በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እንዳትጭበረበር ጥንቃቄ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

እንዳትጭበረበር ጥንቃቄ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

እንዳትጭበረበር ጥንቃቄ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

“ሐቀኛን ሰው ማታለል አይቻልም” ሲባል ሳትሰማ አትቀርም። ይህ አባባል እንደ ብዙዎቹ አባባሎች ሁሉ ሐሰት ነው። ሐቀኛ ሰዎች በየቀኑ ይጭበረበራሉ፤ ስለዚህ ሐቀኝነት ብቻውን ከመታለል አይጠብቃቸውም። በዓለም ላይ በተንኮል እጅግ የተካኑ ሰዎች የሌሎችን ገንዘብ መቀማት የሚያስችላቸውን ተንኮል ሲሸርቡ እንቅልፍ አጥተው ያድራሉ። ከአንድ መቶ ዓመት በፊት አንድ ደራሲ “አንዳንዶቹ የማጭበርበሪያ ዘዴዎች እጅግ የረቀቁ ስለሆኑ በእነዚህ ዘዴዎች አለመታለል እንደ ጅል ያስቆጥራል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተው ነበር።

ማታለል ረዥም ዘመን ያስቆጠረ ተግባር ሲሆን የጀመረው በኤደን ገነት ነው። (ዘፍጥረት 3:1-5) እስከ አሁን በጣም ብዙ የተለያዩ የማታለያ ዘዴዎች የተፈለሰፉ ሲሆን አዳዲስ ዘዴዎች ደግሞ በየጊዜው ብቅ እያሉ ነው። ታዲያ ራስህን መከላከል የምትችለው እንዴት ነው? ወንጀለኞች ሰዎችን የሚያጭበረብሩባቸውን መንገዶች ሁሉ ለማወቅ መሞከር አያስፈልግህም። አንዳንድ መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን ካወቅህና ከተጠነቀቅህ ራስህን ከዚህ አደጋ በእጅጉ መጠበቅ ትችላለህ።

የግል መረጃዎችህን ጠብቅ

አንድ ሰው የቼክ ደብተርህን ወይም ክሬዲት ካርድህን ከሰረቀብህ የፈለገውን ሊገዛበት ይችላል። የባንክ ሒሳብ መረጃህን ከሰረቀብህ በስምህ ገንዘብ ማውጣትና ቼክ መጻፍ ይችላል። ስለ አንተ የግል ሁኔታ በቂ መረጃ ካገኘ አንተን መስሎ ሊቀርብ ይችላል። አንድ ጊዜ ማንነትህ ተሰረቀ ማለት ደግሞ ወንጀለኛው ከባንክ ሒሳብህ ገንዘብ ሊያወጣ፣ በክሬዲት ካርድ ሒሳብህ ዕቃ ሊገዛና በስምህ ብድር ሊወስድ ይችላል። * ይባስ ብሎ ባልሠራኸውና በማታውቀው ወንጀል ተይዘህ ልትታሠር ትችላለህ!

እንደዚህ ካለው የማጭበርበር ወንጀል ራስህን ለመጠበቅ የባንክ ደብተርህን፣ ቼክህን፣ መንጃ ፈቃድህን፣ ፓስፖርትህን ወይም መታወቂያህን ጨምሮ የግል ሰነዶችህን በሙሉ በጥንቃቄ ያዝ። ለሚመለከታቸው ሕጋዊ ሰዎች ካልሆነ በቀር ገንዘብ ነክም ሆነ ሌሎች የግል መረጃዎችህን ለማንም አታሳይ። በተለይ የክሬዲት ካርድ ቁጥርህንና የባንክ ሒሳብ መረጃህን ለማንም ማሳየት የለብህም። የክሬዲት ካርድ ቁጥርህን መንገር ያለብህ ዕቃ ልትገዛበት ስትፈልግ ብቻ ነው።

እንዲህ ዓይነት መረጃዎችን ለማግኘት ሲሉ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳዎችን አንድ በአንድ የሚበረብሩ አጭበርባሪዎች አሉ። የግል መረጃ የያዘ ወረቀት እንዲሁ ጨምድደህ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ በመጣል ፈንታ ብታቃጥለው ወይም ብትቦጫጭቀው የተሻለ ነው። ይህም ጥቅም ላይ የዋሉ ወይም የተሠረዙ ቼኮችን፣ የሽያጭና የግዢ ደረሰኞችን፣ ያገለገሉ ክሬዲት ካርዶችን፣ ያረጀ መንጃ ፈቃድ ወይም ፓስፖርት የመሳሰሉትን ይጨምራል። ሳትፈልግ በደብዳቤ የተላኩልህ ክሬዲት ካርዶችም አታላይ ሰው እጅ ከገቡ ሊጠቀምባቸው የሚያስችሉትን መረጃዎች ስለያዙ አጥፋቸው እንጂ ከቆሻሻ ጋር አትጣላቸው።

የማመዛዘን ችሎታህን ተጠቀም

ብዙዎቹ በማጭበርበር ወንጀል የተሰማሩ ሰዎች ሀብትህን በአንድ ነገር ላይ ካፈሰስክ ከሚገመተው በላይ ከፍተኛ ትርፍ እንደምትዝቅ አድርገው ሊያሳምኑህ ይጥራሉ። በአቋራጭ ሀብታም መሆን ያስችላል ተብሎ የሚታመንበት አንዱ የማታለያ ዘዴ ፒራሚድ ስኪም ይባላል። ምንም እንኳ ይህ የማጭበርበሪያ ዘዴ ብዙ ዓይነት መልክ ያለው ቢሆንም ብዙውን ጊዜ የተወሰኑ ባለሀብቶች ገንዘባቸውን አንድ ላይ ያቀናጁና የገንዘብ አቅማቸውን ለማሳደግ በሚል ሌሎች ባለሀብቶችን መመልመል ይጀምራሉ። እያንዳንዱ ባለሀብት ሌሎች ባለሀብቶችን በመለመለ መጠን የተወሰነ ገንዘብ ያገኛል። * ይህ ምልመላ ደብዳቤዎችን ለተለያዩ ሰዎች በመላክም የሚከናወን ሲሆን አዳዲሶቹ ተመልማዮች ቀደም ብለው በአባልነት ለተመዘገቡት ሰዎች የተወሰነ ገንዘብ እንዲልኩ ይጠየቃሉ። አዳዲሶቹ አባላት ከእነሱ በኋላ ብዙ ሰዎች እንዲመዘገቡ ካደረጉ በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚያገኙ ቃል ይገባላቸዋል።

ይሁን እንጂ ሁልጊዜ አዳዲስ አባሎችን በመመልመል መቀጠል ስለማይቻል ይህ ዘዴ አንድ ደረጃ ላይ ሲደርስ መክሸፉ አይቀርም። የሚከተለውን ስሌት ተመልከት። ይህን ዘዴ አምስት ሰዎች ሆነው ቢጀምሩትና እያንዳንዳቸው ሌሎች አምስት አምስት ሰዎችን ቢመለምሉ ጠቅላላ ቁጥራቸው 25 ይሆናል። እነዚህ ደግሞ እያንዳንዳቸው አምስት አምስት ሰዎች ቢያስገቡ ቁጥራቸው 125 ይደርሳል። ሌሎችን የመመልመል ሂደቱ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የሚሰባሰቡ ሲሆን እነዚህ ደግሞ በተራቸው ከዘጠኝ ሚሊዮን የሚበልጡ ሌሎች ሰዎችን መመልመል ሊኖርባቸው ነው! ይህን ዘዴ በዋነኝነት የሚያቀናብሩት ሰዎች ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሰዎችን መመልመል የማይቻልበት ደረጃ ላይ እንደሚደረስ አሳምረው ያውቃሉ። ተጨማሪ ሰዎችን መመልመል ወደማይቻልበት ደረጃ ላይ እንደተደረሰ ሲገነዘቡ ገንዘቡን ይዘው ይጠፋሉ። አንተም ገንዘብህን ልታጣ ትችላለህ። እንዲሁም የመለመልካቸው ሰዎች ያወጡትን ገንዘብ እንድትመልስላቸው ሊጠይቁህ ይችላሉ። እንግዲህ በዚህ ዓይነቱ አሠራር አንተ ገንዘብ እንድታገኝ ከተፈለገ መክሰር ያለበት ሰው መኖር እንዳለበት አስታውስ።

አንድ ሰው በትንሽ ጥረት ገንዘብ እንደምታገኝ ወይም ባወጣኸው ገንዘብ ከፍተኛ ትርፍ እንደምትዝቅ ለማሳመን እያግባባህ ነው? ታገኝበታለህ የሚልህ ገንዘብ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ለማመን አዳጋች ከሆነ በእርግጥም ማመን የለብህም፤ ውሸት ሊሆን ስለሚችል መጠንቀቅ ይበጃል። በማስታወቂያ ላይ የሚለፈፈውን ወይም አንዳንድ ሰዎች አገኘን እያሉ የሚያወሩትን በማመን “ይኼ እንኳ ማጭበርበር የለበትም” ብለህ ለመደምደም አትቸኩል። መቼም ሰዎች አንተን በገንዘብ ለማበልጸግ ወይም የምትከብርበትን ምሥጢር ለማካፈል ብለው ሥራ እንደማይጀምሩ ማመዛዘን አይሳንህም። አንድ ሰው አንተን ባለጠጋ ለማድረግ የሚያስችል ልዩ እውቀት እንዳለው ቢነግርህ ‘ይህን ልዩ እውቀት ራሱን ባለጠጋ ለማድረግ ለምን አልተጠቀመበትም? እኔን ለማግባባት በመሞከር ጊዜውን ለምን ያጠፋል?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ።

አንድ ውድድር እንዳሸነፍክ ወይም ሽልማት እንዳገኘህ ቢነገርህስ? ይህ አንተን ለማታለል የተሸረበ ተንኮል ሊሆን ስለሚችል ለመፈንደቅ አትቸኩል። በዚህ ተንኮል ብዙዎች ተታልለዋል። ለምሳሌ ያህል በእንግሊዝ አገር የምትኖር አንዲት ሴት ሽልማት እንዳገኘች፣ ሆኖም ሽልማቱን እጅዋ ለማስገባት 25 ዶላር መላክ እንደሚያስፈልጋት የሚገልጽ ደብዳቤ ከካናዳ ደረሳት። ገንዘቡን ከላከች በኋላ እንደገና ከካናዳ የስልክ ጥሪ ደረሳትና 245,000 ዶላር የሚያስገኝ የሦስተኛ ደረጃ የሎተሪ ዕጣ እንዳሸነፈች ሆኖም ይህን ለማግኘት የገንዘቡን አንድ በመቶ መክፈል እንዳለባት ተነገራት። እሷም 2,450 ዶላር ላከች። ሆኖም ምንም ሳታገኝ ባዶ እጅዋን ቀረች። “ለነፃ ስጦታ” ወይም ለሽልማት እንድትከፍል ከተጠየቅህ አንተን ለማጭበርበር የተሸረበ ተንኮል መሆኑን እወቅ። ‘እንዴት ባልገባሁበት ውድድር ላሸንፍና ሽልማት ላገኝ እችላለሁ?’ ብለህ ራስህን መጠየቅ አለብህ።

የንግድ ግንኙነትህ ጥሩ ስም ካላቸው ሰዎች ጋር ይሁን

አጭበርባሪ ሰዎችን በቀላሉ ለይተህ ማወቅ የምትችል ይመስልሃል? በፍጹም በዚህ እንዳትሞኝ ተጠንቀቅ! አታላዮች እንዴት አድርገው የሌሎችን አመኔታ ማትረፍ እንደሚችሉ ያውቃሉ። ሊያታልሉት የፈለጉት ሰው እንዴት እምነት እንዲጥልባቸው ማድረግ እንደሚችሉ አሳምረው ያውቃሉ። ሻጮች፣ ሐቀኞች ሆኑም አልሆኑ፣ አንድ ነገር ከመሸጣቸው በፊት ገዢውን ማሳመን እንዳለባቸው ያውቃሉ። እርግጥ ሁሉንም ሰው መጠርጠር አለብህ ማለት አይደለም። ሆኖም ከመታለል ራስህን ለመጠበቅ በመጠኑም ቢሆን መጠርጠርህ አስፈላጊ ነው። የአንድን ሰው ታማኝነት ለማወቅ በስሜትህ ከመመራት ይልቅ ብዙ አጭበርባሪዎች ተለይተው የሚታወቁባቸውን ምልክቶች ተመልከት:- አንደኛ፣ የሚነግርህ ነገር በጣም ጥሩ ከመሆኑ የተነሳ ለማመን የሚያዳግት ነው? ሁለተኛ፣ ቶሎ ብለህ ለመግዛት እንድትወስን በጣም እየገፋፋህ ነው?

በኢንተርኔት አማካኝነትም ለማመን አዳጋች የሆኑ ግብዣዎች በገፍ ይቀርባሉ። ኢንተርኔት አንዳንድ ጠቃሚ ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ ረገድ ብዙ ጥቅም ቢኖረውም ወንጀለኞች በፍጥነትና ማንነታቸው ሳይታወቅ ሌሎችን እንዲያታልሉ ያስችላቸዋል። የኢ-ሜይል አድራሻ አለህ? ካለህ ገና ሳትጠይቅ ከንግድ ጋር የተያያዙ ቁጥር ስፍር የሌላቸው መልእክቶች ሊጎርፉልህ ይችላሉ። ማለቂያ የሌላቸውን ሸቀጦችና አገልግሎቶች ከሚያስተዋውቁት ከእነዚህ መልእክቶች አብዛኞቹ ማታለያዎች ናቸው። እንዲሁ በኢ-ሜይል አድራሻህ የተላከ መልእክት አይተህ አንድ ዕቃ ለመግዛት ወይም አገልግሎት ለማግኘት ብለህ ገንዘብ ብትልክ በምላሹ ምንም ሳታገኝ ልትቀር ትችላለህ። አንድ ነገር ከደረሰህ ደግሞ ያፈሰስክበትን ገንዘብ የሚያወጣ እንዳልሆነ ጥርጥር የለውም። ከሁሉም የሚሻለው በዚህ መንገድ የሚመጡ የንግድ መልእክቶችን አምኖ ምንም ነገር አለመግዛት ነው።

ይህ ሁኔታ ስልክ ደውለው የሆነ ነገር እንድትገዛቸው ግብዣ ለሚያቀርቡ ሰዎችም ይሠራል። ስልክ በመደወል ምርትንና አገልግሎትን ማስተዋወቅ በአብዛኛው ሕጋዊ የሆኑ ነጋዴዎች የሚሠሩበት ዘዴ ቢሆንም አጭበርባሪዎች በዚህ ዘዴ በመጠቀም በያመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ከሰዎች አታልለው ይወስዳሉ። ከደወለልህ ሰው ጋር በስልክ በመነጋገር ብቻ አንድ ሽያጭ ሕጋዊ መንገድ የተከተለ መሆኑን ልታውቅ የምትችልበት መንገድ የለም። አታላዩ ራሱን የባንክ ወይም የክሬዲት ካርድ አገልግሎት ወኪል አድርጎ ሊያቀርብ ይችላል። አንድ ሰው ገንዘብ በምታስቀምጥበት ባንክ ወይም ኩባንያ እንደሚሠራ አድርጎ ስልክ በመደወል ራሱ ባንኩ ወይም ኩባንያው ሊኖረው የሚገባውን መረጃ እንደ አዲስ ከአንተ ለማግኘት መጠየቅ ከጀመረ ይህን ሰው ልትጠረጥር የምትችልበት በቂ ምክንያት አለህ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥምህ የሰውየውን ስልክ ቁጥር ልትጠይቅ ትችላለህ። ከዚያም የሰጠህ ስልክ ቁጥር በትክክል የባንኩ ወይም የድርጅቱ መሆኑን ካረጋገጥክ በኋላ መልሰህ ደውል።

ስልክ ለደወለልህ የማታውቀው ሰው የክሬዲት ካርድ ቁጥርህን ወይም ሌላ ማንኛውንም ዓይነት መረጃ ባትሰጥ የተሻለ ነው። ስልክ ደውሎ የማትፈልገውን ነገር እንድትገዛው ግብዣ ቢያቀርብልህ “ይቅርታ፣ ከማላውቀው ሰው ጋር በስልክ መገበያየት አልፈልግም” ብለህ በትሕትና መልስ በመስጠት ስልኩን ዝጋው። ምናልባት ሊያታልልህ ከሚፈልግ ሰው ጋር የማያስፈልግ ድርድር ውስጥ የምትገባበት ምንም ምክንያት የለም።

የንግድ ግንኙነትህን ከሚታመኑ የንግድ ድርጅቶችና ሰዎች ጋር ብቻ አድርግ። በስልክም ሆነ በኢንተርኔት ምንም ሳትሰጋ የንግድ ግንኙነት ልታደርግ የምትችልባቸው ብዙ ሕጋዊ ኩባንያዎች አሉ። ከተቻለ ስለ ሻጩ ግለሰብ ወይም ኩባንያ ከሌላ ገለልተኛ ምንጭ መረጃ በመጠየቅ አጣራ። ገንዘብህን እንድታፈስበት ስለተጠየቅክበት ነገር መረጃ ጠይቅ፣ ሕጋዊ መንገድ የተከተለ መሆኑን ለማረጋገጥ በጥንቃቄ አንብበው። በማንም ግፊት ቸኩለህ እጅህን አታስገባ።

በጽሑፍ አስፍሩት

አንዳንዴ የማጭበርበር ድርጊት የመፈጸም ሐሳብ የሚመጣው ከጊዜ በኋላ ነው። በሐቀኝነት የተጀመረ ንግድ አክሳሪ ሆኖ ሊገኝ ይችላል። በዚህ ጊዜ ንግዱን የሚያካሂዱት ሰዎች ሊደናገጡና የከሰሩትን ገንዘብ ለማስመለስ የማጭበርበር ወንጀል ወደመፈጸም ሊያመሩ ይችላሉ። ስለገቢያቸውና ትርፋቸው ውሸት የሚናገሩና ከዚያም ንግዱ ሲከስር የቀረውን ገንዘብ አሟጠው በመውሰድ የሚጠፉ ሰዎች እንዳሉ ሳትሰማ አልቀረህም።

ከማጭበርበር ወንጀልም ሆነ በኋላ ከሚፈጠር አለመግባባት ራስህን ለመጠበቅ ማንኛውንም ከፍተኛ ሀብት ማፍሰስ የሚጠይቅ ንግድ ከመጀመርህ በፊት ዝርዝሩን በጽሑፍ አስፍሩት። የምትፈርምበት ማንኛውም ውል የስምምነቱ ደንብና የገባችሁት ቃል በሙሉ በዝርዝር የሰፈረበት ሰነድ ይሁን። ሀብትህን የምታፈስበት ነገር ምንም ያህል አስተማማኝ ቢመስል ነገሮች በታቀደላቸው መሠረት እንደሚሄዱ ማንም ዋስትና ሊሰጥ እንደማይችል መገንዘብ አለብህ። (መክብብ 9:11) ደግሞም የትኛውም ንግድ ኪሣራ ሊያጋጥመው እንደሚችል ማሰብ ግድ ነው። በመሆኑም ንግዱ ቢከስር እያንዳንዱ ሰው ያለበት ግዴታና ኃላፊነት ምን እንደሆነ በስምምነቱ ላይ በዝርዝር መስፈር ይኖርበታል።

እስካሁን ባጭሩ የተወያየንባቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች አውቀህ በሥራ ላይ በማዋል የማጭበርበር ወንጀል ሰለባ ከመሆን ራስህን መጠበቅ ትችላለህ። አንድ የጥንት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ጠቃሚ ምክር ይሰጣል። እንዲህ ይላል:- “ተላላ ሰው ሁሉን ያምናል፤ አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል።” (ምሳሌ 14:15) አጭበርባሪ ሰው የሚያነጣጥረው የሚናገረውን ሁሉ በሚያምኑለት ተላላ ሰዎች ላይ ነው። የሚያሳዝነው ደግሞ ለማጭበርበር ወንጀል በቀላሉ የተጋለጡ ሰዎች ብዙ ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 የመጋቢት 22, 2001 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 19-21 ተመልከት።

^ አን.9 ፒራሚድ ስኪም የሚባለው ይህ ዘዴ “ሰዎች ገንዘብ በመክፈል በአባልነት ከተመዘገቡ በኋላ ሌሎችን በመመልመል የገንዘብ ጥቅም የሚያገኙበት አሠራር ነው።” ይህ ዘዴ አንድን ምርት በመሸጥ ወይም አገልግሎት በመስጠት የገንዘብ ጥቅም የሚገኝበት አሠራር አይደለም።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ታገኝበታለህ የተባልከው ገንዘብ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ለማመን አዳጋች ከሆነ በእርግጥም ማመን የለብህም

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የማጭበርበር ወንጀል ሰለባ ለሆኑ ሰዎች የሚሆን ምክር

የማጭበርበር ወንጀል የተፈጸመባቸው ሰዎች ከልክ በላይ በሆነ የኃፍረትና የጥፋተኝነት ስሜት ይዋጣሉ እንዲሁም በራሳቸው በጣም ይናደዳሉ። አላግባብ ራስህን አትውቀስ። ጥፋተኛው አንተ ሳትሆን ያጭበረበረህ ሰው ነው። አሁን ያለፈው አልፏል ለወደፊቱ ተጠንቀቅ። የማልረባ ሰው ነኝ ብለህ አትደምድም። አጭበርባሪዎች የአገር መሪዎችን፣ የባንክ ሥራ አስኪያጆችን፣ አስተዳዳሪዎችን፣ የፋይናንስ ኃላፊዎችንና ጠበቆችን ጨምሮ በጣም ብልህና አስተዋይ የሆኑ ሰዎችን እንኳ ሳይቀር በማታለል የተዋጣላቸው እንደሆኑ አስታውስ።

የማጭበርበር ወንጀል ሰለባ የሆኑ ሰዎች የሚነጠቁት ገንዘባቸውን ወይም ንብረታቸውን ብቻ ሳይሆን በራስ የመተማመን ስሜታቸውንና ለራሳቸው ያላቸውን ግምትም ጭምር ነው። “ጓደኛ” ብለው ያመኑት ሰው ካታለላቸው ከእንግዲህ ማንንም ሰው አላምንም ብለው ይደመድማሉ። መታለል ስሜትን ይጎዳል። በደንብ እዘንና ይውጣልህ። ብዙውን ጊዜ ለምታምነው ሰው ጉዳዩን ማዋየቱ ሊረዳህ ይችላል። ጸሎትም በእጅጉ ሊያጽናናህ ይችላል። (ፊልጵስዩስ 4:6-8) ይዋል ይደር እንጂ ጉዳዩን መርሳት እንደሚኖርብህ ተረዳ። ሥቃይህን ለምን ታራዝመዋለህ? ጠቃሚ ግቦችን አውጣና ግቦችህ ላይ ለመድረስ ተጣጣር።

ገንዘብህን እናስመልስልሃለን ከሚሉ አታላዮች ተጠንቀቅ። አታላዮች ገንዘብህን ለማስመለስ እንርዳህ ብለው ወደተታለለው ሰው ስልክ ይደውላሉ። ዓላማቸውም ሰውየውን እንደገና ማታለል ነው።

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በኢ-ሜይል የሚላኩ ስድስት የተለመዱ ማታለያዎች

1. ፒራሚድ ስኪም:- እንደዚህ ዓይነቱ ዘዴ ብዙ ሳይለፉ ጥቂት ገንዘብ በማዋጣት ብቻ ከፍተኛ ገንዘብ ማግኘት የሚያስችል እንደሆነ ተደርጎ ይቀርባል። የቡድኑ አባል ለመሆን ክፍያ ካጠናቀቅክና ሌሎች ተሳታፊዎችንም የምትመለምል ከሆነ ኮምፒውተር ወይም ሌላ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ እንደምታገኝ ሊነገርህ ይችላል። ወይም ደግሞ አንተ የቡድኑ አባል እንድትሆንና በተመሳሳይ መንገድ ሌሎችን እንድትመለምል የሚጠይቅ ደብዳቤ ሊደርስህ ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ አሠራር ሕገ ወጥ በመሆኑ አብዛኞቹ ሰዎች ገንዘባቸውን ከስረው ይቀራሉ።

2. በቤትህ ሆነህ እንድትሠራ የሚቀርብልህ ጥያቄ:- ለምሳሌ ያህል ጌጣጌጦችን፣ አሻንጉሊቶችን ወይም እንደነዚህ ያሉ ሌሎች ነገሮችን በመገጣጠም እንድታቀርብ ልትጠየቅ ትችላለህ። እነዚህን ነገሮች ለመገጣጠም ገንዘብህንና ጊዜህን ካጠፋህ በኋላ የጥራት ደረጃቸውን ስላልጠበቁ ተቀባይነት የላቸውም ልትባል ትችላለህ።

3. ከጤናና ከአመጋገብ ጋር የተያያዙ ማታለያዎች:- ኢንተርኔትን ካጥለቀለቁት ነገሮች መካከል የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ወይም ምግብ መቀነስ ሳያስፈልግህ ውፍረት ለመቀነስ ስለሚረዱ ኪኒኖች፣ የወንዶችን ስንፈተ ወሲብ ስለሚፈውሱ መድኃኒቶች፣ የፀጉር መርገፍን ስለሚከላከሉ ቅባቶችና ስለመሳሰሉት የሚገልጹ ማስታወቂያዎች ይገኙበታል። አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ነገሮች ተጠቅመውባቸው ውጤት እንዳገኙባቸው በሚገልጹ ሰዎች ምሥክርነት ታጅበው ይቀርባሉ። እነዚህን ነገሮች ለማስተዋወቅ ከሚቀርቡት የተለመዱ አባባሎች ውስጥ “አዲስ ሳይንሳዊ ግኝት”፣ “ተአምራዊ ፈውስ”፣ “የረቀቀ ቅመማ” እና “ከጥንታዊ ቅመሞች የተሠራ” እንደሚሉት ያሉ ይገኙበታል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ከእነዚህ ምርቶች ውስጥ አብዛኞቹ የተባለውን ውጤት አያስገኙም።

4. የኢንቨስትመንት አማራጮች:- እነዚህ ዘዴዎች ምንም ያህል ኪሣራ ሳያስከትሉ ከፍተኛ ትርፍ ያስገኛሉ የሚባልላቸው ናቸው። ከሚቀርቡት አማራጮች አንዱ ገንዘብን በውጭ አገር ባንክ ማስቀመጥን ይጨምራል። ባለሀብቶቹ ገንዘባቸውን የሚያስቀምጡላቸው ሰዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንደሚያንቀሳቅሱና የረቀቁ የውስጥ መረጃዎች ያሏቸው መሆናቸው ይነገራቸዋል። በዚህም በቀላሉ ይታለላሉ።

5. የክሬዲት ካርድ ማስተካከያ:- ክሬዲት ካርድ ለማግኘት፣ መኪና ለመግዛት የሚያስችል ብድር ለማግኘት ወይም ሥራ ለማግኘት እንድትችል በቀድሞ ክሬዲት ፋይልህ ላይ ያሉትን አሉታዊ መረጃዎች እናሰርዝልህ የሚል ግብዣ ይቀርብልሃል። ምንም ዓይነት ዋስትና ይስጡህ፣ እናስፈጽማለን ባዮቹ የገቡትን ቃል መፈጸም አይችሉም።

6. የዕረፍት ጊዜ ሽልማት:- ከምትጠብቀው በላይ ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ የዕረፍት ጊዜህን ማሳለፍ የሚያስችልህ ዕጣ እንደደረሰህ የሚገልጹ የኢ-ሜይል መልእክቶች ይደርሱሃል። ይህን አጋጣሚ ያገኘኸው አንተ ብቻ እንደሆንክ ይነግሩሃል። ተመሳሳይ የሆኑ ማስታወቂያዎች በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎችም እንደሚላኩና የምታገኘው መስተንግዶ በማስታወቂያው ላይ የተገለጸውን ደረጃ የጠበቀ እንደማይሆን አስታውስ።

[ምንጭ]

ምንጭ:- የዩናይትድ ስቴትስ የፌደራል ንግድ ኮሚሽን

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፒራሚድ ስኪም የሚባለው ዘዴ መጨረሻ ላይ መክሸፉ አይቀርም

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የምትፈርምበት ማንኛውም ውል የስምምነቱ ደንብና የገባችሁት ቃል በሙሉ በዝርዝር የሰፈረበት ሰነድ ይሁን