በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ውሻህን ማሠልጠን የምትችለው እንዴት ነው?

ውሻህን ማሠልጠን የምትችለው እንዴት ነው?

ውሻህን ማሠልጠን የምትችለው እንዴት ነው?

ሜክሲኮ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

“ውሻዬ ስጠራው አይመጣም።” “ውሻዬ በጣም ስለሚጮኽ ጎረቤቶቼ እያማረሩ ነው።” “ውሻዬ በእኔም ሆነ በእንግዶቼ ላይ ዘሎ እየወጣ ያስቸግራል።” ከላይ ያሉትን ቅሬታዎች ያሰሙት ሰዎች “ምን ባደርግ ይሻላል?” በማለት በብስጭት ይጠይቃሉ።

መልሱ ለውሻህ መሠረታዊ የሆኑ ትእዛዞችን ማስለመድ ይኸውም ቀለል ያሉ መመሪያዎችን እንዲታዘዝ ማሠልጠን ነው። ውሻህ ገና ቡችላ እያለ ሥልጠናውን መጀመሩ የተሻለ ቢሆንም ከፍ ያሉ ውሾችም ሊማሩ ይችላሉ። በሜክሲኮ የሚኖረውና ውሾችን በማሠልጠን ሞያ የተሰማራው ማርኮስ እንዲህ ይላል:- “ለሥልጠና የምንቀበላቸው ውሾች ቢያንስ አራት ወር በዛ ከተባለ ደግሞ አምስት ዓመት የሆናቸው ናቸው። ያም ሆኖ አሥር ዓመት ለሆናቸው ውሾችም መሠረታዊ የሆነ ሥልጠና ሰጥቻለሁ።”

ውሾች የሚሰጣቸውን ሥልጠና በመቀበል ረገድ ጎበዞች ናቸው። የሠለጠኑ ውሾች አደገኛ ዕጾችን እንዲሁም ፈንጂዎችን አነፍንፈው ማግኘት፣ የአካል ጉዳተኞችን መርዳትና በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወይም የጠፉ ሰዎችን ፈልገው ማግኘት ይችላሉ። ሆኖም ውሻህ እንዲታዘዝህ ማሠልጠን የምትችለው እንዴት ነው?

ተፈጥሯዊ ባሕርያቸውን ማወቅ

በመጀመሪያ ስለ ውሻህ ተፈጥሯዊ ባሕርይ ማወቅ ይኖርብሃል። እንደ ተኩላዎች ሁሉ ውሾችም የሥልጣን ተዋረድ አላቸው። በተፈጥሯቸው በቡድን የመኖር ዝንባሌ ያላቸው ሲሆን ቡድኑን የሚመራ አንድ ውሻ ይኖራል። ውሻህ ቤተሰብህን የሚያየው እንደ አንድ ቡድን አድርጎ ነው፤ ስለዚህ የቡድኑ መሪ አንተ መሆንህን ማወቅ አለበት።

በተኩላዎች መንጋ ውስጥ መሪው የሚተኛው በጣም የሚሞቀውንና ከፍ ያለውን ቦታ መርጦ ሲሆን የሚመገበውም ከሌሎቹ በፊት ነው። ስለዚህ ውሻህ በአልጋህ ላይ እንዲተኛ ወይም ቤት ውስጥ ባሉት ዕቃዎች ላይ እንዲወጣ የሚፈቀድለት ከሆነ እንዲሁም በምግብ ሰዓት ከቀረበው ማዕድ ላይ እየተቆነጠረ ከተሰጠው የቡድኑ መሪ እንደሆነ ሊሰማው ይችላል።

ውሻህ ገና ቡችላ እያለም እንኳ የአንተ የበታች መሆኑን ሊማር ይችላል። እንዴት? ዓይኑን እስኪሰብር ድረስ ፍጥጥ ብለህ ዓይን ዓይኑን ተመልከተው። ውሻው በጀርባው ተንጋልሎ እያለ ሆዱን ማሻሸትም ከበታችህ እንዲሆን ስለሚያደርገው መታዘዝን ያስተምረዋል። ውሻህ የሚረብሽና “ተው” ስትለው የማይሰማ ከሆነ ቸል በማለት ወይም ክፍሉን ለቅቀህ በመውጣት እንዳልተደሰትክበት አሳየው።

ውሻህ የምትሰጠውን መመሪያ ሲታዘዝ የቡድኑ መሪ አንተ መሆንህን እንደተቀበለ ያሳያል። የውሻው ባለቤት እንደመሆንህ መጠን የቤተሰቡ መሪ መሆንህን ካላሳወቅኸው እኩል ሥልጣን እንዳላችሁ ወይም እርሱ እንደሚበልጥህ ሊሰማው ይችላል። ይህ ደግሞ በባሕርይው ላይ ለውጥ ያመጣል።

ቀለል ያሉ ትእዛዞችን ማስተማር የሚቻለው እንዴት ነው?

ለውሻህ መሠረታዊ የሆነ ሥልጠና ለመስጠት በአንገቱ ዙሪያ የሚደረግ ቀበቶ፣ የሚታሰርበት ገመድ እንዲሁም ትዕግሥት ሊኖርህ ይገባል። አንድ የማሠልጠኛ መጽሐፍ የሚከተለውን ሐሳብ ይሰጣል:- (1) ቀላልና አጠር ያለ ትእዛዝ ስጠው፣ (2) እንዲያደርግ የምትፈልገውን ነገር በተግባር አሳየው እንዲሁም (3) የታዘዘውን ሲፈጽም ወዲያው አመስግነው። ከምትጠቀምባቸው ቃላት ይበልጥ የድምፅህ ቃና ለውሻህ የሚያስተላልፈው መልእክት አለ። ትእዛዝ ስትሰጥ ድምፅህ ጠንከር ያለ ይሁን፤ ስታመሰግነው ደግሞ ደስ በሚልና እንደምትወደው በሚገልጽ የድምፅ ቃና አናግረው።

በመምታት ወይም በመርገጥ አካላዊ ቅጣት መስጠት አስፈላጊ አይደለም። ቀደም ሲል የተገለጸው ማርኮስ የተባለው የውሻ አሠልጣኝ እንዲህ ይላል:- “ውሻው በሚያደርገው ነገር እንዳልተደሰትኩ እንዲያውቅ ቃሉን ጎተት በማድረግ ‘ተው’ ብዬ በኃይለ ቃል እቆጣዋለሁ።” አክሎም “ውሾች ስታመሰግኗቸውና ተግሣጽ ስትሰጧቸው ይገባቸዋል” በማለት ተናግሯል።

ከዚህ የበለጠ ቅጣት ካስፈለገ ውሻውን ማጅራቱ ላይ ይዘህ በትንሹ ወዝወዝ በማድረግ “ተው” ልትለው ትችላለህ። ተግሣጽ የምትሰጠው ልክ ሲያጠፋ ወይም ከዚያ ብዙም ሳይቆይ መሆን አለበት። የምትቆጣው ድርጊቱን ከፈጸመ ከተወሰኑ ደቂቃዎች ወይም ሰዓታት በኋላ ከሆነ ተግሣጽ የተሰጠው ለምን እንደሆነ ላይገባው ይችላል። ከዚህም በላይ ውሻ አንድ ድርጊት በአንድ ወቅት ተገቢ ቢሆንም በሌላ ጊዜ ግን ትክክል የማይሆንበትን ምክንያት አይረዳም። ስለዚህ የምትሰጠው ሥልጠና ወጥ ይሁን።

ውሻችንን ስናሠለጥን በቅድሚያ ልናስተምረው የሚገባው መሠረታዊ ትእዛዝ “ቁጭ በል!” የሚለው ነው። ውሻው ይህንን ትእዛዝ ካወቀ በጣም ሲረብሽ ልትቆጣጠረው ትችላለህ። ለምሳሌ እንግዶችህ ላይ ዘሎ የሚወጣ ከሆነ አርፎ እንዲቀመጥ ልታዝዘው ትችላለህ። ውሻህ እንዲቀመጥ ለማሠልጠን ገመዱን አንገቱ ላይ ካጠለቅህ በኋላ ወገቡ አካባቢ ወደታች እየተጫንከው በገመዱ ራሱን በቀስታ ወደላይ ጎተት በማድረግ እንዲቀመጥ እዘዘው። ሲታዘዝህ ወዲያው አመስግነው። ውሻው ያለ አንተ እርዳታ በራሱ መቀመጥ እስኪጀምር ድረስ በዚህ መንገድ እየደጋገምህ አሠልጥነው።

ውሻህ ተቀምጦ እንዲቆይ ለማስተማር ፊት ለፊቱ ቆመህ በእጅህ ባለበት እንዲሆን እያሳየህ “ተቀመጥ” በለው። ውሻው ከተቀመጠበት ከተነሳ “ተው” ብለህ እንደገና አስቀምጠው። ይህንን ትእዛዝ እየደጋገምክ አሠልጥነው፤ ውሻው ለተወሰነ ጊዜ ተቀምጦ ሲቆይ አመስግነው። ቀስ በቀስ ተቀምጦ የሚቆይበትን የጊዜ ርዝመት ከዚያም በመካከላችሁ ያለውን ርቀት እየጨመርክ አሠልጥነው።

አንድን ውሻ ስትጠራው ወደ አንተ እንዲመጣ ለማሠልጠን ከሁሉ የተሻለው ዘዴ ውሻውን በረዥም ገመድ አስሮ ስሙን እየጠሩ “ና!” በማለት በቀስታ ጎተት ማድረግ ነው። ውሻው ወደ አንተ መምጣት ሲጀምር እያመሰገንከው ወደኋላ አፈግፍግ። ብዙም ሳይቆይ በገመድ መጎተት ሳያስፈልግህ ስትጠራው ብቻ ይመጣል። ውሻህ ተፈትቶ እያለ “ና!” ስትለው አልሰማ ካለ ጥራውና ፊትህን አዙረህ መሮጥ ጀምር። ብዙውን ጊዜ ውሻው በደመ ነፍስ አንተን ማባረር ይጀምራል።

ሆኖም ልትጠነቀቅበት የሚገባ አንድ ነገር አለ:- ቅጣት እንደ መስጠት ላሉ ነገሮች “ና” ብለህ አትጥራው። ውሻው “ና” ተብሎ ሲጠራ መታዘዙ እንደ ምስጋና ወይም ምግብ ያለ መልካም ነገር እንደሚያስገኝለት መማር አለበት። ይህንን ትእዛዝ በምታስተምረው ጊዜ ትዕግሥትህ አልቆ ከተቆጣህ ውሻህ ይህንን መመሪያ መታዘዙ ጥሩ እንዳልሆነ ሊሰማውና ስትጠራው ለመምጣት አሻፈረኝ ሊል ይችላል።

ውሻህ በጣም ሳይፈጥን ወደኋላም ሳይጎተት ከጎንህ እንዲሄድ ልታሠለጥነውም ትችላለህ። ለዚህም አንገቱ ላይ የሚጠለቅ ቀበቶና አጠር ያለ ገመድ ያስፈልግሃል። ውሻውን በግራህ በኩል ካደረግኸው በኋላ “ተራመድ” ብለህ እዘዘውና ግራ እግርህን አስቀድመህ መራመድ ጀምር። ውሻው ቀድሞህ ከሄደ ወይም ወደኋላ ከቀረ በገመዱ ጎተት አድርገውና ትእዛዙን ድገምለት። ከዚያም ሲታዘዝ አመስግነው።

ውሻህ እየዘለለ ላይህ ላይ እንዳይንጠላጠል ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ወደ ኋላህ እየሸሸህ “ውረድ!” ካልከው በኋላ “ቁጭ በል!” ብሎ ማዘዝ ነው። ወይም ደግሞ ሁለቱን የፊት እግሮቹን በእጆችህ ይዘህ ወደ ውሻው በመራመድ እየደጋገምህ “ውረድ!” በለው። ሲታዘዝህ አመስግነው።

ታማኝ ጓደኛ

ውሻ ማኅበራዊ ኑሮ የሚወድ እንስሳ መሆኑን አትዘንጋ። ረዘም ላለ ጊዜ አንድ ቦታ ከዘጋህበት ቅብጥብጥ ሊሆን፣ አለማቋረጥ ሊጮኽ ወይም አጥፊ ሊሆን ይችላል። ውሻህ ሥልጠና ካገኘ መረበሹን ትቶ አስደሳችና ታማኝ ጓደኛ ይሆንልሃል።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ውሻን ለማሠልጠን የሚረዱ ሐሳቦች

1. የምትሰጠው ትእዛዝ ምንጊዜም ተመሳሳይ መሆን አለበት።

2. ውሾች በስማቸው ሲጠሩ ደስ የሚላቸው ከመሆኑም በላይ በቀላሉ ትኩረታቸው ይሳባል። ስለዚህ ትእዛዞችን ስትሰጥ በስሙ ተጠቀም። (ለምሳሌ “ቦቢ፣ ቁጭ በል!”) ይሁን እንጂ “ተው!” እንደሚለው ካሉ ተግሣጾች ጋር አያይዘህ ስሙን አትጥራ። ውሻህ በስሙ ሲጠራ ምላሽ መስጠቱ ቅጣት የሚያስከትልበት ሳይሆን መልካም ነገር የሚያስገኝለት መሆኑን ማወቅ አለበት።

3. አብዛኛውን ጊዜ ምስጋናህን በቃላት ወይም በመደባበስ ግለጽለት። ብዙ ውሾች ከምግብ ይልቅ ፍቅር ሲያገኙ የበለጠ ደስ ይላቸዋል።

4. ሥልጠናው አጠር ያለና አስደሳች ይሁን።

5. ውሻህ ሲያጠፋ ፍቅር የምታሳየው ከሆነ ሳታውቀው በዚያው እንዲቀጥል እያበረታታኸው ነው። እንዲህ ማድረግህ ጥፋቱን እንዲደግመው ያደርገዋል።

[ሥዕሎች]

አመስግነው

“ቦቢ፣ ቁጭ በል!”

[ምንጭ]

ኔቨር ኔቨር ሂት ዩር ዶግ እና አሜሪካን ዶግ ትሬይነርስ ኔትዎርክ ከተባሉት መጻሕፍት የተወሰደ።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ውሻህ ከቤት ውጪ እንዲጸዳዳ ማሠልጠን

አንድ ቡችላ ከስድስት እስከ ስምንት ሳምንት ሲሆነው ከቤት ውጪ መጸዳዳት እንዲጀምር ሥልጠና ሊሰጠው ይችላል። ዶግ ትሬይኒንግ ቤዚክስ የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው ውሻን ከቤት ውጪ መጸዳዳት ለማስለመድ በአንድ ቦታ ተወስኖ እንዲቀመጥ ማድረግ፣ ማሠልጠን፣ መጸዳዳት የሚፈልግበትን ሰዓት ማወቅና ማመስገን አስፈላጊ ነው። ውሾች በተፈጥሯቸው የሚተኙበት ቦታ ላይ መጸዳዳት አይፈልጉም። ስለዚህ ውሻህን የሚቆጣጠረው ሰው በማይኖርበት ጊዜ አንድ ቦታ ዝጋበት ወይም እሰረው። መጸዳዳት የሚፈልግበትን ሰዓት ካወቅህ በኋላ በተወሰነ ቦታ ላይ እንዲጸዳዳ አሰልጥነው። ከእንቅልፉ እንደነቃ፣ ምግብ ከበላ ወይም ከተጫወተ በኋላ እንዲሁም ከመተኛቱ በፊት (የታሰረበትን ገመድ ይዘህ) ወደዚያ ቦታ ውሰደው። በቦታው ሲጸዳዳ አመስግነው። የሚጸዳዳበት ሰዓት መድረሱን ለማሳወቅ ወይም በተወሰነለት ቦታ ላይ እንዲጸዳዳ ለማድረግ የምትጠቀምበት አንድ ዓይነት ትእዛዝ ልታስለምደው ትችላለህ።

ቡችላህ ሳይታሰር ተለቅቆ ከሆነ መጸዳዳት ሲፈልግ የሚያሳያቸውን ምልክቶች በንቃት ተከታተል፤ በድንገት መጫወቱን ሲያቆም፣ ዙሪያውን እየተሽከረከረ ሲያነፈንፍና ከክፍሉ በሩጫ ሲወጣ መጸዳዳት ፈልጎ ሊሆን ይችላል። ቤት ውስጥ ሲጸዳዳ ከደረስህበት ተቆጥተህ ወዲያው ወደ ውጪ ይዘኸው ውጣ። * በዚህም ጊዜ ቢሆን ቆይተህ እርማት መስጠቱ ምንም እርባና አይኖረውም። ያቆሸሸውን አካባቢ ጠረኑ እንዲጠፋ በኮምጣጤ ሙልጭ አድርገህ አጽዳው፤ አለዚያ ውሻው በዚያ ቦታ መጸዳዳቱን ይቀጥላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.38 ውሾች አንድን ሰው በማግኘታቸው በጣም ሲደሰቱ ሳያስቡት ሽንታቸው ሊያመልጣቸው ይችላል፤ ይህ ተፈጥሯዊ ባህርያቸው ነው። ውሻህ እንዲህ ማድረጉ እንደ ቡድኑ መሪ አድርጎ እንደሚመለከትህ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። በዚህ ጊዜ ውሻህን መቅጣቱ የበታችህ መሆኑን ለማሳየት ሲል ይበልጥ እንዲሸና ስለሚያደርገው ችግሩን ሊያባብሰው ይችላል። ብዙውን ጊዜ ቡችላው ሁለት ዓመት ሲሆነው ይህ ችግር ይወገዳል።