በሰርከስ ዓለም ያሳለፍኩት ሕይወት
በሰርከስ ዓለም ያሳለፍኩት ሕይወት
በጆን ስሞሊ እንደተነገረው
“ክቡራትና ክቡራን እንዲሁም በማንኛውም እድሜ ላይ የምትገኙ ልጆች በዓለም ታላቅ ወደሆነው ትርኢት እንኳን ደህና መጣችሁ!” የሰርከሱ ዋና አዘጋጅ የሚናገራቸው እነዚህ ቃላት ለታዳሚዎቹ አስደሳች የሆነው የእንስሳት፣ የአስቂኝ ተዋናዮችና ጅምናስቲክ የሚያሳዩ ሰዎች ትርኢት ሊጀምር መሆኑን የሚያበስሩ ነበሩ። በሪንግሊንግ ወንድማማቾችና የባርነም እና የቤሊ ሰርከስ ማሳያ ድርጅት ውስጥ ለሚሠራው ለእኔ ቤተሰብ ግን ሌላ የሥራ ክፍለ ጊዜ መጀመሩን የሚገልጹ ቃላት ነበሩ።
የተወለድኩት በ1951 ነው። ከተወለድኩ ጀምሮ “ከጫማዬ ውስጥ ሰጋቱራ ጠፍቶ አያውቅም” ለማለት ይቻላል፤ ይህ አባባል በሰርከስ ማሳያው ድንኳን ወለል ላይ ሁልጊዜ የሚነሰነሰውን ሰጋቱራ ያመለክታል። እኔና ወንድሜ ቆመን መሄድ ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ የሰርከስ ትርኢቶች ተካፍለናል።
ወላጆቼ ሃሪ እና ቢአትሪስ እኔ ከመወለዴ በፊት በክላይድ ቢቲ የሰርከስ ድርጅት ውስጥ መሥራት ጀምረው ነበር። እናቴ ዘፋኝ የነበረች ሲሆን ሙሉ ለሙሉ የሜክሲኮ ባህላዊ ልብስ ለብሳ የስፓንኛ ዘፈን ትዘፍን ነበር። አባቴ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሙዚቃ ጓድ መሪና የሙዚቃ ደራሲ ከነበረው ከጆን ፊሊፕ ሱዛ ጋር አብሮ በሙዚቀኛነት ተጫውቷል። ከዚያም በ1950ዎቹ ታዋቂ በሆነው በሪንግሊንግ ወንድማማቾች ባንድ ውስጥ ቱባ በተባለ የትንፋሽ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋችነት ለመቀጠር ቻለ፤ ይህን አጋጣሚ ያገኘው ከሱዛ ጋር በመሥራቱ ሳይሆን አይቀርም።
በየጊዜው በተለያዩ የሰርከስ ቡድኖች ውስጥ ሠርተናል፤ በመጨረሻ በዩናይትድ ስቴትስ ታዋቂ እየሆነ በመጣው የአል ጂ ኬሊ እና የሚለር ወንድማማቾች የሰርከስ ድርጅት ውስጥ መሥራት ጀመርን። ይህ የሰርከስ ድርጅት ሦስት ትልልቅ ድንኳኖች ነበሩት። በአንደኛው ድንኳን ውስጥ አንበሶች፣ ነብሮች፣ ጅቦች እና ሌሎችም ብርቅዬ የዱር እንስሳት ይኖሩበት ነበር።
ሁለተኛውን ድንኳን ደግሞ ተጨማሪ የሰርከስ ማሳያ ብለን እንጠራው ነበር፤ በአብዛኛው እዚህ ድንኳን ውስጥ ሰይፍ የሚውጡ የሚያስመስሉ፣ የወንድም የሴትም ጾታ አላቸው የሚባሉ፣ ድንኮች፣ ግዙፍ የሆኑና ሌሎችም ያልተለመደ አካላዊ ሁኔታ ያላቸው ሰዎች ትርኢት ይታይ ነበር። የተለያየ ሁኔታ ካላቸው ሰዎች ጋር መኖር ለእኛ ለልጆች ጥሩ ትምህርት የሚሰጥ ነገር ነበር። አንዳንዶች ለእነዚህ ሰዎች መጥፎ ቅጽል ስም ይሰጧቸው የነበረ ቢሆንም ለእኛ ግን እንደ ቤተሰቦቻችን ነበሩ። በዓመት ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ አብረናቸው እናሳልፍ ነበር።
ሦስተኛው ድንኳን ደግሞ ዋነኛው የሰርከስ ማሳያ ሲሆን በውስጡ ትርኢት ለመሥራት የሚያገለግሉ ሦስት መድረኮች ነበሩት፣ ትርኢቱ በሦስቱም መድረኮች ላይ በአንድ ጊዜ ይካሄድ ነበር። በአብዛኛው በጣም አደገኛ የሆነ ወይም በጣም አስደናቂ የሆነ ትርኢት የሚታየው በመካከለኛው መድረክ ላይ ነው።
በሰርከስ ዓለም የነበረን ውሎ
እኔና ወንድሜ የጅምናስቲክ ትርኢት ማሳየት የጀመርነው ገና ከልጅነታችን ጀምሮ ነው። በዋይልድ ዌስት ትርኢትም ላይ እንደ አሜሪካ ሕንዳውያን ሕፃናት ሆነን እንሠራ ነበር። በትርኢቱ ላይ ይካፈሉ የነበሩ የአገሩ ተወላጆች የሆኑ የቾክታው ጎሳ አባላት የአሜሪካ ሕንዶችን ዳንስ አስተምረውን ነበር።
የዕለቱን እንቅስቃሴ በአብዛኛው የምንጀምረው ከጠዋቱ 12 ሰዓት ነበር። በዚያን ሰዓት ወደሚቀጥለው ከተማ ለመሄድ ዝግጅት ማድረግ እንጀምራለን። ሁሉም ተዋናዮች የሰርከሱን ማሳያ ቦታ በመንቀል፣ በማጓጓዝና መልሶ በመገጣጠም ሥራ ይካፈሉ ነበር። ለምሳሌ አባቴ ከሙዚቀኛነት ሥራው በተጨማሪ ሰባት ዝሆኖች የያዘ ትልቅ መኪና ይነዳ ነበር። አንዳንድ ጊዜ እኔ፣ እናቴና ወንድሜ በዚህ ትልቅ መኪና አብረነው እንጓዝ ነበር።
በአብዛኛው በየዕለቱ ወደ አዳዲስ ቦታዎች በመሄድ በቀን ሁለት ጊዜ ትርኢታችንን እናሳያለን። እሁድ ግን ሙዚቃና ድራማ ብቻ ስለምናሳይ የምሽቱን የእረፍት ክፍለ ጊዜ ከቤተሰቦቻችን ጋር ማሳለፍ እንችላለን። አባቴ በዚያን ቀን ሁልጊዜ ከቤተሰቡ ጋር አንድ ለየት ያለ ነገር ያደርጋል፤ ሚልክሼክ (የሚጠጣ ነገር) ለመግዛት ወደ ከተማ እንወጣለን ወይም መኪና ውስጥ ቁጭ ተብሎ ፊልም የሚታይበት ቦታ እንሄዳለን።
ሰርከስ ማዘጋጀት ብዙ ሥራ ይጠይቃል። ዝሆኖቹ ሳይቀሩ በሥራው ይሳተፉ ነበር። እንዴት? የሦስቱን ድንኳኖች ረጃጅም ምሰሶዎች እንዲጎትቱ ይደረጋል። አንዱ የምሰሶው ጫፍ በድንኳኑ ላይ ባለው ቀለበት ውስጥ ይገባል፤ ከዚያም ዝሆኑ ሌላውን የምሰሶ ጫፍ ይዞ ቀጥ ብሎ እስኪቆም ድረስ ይጎትተዋል። ሁሉም ምሰሶዎች ከቆሙና ለመብራት የምንጠቀምበት ጀነሬተር ከተስተካከለ በኋላ ለከሰዓቱ ትርኢት ራሳችንን እናዘጋጃለን።
አዳዲስ ችሎታዎችን መማር
በከሰዓት በኋላውና በምሽቱ ትርኢት ማሳያ ሰዓቶች መሃል በነበረው ጊዜ በሰርከስ ቡድኑ ውስጥ የታቀፍነው በርካታ ልጆች መሬት ሳይነኩ መገለባበጥ፣ አየር ላይ በተወጠረ ገመድ ላይ መራመድ፣ በርከት ያሉ ነገሮችን በአንድ ጊዜ ማንቀላለብና ከዥዋዥዌ ገመድ ላይ መወንጨፍ እንለማመድ ነበር። ያስተምሩን ከነበሩት ሰዎች አብዛኞቹ አያት ቅድመ አያቶቻቸው የሰርከስ ተጫዋቾች የነበሩ ቀደምት የቡድኑ አባላት ናቸው። በአየር ላይ መገለባበጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተማረኝን አንድ ጣሊያናዊ አስታውሳለሁ። ይህን ስጀምር አራት ዓመት ገደማ ይሆነኝ ነበር። መጀመሪያ ላይ እንዳልወድቅ በቀበቶ ታስሬ እንድለማመድ ያደርግ ነበር፤ ከዚያም ከጎን ከጎኔ እየሮጠ በእጁ ብቻ ይደግፈኝ ጀመር። በመጨረሻ በእጁም መደገፉን አቆመና ራሴን ችዬ መገለባበጥ ቻልኩ።
አደጋ የደረሰብኝ በሰርከስ ማሳያው ውስጥ ዙሪያውን በሰልፍ በምንዞርበት ጊዜ ብቻ ነው። እኔና ወንድሜ ሁለት ዝንጀሮዎችን ይዞ ይጓዝ ከነበረ አስቂኝ ትርኢት ከሚያሳይ ሰው ኋላ ነበርን፤ ከኋላችን ደግሞ የዝሆን መንጋ ነበር። እጄን እያውለበለብኩ በመራመድ ላይ ሳለሁ አንደኛው ዝንጀሮ በመደንገጡ እጄን ያዘና በኃይል ነከሰኝ። ደግነቱ ቁስሉ አላመረቀዘም፤ አሁን ድረስ ግን በግራ እጄ ላይ ብዙም የማይታይ ጠባሳ አለብኝ። ይህም የዱር እንስሳት ምንም ያህል ቢያምሩና ለማዳ ቢመስሉ ሁልጊዜ ጠንቃቃ መሆን እንደሚያስፈልግ እንዳስታውስ ያደርገኛል።
ጠቃሚ ትምህርቶች አግኝቻለሁ
ሰርከስ ለቤተሰባችን ሕይወት እንቅፋት ሆኖብን አያውቅም። ወላጆቻችን ጊዜ መድበው ግብረ ገብ ያስተምሩን የነበረ ከመሆኑም በላይ ጥሩ ጥሩ መመሪያዎችን ይሰጡን ነበር። አባቴ ጉልበቱ ላይ አስቀምጦኝ ከእኔ የተለየ ዘር ወይም አስተዳደግ ላላቸው ሰዎች መሠረተ ቢስ ጥላቻ ሊያድርብኝ እንደማይገባ የሰጠኝን ምክር እስከ አሁን ድረስ አስታውሳለሁ። ከእኔ የተለየ አካላዊ ሁኔታ ከነበራቸው ሰዎች ጋር ብቻ ሳይሆን የተለያየ ዜግነት ካላቸው ሰዎች ጋር እኖር ስለነበር ምክሩ በጣም ጠቅሞኛል።
እናቴም ብትሆን ጥሩ ምሳሌያችን ነበረች። ሰርከስ ማሳያ ቦታው አንዳንድ ጊዜ በሰው ይሞላ ነበር፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ብዙ ሰዎች አይኖሩም። እናቴ እንዲህ ትለን ነበር:- “ትርኢት የምታሳዩት ሰዎችን ለማስደሰት ነው እንጂ (እያጨበጨበች) ለገንዘብ ብላችሁ አይደለም። ታዳሚዎቹ በመቶዎች የሚቆጠሩም ሆኑ ጥቂት አቅማችሁ የፈቀደውን ሁሉ አድርጉ።” ይህን ምክር ፈጽሞ አልረሳውም። ወደ ሰርከሱ የመጡት ሰዎች ብዙም ሆኑ ጥቂት አሳቢነት ማሳየት እንዳለብን መግለጿ ነበር።
እኔና ወንድሜ ትርኢት ከማሳየታችንም በተጨማሪ ፕሮግራሙ ካለቀ በኋላ በሰርከስ ማሳያ ቦታው የወዳደቁ ቆሻሻዎችን በማንሳት በጽዳት ሥራው መርዳት ይጠበቅብን ነበር። ይህም ጥሩ ሥልጠና ሆኖልን ነበር።
ከሚያዝያ እስከ መስከረም ድረስ ሰርከስ የምናሳየው ከቦታ ቦታ እየተጓጓዝን ስለነበር እንደ ሌሎቹ ተማሪዎች መማር አንችልም ነበር። ክረምቱን ደግሞ በኦክላሆማ፣ ህዩጎ ከተማ በሚገኘው በዋናው መሥሪያ ቤት እናሳልፋለን። በዚህ ጊዜ ለአምስት ወራት ገደማ ትምህርት እንማራለን። የክረምቱን ወቅት በህዩጎ የሚያሳልፉ ሌሎች የሰርከስ ቡድኖችም ነበሩ፤ ስለዚህ የእኛ ዓይነት ሁኔታ የነበራቸው በርካታ ልጆች ነበሩ። የከተማው የትምህርት ጉዳይ የሚመለከተው አካል የእኛን ልዩ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የተለየ ዝግጅት አደረገልን።
ሕይወታችንን የለወጠው ዕለት
መስከረም 16, 1960 አባቴ ከጠዋቱ አሥራ አንድ ሰዓት ገደማ ላይ ከእንቅልፉ ተነሳና ለጉዞ ያዘገጃጀን ጀመር። በዚያን ቀን እናቴ አባቴ በሚነዳው ዝሆን በጫነው ትልቅ መኪና ሳይሆን የሰርከስ ድርጅቱ ባዘጋጀው መጓጓዣ እንድንሄድ ወሰነች።
እኔና ወንድሜ ለሰርከስ ማሳያነት በታሰበው አዲሱ ቦታ ላይ እንደደረስን አካባቢውን እየዞርን መቃኘት ጀመርን። ከዚያም አንድ ሰው እየጮኸ “ከባድ አደጋ ደርሷል። ስሞሊ እና የሰርከሱ ኃላፊ በአደጋው ሞተዋል” ሲል ሰማን። በእርግጥ መጀመሪያ ‘እውነት ሊሆን አይችልም። የተሳሳቱት ነገር አለ’ ስል አስቤ ነበር። በኋላ ግን እናታችን አደጋው የደረሰበት ቦታ እንደሄደች አወቅኩ። አባቴ በካሊፎርኒያ፣ ፕላሰርቪል ከተማ በሚገኝ ተራራ ስር ባለ አውራ ጎዳና ላይ እየነዳ እያለ ፍሬኑ መሥራቱን አቆመ። የዝሆኖቹ ክብደት ተሳቢው ሚዛኑን ስቶ ወደ ጎን እንዲዞር አደረገው። በዚህ ጊዜ የመኪናው ዋነኛ የነዳጅ ጋን በመጨፍለቁ ፈነዳ፤ ወዲያውም አባቴና አብሮት ሲጓዝ የነበረው የሰርከሱ ኃላፊ ሞቱ። በዚያን ዕለት በጣም ነበር ያዘንኩት። ከአባቴ ጋር በጣም እቀራረብ የነበረ ሲሆን የልብ ወዳጆችም ነበርን።
የሰርከሱ ትርኢት የሚታይበት ጊዜ እስኪያበቃ ድረስ ሌሎቹ አባላት ጉዟቸውን ቀጥለው የነበረ ቢሆንም እኛ አባባን በትውልድ ከተማው በሚዙሪ፣ ሪች ሂል ከቀበርን በኋላ ክረምቱን ወደምናሳልፍበትና ዋናው መሥሪያ ቤት ወደሚገኝበት ኦክላሆማ፣ ህዩጎ ተመለስን። በዚህ ወቅት እኔና ወንድሜ በመደበኛ የትምህርት ክፍለ ጊዜ መማር ጀመርን። ይህ ለእኛ አዲስ ነገር ነበር። እንዲህም ሆኖ ከኬሊ ሚለር የሰርከስ ቡድን ጋር አብረን የምንጓዝበትን የሚቀጥለውን የሰርከስ ማሳያ ጊዜ በጉጉት እንጠባበቅ ነበር። ነገር ግን ሕይወታችን ባልታሰበ መንገድ ተለወጠ።
ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አወቅን
አንድ ቀን ከትምህርት ቤት ስመለስ እናቴ መጽሐፍ ቅዱስን ልታስጠናን ቤት ከመጣች ሴት ጋር አስተዋወቀችኝ። ሴትየዋ ጂሚ ብራውን የምትባል የይሖዋ ምሥክር ነበረች። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ምንም ፍላጎት አልነበረኝም። ለዓመታት ሳልመው የነበረው ነገር ወደ ሰርከስ ቡድኑ ተመልሼ በዥዋዥዌ ገመድ ላይ ጅምናስቲክ የመሥራት ችሎታን መማር ነበር። እኔና ወንድሜ በሰርከስ ማሳያ ቦታ ላይ ካለው ጋር የሚመሳሰል የዥዋዥዌ ገመድ በሁለት ዛፎች ላይ አስረን ልምምድ እናደርግ ነበር። ቢሆንም ሁላችንም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በህዩጎ ያሉ ስምንት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ይገኙበት ከነበረ ከአንድ ራቅ ብሎ የሚገኝ ቡድን ጋር መሰብሰብ ጀመርን። ከጥቂት ጊዜ በኋላ እናቴ የሰርከስ ድርጅቱን ለመልቀቅና በጥናቷም ለመግፋት ወሰነች። በጣም ባዝንም ውሳኔዋን ተቀበልኩ። በተለይ የሰርከስ ቤተሰባችን አባላት የነበሩት ወደ ቤታችን ሲመጡና ለምን አብረናቸው እንደማንሠራ ሲጠይቁን በውሳኔያችን መጽናት በጣም ይከብደን ነበር።
እስከዚያን ጊዜ ድረስ ከሰርከስ ሌላ ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም። በአንድ ወቅት አባታችን ሲሠራው ለነበረው ነገር ጀርባችንን የሰጠን ያህል ሆኖ ተሰምቶኝ ነበር። ይሁንና የእርሱ ሞት መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ምክንያት ሆኖኝ ነበር፤ ትኩረቴን በዋነኝነት ከሳቡት ነገሮች አንዱ የትንሣኤ ተስፋ ነበር። ይህ ተስፋ አሁንም ድረስ ለእኔ ሕያው ነው። አምላክ ቃል በገባልን ራእይ 20:12-14
ምድራዊ ገነት ውስጥ አባቴ ትንሣኤ በሚያገኝበት ጊዜ በመጀመሪያ ከሚቀበሉት ሰዎች መካከል መሆን እፈልጋለሁ።—የይሖዋ ምሥክር የሆኑ አንድ ባልና ሚስት በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ትልቅ ቤተሰብ እንዳለ እንድንገነዘብ ረዱን። ይህ ነገር እውነት ሆኖ አግኝተነዋል! ትንሽ የነበረው የይሖዋ ምሥክሮች ቡድን በርካታ ቤተሰቦች በአንድነት አምልኳቸውን የሚያከናውኑበት ጉባኤ ሆኗል። መንፈሳዊ ልጃቸው አድርገው ያሳደጉኝን ሮበርትና ካረል ኤነልኻርት የተባሉ ባልና ሚስትንም መጥቀስ እፈልጋለሁ። በአሥራዎቹ እድሜ ውስጥ ሳለሁ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ጥብቅ የሆኑ ምክሮችና መመሪያዎች ይሰጡኝ ነበር።
የጎለመሱ ክርስቲያኖች የሚያሳዩት ይህን የመሰለ ፍቅር የብቸኝነትን ስሜት ለማሸነፍ ይረዳል። ክርስቲያን ሆኜ ባሳለፍኳቸው ጊዜያት ሁሉ ይህ ነገር እውነት መሆኑን በተለያዩ መንገዶች ማየት ችያለሁ። ባለፉት ዓመታት በኦክላሆማ እና በቴክሳስ ኖሬያለሁ፤ በሁሉም ጉባኤዎች በርካታ አፍቃሪ ወንድሞችና እህቶችን ተዋውቄያለሁ። በእድሜ ከገፉት ወንድሞች አንዳንዶቹ አባታዊ የሆነ መመሪያና ማበረታቻ ይሰጡኝ ነበር። አዎን፣ መንፈሳዊ አባቶች ሆነውልኛል።
እንደገና መጓዝ
ከጥቂት ዓመታት በፊት እናቴ በሞት አንቀላፍታለች። እስከ ሕይወቷ ፍጻሜ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን አጥብቃ የምትከተል ታማኝ ክርስቲያን ነበረች። አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹን ከሞት በሚያስነሳበት ጊዜ እሷም እንደምትነሳና የደስታው ተካፋይ እንደምትሆን አምናለሁ። እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ያገኘሁት ቤተሰብ ትልቅ መጽናኛ ሆኖልኛል።
በተለይ ከአምላክ ሕዝቦች መሃል ባለቤቴን ኤድናን በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። ከተጋባን በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማሩ ሥራ በሙሉ ጊዜ ለመካፈል እንድንችል ሁኔታችንን አስተካከልን። ለመኖር የሚያስፈልጉንን ነገሮች ለማግኘት በጀማሪ የቴሌቪዥን ዘጋቢነት ተቀጠርኩ። በዚህ የሥራ መስክ ልምድም ሆነ ሥልጠና አልነበረኝም፤ ሆኖም በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር ያገኘሁት ሥልጠና ለሥራው ብቁ እንድሆን አስችሎኛል። ቆይቶም በሬዲዮ ጣቢያ ውስጥ የዜና ክፍል ኃላፊ ሆንኩ። ግቤ ግን በመገናኛ ብዙኃን ዘንድ ታዋቂነት ማግኘት አልነበረም። በመሆኑም እኔና ኤድና የአምላክ አገልጋዮች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት በየትኛውም ቦታ ሄደን መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር ራሳችንን አቀረብን።
በ1987 የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ የይሖዋ ምሥክሮችን ጉባኤዎች እንድጎበኝ ግብዣ ቀረበልኝ። ለዚህ ሥራ ራሴን በፈቃደኝነት በማቅረብ የተለያዩ ጉባኤዎችን በየሳምንቱ እጎበኛለሁ፤ መጽሐፍ ቅዱስን ከማስተማሩ ሥራችን ጋር በተያያዘ ለመንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ ማበረታቻና ማሠልጠኛ እሰጣለሁ። አሁን መንፈሳዊ ቤተሰቤ በጣም አድጓል። ምንም እንኳን እኔና ባለቤቴ ልጆች ባንወልድም በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ብዙ መንፈሳዊ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ማፍራት ችለናል።
ከበርካታ ዓመታት በኋላ እንደገና ከከተማ ወደ ከተማ እየተጓዝኩ በመሥራት ላይ እገኛለሁ። ሥራዬ ሰርከስ ከማሳየት ወደ ተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ተቀይሯል! አንዳንድ ጊዜ በዥዋዥዌ ገመድ ላይ የጅምናስቲክ ትርኢት ለመሥራት የነበረኝን ግብ በእርግጥ ዳር ማድረስ እችል ነበር? እያልኩ አስባለሁ። መሬት ሳልነካ በአየር ላይ በመገለባበጥ የተዋጣልኝ የጅምናስቲክ ስፖርተኛ ለመሆን የነበረኝ የልጅነት ሕልምስ በእርግጥ እውን ሊሆንልኝ ይችል ነበር? እያልኩ ማሰቤም አልቀረም። ይሁን እንጂ አምላክ ምድርን ገነት እንደሚያደርግ ስለገባው ቃል ሳስብ እነዚህ ሐሳቦች ከአእምሮዬ በፍጥነት እልም ብለው ይጠፋሉ።—ራእይ 21:4
እርግጥ ነው፣ ከተወለድኩ ጀምሮ “ከጫማዬ ውስጥ ሰጋቱራ ጠፍቶ አያውቅም” ነበር። ይሁን እንጂ “የምሥራችን የሚያመጡ እግሮች እንዴት ያማሩ ናቸው!” የሚሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት አስታውሳለሁ። (ሮሜ 10:15) ሰዎችን ስለ አምላክ እንዲያውቁ የመርዳት መብት ማግኘት ሰርከስ በመሥራት ላገኘው ከምችለው ከማንኛውም ነገር ይበልጣል። የይሖዋ በረከት እርካታ የሞላበት ሕይወት እንድመራ አስችሎኛል።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የተወሰኑ የሰርከስ “ቤተሰባችን” አባላት፤ እንዲሁም አባቴ ቱባ የተባለውን የትንፋሽ የሙዚቃ መሣሪያ ይዞ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአሁኑ ጊዜ ከባለቤቴ ከኤድና ጋር