ስለ እምነታቸው በድፍረት የተናገሩ ወጣቶች
ስለ እምነታቸው በድፍረት የተናገሩ ወጣቶች
በይሖዋ ምሥክሮች መካከል በርካታ ወጣቶች ይገኛሉ። እነዚህ ወጣቶች አምላክን የሚወዱ ከመሆኑም በላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት የጽድቅ መሥፈርቶቹ ለመመላለስ ይጥራሉ። በእምነታቸው የሚኮሩ ሲሆን በትምህርት ቤት ስለ ሃይማኖታቸው በግልጽ ይናገራሉ። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።
▪ ሆሊ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ በነበረችበት ወቅት እሷና የክፍል ጓደኞቿ “ኃይል ሳይጠቀሙ ሽብርተኝነትን እንዴት ማስወገድ ይቻላል?” በሚል ርዕስ ሪፖርት እንዲያቀርቡ የቤት ሥራ ተሰጥቷቸው ነበር። ሆሊ ይህን አጋጣሚ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተመሠረተው የወደፊት ተስፋዋ ለመጻፍ ተጠቀመችበት። በታሪክ ዘመናት ሁሉ እንደታየው ‘ሰው ሰውን ለመጉዳት ገዢ እንደሆነ’ ተናገረች። (መክብብ 8:9) ከዚያም የሰው ልጅ ብቸኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት መሆኑን ጠቀሰች። “የዚህ መንግሥት ንጉሥ እንዲሆን የተሾመው ኢየሱስ በመሆኑ ሽብርተኝነትን ጨምሮ የሰው ልጅ ችግሮች በሙሉ ይወገዳሉ” በማለት ጻፈች። ከዚያም ሆሊ የትኛውም ሰብዓዊ ገዢ ሊያደርገው ያልቻለውን ነገር ኢየሱስ እንዴት እንደሚያከናውን ስትናገር እንዲህ በማለት ጽፋለች:- “በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ኢየሱስ ምን ዓይነት ገዢ እንደሚሆን አሳይቷል። አፍቃሪና ለሰዎች የሚያስብ ነበር። የታመሙትን በመፈወስና የሞቱትን በማስነሳት ኃይሉን አሳይቷል። የትኛውም ሰብዓዊ መንግሥት ቢሆን የሞቱ ሰዎችን ሊያስነሳ አይችልም። የአምላክ መንግሥት ግን ይህን ማድረግ ይችላል።” ሆሊ ሪፖርቱን የደመደመችው “መፍትሔ ሊያመጣ የሚችለው አምላክ ነው እንጂ ሰዎች አይደሉም” በሚለው ዓረፍተ ነገር ነበር።
መምህሯ በሪፖርቱ ግርጌ ላይ “የሚደነቅ ነው! ግሩም ሪፖርት ነው ሆሊ። ደግሞም በሚገባ የታሰበበት” ብላ ጻፈችላት። ሆሊ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎችንም መጥቀሷ መምህሯን አስገርሟት ነበር። ይህም ሆሊ የይሖዋ ምሥክሮች በየሳምንቱ ስለሚያደርጉት ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ስለሚባለው የመናገርና የማስተማር ሥልጠና የሚሰጥበት ፕሮግራም ለመምህሯ ለመናገር የሚያስችል አጋጣሚ የከፈተላት ሲሆን መምህሯ ይህ ትምህርት ቤት የሚካሄድበትን መጽሐፍ አንድ ቅጂ በደስታ ወስዳለች።
▪ ጄሲካም በትምህርት ቤቷ ሪፖርት ስታዘጋጅ ስለ እምነቷ ለመናገር የሚያስችል አጋጣሚ አግኝታ ነበር። “ስለ እምነቴ ሦስት ጥናታዊ ጽሑፎች ለማዘጋጀት ችያለሁ” ትላለች። “አንደኛው ስለ ይሖዋ ምሥክሮችና ስለ ሃይማኖታዊ መብቶች ነበር። መምህራችን ሊያነበው የፈለገ ሁሉ እንዲያነብበው በትምህርት ቤቱ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ አስቀመጠችው። በቅርቡ ደግሞ ስለ ጥምቀቴና ያ ዕለት በሕይወቴ ውስጥ ምን ያህል ትልቅ ቦታ እንዳለው ሪፖርት ጻፍኩ። ተማሪዎቹ ሪፖርቱን አጠናቅቀው ከመስጠታቸው በፊት ረቂቁን እርስ በርስ እየተለዋወጡ ስለሚያነቡ የክፍል ጓደኞቼ ሪፖርቴን የማንበብ አጋጣሚ አግኝተው ነበር። አንዲት ተማሪ ‘ጥሩ ሪፖርት ነው ያዘጋጀሽው። የይሖዋ ምሥክር መሆን ምን ምን ኃላፊነቶችን እንደሚጨምር ማወቁ ጠቃሚ ነው። በመጠመቅሽ እንኳን ደስ አለሽ!’ ብላኛለች። አንዲት ልጃገረድ ደግሞ ‘የጻፍሽው ታሪክ በጣም ግሩም ነው! እንዲህ ያለ ጠንካራ እምነት ስላለሽ ደስ ብሎኛል!’ ብላለች። ሌላ ልጅ ደግሞ ‘አስተዋይ ነሽ። እንኳን ደስ አለሽ!’ በማለት ጽፏል።”
▪ ሜሊሳ የ11 ዓመት ልጅ ሳለች ስለ እምነቷ ለመናገር የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ አግኝታ ነበር። “የትምህርት ቤቱ ነርስ በሳይንስ ክፍለ ጊዜ ስለ ሰውነታችን የበሽታ መከላከያ ዘዴ ልታስተምረን መጥታ ነበር። በትምህርቱ ወቅት ደም የመውሰድ ጉዳይ ተነሳ። ክፍለ ጊዜው ሲያበቃ ለሳይንስ መምህሬ ደምን በሚመለከት ስለተዘጋጀው የቪዲዮ ፊልማችን ነገርኩት። በቀጣዩ ቀን ፊልሙን ወደ ትምህርት ቤት ይዤ ሄድኩና ለመምህሬ ሰጠሁት፤ እርሱም ቤት ወስዶ ከቤተሰቡ ጋር ተመለከተው። በሚቀጥለው ቀን ይዞት መጣና እኔ የምማርበትን ክፍል ጨምሮ ሁለት ክፍሎች እንዲመለከቱት አደረገ። ከዚያም ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ አስተያየት የሰጠ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች ከፍተኛ ጥረት ባያደርጉ ኖሮ ያለ ደም የሚሰጡ የሕክምና አማራጮችን በቀላሉ ማግኘት አስቸጋሪ ይሆን እንደነበር ተናገረ። የቪዲዮ ፊልሙን ሲመልስልኝ ‘ለትምህርት ቤቱ ቤተ መጻሕፍት የሚሆን አንድ ቅጂ እንዴት ማግኘት እችላለሁ?’ በማለት ጠየቀኝ። የቪዲዮ ካሴቱን አንድ ቅጂ ሰጠሁት። በዚህም ከልቡ የተደሰተ ሲሆን እኔም በጣም ደስ ብሎኛል!”
እንደ ሆሊ፣ ጄሲካና ሜሊሳ ሁሉ ሌሎች በርካታ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮችም ፈጣሪያቸውን እንዲያስቡ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ይከተላሉ። (መክብብ 12:1) አንተስ ይህን ምክር ትከተላለህ? ከሆነ የይሖዋን ልብ እንደምታስደስት እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—ምሳሌ 27:11፤ ዕብራውያን 6:10
ወጣቶች ስለ እምነታችሁ ለክፍል ጓደኞቻችሁና ለመምህራኖቻችሁ ስትናገሩ ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ዓላማው ትልቅ ምሥክርነት ለመስጠት ያስችላችኋል። እንዲህ ማድረጋችሁ እምነታችሁን የሚያጠነክረው ከመሆኑም በላይ ከአምላክ አገልጋዮች መካከል የመሆን መብት በማግኘታችሁ ጤናማ ኩራት እንዲያድርባችሁ ያደርጋል። (ኤርምያስ 9:24) በትምህርት ቤት መመስከራችሁ ጥበቃም ይሆንላችኋል። ጄሲካ ይህን ስትገልጽ እንዲህ ትላለች:- “ስለ እምነቴ መናገሬ ካሉት ጥቅሞች አንዱ ተማሪዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጩ ነገሮችን እንድፈጽም ተጽዕኖ አያደርጉብኝም።”
[በገጽ 12 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ሆሊ
[በገጽ 12, 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ጄሲካ
[በገጽ 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ሜሊሳ