በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆች የሚፈልጉት እንዴት ያለ አባት ነው?

ልጆች የሚፈልጉት እንዴት ያለ አባት ነው?

ልጆች የሚፈልጉት እንዴት ያለ አባት ነው?

ልጆች የሚፈልጉት የሚወዳቸውን፣ ከአጠገባቸው ሳይለይ ኃላፊነት የሚሰማቸውና እምነት የሚጣልባቸው ሆነው እንዲያድጉ ለመርዳት የሚቻለውን ሁሉ የሚያደርግ አባት ነው። ይሁን እንጂ ይህ ተገቢውን ግንዛቤ ሳያገኝ የቆየ ሐቅ ነው።

እርግጥ ነው፣ ልጆችን የሚወልዱት እናቶች ናቸው። ስለሆነም የጥሩ እናቶች አስፈላጊነት ሊካድ አይችልም። ይሁን እንጂ ዘ ዊልሰን ኳርተርሊ የተባለው መጽሔት የአባቶችም ኃላፊነትና ሚና ከእናቶች የማይተናነስ መሆኑን በመጥቀስ ‘የአሜሪካን ኅብረተሰብም ሆነ የመላውን ዓለም ኅብረተሰብ ከሚያምሱት በርካታ ችግሮች መካከል ለአብዛኞቹ ችግሮች ዋነኛው ምክንያት የአባትነት ኃላፊነታቸውን በሚገባ የሚወጡ አባቶች ቁጥር እያነሰ መምጣት ነው’ ብሏል።

ዦርናል ዳ ታርዴ የተባለው የብራዚል ጋዜጣ አንድን ጥናት በመጥቀስ እንደዘገበው እንደ ጠበኝነት፣ ጋጠ ወጥነት፣ በትምህርት እንደ መስነፍና እንደ ግድየለሽነት ላሉት የወጣቶች ችግር ምክንያቱ አብዛኛውን ጊዜ “የአባቶች አለመገኘት” ነው። ማርቼሎ ቤርናርዲ የደረሱት ሊዬ ኢምፔርፌቲ ጄኒቶሪ (ፍጹማን ያልሆኑ ወላጆች) የተባለው የጣልያንኛ መጽሐፍ ልጆች ጥሩ አስተዳደግ እንዲኖራቸው ከተፈለገ የሁለቱንም ወላጆች እንክብካቤ ማግኘት እንዳለባቸው አጠንክሮ ይገልጻል።

የቤተሰብ ሕይወት ሊሻሻል ይችላል

አንድ አባት ግድየለሽ መሆኑ በቤተሰቡ ላይ የሚያስከትለው ችግር ምንም ያህል ይሁን ችግሩ ሊስተካከልና የቤተሰቡም ኑሮ ሊሻሻል አይችልም ማለት አይደለም። እንዴት? አባትየው ምን ማድረግ ይኖርበታል?

ልጆች በቤተሰብ መዋቅር ውስጥ ታቅፈው ማደግ እንደሚያስፈልጋቸውና ስለ ደኅንነታቸው በሚያስብና በሚጨነቅ ሰው ጥላ ሥር እንዳሉ እንዲሰማቸው ማድረግ እንደሚያስፈልግ የታወቀ ነው። ባሁኑ ጊዜ በስፋት እንደሚታየው ይህ ፍላጎታቸው ሳይሟላላቸው ሲቀር ሕይወታቸው ይጎዳል። ይሁን እንጂ አባት ኖረም አልኖረ ሁኔታው ፈጽሞ ተስፋ ቢስ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ በመዝሙር 68:5 ላይ ይሖዋ “በተቀደሰ ማደሪያው፣ ለድኻ አደጉ አባት” እንደሆነ ይገልጻል። *

እርዳታ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?

የተሳካ ውጤት ለማግኘት የአምላክ እርዳታ በጣም አስፈላጊ እንደሆነና ይህንንም እርዳታ ማግኘት እንደሚቻል ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው የፖላንዳዊቷ ልጃገረድ የሊድያ ሁኔታ ያረጋግጣል። እርሷ ያደገችበት ቤተሰብ እንዴት ያለ ነበር? ቤተሰቡስ የአምላክን እርዳታ ሊያገኝ የቻለው እንዴት ነው?

የሊድያ አባት ፍራንቺሼክ ልጆቹ ትንንሾች በነበሩበት ጊዜ የገዛ ልጁ እንደተናገረችው ቤተሰቡን ችላ ይል እንደነበረ አይክድም። “ልጆቼ ስለሚያደርጉት ነገር ምንም ግድ አልነበረኝም። ፈጽሞ ፍቅር አላሳያቸውም ነበር፣ በመካከላችንም ምንም ዓይነት ትስስር አልነበረም” ይላል። ስለዚህ ሊድያ 14 ዓመት እንደሞላት እርሷም ሆነች ታናሽ ወንድሟና ታናሽ እህቷ በየጭፈራ ቤቱ ማምሸት፣ ማጨስ፣ መጠጣትና መደባደብ መጀመራቸውን አላወቀም።

በመጨረሻ ፍራንቺሼክ ልጆቹ የሚገኙበትን ሁኔታ ሲያውቅ በጣም ደነገጠ። አንድ ነገር ማድረግ እንደሚኖርበትም ወሰነ። “አምላክ እንዲረዳኝ ጸለይኩ” ይላል። ብዙም ሳይቆይ የይሖዋ ምሥክሮች እቤቱ ድረስ መጥተው አነጋገሩትና ከባለቤቱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማማ። ከጊዜ በኋላ እነዚህ ወላጆች ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኙትን ትምህርት በሕይወታቸው ውስጥ ሥራ ላይ ማዋል ጀመሩ። ታዲያ ይህ በልጆቹ ላይ እንዴት ያለ ውጤት አስከተለ?

ፍራንቺሼክ እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “ልጆቹ መጠጣት እንዳቆምኩና የተሻልኩ አባት መሆን እንደጀመርኩ መገንዘብ ጀመሩ። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በይበልጥ ለመተዋወቅ ፈለጉ። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትና ከመጥፎ ባልንጀሮቻቸው መራቅ ጀመሩ።” ልጁ ራፋው ስለ አባቱ ሲናገር “ልክ እንደ ጥሩ ጓደኛ እወደው ጀመር። ወሮበላ የሆኑት ጓደኞቼ አስጠሉኝ። ቤተሰባችን በመንፈሳዊ እንቅስቃሴ ተጠመደ” ብሏል።

አሁን ፍራንቺሼክ በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ክርስቲያን ሽማግሌ ሲሆን ለቤተሰቦቹ አስፈላጊውን እርዳታ ያደርጋል እንዲሁም ስለ እያንዳንዳቸው መንፈሳዊ እድገት ያስባል። ሚስቱና ሊድያ አቅኚዎች ወይም የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ናቸው። ራፋውና ታናሽ እህቱ ሲልቪያ በሙሉ ልባቸው መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናት ላይ ሲሆኑ በክርስቲያን ስብሰባዎች ሐሳብ ይሰጣሉ፣ ስለ እምነታቸውም ለሰዎች ይናገራሉ።

የተማረውን ሥራ ላይ አዋለ

የማካሬና አባት ሉዊስ ደግሞ ምን እንዳደረገ እንመልከት። ይህች ልጅ በመግቢያው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው የ21 ዓመቷ ስፔይናዊት ልጃገረድ ነች። ሉዊስ ጠጪ የነበረውን አባቱን መስሏል። ማካሬና እንደምትናገረው ከጓደኞቹ ጋር ሆኖ ለበርካታ ቀናት ከቤት ጠፍቶ ይቆይ ነበር። ከዚህም በላይ ሚስቱን ትልቅ ዋጋ እንዳላት የኑሮ አጋሩ ሳይሆን እንደተናቀች አገልጋይ አድርጎ ይመለከታት ነበር። ትዳራቸው ሊፈርስ የተቃረበ ሲሆን ማካሬና፣ ወንድሟና እህቷ በከባድ ጭንቀት ተውጠው ይኖሩ ነበር።

ከጊዜ በኋላ ግን ሉዊስ መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለማጥናት ተስማማ። “ከሚስቴና ከልጆቼ ጋር አብሬ መሆን ጀመርኩ። አብረን እናወራለን፣ አብረን እንበላለን፣ አብረንም መጽሐፍ ቅዱስ እናጠናለን። በተጨማሪም አብረን የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንሠራለን፣ አብረንም እንዝናናለን” በማለት ሉዊስ ይገልጻል። ማካሬና “ለቤተሰቡ ከልብ የሚያስብ ደግ አባት እንዳለኝ ይሰማኝ ጀመር” ትላለች።

ሉዊስ ቤተሰቦቹ አምላክን እንዲያገለግሉ ከማበረታታት አልፎ ራሱም የሚነግራቸውን ሥራ ላይ አዋለ። ማካሬና እንደምትለው “የነበረው ጥሩ የንግድ ሥራ ብዙ ጊዜ ይወስድበት ስለነበረና ለቤተሰቡ ጉዳዮች ብዙ ትኩረት ለመስጠት ስለፈለገ” ሥራውን ተወ። ይህ እርምጃው ያስከተለው ውጤት በጣም አስደናቂ ነበር። ማካሬና “እሱ ያደረገው ነገር ቀላል ኑሮ እየኖሩ መንፈሳዊ ነገሮችን ማስቀደም እንዴት እንደሚቻል አስተምሮኛል” ትላለች። በአሁኑ ጊዜ አቅኚ ሆና በማገልገል ላይ ስትሆን እናቷ፣ ወንድሟና እህቷ ጥሩ ተሳትፎ የሚያደርጉ የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ናቸው።

የባቡር ድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ያደረገው ውሳኔ

ልጆች የሚያስፈልጋቸው አባት የልጆቹን ደኅንነት ግምት ውስጥ ያስገባ ውሳኔ የሚወስን አባት እንደሆነ ግልጽ ነው። ባለፈው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ጃፓናዊ ሥራ አስኪያጅ ታኬሺ ታሙራ ልጁ ከባለጌ ልጆች ጋር መዋል ጀምሮ ስለነበረ ወደ አደገኛ ሁኔታ እየገባ ያለ ይመስል ነበር። ይህ የሆነው ታኬሺ በጃፓን ብሔራዊ የባቡር ድርጅት የነበረውን የኃላፊነት ቦታ ለመተው በወሰነበት በ1986 ነበር። ታኬሺ ይህን ውሳኔ ካደረገ ከ18 ዓመት በኋላ ስለወሰደው እርምጃ ምን ይሰማዋል?

“እስከ ዛሬ ካደረግኳቸው ውሳኔዎች ሁሉ የሚበልጥ ጥሩ ውሳኔ ነው ልል እችላለሁ” ሲል ገልጿል። “ከልጄ ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፌና መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትን ጨምሮ የተለያዩ ነገሮችን አብረን መሥራታችን ያስገኘው ውጤት በጣም አስደናቂ ነበር። ጥሩ ጓደኝነት ስለመሠረትን ከመጥፎ ባልንጀሮቹ ከመራቁም በላይ መጥፎ ጠባዮቹን እርግፍ አድርጎ ተወ።”

የታኬሺ ባለቤት የይሖዋ ምሥክር የሆነችው ጥቂት ዓመታት ቀደም ብሎ ስለነበረ እሱም መጽሐፍ ቅዱስን እንዲመረምርና ለቤተሰቡ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጥ የገፋፋው የእርሷ መልካም ጠባይ ነበር። ከጊዜ በኋላ እርሱ፣ ወንድ ልጁና ሴት ልጁ የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። በአሁኑ ጊዜ ታኬሺና ወንድ ልጁ በየጉባኤዎቻቸው በሽማግሌነት የሚያገለግሉ ሲሆን ባለቤቱና ሴት ልጃቸው አቅኚዎች ናቸው።

አባቶች እርዳታ ያስፈልጋቸዋል

ብዙ አባቶች ልጆቻቸውን ችላ እንዳሏቸው ቢገነዘቡም ምን እንደሚያደርጉላቸው አያውቁም። ላ ቫንግዋርዲያ የተባለው የስፔይን ጋዜጣ “[ከስፓኝ] ወላጆች መካከል 42 በመቶ የሚሆኑት በአፍላ ጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻቸውን እንዴት ማሳደግ እንዳለባቸው አያውቁም” የሚል ርዕስ አውጥቷል። ይሁን እንጂ የጨቅላ ሕፃናትና የትናንሽ ልጆች አባቶች ሁኔታም ከዚህ የተለየ አይደለም። ብዙዎች እንደሚያስቡት ሳይሆን እነዚህ ትናንሽ ልጆችም የአባታቸው ቅርበትና ትኩረት ያስፈልጋቸዋል።

ጥሩ አባት ስለ መሆን ምን ተጨማሪ እውቀት ማግኘት ይቻላል? ለአባቶች ከሁሉ የተሻለ ምሳሌ የሚሆኑት እነማን ናቸው? ከእነርሱስ ምን መማር ይቻላል? የመደምደሚያው ርዕሳችን እነዚህን ጥያቄዎች ይመረምራል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 እባክዎ በይሖዋ ምሥክሮች በተዘጋጀው ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ላይ የሚገኘውን “በነጠላ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች የተሳካ ሕይወት መምራት ይችላሉ!” የሚለውን ምዕራፍ ይመልከቱ።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የልጆቻቸውን ፍላጎት ያሟሉ አባቶች

ፍራንቺሼክና ቤተሰቡ

ሉዊስና ቤተሰቡ

ታኬሺና ቤተሰቡ