‘ምን እየሆንኩ ነው?’
‘ምን እየሆንኩ ነው?’
“አንድ ቀን ከእንቅልፌ ስነሳ ሁሉ ነገር ተለዋውጦ የጠበቀኝ ያህል ነበር። ፈጽሞ ሌላ ሰው የሆንኩ ሆኖ ተሰማኝ።”—ሳም
ጉርምስና ምንድን ነው? በቀላሉ ለመግለጽ በልጅነትና በጉልምስና ዕድሜ መካከል የሚገኝ የሕይወት ክፍል ነው። በአካል፣ በስሜትና በማኅበራዊ ግንኙነት ሳይቀር በጣም ጉልህ የሆነ ለውጥ የሚካሄድበት ወቅት ነው። በአንድ በኩል ወደ ጉርምስና ዕድሜ መግባት በጣም የሚያጓጓ ነገር ነው። ሙሉ ሰው ወደ መሆን እየተሸጋገርክ ነው ማለት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አዳዲስ ስሜቶች ብቅ ማለት የሚጀምሩበት የዕድሜ ክፍል ከመሆኑም በላይ አንዳንዶቹ ስሜቶች ግራ የሚያጋቡና እንዲያውም የሚያስፈሩ ሊሆኑ ይችላሉ።
ይሁን እንጂ ጉርምስና ገና ከሩቁ የሚያስፈራህ ነገር መሆን የለበትም። የሚያስከትላቸው ጭንቀቶች እንደሚኖሩ አይካድም። ቢሆንም ወደ ጎልማሳነት ዕድሜ የሚያሸጋግርህ ግሩም አጋጣሚ የምታገኝበት አስደሳች የዕድሜ ክፍል ሊሆን ይችላል። እንዴት ይህን ማድረግ እንደሚቻል ለመመልከት በመጀመሪያ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች አንዳንዶቹን እንመልከት።
የጉርምስና አጀማመር
በጉርምስና ዕድሜ አካልህ ለመዋለድ ሂደት ዝግጁ እንዲሆን የሚያስችሉ ለውጦች በሰውነትህ ውስጥ ይካሄዳሉ። እነዚህ ለውጦች ዓመታት ሊፈጁ የሚችሉ ሲሆን በኋላ ላይ እንደምንመለከተው በመራቢያ አካላት ብቻ ተወስነው የሚቀሩ አይደሉም።
ልጃገረዶች መጎርመስ የሚጀምሩት ከ10 እስከ 12 ዓመት ዕድሜ ላይ ሲሆን ወንድ ልጆች ደግሞ ከ12 እስከ 14 ዓመት ባለው ዕድሜ ነው። ይሁን እንጂ ይህ አኃዝ አማካይ አኃዝ ብቻ ነው። ዘ ኒው ቲንኤጅ ቦዲ ቡክ እንደሚለው ከሆነ “እያንዳንዱ ግለሰብ የተለያዩ የጉርምስና
ለውጦች የሚካሄዱበትን ዕድሜ የሚወስን የራሱ የሆነ ልዩ ባዮሎጂያዊ የጊዜ መቁጠሪያ አለው።” በማከልም “የጉርምስና ዕድሜ የሚጀምርበትን ጊዜ በተመለከተ በግለሰቦች መካከል ያለው ልዩነት በጣም የሰፋ ነው” ይላል። ስለዚህ ከእኩዮችህ ቀደም ብለህ ወይም ዘግይተህ የጉርምስና ምልክት ቢታይብህ አንድ ዓይነት ጉድለት አለብህ ማለት አይደለም።መጎርመስ የጀመርከው መቼም ይሁን መቼ በአካልህ፣ በስሜትህና በአካባቢህ ላለው ዓለም ባለህ አመለካከት ላይ ለውጥ ማስከተሉ አይቀርም። በዚህ ልዩ የሆነ የዕድሜ ክፍል ከሚታዩት አስደሳች፣ ግን ተፈታታኝ ገጽታዎች መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት።
‘ሰውነቴ ምን እየሆነ ነው?’
ጉርምስና በሚጀምርበት ጊዜ በሴቶች ኢስትሮጅን፣ በወንዶች ደግሞ ቴስቶስትሮን የተባለው ሆርሞን መጠን ይጨምራል። በዚህ ዕድሜ ተአምራዊ የሚመስል የአካል ለውጥ የሚከሰተው በከፊል በሆርሞን ለውጥ ምክንያት ነው። እንዲያውም ጉርምስና ከጀመረህ በኋላ ሰውነትህ ከሕፃንነትህ ወዲህ ሆኖ በማያውቅ ፍጥነት ያድጋል።
በዚህ ጊዜ ላይ የመራቢያ አካላትህ መጎልመስ ይጀምራሉ። ይሁን እንጂ ይህ የአካላዊ እድገትህ አንዱ ገጽታ ብቻ ነው። በተጨማሪም ቁመትህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊጨምር ይችላል። ይህም መመንደግ ይባላል። በሕፃንነትህ በዓመት 5 ሳንቲ ሜትር ያህል ቁመት የምትጨምር ቢሆን በጉርምስና ዕድሜህ ግን የዚህን እጥፍ ማለትም በዓመት 10 ሳንቲ ሜትር ያህል ልታድግ ትችላለህ።
በዚህ ወቅት ሰውነትህ እንደልብ እንደማይታዘዝልህ ሆኖ ሊሰማህ ይችላል። ይህም እንግዳ ነገር አይደለም። የተለያዩ የሰውነትህ ክፍሎች በተለያየ ፍጥነት እያደጉ ሊሆን እንደሚችል አትዘንጋ። በዚህ ምክንያት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሰውነትህ ቅርፍፍ ሊልብህ ይችላል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚያጋጥም ሁኔታ የሚያልፍ ነገር ስለሆነ ተስፋ አትቁረጥ።
በጉርምስና ወቅት ሴቶች የወር አበባ ማየት ይጀምራሉ። በየወሩ ከማህፀን የሚወጡ ፈሳሾች የተቀላቀሉበት ደም ይፈሳቸዋል ማለት ነው። * የወር አበባ በሚታይበት ጊዜ ቁርጠትና የሆርሞን መጠን መቀነስ ይኖራል። ይህም በሰውነትና በስሜት ላይ ተጽዕኖ ስለሚኖረው ሊረበሹ ይችላሉ። ባሁኑ ጊዜ 17 ዓመት የሆናት ቴሬሳ “ይህን ሁሉ አዲስ ነገር ድንገት በአንድ ጊዜ ማስተናገድ ነበረብኝ” በማለት ታስታውሳለች። “ስሜቴ ከመረበሹም በላይ ሕመም ነበረኝ። ከዚህም በላይ በየወሩ የሚደጋገም ነገር ነው!”
የወር አበባ መታየት መጀመሩ ምንም የሚያስፈራ ነገር የለውም። ሰውነትሽ ትክክለኛ ተግባሩን በማከናወን ላይ እንዳለ የሚያሳይ ምልክት ነው። ከጊዜ በኋላ ከወር አበባ ጋር የሚመጡትን ችግሮች መቋቋም የምትችይበትን መንገድ ትለምጃለሽ። ለምሳሌ አንዳንዶች የሰውነት እንቅስቃሴ ማዘውተር ቁርጠት እንደሚቀንስላቸው ተገንዝበዋል። ቢሆንም ሁሉም ሰው አንድ አይነት አይደለም። አንቺ ደግሞ የወር አበባሽ ሲመጣ አካላዊ እንቅስቃሴ መቀነስ እንደሚሻልሽ ትገነዘቢ ይሆናል። ሰውነትሽን “ማዳመጥ” እና የሚፈልገውን ማድረግ ልመጂ።
ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በጉርምስናቸው ወቅት ስለ መልካቸውና ስለ ቁመናቸው መጨነቅ ይጀምራሉ። ቴሬሳ “ሰዎች ሲያዩኝ ምን መስዬ እታያቸዋለሁ ብዬ ማሰብ የጀመርኩት በዚህ ወቅት ነበር” ትላለች። “አሁንም ቢሆን አብዛኛውን ጊዜ መልኬና ቁመናዬ ጥሩ ሆኖ አይታየኝም። ፀጉሬ እንደምፈልገው አይሆንልኝም፤ ልብሴ ልኬ አይሆንም፣ ሌላው ቀርቶ የምወደው ልብስ አጣለሁ!” በማለት አክላ ተናግራለች።
ሰውነታችሁ ሊያሳፍራችሁ የሚችልባቸው ሌሎች መንገዶችም ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ላብ አመንጪ እጢዎች በጉርምስና ጊዜ ይበልጥ ንቁዎች ስለሚሆኑ በጣም ሊያልባችሁ ይችላል። ቶሎ ቶሎ ገላ መታጠብና ንጹሕ ልብስ መቀየር የሰውነታችሁን ጠረን ለመቆጣጠር ሊረዳችሁ ይችላል። ላብ የሚቀንሱ ወይም ሽታ የሚያጠፉ እንደ ዲዮድራንት ያሉ ነገሮች መጠቀምም ይቻላል።
በተጨማሪም በጉርምስና ወቅት በቆዳችሁ ሥር ያሉት ቅባት አመንጪ እጢዎች ከሌላው ጊዜ ይበልጥ ብዙ ቅባት ስለሚያመነጩ ብጉር ሊወጣባችሁ ይችላል። አን የተባለች ልጃገረድ “አምሬ መታየት በምፈልግበት ጊዜ ሁሉ ድንገት ብጉር ይወጣብኛል። የራሴ ግምት ነው ወይስ ብጉሮቹ የማይፈለጉበትን ጊዜ ያውቃሉ?” ስትል አማርራለች። ቴሬሳንም ቢሆን ብጉር አስቸግሯታል። “አስቀያሚ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ስለሚያደርግ ያሳፍረኛል። ሰዎች ሲያዩኝ የሚመለከቱት ብጉሬን ይመስለኛል” ብላለች።
ወንዶችም ቢሆኑ የቆዳ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል። እንዲያውም አንዳንድ ጠበብት እንደሚሉት ከሴቶች ይበልጥ ለዚህ ዓይነቱ ችግር የሚጋለጡት ወንዶች ናቸው። ወጣት ወንዶችም ሆናችሁ ሴቶች ፊታችሁን፣ አንገታችሁን፣ ትከሻችሁን፣ ጀርባችሁንና ደረታችሁን ጨምሮ ቅባት አመንጪ የሆኑትን የሰውነታችሁን ክፍሎች አዘውትራችሁ ብትታጠቡ ችግራችሁ ሊቀንስ ይችላል። በተጨማሪም ፀጉራችሁን አዘውትራችሁ ብትታጠቡ ከፀጉራችሁ የሚወጣው ቅባት ወደ ቆዳችሁ እንዳይዛመት ይረዳል። ከዚህም በላይ ብጉርን የሚከላከሉ መድኃኒቶች አሉ። ቴሬሳ “ቆዳ የሚያጠሩ መታጠቢያዎችና ቅባት የሚያጠፉ መድኃኒቶች እንዳገኝ ወላጆቼ ረድተውኛል” ትላለች። “በተጨማሪም ጣፋጭ ምግቦች እንዳላበዛ መክረውኛል። ጣፋጭ ምግቦች መብላት ሳቆምና ብዙ ውኃ ስጠጣ ብጉሬ በአብዛኛው ይጠፋል” ስትል አክላ ተናግራለች።
በተለይ ወንዶችን የሚያጋጥም ሌላው አካላዊ ለውጥ ደግሞ የድምፅ መለወጥ ነው። የድምፅ አውታሮች በጉርምስና ወቅት ስለሚወፍሩና ስለሚረዝሙ ድምፅ ጎርናና ይሆናል። ቢል ይህ ለውጥ የደረሰበት ሳይታወቀው ነው። “ስልክ በማነሳበት ጊዜ ሰዎች እናቴ ወይም እህቴ እንደሆንኩ መጠየቅ ከማቆማቸው በቀር ምንም የታወቀኝ ለውጥ አልነበረም።”
የድምፅ ውፍረት በለውጥ ላይ በሚሆንበት ጊዜ ድንገት ስልል ሊልና ወዲያው ሊጎረንን ይችላል። ታይረን ስለ ጉርምስና ዕድሜው ሲያስታውስ “ከሁሉ በላይ የሚያሳፍረው ይህ ነበር” ይላል። “አብዛኛውን ጊዜ የሚያጋጥመኝ ስጨነቅ ወይም ስደነግጥ ነበር። የስሜት መረበሽ እንዳያጋጥመኝ የተቻለኝን ያህል ብሞክርም ፈጽሞ ማስወገድ አልቻልኩም።” አንተም ይህ ችግር እያጋጠመህ ከሆነ አትጨነቅ! “ከአንድ ወይም ከሁለት ዓመት በኋላ ነው መሰለኝ ፈጽሞ ለቀቀኝ” ይላል ታይረን። ያንተም ድምፅ አንዴ መጎርነኑን አንዴ ደግሞ ስልል ማለቱን አቁሞ እንደወፈረ ይቀጥላል።
‘እንዲህ የሚሰማኝ ለምንድን ነው?’
በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች የተለያየ ዓይነት የስሜት መቃወስ ቢያጋጥማቸው እንግዳ ነገር አይሆንም። ለምሳሌ ከምትወዷቸው የልጅነት ጓደኞቻችሁ ጋር መራራቅ ልትጀምሩ ትችላላችሁ። ይህን ያህል የሚያራርቅ ጥል ተፈጥሮ ላይሆን ይችላል። በመካከላችሁ እምብዛም የጋራ ጉዳይ እንደሌለ ስለተሰማችሁ ብቻ ሊሆን ይችላል። በአንድ ወቅት እንዲያጽናኗችሁና አይዞህ እንዲሏችሁ ሮጣችሁ ትሄዱባቸው የነበሩት ወላጆቻችሁ እንኳን ድንገት ጊዜ ያለፈባቸውና ለመቅረብ የሚያስቸግሩ ሆነው ሊታይዋችሁ ይችላሉ።
ይህ ሁኔታ አንድን በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ወጣት ከማኅበረሰቡ የተገለለ እንደሆነ እንዲሰማው ሊያደርግ ይችላል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ “ከልጅነትም ሆነ ከጎልማሳነት ዕድሜ ይበልጥ ብቸኝነት የሚሰማው በጉርምስና ዕድሜ እንደሆነ አንዳንድ ተመራማሪዎች ይናገራሉ” ይላል። ሌሎች እንግዳ ዓይነት ባሕርይ እንዳላችሁ ይሰማቸዋል ብላችሁ ስለምትሰጉ ሐሳባችሁንና ስሜታችሁን ለራሳችሁ ብቻ
አምቃችሁ ትይዛላችሁ። ምናልባትም በውስጣችሁ ማንም ሊያስጠጋችሁ እንደማይፈልግ ስለሚሰማችሁ ሌሎችን ለመቅረብ ታመነታላችሁ።በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ አብዛኞቹ ወጣቶች አልፎ አልፎ ብቸኝነት ይሰማቸዋል፤ አብዛኞቹ ትላልቅ ሰዎችም እንደዚሁ። ልትዘነጉት የማይገባው አስፈላጊ ነገር ይህ ዓይነቱ ስሜት ዘላቂ እንዳልሆነና የሚጠፋበት ጊዜ እንዳለ ነው። * በጉርምስና ዕድሜ የምትገኙ ስለሆነ ሁለንተናችሁ ማለት ይቻላል፣ በመለዋወጥ ላይ መሆኑን አስታውሱ። ስለ ሕይወት፣ ስለ ሌሎችና ስለራሳችሁ ሳይቀር ያላችሁ አመለካከት በመለወጥ ላይ ነው። እንዲያውም የራሳችሁ ባሕርይ ለራሳችሁ እንግዳ ሆኖ ሊታያችሁ የሚችልበት ጊዜ ይኖራል! “በከፍተኛ የለውጥ ሂደት ላይ ባላችሁበት በዚህ ዕድሜ ራሴን አውቀዋለሁ ማለት ያስቸግራችኋል” እንዳለው እንደ 17 ዓመቱ ስቲቭ ሊሰማችሁ ይችላል።
የብቸኝነትን ስሜት ለማስወገድ ከሁሉ የሚሻለው ዘዴ ከሌሎች ሰዎች ጋር መቀራረብ ነው። የዕድሜ እኩዮቻችሁ ካልሆኑ ሰዎች ጋር መቀራረብ ሊኖርባችሁ ይችላል። ብትጠይቋቸው ደስ የሚላቸው አረጋውያን ይኖሩ ይሆን? በተለይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ከሆኑ ልታግዟቸው የምትችሉት ሥራ ይኖራል? መጽሐፍ ቅዱስ ወጣቶችንም ሆነ ጎልማሶችን ‘ፍቅራቸውን እንዲያሰፉ’ ይመክራል። (2 ቆሮንቶስ 6:11-13) እንዲህ ማድረጋችሁ አስደናቂ አጋጣሚዎችን ሊከፍትላችሁ ይችላል።
ከላይ የተጠቀሰው ጥቅስ ክርስቲያን ወጣቶች ጉርምስና የሚያስከትላቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዲቋቋሙ ከረዷቸው በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አንዱ ብቻ ነው። የሚቀጥለውን ርዕስ በምታነቡበት ጊዜ የአምላክ ቃል ጎልማሳ ሰው ወደ መሆን በምታደርጉት እድገት እንዴት በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድርባችሁ እንደሚችል አስቡ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.13 የወር አበባ ሲጀምር በወር ከአንድ ጊዜ የበለጠ ወይም ያነሰ ጊዜ ሊታይ ይችላል። የፍሰቱም መጠን ሊለያይ ይችላል። ይህ ሁሉ ሊያስደነግጥ አይገባም። ይሁንና ከአንድ ወይም ከሁለት ዓመት በኋላ ካልተስተካከለ ሐኪም ማማከር ሊያስፈልግ ይችላል።
^ አን.24 ለረዥም ጊዜ የቆየ የብቸኝነት ስሜት የሚሰማችሁ ወይም ራሳችሁን የመግደል ሐሳብ የሚመጣባችሁ ከሆነ እንዲህ ያለውን ራስን የማጥፋት ስሜት ለማስወገድ እርዳታ ማግኘት ሊያስፈልጋችሁ ይችላል። ሳትዘገዩ ወላጆቻችሁን ወይም የምትተማመኑባቸውን የጎለመሱ ሰዎች አነጋግሩ።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ወላጆች ፍጹማን አይደሉም
“ልጅ ሳለሁ ወላጆቼ ፍጹማን ይመስሉኝ ነበር። ወጣትነት ዕድሜ ላይ ስደርስ ግን በመጠኑም ቢሆን አላዋቂዎች መስለው ታዩኝ። ወላጆቼ ፍጹማን እንዳልሆኑ ተገነዘብኩ ማለቴ ነው። ይህም ስሜቴን ረበሸው። ይህን መገንዘቤ አስተሳሰባቸውንና ውሳኔያቸውን እንድጠራጠር አደረገኝ። ከብዙ ችግር በኋላ ግን ለእነርሱ የነበረኝ አክብሮት ሊመለስልኝ ችሏል። እርግጥ ፍጹማን አይደሉም፤ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ትክክል ናቸው። ቢሳሳቱ እንኳ ምንጊዜም ወላጆቼ ናቸው። ቀስ በቀስ ጥሩ ወዳጆች እየሆንን ነው። ይዋል ይደር እንጂ ወላጆችና ልጆች እዚህ ደረጃ ላይ መድረሳቸው አይቀርም ብዬ አስባለሁ።”—ቴሬሳ፣ 17 ዓመት
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ብዙ ወጣቶች በዕድሜ ከገፉ ሰዎች ጋር የቅርብ ወዳጅነት መስርተዋል