ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት መፈጸም ምን ስህተት አለው?
የወጣቶች ጥያቄ . . .
ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት መፈጸም ምን ስህተት አለው?
“አንዳንድ ጊዜ ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ቢፈጸም ምን አለበት ብዬ አስባለሁ። በተለይ ደግሞ እስካሁን ድረስ ምንም የጾታ ግንኙነት አድርጌ የማላውቅ መሆኔ ሲያሳፍረኝ ይህ ጥያቄ ወደ አእምሮዬ ይመጣል።”—ጆርደን *
“አንዳንድ ጊዜ ወሲብን እንድሞክር የሚገፋፋ ኃይለኛ ስሜት ያድርብኛል። ሁላችንም ይህን የማድረግ የተፈጥሮ ዝንባሌ ያለን ይመስለኛል” ትላለች ኬሊ። “በሄዳችሁበት ሁሉ የሚወራው ስለ ወሲብ ነው!”
አንተም ጆርደንና ኬሊ የሚሰማቸው ዓይነት ስሜት ይሰማሃል? ደግሞም ቀደም ሲል ከጋብቻ በፊት ወሲብ መፈጸምን ይከለክሉ የነበሩ ወጎችና ባሕሎች አሁን የሉም። (ዕብራውያን 13:4) በአንድ የእስያ አገር ከ15 እስከ 24 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ወንዶች ላይ የተደረገ ጥናት እንዳሳየው አብዛኞቹ ከጋብቻ በፊት ወሲብ መፈጸማቸው ተቀባይነት ያለው ብቻ ሳይሆን የሚጠበቅባቸው ነገር እንደሆነ ጭምር ተሰምቷቸዋል። እንግዲያው በመላው ዓለም የሚገኙ አብዛኞቹ ወጣቶች ዕድሜያቸው 19 ዓመት ከመሆኑ በፊት ወሲብ መፈጸማቸው አያስገርምም።
አንዳንድ ወጣቶች ደግሞ ከተፈጥሯዊው ወሲባዊ ድርጊት ቢቆጠቡም እንኳ አማራጭ እንደሆኑ ተደርገው የሚቆጠሩትን ዘዴዎች በመጠቀም ማለትም አንዳቸው የሌላውን ብልት በመደባበስና በማሻሸት እንዲሁም በአፍ በሚፈጸም ወሲብ እርካታን ለማግኘት ይጥራሉ። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ በተሰኘው ጋዜጣ ላይ የወጣ በጣም አሳሳቢ የሆነ አንድ ዘገባ እንደገለጸው “በአፍ የሚፈጸም ወሲብ ወደ ወሲባዊ ተግባር ከመግባት በፊት የሚዘወተር ነገር እየሆነ የመጣ ሲሆን ብዙ ወጣቶች ይህን ድርጊት አቅልለው የሚመለከቱት ከመሆኑም በላይ የተለመደውን የጾታ ግንኙነት ያህል ለአደጋ እንደማያጋልጣቸው ይሰማቸዋል። . . . [በተጨማሪም] እርግዝናን ለመከላከልና ድንግልናንም ለመጠበቅ የሚረዳ ዘዴ እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል።”
ታዲያ አንድ ክርስቲያን ከጋብቻ በፊት ወሲብ መፈጸምን በተመለከተ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረው ይገባል? እንደ አማራጭ የእርካታ ማግኛ ተደርገው የሚታዩትን ዘዴዎችስ እንዴት ሊያያቸው ይገባል? እነዚህ አማራጭ ዘዴዎች በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አላቸው? ደግሞስ ጉዳት የማያስከትሉ ናቸው? በእርግጥ የአንድን ሰው ድንግልና ጠብቆ ለማቆየት ይረዳሉ?
ዝሙት የሚያጠቃልላቸው ነገሮች
ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የሚገኝበት የታመነ ምንጭ ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። ይሖዋ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት “ከዝሙት ሽሹ” በማለት ይነግረናል። (1 ቆሮንቶስ 6:18) ይህ ምን ማለት ነው? “ዝሙት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ትርጉሙ ወሲባዊ ግንኙነትን ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የብልግና ድርጊቶችንም ይጨምራል። ስለዚህ ሁለት ያልተጋቡ ሰዎች በአፍ በሚፈጸም ወሲባዊ ድርጊት የሚካፈሉ ወይም አንዳቸው የሌላውን የጾታ ብልት የሚያሻሹ ከሆነ ዝሙት ፈጽመዋል።
ታዲያ ከዚህ በኋላ በአምላክ ፊት እንደ ድንግሎች ሊቆጠሩ ይችላሉ? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ድንግል” የሚለው ቃል የተሠራበት የሥነ ምግባር ንጽሕናን ለማመልከት ነው። (2 ቆሮንቶስ 11:2-6) ይሁን እንጂ ይህ ቃል አካላዊ ሁኔታንም ለማመልከት ተሠርቶበታል። መጽሐፍ ቅዱስ ርብቃ ስለተባለች አንዲት ወጣት ሴት ይናገራል። ርብቃ “ወንድ ያልደረሰባት ድንግል ነበረች” ይላል። (ዘፍጥረት 24:16) በነገራችን ላይ፣ በጥንታዊው ዕብራይስጥ ቋንቋ “ወሲብ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል በወንድና በሴት መካከል ከሚደረገው የጾታ ግንኙነት ውጭ የሆኑ ድርጊቶችንም ያመለክት ነበር። (ዘፍጥረት 19:5) ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት አንድ ወጣት በማንኛውም ዓይነት ዝሙት ተካፋይ ከሆነ እንደ ድንግል ሊቆጠር አይችልም።
መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖችን አጥብቆ የሚያሳስባቸው ከዝሙት ብቻ ሳይሆን ወደ ዝሙት ሊመራ ከሚችል ማንኛውም ዓይነት ርኩስ ምግባር ጭምር እንዲርቁ ነው። * (ቆላስይስ 3:5) እንዲህ ያለ አቋም በመያዝህ ሌሎች ያሾፉብህ ይሆናል። ኬሊ የምትባል ወጣት “ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በነበርኩባቸው ዓመታት ሁሉ አዘውትሬ የምሰማው ነገር ‘ምን እንደቀረብሽ አታውቂም!’ የሚል ነበር” ትላለች። ይሁን እንጂ ከጋብቻ በፊት ወሲብ መፈጸም “ለጥቂት ጊዜ በኀጢአት ከሚገኝ ደስታ” የተለየ ትርጉም የለውም። (ዕብራውያን 11:25) ዘላቂ የሆነ አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።
ከባድ አደጋዎች
ንጉሥ ሰሎሞን በአንድ ወቅት አንዲት ሴት አንዱን ወጣት ከእሷ ጋር ከጋብቻ በፊት ወሲብ እንዲፈጽም ስታባብለው እንደተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ሰሎሞን ወጣቱን ሰው ‘ለዕርድ ከሚነዳ በሬ’ ጋር አነጻጽሮታል። ለዕርድ የሚነዳ በሬ ምን ሊደርስበት እንደሆነ የሚያውቀው ነገር የለም። ከጋብቻ በፊት ወሲብ የሚፈጽሙ ወጣቶችም እንዲሁ ናቸው። ድርጊታቸው የሚያስከትለውን ከባድ መዘዝ የሚገነዘቡት አይመስሉም! ሰሎሞን ስለዚያ ወጣት ሲናገር “ነገሩ ሕይወቱን እንደሚያሳጣው አላወቀም” ብሏል። (ምሳሌ 7:22, 23) አዎን፣ አደጋ ላይ የሚወድቀው ሕይወታችሁ ነው።
ለምሳሌ ያህል በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በጾታ ግንኙነት በሚተላለፉ በሽታዎች ይያዛሉ። “ኸርፐዝ የሚባለው በሽታ እንደያዘኝ ሳውቅ ወደሆነ ቦታ ጠፍቼ መሄድ ነበር ያሰኘኝ” በማለት ሊዲያ ትናገራለች። “ፈጽሞ ሊድን የማይችል የሚያሰቃይ በሽታ ነው” በማለት በቁጭት ትናገራለች። በዓለም ዙሪያ በየቀኑ በኤች አይ ቪ ከሚያዙት 6,000 ሰዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከ15 እስከ 24 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል የሚገኙ ናቸው።
በተለይ ደግሞ ከጋብቻ በፊት ወሲብ ከመፈጸም ጋር በተያያዘ ለብዙ ችግሮች የሚጋለጡት ሴቶች ናቸው። እንዲያውም ከወንዶች ይበልጥ ሴቶች ኤች አይ ቪን ጨምሮ በጾታ ግንኙነት በሚተላለፉ በሽታዎች የመያዝ አጋጣሚያቸው ከፍተኛ ነው። አንዲት ወጣት ብታረግዝ ራሷንም ሆነ ገና ያልተወለደውን ልጅዋን ለተጨማሪ አደጋ ታጋልጣለች። ለምን? ምክንያቱም ሰውነቷ በደህና ለመውለድ በሚያስችላት ደረጃ ገና አልዳበረ ይሆናል።
በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ አንዲት እናት በመውለድ
ሳቢያ ሊደርሱ ከሚችሉ የጤና መዘዞች ብታመልጥ እንኳ ወላጅ መሆን የሚያስከትላቸውን ከባድ ኃላፊነቶች መጋፈጥ ይኖርባታል። ብዙ ወጣት ሴቶች ለራሳቸውና ለተወለደው ልጃቸው መተዳደሪያ ማግኘት ካሰቡት በላይ አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል።ከዚህም ሌላ መንፈሳዊና ስሜታዊ መዘዞች አሉ። ንጉሥ ዳዊት የፈጸመው ወሲባዊ ኃጢአት ከአምላክ ጋር የነበረውን ወዳጅነት በአደጋ ላይ ጥሎት መንፈሳዊ ጥፋት ሊያስከትልበት ተቃርቦ ነበር። (መዝሙር 51) ዳዊት በመንፈሳዊ ቢያገግምም እንኳን በቀሪ ሕይወቱ ኃጢአቱ ያስከተለበትን መዘዝ ለመቀበል ተገድዷል።
በዛሬው ጊዜም ወጣቶች ተመሳሳይ ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል። ለምሳሌ ያህል ሼሪ ገና በ17 ዓመት ዕድሜዋ ከአንድ ልጅ ጋር ወሲባዊ ቅርርብ ፈጠረች። የሚወዳት መስሏት ነበር። ይህ ከሆነ ዓመታት ቢያልፉም እንኳን ድርጊቷ እስካሁንም ድረስ ይቆጫታል። “የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አቅልዬ በመመልከቴ መዘዙን ለመቀበል ተገድጃለሁ። ከሁሉ የከፋው ደግሞ የይሖዋን ሞገስ ማጣቴ ነበር” በማለት በምሬት ትናገራለች። ትሪሽ የተባለች የ23 ዓመት ወጣትም በተመሳሳይ ጥፋቷን በማመን “በሕይወቴ የፈጸምኩት ትልቅ ስህተት ቢኖር ከጋብቻ በፊት ወሲብ መፈጸሜ ነው። እንደገና ድንግል ለመሆን ላደርገው የምችለው ነገር ቢኖር ኖሮ ደስ ይለኝ ነበር” ብላለች። አዎን፣ ስሜታዊ ቁስሎች ለዓመታት ሊዘልቁና ጭንቀትና የሕሊና ስቃይ ሊያስከትሉ ይችላሉ።
ራስን የመግዛት ባሕርይ ማዳበር
ወጣቷ ሻንዳ “ከጋብቻ በኋላ ካልሆነ በቀር ሊጠቀሙበት እንደማይችሉ እያወቀ አምላክ ለወጣቶች ወሲባዊ ፍላጎትን ለምን ሰጣቸው?” በማለት አስፈላጊ የሆነ ጥያቄ አንስታለች። ወሲባዊ ፍላጎት በተለይ “በአፍላ ጉርምስና” ወቅት በጣም ኃይለኛ ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:36 NW) እንዲያውም በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ድንገት ሳይታሰብ የወሲብ ስሜት መነሳሳት ሊያጋጥማቸው ይችላል። ይሁንና ይህ በራሱ መጥፎ አይደለም። የመዋለጃ አካላት መዳበራቸውን የሚያሳይ ተፈጥሯዊ ነገር ነው። *
ይሖዋ ወሲባዊ ግንኙነት አስደሳች እንዲሆን አድርጎ የፈጠረው መሆኑም እውነት ነው። ይህም ሰዎች በመዋለድ ምድርን እንዲሞሉ ከነበረው የመጀመሪያ ዓላማው ጋር የሚስማማ ነው። (ዘፍጥረት 1:28) ይሁንና አምላክ የመዋለድ ችሎታ የሰጠን አላግባብ እንድንጠቀምበት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ የገዛ ሰውነቱን በቅድስናና በክብር መያዝ እንዳለበት እንዲያውቅ ነው” ይላል። (1 ተሰሎንቄ 4:4) ወሲባዊ ስሜት በተሰማህ ቁጥር ፍላጎትህን ለማርካት መነሳት አንድ ሰው ባናደደህ ቁጥር ከመማታት ጋር የሚተካከል የቂልነት ተግባር ነው።
ወሲባዊ ግንኙነት ተገቢው ጊዜ ሲደርስ ማለትም አንድ ሰው ሲያገባ የሚደሰትበት ከአምላክ የተሰጠ ስጦታ ነው። ከጋብቻ ውጪ በወሲብ ለመደሰት ስንሞክር አምላክ ምን ይሰማዋል? ለአንድ ጓደኛህ ስጦታ ገዝተሃል እንበል። ይሁንና ጓደኛህ ስጦታውን ከመስጠትህ በፊት ሰርቆ ቢወስደው በሁኔታው አትበሳጭም? አንድ ሰውም ከጋብቻ በፊት ወሲብ ፈጽሞ አምላክ በሰጠው ስጦታ አላግባብ ሲጠቀምበት አምላክ ምን እንደሚሰማው ልትገምት ትችላለህ።
ታዲያ በጾታ ስሜትህ ረገድ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? እቅጩን ለመናገር ስሜትህን እንዴት እንደምትቆጣጠር ተማር። “እግዚአብሔር በቅንነት የሚሄዱትን፣ መልካም ነገር” እንደማይነፍጋቸው ለራስህ ደጋግመህ ንገረው። (መዝሙር 84:11) ጎርደን የተባለ አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል:- “ከጋብቻ በፊት ወሲብ መፈጸም ያን ያህል መጥፎ እንዳልሆነ ማሰብ ስጀምር ስለሚያስከትላቸው መንፈሳዊ መዘዞች ስለማሰላስል ከይሖዋ ጋር ያለኝን ዝምድና እስክሠዋ ድረስ ልቋምጥለት የሚገባ ምንም ዓይነት የኃጢአት ድርጊት እንደሌለ እገነዘባለሁ።” ራስን መግዛት ቀላል ላይሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ወጣቱ አድሪያን እንደሚያሳስበን “ራስን መግዛት ከዚህ በፊት በፈጸማችሁት ድርጊት ምክንያት በጥፋተኝነት ስሜት ወይም በጸጸት ከመሰቃየት ነፃ ሆናችሁ ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑት ነገሮች ላይ እንድታተኩሩ ስለሚያስችላችሁ ንጹሕ ሕሊና ያስገኝላችኋል እንዲሁም ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖራችሁ ያደርጋል።”—መዝሙር 16:11
ከማንኛውም ዓይነት ‘ዝሙት እንድትርቁ’ የሚያስገድዱ አሳማኝ የሆኑ በርካታ ምክንያቶች አሉ። (1 ተሰሎንቄ 4:3) ይህ ሁልጊዜ ቀላል እንደማይሆን አይካድም። ወደፊት የሚወጣው ርዕስ ‘ራስህን በንጽሕና ልትጠብቅ’ የምትችልባቸውን ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ መንገዶች ይዘረዝራል።—1 ጢሞቴዎስ 5:22
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
^ አን.11 ዝሙትን፣ ርኩሰትንና ልቅ ምግባርን በሚመለከት በጥቅምት 22, 1993 ንቁ! (እንግሊዝኛ) እትም ላይ የወጣውን “የወጣቶች ጥያቄ . . . አንድ ሰው ገደቡን አልፎ ሄዷል ሊባል የሚችለው መቼ ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
^ አን.20 በየካቲት 8, 1990 ንቁ! (እንግሊዝኛ) እትም ላይ የወጣውን “የወጣቶች ጥያቄ . . . ይህ በሰውነቴ ላይ እየደረሰ ያለው ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አንድ ወጣት በየትኛውም ዓይነት ዝሙት ተካፋይ ከሆነ በአምላክ ፊት እንደ ድንግል ሊቆጠር ይችላል?
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከጋብቻ በፊት ወሲብ መፈጸም የአንድን ፈሪሃ አምላክ ያለው ወጣት ሕሊና ሊያቆስል ይችላል
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከጋብቻ በፊት ወሲብ የሚፈጽሙ ራሳቸውን በጾታ ግንኙነት ለሚተላለፉ በሽታዎች ያጋልጣሉ