“ፈጣሪህን አስብ”
“ፈጣሪህን አስብ”
“የጭንቀት ጊዜ ሳይመጣ፣ ‘ደስ አያሰኙኝም’ የምትላቸው ዓመታት ሳይደርሱ፣ በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን አስብ።”—መክብብ 12:1
ከላይ የተጠቀሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ትልቅ ቁምነገር ይዟል። ወጣትነት ተመልሶ የሚመጣ ነገር አይደለም። የጉርምስና ዕድሜህ ካለፈ በኋላ ያለፉትን ዓመታት በደስታና በእርካታ ወይም በጸጸትና በምሬት ወደኋላ መለስ ብለህ ማስታወስህ አይቀርም። ታዲያ አንተ የትኛው ሁኔታ ይገጥምህ ይሆን? መጨረሻህ ያማረ እንዲሆን ከወዲሁ ምን ልታደርግ ትችላለህ?
ከላይ እንደተጠቀሰው መጽሐፍ ቅዱስ “ፈጣሪህን አስብ” በማለት ጥብቅ ማሳሰቢያ ይሰጣል። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹትን የአምላክ ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች በመጠበቅና በማክበር ነው። እንዲህ ሲባል ከማንኛውም ዓይነት ደስታ ርቀህ የመናኝና የሃይማኖታዊ አክራሪነት ኑሮ ትኖራለህ ማለት አይደለም። እንዲያውም ፈጣሪህን ማሰብ ልትገምተው ከምትችለው የበለጠ ትልቅ ደስታ ያስገኝልሃል። እንዴት እንዲህ ሊሆን ይችላል?
ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት አንድ መኪናና የመንጃ ፈቃድ ተሰጥቶሃል እንበል። ብዙ ደስታ ሊያስገኝልህ የሚችል አስደሳችና አዲስ ዓይነት ነጻነት አገኘህ ማለት ነው። እንዴት ወዳሉ ቦታዎች ልትሄድ እንደምትችል አስብ! ይሁን እንጂ ይህ አዲስ ነጻነት ከባድ ኃላፊነትም ያስከትልብሃል። በምታሽከረክርበት ጊዜ የትራፊክ ምልክቶችን፣ የፍጥነት መጠኖችንና የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን የመሰሉትን የትራፊክ ሕጎች ማክበር ይኖርብሃል። ታዲያ ይህ ኃላፊነት መኪና በማሽከርከር ለምታገኘው ደስታ እንቅፋት ይሆንብሃል? በፍጹም! እንዲያውም ላንተው ጥበቃ ነው። አደጋ ምንም የሚያስደስት ነገር የለውም።
ፈጣሪህ ይሖዋ አምላክ በሰጠህ ነጻነት ረገድም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ሙሉ ሰው ወደ መሆን እያደግህ ስትሄድ ሕይወትህን እንዴት እንደምትጠቀምበት የራስህን ምርጫ እንድታደርግ ነጻነት ይሰጥሃል። (ዘዳግም 30:19፤ ምሳሌ 27:11) ይህ እንዴት ትልቅ መብት ነው! ይሁን እንጂ ከዚህ ጋር አብሮ የሚመጣ ከባድ ኃላፊነት አለ። ይሖዋ በቃሉ ውስጥ ልናከብረው የሚገባ ‘የትራፊክ ሕግ’ አስፍሮልናል። እነዚህ ሕግጋት ለደስታህ እንቅፋት ይሆኑብሃል? በፍጹም አይሆኑም! ከዚህ ይልቅ በዛሬው ጊዜ ብዙ ወጣቶች ከሚያጋጥማቸው ችግርና መከራ ይጠብቁሃል።
በአሁኑ ጊዜ በ30ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የሚገኘው
ፌዴሪኮ ይህን ሐቅ በተግባር ተመልክቷል። በወጣትነቱ የትምህርት ቤት ጓደኞቹ እርሱ ሊያደርጋቸው የማይገቡትን ብዙ ነገሮች ሲያደርጉ ተመልክቷል። “እንዲሁ ሲታይ እንደልባቸው የፈለጉትን በማድረግ እየተደሰቱ ያሉ ይመስላል። እኔ ግን እውነተኛ ደስታ እንደሌላቸው አውቅ ነበር” ይላል። ፌዴሪኮ ወደኋላ መለስ ብሎ ሲመለከት በጉርምስና ዕድሜው በመጽሐፍ ቅዱስ ሕግጋት በመመራቱ ደስ ይለዋል። “እርግጥ ነው፣ እንደ ማንኛውም ወጣት የሚፈታተኑኝ ችግሮች አጋጥመውኛል። ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ከብዙ ችግር ጠብቆኛል። በተጨማሪም ከአጠገቤ ሆኖ የሚረዳኝ ክርስቲያን ወዳጅ አጥቼ አላውቅም። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን መከተል ልገምተው ከምችለው የበለጠ ደስታ አጎናጽፎኛል” ይላል።ይሖዋ አምላክ ደስተኛ እንድትሆን፣ አዎን እውነተኛ ደስታ እንድታገኝ ይፈልጋል። ይህ ደስታ የውስጥ ምሬትና ሐዘን መሸፈኛ ከሆነ ተራ ፈንጠዝያ በጣም የበለጠ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “በወጣትነትህ ጊዜ ደስ ይበልህ፣ በወጣትነትህም ዘመን ልብህ ደስ ያሰኝህ” ይላል። ይሁን እንጂ ይኸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የሚያክለው ማስጠንቀቂያ አለ። “እግዚአብሔር ወደ ፍርድ እንደሚያመጣህ ዕወቅ” ይላል።—መክብብ 11:9
አምላክ የሰጠህን ነጻነት በጥበብ በመጠቀም ፈጣሪህን አስብ። ይህን ብታደርግ ፈጣሪህም እንደሚያስብህ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔር በረከት ብልጽግናን ታመጣለች፤ መከራንም አያክልባትም” ይላል።—ምሳሌ 10:22
የይሖዋ ምሥክሮች፣ ወጣቶች በጉርምስና ዕድሜ የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች እንዲቋቋሙ ለመርዳት ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ መልሶቻቸው የተባለ ባለ 320 ገጽ መጽሐፍ አዘጋጅተዋል። እስካሁን ድረስ ይህ መጽሐፍ በ77 ቋንቋዎችና በ34 ሚሊዮን ቅጂዎች ታትሟል። በአቅራቢያህ የሚገኙትን የይሖዋ ምሥክሮች በመጠየቅ የዚህን መጽሐፍ ቅጂ ማግኘት ትችላለህ።
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጉርምስና ዕድሜህ የተሳካ እንዲሆን
ጊዜ ወስደህ የአምላክን ቃል አንብብ
በአገልግሎት በትጋት ተሳተፍ
ከመጥፎ ባልንጀርነት ራቅ
ከወላጆችህ ጋር የተቀራረበ ግንኙነት ይኑርህ
[ምንጭ]
የብሮሹሩ ሽፋን:- Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.