በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ደመናዎችና ዝሆኖች

የደመና ክብደት ምን ያህል ይሆናል? ኤቢሲ ኒውስ አንድ ቁልል ደመና 550 ቶን የሚመዝን ውኃ ሊይዝ እንደሚችል ዘግቧል። “ወይም ይበልጥ ለመረዳት በሚቀል መጠን ለመግለጽ ከተፈለገ . . . ከዝሆን ጋር እናወዳድረው” ይላሉ የአየር ሁኔታ ተመራማሪ የሆኑት ፔጊ ለሞን። አንድ ዝሆን 6 ቶን ይመዝናል ብለን ብናስብ በአንድ አማካይ ቁልል ደመና ውስጥ የሚገኘው የውኃ ክብደት 100 ዝሆኖችን ያህል ይሆናል። ይህ ሁሉ ውኃ በጥቃቅን ነጠብጣብ መልክ ከሥር በሚገኘው ሞቃት አየር ተንሳፍፎ ይቆያል። ከባድ ዝናብ አዘል ደመና ከዘርዛራ ቁልል ደመና ጋር ሲወዳደር 200,000 ዝሆኖችን የሚያክል ክብደት ሊኖረው ይችላል። ዶፍ ዝናብ ያዘለ ደመናስ? ለሞን በአንድ ሜትር ኩብ ዶፍ አዘል ደመና ውስጥ የሚኖረውን ውኃ መጠን ከገመቱ በኋላ በጠቅላላው ደመና ይዘት አባዝተውታል። ውጤቱስ? የአርባ ሚሊዮን ዝሆኖች ክብደት ይኖረዋል። ዘገባው እንዲህ ይላል:- “በአንድ ዶፍ አዘል ደመና ውስጥ የሚኖረው ውኃ ክብደት በምድራችን ላይ ከሚኖሩት ዝሆኖች በሙሉ ይበልጣል ማለት ነው። ምናልባትም እስካሁን ድረስ በምድር ላይ ከኖሩት ዝሆኖች በሙሉ ሊበልጥ ይችላል።”

ጥርስህን መቦረሽ ያለብህ መቼ ነው?

የሜክሲኮ ሲቲው ሚሌንዮ ጋዜጣ ኮምጣጣ ምግብ ከተመገቡ ወይም ኮምጣጣ መጠጥ ከጠጡ በኋላ ወዲያው ጥርስ መቦረሽ በጥርስ መስተዋት ላይ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ገልጿል። ጋዜጣው የጀርመኑ ጎቲንገን ዩኒቨርሲቲ ያደረገውን ጥናት ዘግቦ ኮምጣጣ ወይም አሲድነት ያላቸው ምግቦች “ኢናመል የተባለውን የጥርስ ውጨኛ ክፍል ለጊዜው ያዳክማሉ” ሲል አስጠንቅቋል። ስለዚህ ከምሳ በኋላ ወዲያው ጥርስ መቦረሽ ጎጂ ሊሆን ይችላል። ከዚህ ይልቅ “ጥርሶች ጥንካሬያቸውን እስኪያገኙ ድረስ ለጥቂት ደቂቃዎች ቆይቶ መቦረሽ የተሻለ ይሆናል።”

የመኖሪያ አካባቢዋ ከወደመ በኋላ የተገኘች አዲስ ዝርያ

የቬኔዝዌላ ይዞታ በሆነው በካሮኒ ወንዝ ላይ በምትገኘው ካሪሳል የተባለች ሰው የማይኖርባት ደሴት አዲስ ግድብ ለመገንባት ታስቦ ስትመነጠር ከዚህ በፊት የማትታወቅ የወፍ ዝርያ እንደተገኘች የካራካሱ ዴይሊ ጆርናል ዘግቧል። የደኑ ምንጠራ ከመጀመሩ በፊት በተወሰደ የአእዋፍ ናሙና፣ ሰው በማያሳልፈው ጥቅጥቅ ያለ የቀርከሃ ጫካ ውስጥ ባለሰማያዊ ቀለም ፊንች የተባለች ትንሽ ወፍ ተገኝታለች። የተፈጥሮ ተመራማሪዎች የዚህችን አዲስ የተገኘች ወፍ ዝርያ በአጎራባች አካባቢዎች እናገኛለን ብለው ተስፋ ያደርጋሉ። እስከዚያው ድረስ ግን፣ ሮቢን ሬስቶል የተባሉት ተመራማሪ “ካሪሳል ሲድኢተር የተባለችው ይህች የወፍ ዝርያ መገኘቷ . . . በጣም የሚያስደንቅ ግኝት ቢሆንም ይህች የወፍ ዝርያ ይህን ለሚያክል ዘመን ከእኛ ተደብቃ የቆየችበትን የመኖሪያ አካባቢ ማጥፋታችን ያሳዝናል” ብለዋል።

መክተፊያችሁን በንጽሕና ያዙ!

ከእንጨት መክተፊያና ከፕላስቲክ መክተፊያ ለጤና የትኛው ይሻላል? “በንጽሕና እስከተያዘ ድረስ ሁለቱም ዓይነት መክተፊያ ጥሩ ነው” ይላል የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲው በርክለይ ዌልነስ ሌተር። “ጥሬ ሥጋና የመሳሰሉትን ምግቦች የምትከትፉበት መክተፊያ የእንጨትም ይሁን የፕላስቲክ ከተገለገላችሁበት በኋላ በሙቅ ውኃና በሳሙና ሙልጭ አድርጋችሁ እጠቡት።” መክተፊያው ብዙ ጭረቶች ወይም ቅባት ካለበት ሙሉ በሙሉ ለማጽዳት ተጨማሪ ጥንቃቄ መውሰድ ያስፈልጋል። “በተጨማሪም መክተፊያችሁን በውኃ በተበረዘ በረኪና (አንድ የሻይ ማንኪያ ሩብ ሊትር ውኃ ውስጥ በመጨመር) በማለቅለቅ ከጀርሞች ማንጻት ይቻላል” ይላል ዌልነስ ሌተር። እጆቻችንንና የተጠቀምንባቸውን ቢላዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ በደንብ አጥበን ማድረቅ ይኖርብናል።

ለትምህርት ያልደረሱ ሕፃናትና ኮምፒውተሮች

አንዳንድ ተመራማሪዎች “ከድሮዎቹ የጨዋታ ዓይነቶች ይልቅ ለረዥም ጊዜ በኮምፒውተሮች መጫወት” ለትምህርት ዕድሜ ላልደረሱ ሕፃናት የሚሰጠው ጥቅም በጣም አነስተኛ ከመሆኑም በላይ “ከሰው እንደ መራቅ፣ በአንድ ነገር ላይ ለማተኮር እንዳለመቻል፣ የፈጠራ ችሎታ እንደ ማጣትና ጭንቀት ያሉ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል” ሲል ቫንኮቨር ሰን የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። ኮምፒውተሮች የአንድን ሕፃን ዓለም “ሊዳሰስና ሊጨበጥ ከሚችለው የገሃዱ ዓለም ኮምፒውተር ላይ ብቻ ወደሚታይ ዓለም ይለውጣሉ” ሲሉ ሻርነ ኦልፍመን የተባሉት የሥነ አእምሮ ተመራማሪ ገልጸዋል። ተመራማሪዎች ለልጆች “ቃላትን፣ ቀለሞችን፣ ቅርጾችን፣ ቁጥሮችን፣ መልካም ሥነ ምግባርንና የዕለት ተዕለት ክስተቶችን” ለማስተማር “የወላጆች ቁጥጥር የታከለበት ልማዳዊ ጨዋታ መጫወት” በጣም አስፈላጊ መሆኑን አጥብቀው ይመክራሉ። በተለይ ከልደት እስከ ሰባት ዓመት ዕድሜ ባለው ጊዜ ውስጥ የድሮዎቹ ዓይነት ጨዋታዎች በጣም አስፈላጊ መሆናቸውን የስነ አእምሮ ተመራማሪ ጄን ሂሊ ይናገራሉ። እንደዚህ ያሉት ጨዋታዎች ሕፃናትን በአንድ ነገር ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ የሚያስተምሩ ሲሆኑ የኮምፒውተር ጨዋታዎች ግን የሚያስከትሉት ውጤት የዚህ ተቃራኒ ነው።

ቴሌቪዥን “ከባድ አደንዛዥ እጽ” ነው

“በቀን ከሁለት ሰዓት በላይ ቴሌቪዥን የማየት ልማድ ያላቸው ልጆች የትምህርት ቤት ውጤታቸው አነስተኛ” እንደሆነ ላ ቫንግዋርዲያ የተባለው የስፓንኛ ጋዜጣ ዘግቧል። የሕፃናት ሐኪም የሆኑት ፍራንቲስኮ ሙኞስ ቴሌቪዥን በጣም ጥሩ የማስተማሪያ መሣሪያ እንደሆነ ቢያምኑም ቴሌቪዥንን ለዚህ ዓላማ መጠቀም የሚያስከትለውን መጥፎ ውጤት ገልጸዋል። የቴሌቪዥን አዘውታሪዎች የትምህርት ውጤታቸው ዝቅተኛ የሆነበት ምክንያት “የጉልምስና እድገታቸው አዝጋሚ ስለሚሆንና ጽንሰ ሐሳቦችን የመረዳት ችሎታቸው ስለሚቀንስ” እንደሆነ ሙኞስ ያምናሉ። በተጨማሪም “ወጣቶች አንዳንድ ፕሮግራሞችን፣ ማስታወቂያዎችንና የሙዚቃ ቪዲዮዎችን በመመልከታቸውና አልኮል፣ ትንባሆና እጽ የመውሰድ ልማድ በማዳበራቸው መካከል ቀጥተኛ ዝምድና እንዳለ ግልጽ ነው” ብለዋል። የሕፃናት የሥነ ልቦና ሐኪም የሆኑት ፖውሊኖ ካስቴልስ ሁሉም ወጣቶች በቴሌቪዥን ላይ የሚያዩትን መጥፎ ነገር ወደ ተግባር ይተረጉማሉ ሊባል እንደማይቻል ቢያምኑም ቴሌቪዥን “ገና ባልበሰለ የወጣቶች አእምሮ ላይ በሚያስከትለው ከፍተኛ ጉዳት” የተነሳ “ከባድ አደንዛዥ እጽ” ተደርጎ ሊቆጠር እንደሚችል ተናግረዋል።

ጫጫታ የበዛባቸው የትምህርት ክፍሎች

በክፍል ውስጥ በሚሰሙ የገደል ማሚቶዎችና ከአካባቢው በሚመጣ የጫጫታ ድምፅ ምክንያት በትምህርት ላይ የሚገኙ ተማሪዎች መስማት እንደሚቸገሩ ደር ሽፒገል የተባለው የጀርመን መጽሔት ገልጿል። ማሪያ ክላተ የተባሉት የሥነ አእምሮ ተመራማሪ “ልጆች ለመረዳት በተቸገሩ መጠን የሚቀስሙት ትምህርት እያነሰ ይሄዳል” ብለዋል። ተመራማሪዎች በአንዳንድ የጀርመን ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ70 እስከ 90 ዴሲብል የሚደርስ የድምፅ መጠን ለክተዋል። በመስኩ ምርምር የሚያደርጉት ጌርሐርት ቲስለ “ብዙ የአእምሮ ሥራ በሚከናወንባቸው መሥሪያ ቤቶች የድምፅ መጠን ከ55 ዴሲብል መብለጥ የለበትም” ሲሉ ገልጸዋል። “በኢንዱስትሪዎች የድምፅ መጠን ከ85 ዴሲብል ካለፈ ጆሮ ላይ መከላከያ እንዲደረግ ይመከራል።” ከዚህም በላይ በአንድ ክፍል ውስጥ በሰዎች ንግግር፣ በወንበር እንቅስቃሴ ወይም በሳል ምክንያት የሚፈጠር ድምፅ የሚያስተጋባበት ጊዜ በረዘመ መጠን በትምህርት ላይ ማተኮር ይበልጥ አስቸጋሪ ይሆናል። ድምፅ የመዋጥ ችሎታ ያላቸው ኮርኒሶች ጫጫታና የገደል ማሚቶ እንዲቀንስ በማድረግ የመምህራንን ድካምና የተማሪዎችን ችግር በእጅጉ ሊቀንሱ ቢችሉም ብዙ ትምህርት ቤቶች እንደነዚህ ያሉትን ኮርኒሶች የሚያስገጥሙበት የገንዘብ አቅም የላቸውም።

ትላልቅ የገበያ አዳራሾች የቀድሞዎቹን የተለመዱ ሱቆች እያፈናቀሉ ነው

“ትላልቅ የገበያ አዳራሾች በምሥራቃዊና በደቡባዊ አፍሪካ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፉ መምጣታቸው የትናንሽ ሱቆችን ሕልውና ከመፈታተኑም በላይ በዚሁ ምክንያት በገጠር አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮች መተዳደሪያቸውን እንዲያጡ እያደረገ ነው” ሲል የጀርመኑ ቪሰንሻፍት ኦንላይን የተባለ ዜና መጽሔት ገልጿል። በአሁኑ ጊዜ እንኳን በኬንያ 30 በመቶ የሚሆነውን የምግብ ሸቀጥ ችርቻሮ ድርሻ የያዙት 200 የሚሆኑ የገበያ አዳራሾችና 10 ትላልቅ የገበያ ማዕከሎች ሲሆኑ ይህም የ90,000 ትናንሽ ሱቆችን ሽያጭ ያክላል። በተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት ባልደረባ የሆኑት ኮስታስ ስታሙሊስ እንደሚሉት በጣም የተፋጠነው የከተሞች መስፋፋትና ግሎባላይዜሽን “አፍሪካ ውስጥ በበለጸጉ አገሮች ከተመለከትነው የበለጠ የምግብ አቅርቦት ለውጥ እንዲከሰት ያደርጋል” ብለዋል። በጣም የከፋ ጥፋት እንዳይደርስ በየአካባቢው ለሚመረቱ ሰብሎችና ምርቶች ገበያ የሚያስገኙ የኅብረት ሥራ ማህበራት ማቋቋምና ገበሬዎች ከለውጡ ጋር እንዲላመዱ የሚረዳ ሥልጠና መስጠት እንደሚያስፈልግ የመስኩ ሊቃውንት ይመክራሉ።