በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቢራ—ወርቃማው መጠጥ

ቢራ—ወርቃማው መጠጥ

ቢራ—ወርቃማው መጠጥ

ቼክ ሪፑብሊክ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

በጥም የተቃጠለ ሰው የሚናፍቀው ምንድን ነው? በብዙ አገሮች የጉልበት ሠራተኛም ሆነ ሀብታም ነጋዴ የሚመኘው የሚወደውን ቢራ ግጥም አድርጎ መጠጣት ነው። ከብርጭቆው አናት የሚኩረፈረፈው ነጭ አረፋና ደስ ­የሚለው መራራ ጣዕም ውል ይለዋል። ከዚያም “አቤት ቀዝቃዛ ቢራ ባገኝ!” በማለት ምኞቱን ይገልጻል።

ቢራ የሰውን ልጅ ዕድሜ ያህል ረዥም ታሪክ ያለው መጠጥ ነው ሊባል ይችላል። በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ተወዳጅነቱን ሳያጣ የቆየ ከመሆኑም በላይ በብዙ አካባቢዎች የአካባቢው ባሕል ክፍል ሆኗል። የሚያሳዝነው ግን በተለይ በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች ቢራ ከመጠን በላይ ለሚጠጡት ሰዎች የችግር ምንጭ መሆኑ ነው። ይሁን እንጂ ልካቸውን ጠብቀው ለሚጠጡ ሰዎች ቢራ ልዩ ጣዕም ያለው በጣም አስደሳች መጠጥ ነው። እስቲ የዚህን ተወዳጅ መጠጥ ታሪክ እንመርምር።

ቢራ ምን ያህል ጥንታዊ መጠጥ ነው?

በሜሶጶጣሚያ በሱሜራውያን ግዛት ውስጥ በድንጋይ ጽላት ላይ ተቀርጾ የተገኘ ጽሑፍ እንደሚያመለክተው በዚህ አካባቢ ቢራ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከሦስተኛ ሺህ ዓመት ጀምሮ ይጠመቅ ነበር። በዚሁ ዘመን ይኸው መጠጥ በባቢሎናውያንና በግብጻውያን ገበታ ላይ ይቀርብ ነበር። አሥራ ዘጠኝ ዓይነት የተለያዩ ቢራዎች ይታወቁባት በነበረችው በባቢሎን የቢራ መጥመቅ ሥራን የሚመለከቱ አንቀጾች በሐሙራቢ ሕጎች ውስጥ ተካትተው ነበር። እነዚህ ደንቦች ለምሳሌ የቢራን ዋጋ ይተምኑ የነበረ ከመሆኑም በላይ ከደንቦቹ መካከል አንዳቸውን የጣሰ እስከሞት በሚደርስ ቅጣት እንደሚቀጣ ይደነግጉ ነበር። በጥንቷ ግብጽ የቢራ ጠመቃ በጣም የተስፋፋ ሥራ ከመሆኑም በላይ ቢራም በጣም ተወዳጅነት ያተረፈ መጠጥ ሆኖ ነበር። በዚያ የተገኙ የአርኪኦሎጂ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ስለ ቢራ አጠማመቅ የሚገልጹ ጽሑፎችም ነበሩ።

ቀስ በቀስ የቢራ ጠመቃ ቴክኖሎጂ ወደ አውሮፓ ተዛመተ። በዘመናችን አቆጣጠር መጀመሪያ ላይ ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ሮማውያን ታሪክ ጸሐፊዎች ሴልቲኮች፣ ጀርመኖችና ሌሎች ነገዶች ቢራ ይጠጡ እንደነበረ ጠቅሰዋል። ቫይኪንጎች በኖርዲኮች አፈ ታሪክ መሠረት ጀግና የሆኑ ሰዎች ከሞቱ በኋላ በሚወሰዱበት ቫልሃላ የተባለ አዳራሽ ውስጥ ቢራ የሞላ ጽዋ እንደሚጠብቃቸው ያምኑ ነበር።

በመካከለኛው ዘመን በአውሮፓ ውስጥ የቢራ ጠመቃ ወደ ገዳማት ተዛወረ። የአውሮፓ መነኮሳት ቢራው ሳይበላሽ እንዲቆይ የሚያደርገውን ሆፕስ የተባለ ቅጠል በመጨመር የቢራ ጠመቃን ቴክኖሎጂ አሻሽለዋል። በ19ኛው መቶ ዘመን የተካሄደው የኢንዱስትሪ አብዮት የቢራ ጠመቃ በሞተር በሚንቀሳቀሱ መሣሪያዎች እንዲካሄድ በማስቻሉ ለዚህ ተወዳጅ መጠጥ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተከፈተ። ከዚያ በኋላ ደግሞ አንዳንድ አስፈላጊ የሆኑ አዳዲስ ሳይንሳዊ ግኝቶች ብቅ አሉ።

ሉዊ ፓስተር የተባለው ፈረንሳዊ ቀማሚና ማይክሮባዮሎጂስት ቢራ እንዲፈላ በሚያደርገው እርሾ ውስጥ ሕይወት ያላቸው ነፍሳት እንደሚገኙ አወቀ። ይህ ግኝት ስኳር ወደ አልኮል የሚለወጥበትን ሂደት ለመቆጣጠር አስቻለ። በቢራ ጠመቃ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉ ሰዎች መካከል ዴንማርካዊው የእጽዋት ተመራማሪ ኤሚል ክርስቲያን ሐንሰን አንዱ ነበር። ዕድሜውን በሙሉ የተለያዩ ዓይነት እርሾዎችን ሲያጠናና በክፍል በክፍል ሲመድብ ኖሯል። በተጨማሪም ንጹሕ የቢራ እርሾ ለማግኘት ምርምር ሲያደርግ ቆይቷል። ይህን በማድረጉም ሐንሰን በቢራ ጠመቃ ኢንዱስትሪ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል ማለት ይቻላል።

ይሁን እንጂ ቢራ መጥመቅ ይህን ያህል አስቸጋሪ ነገር ነው? ላይመስል ይችላል ግን አስቸጋሪ ነው። ቢራ በጣም ጥሩ ጣዕም እንዲኖረው የሚያስችለው ምሥጢር ምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

በብርጭቆህ ከመቀዳቱ በፊት

የቢራ ጠመቃ ቴክኖሎጂ ባለፉት መቶ ዘመናት ቀላል ነው የማይባል ለውጥ አድርጓል። ዛሬም ቢሆን የአንዱ ፋብሪካ ቢራ አጠማመቅ ከሌላው ይለያል። ቢሆንም ቢራዎች ሁሉም በአጠቃላይ አራት ዋና ዋና ግብዐቶች ይኖሯቸዋል። እነርሱም ገብስ፣ ሆፕስ፣ ውኃና እርሾ ናቸው። መላው የቢራ ጠመቃ ሂደት በአራት ንዑሳን ክፍሎች ሊከፈል ይችላል። እነርሱም የብቅል ዝግጅት፣ የድፍድፍ ዝግጅት፣ መፍላትና መብሰል ናቸው።

የብቅል ዝግጅት:- በዚህ ደረጃ ላይ ገብሱ ከተለቀመና ባዕድ ከሆኑ ነገሮች በሙሉ ከጸዳ በኋላ ይመዘናል። ከዚያም ውኃ ውስጥ ከተነከረ በኋላ እንዲበቅል ይደረጋል። ገብሱ ለመብቀል የሚያስፈልገው ጊዜ ከአምስት እስከ ሰባት ቀን ሲሆን 14 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በሚያክል ሙቀት ውስጥ እንዲቆይ ይደረጋል። ከዚህ የሚገኘው ውጤት እርጥብ ብቅል ሲባል ልዩ ወደሆነ ማድረቂያ ክፍል ገብቶ እንዲደርቅ ይደረጋል። ገብሱ መብቀሉን እንዲያቆም የብቅሉ እርጥበት መጠን ከ2 እስከ 5 በመቶ እንዲቀንስ ይደረጋል። ብቅሉ ከደረቀ በኋላ የበቀለው ጫፍ ተወግዶ ይፈጫል። ከዚህ በኋላ ለቀጣዩ ሂደት ዝግጁ ይሆናል።

የድፍድፍ ዝግጅት:- የተፈጨው ብቅል በውኃ ከተበጠበጠ በኋላ ቀስ ብሎ እንዲሞቅ ይደረጋል። የተወሰነ ሙቀት ላይ ሲደርስ በብቅሉ ውስጥ የሚገኙት ኢንዛይሞች ስታርቹን ወደ ስኳር መለወጥ ይጀምራሉ። ይህ ሂደት ለአራት ሰዓት ያህል የሚቆይ ሲሆን ተጣርቶ ወደሚቀጥለው ሂደት የሚወሰደውን ድፍድፍ ያስገኛል። ከዚህ በኋላ የኢንዛይሞቹ ሥራ እንዲቆም ድፍድፉ በሙቀት እንዲንተከተክ ይደረጋል። ድፍድፉ እየተንተከተከ ሳለ የቢራ ልዩ ባሕርይ የሆነውን መራራ ጣዕም እንዲያገኝ ሆፕስ ይጨመርበታል። ለሁለት ሰዓት ያህል ከተንተከተከ በኋላ ድፍድፉ ወደሚፈለገው የሙቀት መጠን እንዲቀዘቅዝ ይደረጋል።

መፍላት:- ከቢራ ጠመቃ ሂደት በጣም አስፈላጊ የሆነው ክፍል ይህ ሳይሆን አይቀርም። በድፍድፉ ውስጥ የሚገኙት የስኳር ቅንጣቶች በእርሾ አማካኝነት ወደ አልኮልና ካርቦን ዳይኦክሳይድ ይለወጣሉ። ይህ ሂደት የሚፈጀው ጊዜ ከአንድ ሳምንት የማይበልጥ ሲሆን የሚቆይበት የሙቀት መጠን እንደሚፈለገው የቢራ ዓይነት ይለያያል። ከዚያ በኋላ ጉሽ የሆነው ቢራ በሚበስልበት ማጠራቀሚያ ውስጥ እንዲቆይ ይደረጋል።

መብሰል:- ቢራው የራሱን ጣዕምና ቃና የሚያገኘው በዚህ ደረጃ ሲቆይ ሲሆን የሚፈላውም ከውስጡ በሚወጣው ካርቦን ዳይኦክሳይድ ምክንያት ነው። ቢራ ለመብሰል የሚያስፈልገው ጊዜ እንደ ቢራው ዓይነት ከሦስት ሳምንት እስከ ጥቂት ወራት ሊደርስ ይችላል። በመጨረሻ ያለቀለት ቢራ በቢራ ጋኖች ወይም በጠርሙሶች ውስጥ ተሞልቶ ከታሸገ በኋላ ወደሚፈለግበት ቦታ፣ ምናልባትም ወደ ራስህ ገበታ ለመድረስ ዝግጁ ይሆናል። ይሁን እንጂ መቅመስ የምትፈልገው የትኛውን ዓይነት ቢራ ነው?

ዓይነቱ ብዙ የሆነ መጠጥ

የተለያዩ ዓይነት ቢራዎች አሉ። ነጣ ያለ ወይም ጥቁር ቢራ፣ ጣፋጭ ወይም መራራ ቢራ፣ አለበለዚያም ከገብስ ወይም ከስንዴ የተጠመቀ ቢራ መጠጣት ይቻላል። የቢራ ጣዕም የመጥመቂያ ውኃውን ጥራት፣ የብቅሉን ዓይነት፣ የአጠማመቁን ቴክኖሎጂና የእርሾውን ዓይነት ጨምሮ በብዙ ነገሮች ላይ የተመካ ሊሆን ይችላል።

በጣም እውቅ ከሆኑት ቢራዎች አንዱ በጣም ደማቅ ያልሆነ ቀለም ያለው ፒልስነር የተባለው ቢራ ነው። ይህ ዓይነቱ ቢራ በመላው ዓለም በሚገኙ በመቶዎች በሚቆጠሩ የቢራ ፋብሪካዎች ይጠመቃል። ይሁን እንጂ ትክክለኛው ፒልስነር ቢራ የሚጠመቀው በቼክ ሪፑብሊክ በሚገኘው በፒልሰን (ፐልዘን) ከተማ ብቻ ነው። ይህ ቢራ ልዩ የሆነበት ምሥጢር የአጠማመቁ ቴክኖሎጂ ብቻ ሳይሆን የሚጠመቅበት ውኃ ዓይነት፣ የብቅሉ ጥራትና የእርሾው ዓይነት ጭምር ነው።—“ፒልስነር—ለመኮረጅ ብዙ ሙከራ የተደረገበት ቢራ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ሌላው በጣም ጥሩ ዓይነት ቢራ በተለይ በጀርመን አገር በጣም ተወዳጅ የሆነው ቫይስ ቢር የተባለው የስንዴ ቢራ ነው። የብሪታንያውያን ምርጥ ቢራዎች ደግሞ ፖርተር እና ስታውት ይባላሉ። ፖርተር የሚባለው ላይ ላዩን ከሚፈላ እርሾና ከተቆላ ብቅል የሚጠመቅ ቢራ ሲሆን በዚህም ምክንያት ደማቅ ጥቁር ቀለም ያለው መጠጥ ነው። ፖርተር ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠመቀው በ18ኛው መቶ ዘመን በለንደን ከተማ ነው። በመጀመሪያ የተጠመቀው እንደ ተሸካሚዎች ላሉ የጉልበት ሠራተኞች “ኃይል እንዲሰጥ” ታስቦ ነበር። ስታውት በጣም ጥቁር የሆነ ወፍራም ቢራ ሲሆን በአየርላንድና በመላው ዓለም ሠፊ እውቅና ያገኘው በጊነስ ቤተሰብ አማካኝነት ሲሆን ከባሕላዊው የፖርተር ቢራ ትንሽ ለየት ያለ ነው። የእንግሊዙን የወተት ስኳር (ላክቶስ) የተጨመረበት ስታውት ወይም የአየርላንዱን መራራና ከፍ ያለ የአልኮል መጠን ያለው ደረቅ ስታውት መቅመስ ይቻላል።

የጠርሙስም ይሁን የቆርቆሮ ወይም ከበርሜል የሚቀዳ፣ ብቻ ቢራ የሚወዱ ሰዎች የሚያማርጡት ሌላው ነገር የቀዘቀዘ ይሁን ወይስ ያልቀዘቀዘ የሚለው ነው። አሜሪካውያን በጣም የቀዘቀዘ ቢራ መጠጣት ይወዳሉ። ሌሎች ደግሞ ያልቀዘቀዘ ወይም እምብዛም ሳይቀዘቅዝ ከበርሜሉ በቀጥታ የሚቀዳ ቢሆን ይመርጣሉ።

በእርግጥም ቢራ ዓይነቱ ብዙ የሆነ መጠጥ ነው። መጠንን ጠብቆ መጠጣት አንዳንድ የጤና ጠቀሜታዎች ሊኖሩት ይችላል። እንዲያውም እንደ ሪቦፍላቪን፣ ፎሊክ አሲድ፣ ክርምየምና ዚንክ የመሰሉ አስፈላጊ ቪታሚኖችና ማዕድናት ይገኙበታል። አንዳንድ ሊቃውንት እንደሚሉት በመጠኑ ቢራ መጠጣት የልብ ሕመምና የቆዳ ችግር ለማስወገድ ይረዳል። ከበርካታዎቹ የቢራ ዓይነቶች ጥሩውን መምረጥ ከቻልክና ሚዛንህን ጠብቀህ የምትጠጣ ከሆነ በዚህ የሚያረካና የሚጣፍጥ መጠጥ መደሰት ትችላለህ። ስለዚህ ነጭ አረፋ የሚደፍቅ ወርቃማ መጠጥ በብርጭቆ ተሞልቶ በሚቀርብልህ ጊዜ ይህን አስደናቂ የሆነ ታሪኩን ማስታወስ ትችላለህ!

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ተቀዳሚዎቹ ተዋንያን

በጥንቶቹ ዘመናት የቢራ ጠመቃ ሥራ የበርካታ ባለሞያዎችን ተሳትፎ ይጠይቅ ነበር። ከእነዚህ ባለሞያዎች መካከል አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው።

ብቅል አብቃይ—በቢራ ጠመቃ ድራማ ውስጥ የመጀመሪያው ተዋናይ ነው። ከገብስ ወይም ከስንዴ ብቅል ያበቅላል። የእህሉን መብቀልና የእርጥቡን ብቅል መድረቅ ይቆጣጠራል። የሚጠመቀው ቢራ ጣዕም በአብዛኛው የሚመካው በብቅሉ ጥራት ላይ ስለሆነ የሚጣልበት ኃላፊነት በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ጠማቂ (ከላይ የሚታየው)ድፍድፉን የማንተክተክ ኃላፊነት የሚጫነው በዚህ ባለሞያ ላይ ነው። በመጀመሪያ የተፈጨውን ዱቄት በውኃ ከለወሰ በኋላ አፍልቶ ሆፕስ ይጨምርበታል። የዚህ ባለሞያ የመጨረሻ ውጤት ድፍድፍ ይባላል።

የጋን ኃላፊ—ቢራው በሚቀመጥበት በርሜል በሚገባ መፍላቱንና በኋላም በሚጨመርበት ትልቅ ጋን ውስጥ በስሎ ለመጠጥ መድረሱን የሚቆጣጠር ብዙ ልምድ ያለው ባለሞያ ነው። በመጨረሻም ያለቀለትን ቢራ ወደ ትናንሽ ዕቃዎች ያጋባል።

[ምንጭ]

S laskavým svolením Pivovarského muzea v Plzni

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ፒልስነር—ለመኮረጅ ብዙ ሙከራ የተደረገበት ቢራ

ይህ ቢራ መመረት የጀመረው በ1295 ነው። የቦሄምያ ንጉሥ የነበረው ዳግማዊ ወንሰስላስ፣ ፐልዘን የተባለችውን ከተማ ከቆረቆረ በኋላ 260 ለሚያክሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ቢራ የመጥመቅ ፈቃድ ሰጠ። እነዚህ የፐልዘን ነዋሪዎች መጀመሪያ ላይ ቢራ ይጠምቁ የነበረው በየቤቶቻቸው በትናንሽ መጠን ሲሆን በኋላ ግን በማኅበር ተደራጅተው ትላልቅ ፋብሪካዎችን አቋቋሙ። ይሁን እንጂ በተለይ በመካከለኛው ዘመን የቦሄምያ ኢኮኖሚና ባሕል እየወደቀ መምጣቱ የቢራ ጠመቃ ሥራ እየተዳከመ እንዲሄድ ምክንያት ሆነ። ጠማቂዎቹ የታወቀውንና ትክክለኛውን የቢራ አጠማመቅ ቴክኖሎጂ ትተው የየራሳቸውን ዘዴዎች መጠቀም በመጀመራቸው አብዛኛውን ጊዜ ቢራ ተብሎ ሊጠራ እንኳን የማይችል መጥፎ ጣዕም ያለው መጠጥ መጥመቅ ጀመሩ።

በዚያ ዘመን በአውሮፓ ሁለት ዓይነት ቢራ ይጠመቅ ነበር። በተለይ በቦሄምያ ቶሎ የሚፈላ ቢራ ሲጠመቅ በባቫርያ ግን ድፍድፉ ለረዥም ጊዜ የሚቀመጥና የተሻለ ጥራት ያለው ቢራ ይጠመቅ ነበር። ላገር በሚባለው የባቫርያ ቢራና በፐልዘን ቢራ መካከል በጣም ከፍተኛ የሆነ ልዩነት ነበር።

በ1839 አዲስ ምዕራፍ ከፋች የሆነ ለውጥ ተከናወነ። ሁለት መቶ የሚያክሉ የፐልዘን ነዋሪዎች አንድ ነገር ማድረግ እንደሚገባቸው ወሰኑ። የባቫርያ ዓይነት ቢራ ብቻ የሚጠመቅበትን የበርጀስ ቢራ ፋብሪካ አቋቋሙ። ዝነኛ ቢራ ጠማቂ የነበረው ዮዜፍ ግሮል ከባቫርያ እንዲመጣ ተደረገ። ወዲያው እንደመጣ የባቫርያ ዓይነቱን ቢራ መጥመቅ ጀመረ። የተገኘው ውጤት ከባቫርያ የተለየና በጣም የተሻለ ቢራ ሆነ። በአካባቢው ይገኝ የነበረው ጥሩ የቢራ ጥሬ ዕቃ የግሮል ተሞክሮ ሲታከልበት በመላው ዓለም ሠፊ ተወዳጅነት ያገኘ ግሩም ቢራ አስገኘ። ቢራውን ልዩ ያደረገው ነገር ምን ነበር? ልዩ ዓይነት ጣዕም፣ ቀለምና መዓዛ ስለነበረው ነው። ይሁን እንጂ የፐልዘን ቢራ ዝነኛ መሆኑ አሉታዊ ገጽታም ነበረው። ከዚህ ክስተት ተጠቃሚ ለመሆን የቋመጡ በርካታ ቢራ ጠማቂዎች ምርቶቻቸውን ፒልስነር ብለው መጥራት ጀመሩ። በዚህ ምክንያት ፒልስነር በጣም ዝነኛ ብቻ ሳይሆን በጣም ብዙ የመኮረጅ ሙከራ የተደረገበት ወርቃማ መጠጥ ለመሆን በቃ።

[ሥዕሎች]

ዮዜፍ ግሮል

የፐልዘን ቢራ ፋብሪካ የውኃ ማጠራቀሚያ ማማ

[ምንጭ]

S laskavým svolením Pivovarského muzea v Plzni

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ፐልዘን

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የዳቦና የቢራ አዘገጃጀት የሚያሳይ የግብጽ ሞዴል

[ምንጭ]

Su concessione del Ministero per i Beni e le Attività Culturali-Museo Egizio-Torino

[በገጽ 19 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሆፕስ፣ ብቅልና የቢራ መጥመቂያ ቤት