በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የቤተሰብ ራስ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

የቤተሰብ ራስ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

የቤተሰብ ራስ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ‘የሴት ራስ ወንድ ነው’ ይላል። (1 ቆሮንቶስ 11:3፤ ኤፌሶን 5:23) ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት አለን የሚሉ በርካታ ሰዎች ግን ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ጊዜ ያለፈበት ብቻ ሳይሆን አደገኛም ነው ይላሉ። አንድ ባልና ሚስት “ሴቶች [ለባሎቻቸው] ‘በአክብሮት መገዛት’ እንዳለባቸው የሚገልጸው ሕግ ገደብ ካልተበጀለት አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ጭቆና ያስከትልባቸዋል” ሲሉ ገልጸዋል። የራስነት ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀም እየተስፋፋ መሆኑ የሚያሳዝን ነው። አንዲት ደራሲ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል “በበርካታ አገሮች ሚስትን መደብደብ እንደ ተፈጥሮ ሕግ ይቆጠራል፤ የወንዶች የበላይነት በመዝሙሮች፣ በምሳሌያዊ አነጋገሮችና በሠርግ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ይወደሳል።”

አንዳንዶች ሰዎችን ወደዚህ ጭካኔ ያመራቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው የራስነት መሠረታዊ ሥርዓት ነው በማለት ይናገራሉ። በእርግጥ ስለ ራስነት ሥልጣን የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ሴቶችን ዝቅ የሚያደርግና በቤት ውስጥ ዓመጽ እንዲፈጸምባቸው የሚያበረታታ ነው? የቤተሰብ ራስ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? *

የራስነት ሥልጣን የመጨቆኛ መሣሪያ አይደለም

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው የራስነት ሥልጣን ከጭቆና ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ፍቅራዊ ዝግጅት ነው። ወንዶች ሴቶችን በጭካኔ መግዛት የጀመሩት ሰዎች በአምላክ አገዛዝ ላይ ባመጹ ጊዜ ነበር። (ዘፍጥረት 3:16) አዳምና ሔዋን ከዔድን ገነት ከተባረሩበት ጊዜ ጀምሮ ወንዶች ብዙውን ጊዜ ሴቶችንና ልጆችን ጨምሮ ሌሎችን በጭካኔ በመግዛት ሥልጣናቸውን ያላግባብ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል።

ይሁን እንጂ ይህ ፈጽሞ የአምላክ ዓላማ አልነበረም። እንዲያውም ይሖዋ ሥልጣናቸውን ያላግባብ የሚጠቀሙ ሰዎችን ይጠላል። ‘ሚስቶቻቸውን ያታልሉ’ የነበሩ እስራኤላውያን ወንዶችን አውግዟቸዋል። (ሚልክያስ 2:13-16) ከዚህም በላይ አምላክ ‘ዐመፃን የሚወዱትን ነፍሱ እንደምትጠላቸው’ ተናግሯል። (መዝሙር 11:5) ስለዚህም ሚስቶቻቸውን የሚደበድቡም ሆኑ የሚበድሉ ሰዎች በምንም መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን ለዓመጽ ተግባራቸው ማሳበቢያ አድርገው ማቅረብ አይችሉም።

ትክክለኛው የራስነት ሥልጣን ምን ዓይነት ነው?

አምላክ ጽንፈ ዓለም ሥርዓት ባለው መንገድ እንዲተዳደር ለማስቻል የራስነትን መሠረታዊ ሥርዓት አቋቁሟል። ከአምላክ በስተቀር ሁሉም ፍጡር የበላይ አለው። የወንዶች ራስ ክርስቶስ ሲሆን ልጆች ደግሞ ለወላጆቻቸው ይገዛሉ፤ እንዲሁም ክርስቲያኖች ሁሉ ለመንግሥታት ተገዢዎች ናቸው። ኢየሱስ እንኳ ለአምላክ ይገዛል።—ሮሜ 13:1፤ 1 ቆሮንቶስ 11:3፤ 15:28፤ ኤፌሶን 6:1

ሥርዓታማና የተረጋጋ ኅብረተሰብ እንዲኖር ዜጎች ለባለ ሥልጣናት መገዛታቸው አስፈላጊ ነው። በተመሳሳይም ለቤተሰብ ራስ ተገዥ መሆን ጠንካራ፣ ደስተኛና ሰላማዊ ቤተሰብ ለመመሥረት ያስችላል። በቤተሰብ ውስጥ ባል ወይም አባት አለመኖሩ በዚህ ጉዳይ ላይ ለውጥ አያመጣም። እንዲህ ባሉ ቤተሰቦች ውስጥ እናት የራስነቱን ቦታ ትይዛለች። አባትም እናትም በሌሉበት ቤት ውስጥ ደግሞ ታላቅ ልጅ ወይም ዘመድ የቤተሰብ ራስነት ቦታውን ሊይዝ ይችላል። ያም ሆነ ይህ የቤተሰቡ አባላት ለቤተሰቡ ራስ ተገቢውን አክብሮት ማሳየታቸው ጥቅም ያመጣላቸዋል።

የራስነትን መሠረታዊ ሥርዓት ከመቃወም ይልቅ ራስ ለሆነው ሰው ለመገዛት መጣጣርና ለሥልጣን ተገቢውን አመለካከት ማዳበር ይበልጥ የተሻለ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ክርስቶስ . . . [የ]ቤተክርስቲያን ራስ እንደሆነ ሁሉ” ክርስቲያን ባሎችም የቤተሰባቸው ራስ እንደሆኑ ገልጿል። (ኤፌሶን 5:21-23) ጳውሎስ ክርስቶስ ጉባኤውን የያዘበት መንገድ የራስነት ሥልጣንን በአግባቡ በመጠቀም በኩል ፍፁም ምሳሌ እንደሚሆን አመልክቷል። ክርስቶስ በዚህ ረገድ የተወው ምሳሌ ምንድን ነው?

ኢየሱስ መሲሕና የወደፊቱ ንጉሥ ሆኖ በአምላክ በቀጥታ የተሾመ እንዲሁም ከደቀ መዛሙርቱ በእጅጉ የሚልቅ ጥበብና የሕይወት ተሞክሮ የነበረው ቢሆንም አፍቃሪ፣ ለሰው አዛኝና ርኅሩኅ ነበር። ጨካኝ፣ ጥብቅ ወይም ከሰዎች ብዙ የሚጠብቅ አልነበረም። ሥልጣኑን በኃይል አልተጠቀመበትም፤ እንዲሁም ላገኘው ሁሉ የአምላክ ልጅ እንደሆነ በመናገር ሰዎችን ለማስደመም አልሞከረም። ኢየሱስ ትሑትና በልቡ የዋህ ነበረ። በመሆኑም ‘ቀንበሩ ልዝብ ሸክሙም ቀላል’ ሊሆን ችሏል። (ማቴዎስ 11:28-30) ስለዚህም ሊቀረብ የሚችልና ምክንያታዊ ነበር። እንዲያውም ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ‘ራሱን አሳልፎ እስከሚሰጥ ድረስ’ ቤተ ክርስቲያንን እንደወደደ ተናግሯል።—ኤፌሶን 5:25

የቤተሰብ ራሶች የኢየሱስን ምሳሌ መኮረጅ የሚችሉት እንዴት ነው?

የቤተሰብ ራሶች የክርስቶስን ባሕርያት ማንፀባረቅ የሚችሉት እንዴት ነው? ኃላፊነት የሚሰማው የቤተሰብ ራስ ለቤተሰቡ አካላዊና መንፈሳዊ ደኅንነት ያስባል። የቤተሰቡ አባላት በተናጠልና በጋራ ለሚያስፈልጋቸው ነገር ተገቢውን ጊዜና ትኩረት ለመስጠት ጥረት ያደርጋል። ከራሱ ይልቅ የትዳር ጓደኛውንና የልጆቹን ፍላጎት ያስቀድማል። * (1 ቆሮንቶስ 10:24፤ ፊልጵስዩስ 2:4) ባል በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶችና ትምህርቶች በሥራ ላይ በማዋል የሚስቱንና የልጆቹን አክብሮት እንዲሁም ድጋፍ ማግኘት ይችላል። የባልየው ፍቅራዊ አመራር ቤተሰቡ የሚያጋጥመውን ማንኛውንም ፈተና በጋራ እንዲወጣ ያስችለዋል። እንዲህ ባለ ቅዱስ ጽሑፋዊ መንገድ የራስነት ሥልጣኑን የሚጠቀም ባል ለይሖዋ ክብርና ምስጋና የሚያመጣ ደስተኛ ቤተሰብ መገንባት ይችላል።

በተጨማሪም ጥበበኛ የሆነ የቤተሰብ ራስ ትሑት ነው። እንዳልተሳሳተ ቢሰማውም እንኳ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ይቅርታ ለመጠየቅ አያንገራግርም። እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ “ብዙ አማካሪዎች” ባሉበት መዳን እንዳለ ይገልጻል። (ምሳሌ 24:6) አዎን፣ ትሑት የሆነ የቤተሰብ ራስ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሚስቱንና ልጆቹን ሐሳብ ይጠይቃል፤ እንዲሁም የሚሰጡትን አስተያየት ግምት ውስጥ ያስገባል። አንድ የቤተሰብ ራስ የኢየሱስን ምሳሌ ከተከተለ በቤተሰቡ ውስጥ ደስታና መረጋጋት የሚሰፍን ከመሆኑም በላይ የቤተሰብ መሥራች ለሆነው ለይሖዋ አምላክ ክብርና ውዳሴ ያመጣል።—ኤፌሶን 3:14, 15

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 ምንም እንኳን ይህ ርዕሰ ትምህርት ባልና አባት በቤተሰብ ውስጥ ባለው ሚና ላይ ያተኮረ ቢሆንም ነጠላ የሆኑ እናቶች እንዲሁም ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን የሚያሳድጉ ወላጅ የሌላቸው ልጆች ከዚህ ትምህርት ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ።

^ አን.14 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀው ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለው መጽሐፍ ለቤተሰብ ፍቅራዊ እንክብካቤ ማድረግ የሚቻልባቸውን ተግባራዊ የሆኑ ምክሮች ይዟል።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ምክንያታዊ የሆነ ባል ሚስቱና ልጆቹ የሚሰጡትን አስተያየት ግምት ውስጥ ያስገባል