ጥሩ ሥነ ምግባር የት ልታገኝ ትችላለህ?
ጥሩ ሥነ ምግባር የት ልታገኝ ትችላለህ?
የምንኖረው ግብረ ገብነት እየተለወጠ ባለበት ጊዜ ነው። ድሮ እንደ ትልቅ ነውር ይታይ የነበረው ማንኛውም ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት ዛሬ በቸልታ ይታለፋል። ሌቦችና አታላዮች ብዙውን ጊዜ በመገናኛ ብዙኃን ሲወደሱና እንደ ጀግኖች ሲቆጠሩ ይታያል። ይህም በመሆኑ ብዙ ሰዎች “ሌባውን ስታይ አብረኸው ነጎድህ” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ መግለጫ ጋር የሚስማሙ መሆናቸውን አሳይተዋል።—መዝሙር 50:18
ሆኖም አጭበርባሪዎችና አታላዮች የሚደነቁበት ምንም ምክንያት የለም። አንድ ደራሲ እንደሚከተለው ሲሉ ገልጸዋል:- “የአታላዮች ልዩ ተሰጥኦ ገና ከልጅነታቸው ሰዎችን በቀላሉ የማታለል ችሎታቸው
ነው። ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ ዓይነቱ የማታለል ድርጊት ምንም ዓይነት የጥፋተኝነት ወይም የጸጸት ስሜት አያሳድርባቸውም። እንዲያውም ድርጊታቸው ባታለሉት ሰው ላይ ምንም ያህል ጉዳት ያድርስ፣ ለእነሱ ግን ከፍተኛ እርካታ፣ ይኸውም የሚፈልጉትን ነገር ለማግኘት ሲሉ ማታለላቸውን እንዲቀጥሉበት የሚያበረታታቸው ልዩ የሆነ የደስታ ስሜት ይፈጥርላቸዋል።”እርግጥ ነው፣ አንዲት መበለት ዕድሜ ልካቸውን ያጠራቀሟትን ገንዘብ በአታላዮች ቢነጠቁ ሰው ሁሉ ያዝንላቸዋል። ነገር ግን አንድ ሰው ከአንድ ትልቅ የንግድ ድርጅት ወይም የኢንሹራንስ ኩባንያ ገንዘብ አጭበርብሮ ቢወስድ የሚያዝን ሰው የለም። ብዙዎቹ የሚያስቡት የንግድ ድርጅቶች ሀብታሞች ስለሆኑ ቢታለሉም በዚህ አይጎዱም ብለው ነው። ይሁን እንጂ ጉዳቱ የንግድ ድርጅቱን ብቻ ሳይሆን ተጠቃሚውንም ይነካል። ድርጅቱ የተጭበረበረውን ገንዘብ ተጠቃሚውን ኅብረተሰብ እላፊ በማስከፈል ያጣጣዋል። ለምሳሌ ያህል በዩናይትድ ስቴትስ መካከለኛ ገቢ ያለው እያንዳንዱ ቤተሰብ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በአጭበርባሪዎች የከሰሩትን ለማካካስ በያመቱ ከ1,000 ዶላር በላይ ተጨማሪ ገንዘብ ይከፍላል።
በተጨማሪም ብዙ ሰዎች እንደ ልብስ፣ ሰዓቶች፣ ሽቶዎች፣ መዋቢያዎችና የእጅ ቦርሳዎች ያሉ ከእውነተኞቹ ምርቶች ጋር ተመሳስለው የሚሠሩ ጥራታቸውን ያልጠበቁ ሸቀጦች በርካሽ ዋጋ ሲቀርቡላቸው ተሽቀዳድመው ይገዛሉ። እነዚህ ተመሳስለው የሚሠሩ ሸቀጦች ነጋዴውን ኅብረተሰብ በያመቱ በመቶ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚያከስሩት ቢገነዘቡም እነሱን ግን የሚነካቸው አይመስላቸውም። ውሎ አድሮ ግን ተጠቃሚው ኅብረተሰብ ሕጋዊ ለሆኑ ሸቀጦችና አገልግሎቶች ከበፊቱ የበለጠ ክፍያ ለመክፈል መገደዱ አይቀርም። በተጨማሪም ተመሳስለው የተሠሩ የሐሰት ሸቀጦችን መግዛት የወንጀለኞችን ኪስ ማደለብ ነው።
የማጭበርበርን ወንጀል በመዋጋት መስክ የተሠማሩ አንድ ደራሲ እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል:- “በዛሬው ጊዜ የማጭበርበር ወንጀል እንዲህ ሊበዛ የቻለበት ዋነኛ ምክንያት ምንም ግብረ ገብነት በሌለው ኅብረተሰብ ውስጥ ስለምንኖር መሆኑን ተረድቻለሁ። ማጭበርበር በብዙዎች ዘንድ እንደ ባሕል ተደርጎ እንዲያዝ ያደረገው የሥነ ምግባር ማሽቆልቆል ነው። . . . የምንኖረው በቤት ውስጥ ግብረ ገብነትን በማያስተምር ኅብረተሰብ ውስጥ ነው። መምህራን ጥሩ ሥነ ምግባርን ቢያስተምሩ ስለሚከሰሱ የምንኖረው በትምህርት ቤት ግብረ ገብነትን በማያስተምር ኅብረተሰብ ውስጥ ነው።”
በአንፃሩ ግን የይሖዋ ምሥክሮች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን የሥነ ምግባር ደንብ ያስተምራሉ፤ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ይጣጣራሉ። እንደሚከተሉት ባሉ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይመራሉ:-
● “ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ።”—ማቴዎስ 22:39
● “አታታልል።”—ማርቆስ 10:19
● “ይሰርቅ የነበረ ከእንግዲህ አይስረቅ፤ ነገር ግን ለተቸገሩት የሚያካፍለው ነገር እንዲኖረው በገዛ እጆቹ በጎ የሆነውን እየሠራ ለማግኘት ይድከም።”—ኤፌሶን 4:28
● “በሁሉም ነገር ሐቀኞች ሆነን መኖር እንፈልጋለን።”—ዕብራውያን 13:18 NW
የይሖዋ ምሥክሮች ራሳቸውን የሚያመጻድቁ ወይም በራሳቸው ጽድቅ የሚመኩ ባይሆኑም ሁሉም ሰው እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ቢያውል ኖሮ ዓለም ለመኖር ምቹ ቦታ ትሆን እንደነበር ያምናሉ። ደግሞም አንድ ቀን እንዲህ ዓይነት ምቹ ቦታ እንደምትሆን አምላክ በሰጠው ተስፋ ያምናሉ።—2 ጴጥሮስ 3:13
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ሁሉም ሰው በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች በሥራ ላይ ቢያውል ኖሮ ዓለም ለመኖር ምቹ ቦታ ትሆን ነበር
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እውነተኛ ክርስቲያኖች “ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ” እንደሚለው ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይከተላሉ