አምላክ በእርግጥ ለልጆች ያስባል?
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
አምላክ በእርግጥ ለልጆች ያስባል?
በየዓመቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ልጆች ጉልበታቸው አላግባብ ይበዘበዛል፣ ግፍ ይፈጸምባቸዋል እንዲሁም የኃይል ጥቃት ይደርስባቸዋል። ብዙዎቹ ልክ እንደ ባሪያ ደም እስኪተፉ ይሠራሉ። ሌሎች ደግሞ ታፍነው ይወሰዱና ወታደር አሊያም ዝሙት አዳሪ እንዲሆኑ ይገደዳሉ። ብዙ ልጆች በገዛ ዘመዶቻቸው በጾታ ይነወራሉ እንዲሁም አሰቃቂ ግፎች ይፈጸሙባቸዋል።
ቅንና አሳቢ የሆኑ ሰዎች በልጆች ላይ የሚደርሰው ይህ ሥቃይ እንደሚያሳስባቸው እሙን ነው። በልጆች ላይ ለሚደርሰው በደል ዋነኛው መንስኤ የሰዎች ራስ ወዳድነትና ሕገ ወጥነት መሆኑ ቢታወቅም አንዳንዶች አፍቃሪ የሆነው አምላክ በልጆች ላይ እንዲህ ያለ ግፍ ሲፈጸም ዝም ብሎ መመልከቱ አይዋጥላቸውም። አምላክ እነዚህን ልጆች እንደተዋቸውና ስለ እነርሱ ፈጽሞ እንደማያስብ ይሰማቸው ይሆናል። ይህ አባባል እውነት ነው? ሕፃናት ጉልበታቸው አላግባብ መበዝበዙና የተለያየ በደል የሚፈጸምባቸው መሆኑ አምላክ እንደማያስብላቸው የሚያሳይ ነው? መጽሐፍ ቅዱስስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?
አምላክ ግፈኞችን ያወግዛል
ይሖዋ አምላክ ልጆች ጨካኝ በሆኑ ሰዎች ጉልበታቸው እንዲበዘበዝ ዓላማው አልነበረም። በልጆች ላይ የሚፈጸመው ግፍ የሰው ልጅ በኤደን ገነት ማመጹ ካስከተላቸው አሳዛኝ መዘዞች አንዱ ነው። ሰዎች በአምላክ ሉዓላዊነት ላይ ማመጻቸው አንዳቸው የሌላውን ዘፍጥረት 3:11-13, 16፤ መክብብ 8:9
ጉልበት እንዲበዘብዙ መንገድ ከፍቷል።—አምላክ የደካሞችንና ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ሰዎችን ጉልበት የሚበዘብዙ ግለሰቦችን ይጠላል። ጥንት የነበሩ ይሖዋን የማያመልኩ በርካታ ብሔራት ልጆቻቸውን መሥዋዕት ያደርጉ ነበር፤ ይሁን እንጂ ይሖዋ ይህ እርሱ ‘ያላዘዘው ከቶም ያላሰበው’ ነገር እንደሆነ ተናግሯል። (ኤርምያስ 7:31) አምላክ ጥንት የነበሩ ሕዝቦቹን እንዲህ ሲል አስጠንቅቋቸው ነበር:- “[አባትና እናት የሌላቸውን ልጆች] ግፍ ብትውሉባቸውና ወደ እኔ ቢጮኹ፣ ጩኸታቸውን በእርግጥ እሰማለሁ። ቁጣዬ ይነሣል።”—ዘፀአት 22:22-24
ይሖዋ ልጆችን ይወዳል
አምላክ ለወላጆች የሰጠው ጥበብ ያለበት መመሪያ ለልጆች ምን ያህል እንደሚያስብ ማረጋገጫ ይሆነናል። ሰላማዊ በሆነና በተረጋጋ ቤት ውስጥ ያደጉ ልጆች በሳልና ሥርዓታማ የመሆን አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው። ፈጣሪያችን “ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ብሎ በመደንገግ የዕድሜ ልክ ጥምረት የሆነውን ጋብቻን ያቋቋመው በዚህ ምክንያት ነው። (ዘፍጥረት 2:24) መጽሐፍ ቅዱስ የጾታ ግንኙነት ማድረግ ያለባቸው የተጋቡ ሰዎች ብቻ መሆናቸውን ይናገራል፤ ይህም ልጆች ቢወለዱ በሥርዓት ማደግ እንዲችሉ አስተዋጽኦ ያደርጋል።—ዕብራውያን 13:4
ቅዱሳን ጽሑፎች ወላጆች ልጆቻቸውን ማሠልጠናቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነም ጭምር ጠበቅ አድርገው ይገልጻሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፤ የማሕፀንም ፍሬ ከቸርነቱ የሚገኝ ነው። በወጣትነት የተገኙ ወንዶች ልጆች፣ በጦረኛ እጅ እንዳሉ ፍላጾች ናቸው።” (መዝሙር 127:3, 4) ልጆች ከአምላክ የተገኙ ውድ ስጦታዎች ናቸው፤ ስለሆነም ተገቢው እንክብካቤ ተደርጎላቸው እንዲያድጉ ይፈልጋል። አንድ ቀስተኛ ቀስቱን በሚወረውርበት ጊዜ ዒላማው ላይ ማነጣጠር እንደሚገባው ሁሉ ወላጆች ለልጆቻቸው ትክክለኛውን የሕይወት አቅጣጫ ማሳየት እንደሚገባቸው አምላክ አጥብቆ አሳስቧቸዋል። የአምላክ ቃል “አባቶች ሆይ፤ እናንተም ልጆቻችሁን አታስቈጧቸው፤ ነገር ግን በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጓቸው” ሲል ያዛል።—ኤፌሶን 6:4
አምላክ ለልጆች ያለውን ፍቅር ያሳየበት ሌላው መንገድ ደግሞ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዴት አድርገው ከጨካኝ ሰዎች መጠበቅ እንደሚችሉ በማስተማር ነው። በጥንቷ እስራኤል ጾታን በተመለከተ ትክክልና ስህተት ስለሆነ ምግባር የሚገልጸውን ደንብ ያካተተው የሙሴ ሕግ ሲነበብ ‘ልጆችም’ እንዲያዳምጡ ታዝዘው ነበር። (ዘዳግም 31:12፤ ዘሌዋውያን 18:6-24) አምላክ ወላጆች ልጆቻቸውን ከጉልበት ብዝበዛም ሆነ ከግፍ ለመጠበቅ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ እንዲያደርጉ ይፈልግባቸዋል።
ልጆች ያላቸው ተስፋ
ይሖዋ ለልጆች ያለውን የማይለወጥ ፍቅር ፍፁም ነፀብራቁ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ግሩም በሆነ መንገድ አሳይቷል። (ዮሐንስ 5:19) ሐዋርያቱ ኢየሱስን የጠቀሙ መስሏቸው ወላጆች ትንንሽ ልጆቻቸውን ወደ እርሱ ይዘው እንዳይመጡ በከለከሏቸው ጊዜ በቁጣ እርማት ሰጣቸው። “ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ” አለና “ዐቀፋቸው፤ እጁንም ጭኖ ባረካቸው።” (ማርቆስ 10:13-16) ልጆች በይሖዋ አምላክም ሆነ በልጁ ዓይን ዝቅ ተደርገው አይታዩም።
እንዲያውም አምላክ በሾመው ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ልጆችን ከሚደርስባቸው እንግልት ለመገላገል በቅርቡ እርምጃ ይወስዳል። የዚህ ዓለም ስግብግብ በዝባዦችና ርኅራኄ የሌላቸው ግፈኞች ለዘላለም ይጠፋሉ። (መዝሙር 37:10, 11) መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን የሚፈልጉ የዋህ ሰዎችን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።”—ራእይ 21:3, 4
እስከዚያው ድረስ ግን አምላክ የጉልበት ብዝበዛና ግፍ ለተፈጸመባቸው ሰዎች መንፈሳዊና ስሜታዊ ድጋፍ በማድረግ ፍቅሩን እየገለጸ ነው። እንዲህ ሲል ቃል ገብቷል:- “የጠፉትን እፈልጋለሁ፤ የባዘኑትንም እመልሳለሁ። የተጐዱትን እጠግናለሁ፤ የደከሙትንም አበረታለሁ።” (ሕዝቅኤል 34:16) በቃሉ፣ በቅዱስ መንፈሱና በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት በግፍና በድህነት የተደቆሱትን ልጆች ያጽናናቸዋል። አሁንም ሆነ ወደፊት ‘የርኅራኄ አባት፤ የመጽናናትም ሁሉ አምላክ በመከራችን ሁሉ እንደሚያጽናናን’ ማወቁ እጅግ ያስደስታል።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4
[በገጽ 14 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]
© Mikkel Ostergaard /Panos Pictures