በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጓደኛዬ የሚፈጽምብኝን አግባብ ያልሆነ ድርጊት ማስተው የምችለው እንዴት ነው?

ጓደኛዬ የሚፈጽምብኝን አግባብ ያልሆነ ድርጊት ማስተው የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

ጓደኛዬ የሚፈጽምብኝን አግባብ ያልሆነ ድርጊት ማስተው የምችለው እንዴት ነው?

“ጓደኛዬ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ መታኝ። ይቅርታ ቢጠይቀኝም ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግን ግራ ገብቶኛል።”—ሽቴላ *

ዘ ጆርናል ኦቭ ዚ አሜሪካን ሜዲካል አሶሲዬሽን በተባለው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ “በግምት ከአምስት ሴት ተማሪዎች መካከል አንዷ በወንድ ጓደኛዋ አካላዊ ወይም ጾታዊ አሊያም ሁለቱንም ዓይነት ጥቃት እንደተሰነዘረባት ሪፖርት አድርጋለች” ሲል ዘግቧል። ጀርመን ውስጥ ከ17 እስከ 20 ዓመት ዕድሜ ባላቸው ወጣቶች ላይ በተካሄደ ጥናት ከአንድ አራተኛ በላይ የሚሆኑት ልጃገረዶች የወንድ ጓደኞቻቸው በኃይል በመጠቀም፣ በማባበልና በማስፈራራት እንዲሁም አደገኛ ዕፆችን ወይም የአልኮል መጠጦችን እንዲወስዱ በማድረግ ሳይፈልጉ የጾታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ እንዳስገደዷቸው ተናግረዋል። በዩናይትድ ስቴትስ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው በጥናቱ ከተካፈሉት ወጣቶች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት አብረዋቸው የሚማሩትን ልጆች “የወንድ ጓደኞቻቸው ስሜት በሚነካ መንገድ ሲሰድቧቸው” መመልከታቸውን ሪፖርት አድርገዋል። *

ልታገቢው ያሰብሽው ሰው በመሳደብ፣ በቁጣ በማንባረቅ፣ በማንቋሸሽ አሊያም በመገፍተርና በጥፊ በመማታት ሥነ ልቦናዊና አካላዊ ጥቃት ያደርስብሻል? ከዚህ ቀደም በዚህ ዓምድ ሥር በወጣ ርዕስ ላይ እንደዚህ ያለው አግባብ ያልሆነ ድርጊት በብዙዎች ዘንድ የተለመደ እንደሆነ ተገልጿል። * ከዚህም በላይ አምላክ በንግግርም ሆነ በድርጊት በሌሎች ላይ ጥቃት መሰንዘርን እንደሚጠላና የዚህ ዓይነት ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ሁኔታውን በዝምታ መቀበልም ሆነ ችግሩን እነርሱ ያመጡት እንደሆነ አድርገው ማሰብ እንደማይኖርባቸው ተገልጾ ነበር። (ኤፌሶን 4:31) ያም ሆኖ ግን የዚህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥምሽ ምን ማድረግ እንዳለብሽ አታውቂ ይሆናል። እንደዚህ ዓይነት አስቸጋሪ ባሕርይ እያለውም ጓደኛሽን ትወጂው ይሆናል። ከዚያ የባሰው ደግሞ ጥፋቱን አንስተሽ ብትወቅሺው የሚሰጠውን ምላሽ ልትፈሪ ትችያለሽ። ታዲያ ምን ማድረግ ይኖርብሻል?

ሁኔታውን መርምሪ

በቅድሚያ ራስሽን አረጋግተሽ ምን እንደተፈጠረ በጥሞና ለማገናዘብ ሞክሪ። (መክብብ 2:14) ጓደኛሽ ስሜትሽን የሚጎዳ ነገር የተናገረው ሆን ብሎ በተንኮል ነው ወይስ ሳያስብ ‘በግዴለሽነት’ ያደረገው ነገር ነው? (ምሳሌ 12:18) እንዲህ ሲያደርግ የመጀመሪያው ነው? በይቅርታ ልታልፊው የምትችይው አንድ ጊዜ የተፈጠረ ስሕተት ነው ወይስ ጓደኛሽ ማንቋሸሽና መሳደብ ልማድ ሆኖበታል?

ለእነዚህ ጥያቄዎች ምን መልስ እንደምትሰጪ እርግጠኛ መሆን ካልቻልሽ ስለ ጉዳዩ ከአንድ ሰው ጋር ተወያዪበት፤ ሆኖም የምታማክሪው እኩዮችሽን ሳይሆን ጥበብ ያዘለ ሐሳብ ሊሰጥሽ የሚችል ትልቅ ሰው መሆን አለበት። ምናልባትም ወላጆችሽን ወይም አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ልታናግሪ ትችያለሽ። እንደዚህ ማድረግሽ ችግሩ በእርግጥ አሳሳቢ ይሁን ወይም አንቺ አጋንነሽ ተመልክተሽው እንደሆነ ለማወቅ ይረዳሻል።

ምንም ችግር እንደማያስከትል ከተሰማሽ ስለ ሁኔታው ጓደኛሽን አነጋግሪው። (ምሳሌ 25:9) እንደዚህ ያለ ባሕርይ ሲያሳይ ምን እንደሚሰማሽ ረጋ ብለሽ ንገሪው። ቅር ያሰኘሽን ነገር ጠቅሰሽ በትዕግሥት ልታልፊያቸው የማትችያቸውን ነገሮች በግልጽ ተናገሪ። ስሜትሽን ስትነግሪው ምን ምላሽ ሰጠሽ? ሐሳብሽን ያናንቀዋል ወይም ይበልጥ ይቆጣል? እንደዚህ ካደረገ ለመለወጥ እንደማይፈልግ የሚያሳይ የማያሻማ ምልክት ነው።

በትሕትና ጥፋቱን አምኖ ከተቀበለና ከልቡ ከተፀፀተስ? ግንኙነታችሁ እንዲቀጥል ማድረግ ይቻል ይሆናል። ሆኖም መጠንቀቅ ይኖርብሻል። ሌሎችን የሚጎዳ ነገር የመናገር ልማድ ያላቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ የተፀፀቱ ለማስመሰል የሽንገላ ቃላት የሚደረድሩ ቢሆንም የሚያበሳጫቸው ነገር ሲገጥማቸው መልሰው ስድብና ትችት መሰንዘራቸው አይቀርም። ለውጥ ለማድረግ የተነሳሳው ከልቡ መሆን አለመሆኑን ጊዜ የሚያሳየው ይሆናል። ጉዳዩን በቁም ነገር እንዳሰበበት የሚጠቁመው አንዱ ፍንጭ የክርስቲያን ሽማግሌዎችን እርዳታ ለማግኘት ፈቃደኛ መሆኑ ነው።—ያዕቆብ 5:14-16

“ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል” የሚለውን ጥቅስ አስታውሺ። (ሮሜ 3:23) ፍጹም ሰው አገኛለሁ ብለሽ በከንቱ አትድከሚ። ያገቡ ሰዎች ሁሉ ፍጹማን ባለመሆናቸው በተወሰነ መጠን “ችግር ይገጥማቸዋል።” (1 ቆሮንቶስ 7:28) በዚህም ሆነ በዚያ ያሉበትን ድክመቶች ተቀብለሽ በደስታ አብረሽው መኖር ትችይ እንደሆነና እንዳልሆነ መወሰን ያስፈልግሻል። እንደዚህ ያለውን ውሳኔ ለማድረግም ቢሆን ለተወሰነ ጊዜ መቆየትና ሁኔታዎችን ማየቱ የተሻለ ነው።

አካላዊ ጥቃት ቢሰነዝርብሽስ?

ይሁን እንጂ ጓደኛሽ ከመሳደብም አልፎ በንዴት ጸያፍ ነገር የሚናገር ወይም የሚዝትብሽ አሊያም በመገፍተርና በጥፊ በመማታት አካላዊ ጥቃት የሚሰነዝርብሽ ከሆነ ሁኔታው የተለየ ይሆናል። ይህ ራሱን የመቆጣጠር ከፍተኛ ችግር እንዳለበት የሚጠቁም ነው፤ ጓደኛሽ ከዚህ የከፋ የኃይል ድርጊት ወደ መፈጸምም ሊያመራ ይችላል።

መጀመሪያውኑም ቢሆን ያልተጋቡ ወንድና ሴት ሰው በሌለበት ቦታ ብቻቸውን ባይሆኑ ጥሩ ነው። ሆኖም ግልፍተኛ ከሆነ ሰው ጋር በሆነ አጋጣሚ ብቻሽን ብትሆኚ ‘ክፉን በክፉ አትመልሺ።’ (ሮሜ 12:17) “የለዘበ መልስ ቁጣን ያበርዳል፤ ክፉ ቃል ግን ቁጣን ይጭራል” የሚለውን ጥቅስ አስታውሺ። (ምሳሌ 15:1) ለመረጋጋት ሞክሪ። ወደ ቤትሽ መሄድ እንደምትፈልጊ ንገሪው። አስፈላጊ ከሆነም ጥለሽው ሂጂ ወይም ሮጠሽ አምልጪ!

የጾታ ግንኙነት እንድትፈጽሙ ሊያስገድድሽ ቢሞክርስ? በእርግጥ፣ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ገና መጠናናት ሲጀምሩ አንስቶ ፍቅራቸውን በሚገልጹበት መንገድ ረገድ ገደብ ማበጀታቸው አስፈላጊ ነው። (1 ተሰሎንቄ 4:3-5) አንድ ወጣት አንዲትን ሴት የመጽሐፍ ቅዱስን ሥርዓት እንድትጥስ ሊያስገድዳት ከሞከረ በምንም ዓይነት ፈቃደኛ እንደማትሆን በማያወላውል መንገድ ልትገልጽለት ይገባል። (ዘፍጥረት 39:7-13) የጾታ ግንኙነት እንድትፈጽም ለተደረገባት ግፊት የተሸነፈችው አን “በፍጹም እጃችሁን አትስጡ” የሚል ልመና አዘል ምክር ሰጥታለች። “ለራሳችሁ አክብሮት ይኑራችሁ። የቱንም ያህል ብታፈቅሩት የዚህ ዓይነት ስህተት አትፈጽሙ!” እምቢታሽን ለመስማት አሻፈረኝ ካለ ከዚያ በኋላ የሚያደርገውን ማንኛውንም ሙከራ አስገድዶ ከመድፈር ለይተሽ እንደማታይው ንገሪው። ይህም ሆኖ ከድርጊቱ ካልታቀበ እርዳታ ለማግኘት ጩኺ እንዲሁም አንድ ሰው አስገድዶ ሊደፍርሽ ቢሞክር ራስሽን ለመከላከል የምትወስጂውን እርምጃ በዚህ ወቅትም ተግባራዊ አድርጊ። *

ጓደኛሽ የኃይል ድርጊት የሚፈጽም ወይም የጾታ ግንኙነት እንድታደርጉ ሊያስገድድሽ የሚሞክር ከሆነ “ከግልፍተኛ ጋር ወዳጅ አትሁን፤ በቀላሉ ቱግ ከሚልም ሰው ጋር አትወዳጅ” የሚለውን በምሳሌ 22:24 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ ማድረጉ ይጠቅማል። አካላዊም ሆነ ሥነ ልቦናዊ ጥቃት እየተሰነዘረብሽ ግንኙነታችሁ እንዲቀጥል የማድረግ ግዴታ የለብሽም። በእርግጥ፣ እንደዚህ ላለው ሰው ግንኙነታችሁ ማብቃቱን ለመንገር ብቻሽን መሄዱ ሞኝነት ይሆናል። ልትወስጅው የምትችይው ከሁሉ የተሻለ እርምጃ ስለ ሁኔታው ለወላጆችሽ መንገር ነው። አግባብ ያልሆነ ድርጊት ስለተፈጸመብሽ ቢናደዱና ቢቆጡ ሊያስገርምሽ አይገባም። ሆኖም ምን ማድረግ እንዳለብሽ በመወሰን ረገድ ሊረዱሽ ይችላሉ። *

ግለሰቡን ለመለወጥ መሞከር

ጓደኛሽ እንዲለወጥ ማድረግ ያንቺ ኃላፊነት አይደለም። ኢሬና እንዲህ በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች:- “እንደምትወዱትና ሁኔታውን ችላችሁ መኖር እንደምትችሉ እንዲሁም እንደምትለውጡት ታስቡ ይሆናል። ሆኖም የማይቻል ነገር ነው።” ናዲንም በተመሳሳይ “ልለውጠው እችላለሁ ብዬ አስብ ነበር” ብላለች። ሐቁ ግን ‘አእምሮውን ማደስና’ ራሱን መለወጥ የሚችለው ግለሰቡ ብቻ ነው። (ሮሜ 12:2) ይህ ደግሞ ረጅምና ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ተግባር ነው።

ስለዚህ በውሳኔሽ ጽኚ፤ ሐሳብሽን ለማስቀየር በሚያደርጋቸው ሙከራዎች አትታለይ። በተቻለ መጠን ከእርሱ ጋር ስሜታዊም ሆነ አካላዊ ቅርርብ ላለመፍጠር ጥረት አድርጊ። በማባበል፣ በልመና ወይም በማስፈራራት ግንኙነታችሁን እንድትቀጥሉ ለማድረግ ቢሞክርም አትስማሚ። ኢሬና ይደበድባት ከነበረው ጓደኛዋ ጋር የነበራትን ግንኙነት ስታቆም ራሱን እንደሚገድል ዝቶ ነበር። እንደዚህ ያለው ሰው እርዳታ እንደሚያስፈልገው ግልጽ ቢሆንም የምትረጂው ግን አንቺ አይደለሽም። አንቺ ልታደርጊለት የምትችይው ከሁሉ የላቀ እርዳታ ክርስቲያናዊ ያልሆነ ባሕርዩን መቃወም ነው። መለወጥ ከፈለገ እርዳታ መጠየቅ ይችላል።

ይሁን እንጂ አንዳንዶች ጋብቻ ለችግሩ መፍትሔ እንደሆነ ያስባሉ። አንድ ተመራማሪ እንዲህ ብለዋል:- “አካላዊም ሆነ ሥነ ልቦናዊ ጥቃት የሚያደርሱባቸውን ጓደኞቻቸውን ያገቡ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ከጋብቻ በኋላም ቢሆን ሁኔታው እንዳልተለወጠ ሲመለከቱ ይገረማሉ። ብዙ ሰዎች ባልና ሚስቱ አንድ ጊዜ ከተፈራረሙ በኋላ እነዚህ ችግሮች በሙሉ ይወገዳሉ የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት ያምናሉ። እንዲህ ዓይነቱን አስተሳሰብ አትመኑ።” እውነታው እንደሚያሳየው ለጋብቻ በምትጠናኑበት ጊዜ አካላዊ ጥቃት የመሰንዘር ልማድ ካለው በአብዛኛው ከተጋባችሁ በኋላም ይቀጥላል።

መጽሐፍ ቅዱስ “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል” ይላል። (ምሳሌ 22:3) ከምትወጂው ሰው ጋር ያለሽን ግንኙነት ማቋረጥ ይከብዳል። ሆኖም በትዳር ውስጥ ጥቃት እየተሰነዘረብሽ መኖር ከዚያ የባሰ ነው። ከዚህም በላይ የሚሆነኝ የትዳር ጓደኛ አላገኝ ይሆናል ብለሽ ልትፈሪ አይገባም። ያገኘሽው ልምድ ደግ፣ ርኅሩኅና ራሱን የሚቆጣጠር ሰው ለመምረጥ ያስችልሻል።

ከደረሰብሽ የስሜት መጎዳት ማገገም

አካላዊም ሆነ ሥነ ልቦናዊ ጥቃት ጠባሳ መተዉ አይቀርም። የዚህ ዓይነት ጥቃት ሰለባ የሆነችው ሜሪ እንዲህ ብላለች:- “እርዳታ ለማግኘት ሞክሩ፤ ጊዜ ሳታጠፉ ስለ ሁኔታው ለአንድ ሰው ተናገሩ። እኔ ችግሩን በራሴ እወጣዋለሁ ብዬ አስቤ ነበር፤ ሆኖም ከሰዎች ጋር ማውራቴ ጠቅሞኛል።” ያጋጠመሽን ነገር ለወላጆችሽ፣ ለምታምኚው የጎለመሰ ወዳጅሽ ወይም ለአንድ ክርስቲያን ሽማግሌ አጫውቻቸው። *

አንዳንዶች ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን ማንበብ፣ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መሳተፍ ወይም በተለያዩ የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዎች መካፈል ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። ኢሬና “ከሁሉ በላይ የረዳኝ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ነው” በማለት ታስታውሳለች።

በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው ይሖዋ ስድብንም ሆነ አካላዊ ጥቃት መሰንዘርን ይጠላል። ከእርሱ በምታገኚው እርዳታ በመታገዝ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት እንዳይፈጸምብሽ ራስሽን መከላከል ትችያለሽ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.4 ወንዶችም ሆኑ ሴቶች የስድብ፣ የትችትና የአካላዊ ጥቃት ሰለባ ሊሆኑ የሚችሉ ቢሆንም የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል እንደገለጸው “ከወንዶች ይበልጥ ሴቶች የጎላ ጥቃት ይደርስባቸዋል።” ሆኖም ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል በዚህ ርዕስ ውስጥ ጥቃቱን የሚፈጽሙት ወንዶች እንደሆኑ ተደርጎ ተገልጿል።

^ አን.15 የሚያዝያ—ሰኔ 1994 ንቁ! ተገዶ መደፈርን መከላከል ስለሚቻልበት መንገድ ይናገራል።

^ አን.16 አስገድዶ የመድፈር ሙከራ እንደማድረግ ያሉ አንዳንድ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ወላጆችሽ ጉዳዩን ለፖሊስ ለማሳወቅ ይወስኑ ይሆናል። እንደዚህ ማድረጋቸው ግለሰቡ በሌሎች ወጣቶች ላይም ተመሳሳይ ነገር እንዳይፈጽም ለመከላከል ያስችላል።

^ አን.23 ከባድ የስሜት ቀውስ ያጋጠማቸው ሰዎች የሐኪም ወይም የሥነ ልቦና ባለሞያ እርዳታ ይሹ ይሆናል።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለጋብቻ በምትጠናኑበት ጊዜ ሥነ ልቦናዊና አካላዊ ጥቃት የመሰንዘር ልማድ ካለ ከተጋባችሁ በኋላም ሊቀጥል ይችላል

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ተገቢ ባልሆኑ የፍቅር መግለጫዎች እንድትካፈዪ ሊያስገድድሽ ቢሞክር እጅ አትስጪ