በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማጭበርበር—ዓለም አቀፍ ችግር

ማጭበርበር—ዓለም አቀፍ ችግር

ማጭበርበር—ዓለም አቀፍ ችግር

ዌይን ይባላል። ቁመናው ያማረና በአነጋገሩ ረጋ ያለ ሰው ነው። ካረን ባሏ እንዲሆን የምትፈልገው ደግሞ እንዲህ ዓይነት ሰው ነው። “አምላክን ስለምንና ስመኘው የነበረው ዓይነት ሰው ነበር” ትላለች ካረን። “ያየን ሰው ሁሉ ፍጹም ተስማሚ ባልና ሚስት እንደምንሆን አድርጎ ያስብ ነበር። ዌይን እኔን ከመውደዱ የተነሳ ሊያመልከኝ የሚፈልግ ሁሉ ይመስለኝ ነበር።”

ይሁን እንጂ አንድ ችግር ነበር። ዌይን በአውስትራሊያ የስለላ ድርጅት ውስጥ በሦስተኛ ደረጃ የሚገኝ ባለ ሥልጣን እንደሆነ ለካረን ነገራት። ሥራውን መልቀቅ ፈልጎ ነበር፤ ሆኖም ስለ ስለላ ድርጅቱ እንቅስቃሴ ብዙ ምሥጢር ስለሚያውቅ ሥራውን ከለቀቀ ይገድሉታል! ስለዚህ ሁለቱም አንድ ላይ ሆነው እቅድ ነደፉ። ተጋብተው ንብረቶቻቸውን በአንድ ላይ ካዋሀዱ በኋላ ወደ ካናዳ ለመጥፋት ተስማሙ። ካረን ቤቷንና የነበራትን ንብረት ሁሉ ሸጠችና ገንዘቡን ለዌይን ሰጠችው።

ጋብቻው በታቀደው መሠረት ተከናወነ። ዌይን ካረንን በባንክ ከቀራት ስድስት ዶላር የማይሞላ ገንዘብ ጋር ብቻዋን ትቷት አገሩን ለቆ ተሰወረ። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ካረን እሷን ለማታለል ብቻ ተብሎ በተጎነጎነ የውሸት መረብ እንደተተበተበች ደረሰችበት። ራሱን ለእሷ ብቻ እንደተፈጠረ ልዩ ሰው አድርጎ ያቀረበው ሆን ብሎ ነበር። የነገራት የኋላ ታሪኩ፣ ፍላጎቱ፣ ባሕርይውና ለእሷ ያለው ይመስል የነበረው ፍቅር ሁሉ የእሷን አመኔታ ለማትረፍ ተብሎ የተፈጠረ ውሸት የነበረ ሲሆን ይህ አመኔታ ከ200,000 የአሜሪካ ዶላር በላይ ኪሳራ አስከትሎባታል። አንድ የፖሊስ መኮንን “ስሜቷ እጅግ ተጎድቷል። የተታለለችውን ገንዘብ ተወውና የደረሰባት የስሜት ስቃይ ይህ ነው የሚባል አይደለም” በማለት ተናግሯል።

ካረን “አሁን ሁሉ ነገር ተመሰቃቅሎብኛል። እኔ እንደምወደው ዓይነት ሰው ሆኖ የቀረበኝ ግለሰብ ለካስ በምናብ የተፈጠረ ነበር” በማለት ተናግራለች።

ይሁን እንጂ ካረን በዓለም አቀፍ ደረጃ የማጭበርበር ወንጀል ሰለባ ከሚሆኑት ቁጥር ስፍር ከሌላቸው ሰዎች መካከል አንዷ ብቻ ናት። በማጭበርበር ወንጀል ከሌሎች ላይ የሚወሰደው ገንዘብ መጠን በትክክል ባይታወቅም በመቶ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሲሆን አኃዙ በየዓመቱ እየጨመረ ይሄዳል። እንደ ካረን ያሉ የማጭበርበር ወንጀል ሰለባ የሆኑ ሰዎች ከሚደርስባቸው የገንዘብ ኪሣራ በተጨማሪ የሚያምኑት ሰው መጠቀሚያ እንዳደረጋቸው ሲገነዘቡ ስሜታቸው በእጅጉ ይጎዳል።

አስቀድሞ መጠንቀቅ ከሁሉ የተሻለው ነው

ማጭበርበር “አስመስሎ በመቅረብ፣ በማምታታት ወይም የውሸት ቃል በመግባት አታልሎ ገንዘብ መውሰድ” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። የሚያሳዝነው ነገር ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ ዓይነቱን ሆን ተብሎ የተፈጸመ የማጭበርበር ወንጀል በማስረጃ ማረጋገጥ አስቸጋሪ ስለሆነ ጥፋተኛው ሕግ ፊት ቀርቦ አይቀጣም። ብዙዎቹ አጭበርባሪዎች ሕግ ፊት እንዲቀርቡ በማያደርጋቸው መንገድ ሰዎችን እንዴት ማታለል እንደሚችሉ አሳምረው ስለሚያውቁ ከሕግ አንጻር ሊያስኬዱ የሚችሉ ማምለጫ ቀዳዳዎችን ሁሉ ጥሩ አድርገው ይጠቀሙባቸዋል። ከዚህም በላይ አንድን አታላይ ሕግ ፊት ማቅረብ የሚጠይቀው ጊዜና ገንዘብ እንዲህ የዋዛ አይደለም። ሕግ ፊት ቀርበው የሚፈረድባቸውም ቢሆኑ አብዛኛውን ጊዜ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሲሰርቁ የኖሩ ወይም በጣም ገሃድ የሆነ አንድ ከፍተኛ የማጭበርበር ወንጀል የሠሩ ናቸው። የማጭበርበር ወንጀሉን የፈጸመው ሰው ተይዞ ቢቀጣ እንኳ የወሰደውን ገንዘብ አውድሞት ወይም እንዳይገኝ ደብዛውን አጥፍቶት ሊሆን ይችላል። በመሆኑም የማጭበርበር ወንጀል የተፈጸመባቸው ሰዎች የተወሰደባቸውን ገንዘብ መልሰው የሚያገኙት ከስንት አንዴ ነው።

በአጭሩ የማጭበርበር ወንጀል ተፈጽሞብህ ከሆነ መፍትሔ የማግኘትህ ጉዳይ የመነመነ ነው። በማጭበርበር የተወሰደብህን ገንዘብ መልሰህ ለማግኘት መላ ከማፈላለግ ይልቅ የተሻለው ነገር መጀመሪያውኑ እንዳትታለል መጠንቀቅ ነው። አንድ ጠቢብ ሰው ከረዥም ጊዜ በፊት “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል፤ ብስለት የጐደለው ግን በዚያው ይቀጥላል፤ መከራም ያገኘዋል” ሲል ጽፏል። (ምሳሌ 22:3) የሚቀጥለው ርዕስ የማጭበርበር ወንጀል ሰለባ እንዳትሆን ራስህን መጠበቅ የምትችልባቸውን መንገዶች ያብራራል።