩ። ከዚያም ጋብቻ ብቸኝነት የፈጠረብኝን ክፍተት ይዘጋልኝ ይሆናል ብዬ አሰብኩ። ማምለጫ ይሆነኛል ብዬ ስላሰብኩ ለማግባት ፈለግኩ። ይሁን እንጂ ወዲያው ‘ለምን የሌላ ሰው ሕይወት አበላሻለሁ? ከዚያ በፊት የራሴን አስተሳሰብ ማስተካከል አለብኝ!’ ብዬ አሰብኩ። ጭንቀቴን በሙሉ ለይሖዋ በጸሎት በመግለጽ እንዲረዳኝ ለመንኩት።

“በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በኢሳይያስ 41:10 ላይ እንደሚገኘው ያሉትን የሚያጽናኑ ቃላት አገኘሁ። ‘እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ። አበረታሃለሁ፤ እረዳሃለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ’ ይላል። አባት እንደሌለኝ ይሰማኝ ስለነበረ እነዚህ ቃላት በጣም ረዱኝ። አሁን መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትሬ አነባለሁ እንዲሁም ወደ ሰማዩ አባቴም እጸልያለሁ። ብቸኝነቴን ማሸነፍ አውቄያለሁ።”

የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት ሐዘን ያስከትላል። ይህ ደግሞ የብቸኝነት ስሜት ሊያሳድር ይችላል። የ16 ዓመቷ ሉዊዛ የደረሰባትን መከራ እንዲህ በማለት ትገልጻለች:- “አባቴ የተገደለብኝ ገና የአምስት ዓመት ልጅ ሳለሁ ነበር። አያቴ ታጽናናኛለች ብዬ አስቤ ነበር። ይሁን እንጂ የምትወደኝ ሆና አላገኘኋትም። ፍቅር ማግኘት በጣም እፈልግ በነበረበት የልጅነት ዕድሜዬ ፍቅር አላገኘሁም። በስምንትና በዘጠኝ ዓመት ዕድሜዬ ሦስት ጊዜ ራሴን ለመግደል ሞክሬያለሁ። እናቴ ለእኔና ለሦስት እህቶቼ የዕለት ጉርስ ለማግኘት ብዙ ትለፋ ስለነበረ የእኔ መሞት ለቤተሰቤ የተሻለ እንደሚሆን ይሰማኝ ነበር። ከዚያም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘት ጀመርን። አንድ ወጣት ባልና ሚስት ከልብ አቀረቡኝ። ‘እንወድሻለን፣ ደግሞም በጣም እንፈልግሻለን’ ይሉኝ ነበር። ‘እንፈልግሻለን’ የሚለው ቃል ልዩ ብርታት ሰጠኝ። አንዳንድ ጊዜ ስሜቴን ለሌላ ሰው መግለጽ ያቅተኛል። በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! ላይ የሚወጡትን ርዕሶች ሳነብ ግን ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። ይሖዋ እንደሚወደኝ ሊሰማኝ የቻለው በእነዚህ ጽሑፎች አማካኝነት ነው። ብዙ ለውጥ አድርጌያለሁ። ዛሬ ፈገግ ማለት እችላለሁ። ሐዘኔንም ሆነ ደስታዬን ለእናቴ መግለጽ እችላለሁ። የቀድሞ ሁኔታዬ ትዝ የሚለኝ ጊዜ ቢኖርም ራሴን ለመግደል እንደሞከርኩበት ወይም ቤተሰቦቼን በሙሉ እንዳኮረፍኩበት ወቅት ያለ ስሜት አይሰማኝም። ሁልጊዜ መዝሙራዊው ዳዊት የተናገረው ትዝ ይለኛል:- ‘ስለ ወንድሞቼና ስለ ባልንጀሮቼ፣ “በውስጥሽ ሰላም ይስፈን” እላለሁ።’”—መዝሙር 122:8

ማርታ ከባሏ ከተፋታች 22 ዓመት ሆኗታል። ልጆቿን ያሳደገችውም ብቻዋን ነው። “ያልተሳካልኝ ነገር እንዳለ ሳስብ የከንቱነትና የብቸኝነት ስሜት ይሰማኛል” ትላለች። ይህን ስሜቷን የምትቋቋመው እንዴት ነው? እንዲህ በማለት ትገልጻለች:- “ከሁሉ የተሻለ ሆኖ ያገኘሁት ቶሎ ብዬ ይህን ስሜቴን ለይሖዋ አምላክ መናገር ነው። ስጸልይ ብቻዬን እንዳልሆንኩ ይሰማኛል። ይሖዋ እኔ ራሴን ከምረዳው በላይ ይረዳኛል። በተጨማሪም ለሌሎች መልካም ነገር የማደርግበትን አጋጣሚ እፈልጋለሁ። እንደነዚህ ያሉትን አሉታዊ ስሜቶች ለማሸነፍ የሙሉ ጊዜ አገልግሎቴ በጣም ኃይለኛ መሣሪያ ሆኖልኛል። የአምላክ መንግሥት ስለሚያመጣቸው በረከቶች ለሰዎች ስትናገርና አድማጮችህ ያጋጠማቸው ችግር ዘላቂ እንደሆነ እንጂ ምንም ዓይነት ተስፋ እንደማይታያቸው ስትገነዘብ ከችግርህ ጋር እየታገልክ ለመኖር የሚገፋፋህ ጠንካራ ምክንያት እንዳለህ ይሰማሃል።”

በባዕድ አገር በሚስዮናዊነት የምታገለግል አንድ ልጅ ብቻ ያለቻቸው የ93 ዓመቷ ኤልባ ብቸኝነታቸውን እንዴት ሊቋቋሙ እንደቻሉ ይነግሩናል:- “ሴት ልጄና ባለቤቷ ሚስዮናውያን በሚሠለጥኑበት የጊልያድ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ግብዣ ሲቀርብላቸውና በጣም ሲደሰቱ እኔም አብሬ ተደሰትኩ። በባዕድ አገር እንዲያገለግሉ ሲመደቡ ግን ትንሽ የራስ ወዳድነት ስሜት ተሰማኝ። በቅርቤ ላገኛቸው እንደማልችል ስላወቅኩ አዘንኩ። በመሳፍንት ምዕራፍ 11 ላይ እንደተገለጸው ዮፍታሔና አንድ ልጁ ያጋጠማቸው ዓይነት ሁኔታ የደረሰብኝ መሰለኝ። ይሖዋ ይቅር እንዲለኝ እያለቀስኩ ለመንኩት። የልጆቼ ወሬ ሁልጊዜ ርቆኝ አያውቅም። ሥራ እንደሚበዛባቸው ባውቅም የትም ቢያገለግሉ ደኅንነታቸውንና በመስክ አገልግሎት ያጋጠማቸውን ተሞክሮ ይጽፉልኛል። ደብዳቤያቸውን ደግሜ ደጋግሜ አነበዋለሁ። በየሳምንቱ አጠገቤ ሆነው እንደሚያነጋግሩኝ ያህል ነው። ለዚህም በጣም አመሰግናቸዋለሁ። በተጨማሪም በጉባዔያችን ያሉ ሽማግሌዎች ለእኛ ለአረጋውያንና ለአቅመ ደካሞች ብዙ ትኩረት ይሰጣሉ። ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች የሚያደርሰን መጓጓዣ መኖሩንና ሌሎች ፍላጎቶቻችን መሟላታቸውን ይከታተላሉ። መንፈሳዊ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ከይሖዋ እንደተሰጡ በረከቶች እቆጥራቸዋለሁ።”

አንተም ብቸኝነትን መቋቋም ትችላለህ

ወጣትም ሆንክ አረጋዊ፣ ነጠላም ሆንክ ባለትዳር፣ ወላጆች ኖሩህም አልኖሩህ፣ የቅርብ ዘመዶችህን በሞት ያጣህም ሆንክ ሌላ ዓይነት ብቸኝነት ያጋጠመህ ስሜትህን ለመቋቋም የሚረዱህ መንገዶች አሉ። አባቷ ስድስት ቤተሰቦቹን እርግፍ አደርጎ ወደ ሌላ አገር የሄደባት የ18 ዓመቷ ዮካቤድ እንዲህ ትላለች:- “አውጥተህ ተናገር! ስሜታችንን መግለጻችን በጣም አስፈላጊ ነው። ካልተናገርን ማንም ችግራችንን ሊረዳልን አይችልም።” “ስለራስህ ብዙ አታስብ። ካንተ የባሰ ችግር ሊኖርባቸው የሚችሉትን ወጣቶች ሳይሆን የጎለመሱ ሰዎችን እንዲረዱህ ጠይቅ” በማለት ጨምራ ትመክራለች። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሉዊዛ ደግሞ “ለይሖዋ ከልብ መጸለይ በጣም ይረዳል። ዙሪያው ገደል ሲሆንብን መውጫውን ያሳየናል” ትላለች። ሚስቱን በሞት ያጣው ኮርከ ብቸኝነቱን እንዴት እንደተቋቋመ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “መንፈሰ ጠንካራነት በጣም ያስፈልጋል። ለሌሎች አሳቢ መሆን በጣም ይረዳኛል። ከሌሎች ጋር በምንነጋገርበት ጊዜ አሳቢነት ማሳየታችን ጭውውቱን ትርጉም ያለው እንዲሆን ከማድረጉም በላይ የሌሎችን መልካም ባሕርያት እንድናይ ያስችለናል።”—1 ጴጥሮስ 3:8

ብቸኝነትን ለመቋቋም ብዙ ሊደረጉ የሚችሉ ነገሮች አሉ። ይሁን እንጂ ብቸኝነት ፈጽሞ የሚረሳበትና የማይኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? ከሆነስ ይህ የሚፈጸመው እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 አንዳንዶቹ ስሞች ተለውጠዋል።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ለይሖዋ ከልብ መጸለይ በጣም ይረዳል። ዙሪያው ገደል ሲሆንብን መውጫውን ያሳየናል።”—ሉዊዛ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

የብቸኝነትን ስሜት ለማሸነፍ ልታደርግ የምትችላቸው ነገሮች

▪ የአንተ ሁኔታ ፈጽሞ ሊለወጥ የማይችል እንደሆነ አድርገህ አታስብ፤ ደግሞም አንተ ብቻ ሳትሆን ሌሎችም እንዲህ እንደሚሰማቸው አስታውስ።

▪ ከልክ በላይ ከራስህ አትጠብቅ።

▪ በማንኛውም ረገድ ባለህ የምትረካ ሁን።

▪ ጥሩ የአመጋገብና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ልማድ አዳብር፤ በቂ እንቅልፍ ተኛ።

▪ ብቻህን የምትሆንባቸውን ጊዜያት አንዳንድ የፈጠራ ሥራዎችን ለመሥራትና አዳዲስ ክህሎቶችን ለማዳበር ተጠቀምባቸው።

▪ ከዚህ ቀደም የገጠመህን ሁኔታ በማሰብ ሰውን ሁሉ በአንድ እንዳትፈርጅ ተጠንቀቅ።

▪ ለጓደኞችህና ላሏቸው መልካም ባሕርያት አድናቆት ይኑርህ። ምንጊዜም ውሎህ ከጥሩ ጓደኞች ጋር እንዲሆን ጥረት አድርግ። ከትላልቆችና ተሞክሮ ካላቸው ምክርና አስተያየት ጠይቅ።

▪ ለሌሎች መልካም ነገር ለማድረግ ጣር፤ ፈገግታ ማሳየት፣ የደግነት ቃል መሰንዘር ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘኸውን ሐሳብ ማካፈል ትችላለህ። በሌሎች ዘንድ ተፈላጊ እንደሆንክ ማወቅ የብቸኝነትን ስሜት ለማሸነፍ የሚረዳ ፍቱን መድኃኒት ነው።

▪ የፊልም ወይም የቴሌቪዥን ኮከቦችን ወይም በተለያዩ መጻሕፍት ላይ የተገለጹ ገጸ ባሕርያትን በማፍቀር ሁሌ ስለ እነሱ ከማለም ተቆጠብ።

▪ ባለትዳር ከሆንክ የትዳር ጓደኛህ ስሜታዊ ፍላጎቶችህን ሁሉ እንድታሟላልህ አትጠብቅ። መስጠትንና መቀበልን እንዲሁም እርስ በርስ መረዳዳትን ተማር።

▪ ሐሳብህን ለሌሎች መናገርንም ሆነ ሌሎች ሲናገሩ በጥሞና ማዳመጥን ተማር። ለሌሎች ሰዎች ከልብ የምትጨነቅና አሳቢ ሁን።

▪ ብቸኝነት እንደሚሰማህ አምነህ ተቀበል፤ ይህን ስሜትህን ለምታምነው የጎለመሰ ወዳጅህ አዋየው። በውስጥህ ይዘህ አትብሰልሰል።

▪ ከመጠን በላይ አትጠጣ፤ ወይም እስከ ጭራሹ ከአልኮል መጠጥ ራቅ። የአልኮል መጠጥ ችግርህን አያስወግድልህም፤ ለጊዜው የተወገደልህ ቢመስልህ እንኳ ተመልሰህ ራስህን የምታገኘው እዚያው ነው።

▪ ትሁት ሁን። የበደሉህን ሰዎች ይቅር በል፤ እንዲሁም ከእነሱ ጋር ያለህን ግንኙነት ለማሻሻል የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ። በጣም ተጠራጣሪ አትሁን።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ሰው የብቸኝነትን ስሜት እንዴት መቋቋም ይችላል?