በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መፍትሄው መፋታት ነው?

መፍትሄው መፋታት ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

መፍትሄው መፋታት ነው?

በብሪታንያ፣ አንድ ቄስ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለተገኙት ሰዎች ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉላቸው። ከፊት ለፊታቸው አንድ ወንድና ሴት በቅርብ ወዳጆቻቸውና በልጆች ታጅበው ቆመዋል። የጋብቻ ሥነ ሥርዓት እየፈጸሙ ነው? በፍጹም! መፋታታቸውን ለማሳወቅ የተዘጋጀ ሥነ ሥርዓት ነው። አዎን፣ ፍቺ በጣም የተለመደ ነገር በመሆኑ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት የፍቺ ሥነ ሥርዓቶችን እስከ ማዘጋጀት ደርሰዋል!

አንተስ ከትዳር ጓደኛህ ጋር ለመፋታት አስበሃል? አስበህ ከሆነ በእርግጥ ፍቺ ደስተኛ ሕይወት እንድትመራ ያስችልሃል? ከትዳር ጓደኛህ ጋር በደስታ ለመኖር የሚያስችሉ ልትወስዳቸው የምትችላቸው ተግባራዊ እርምጃዎች ይኖሩ ይሆን?

“ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ”

የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት በተጋቡበት ጊዜ አምላክ ሰው “ከሚስቱ ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” በማለት ደንግጎ ነበር። (ዘፍጥረት 2:24) በመሆኑም ጋብቻ የተቋቋመው የዕድሜ ልክ ጥምረት እንዲሆን ታስቦ ነው። ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ለመፋታትና ሌላ ትዳር ለመያዝ መሠረት የሚሆነው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት “ዝሙት” ብቻ መሆኑን የገለጸው ለዚህ ነው።—ማቴዎስ 19:3-9 *

ይህም ለጋብቻ ቃል ኪዳን ታማኝ የመሆንን አስፈላጊነት ያሳያል። ነገር ግን በትዳርህ ውስጥ ያሉት ችግሮች ሥር የሰደዱ ቢሆኑስ?

ፍቺ የጥበብ እርምጃ ነው?

ኢየሱስ “ጥበብ ግን በሥራዋ ጸደቀች” በማለት የምንሠራውን ነገር በምን መመዘን እንደምንችል መመሪያ ሰጥቶናል። (ማቴዎስ 11:19) በዛሬው ጊዜ ያለ በቂ ምክንያት እየፈረሱ ያሉ በርካታ ትዳሮች ያስከተሉት ውጤት ምንድን ነው?

ችግር ያለባቸውን ትዳሮች የሚያጠኑ ምሑራንን ቡድን በበላይነት የሚመሩት የቺካጎ ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስ ጥናት ፕሮፌሰር ሊንዳ ዌት “ፍቺ የሚያስገኛቸው ጥቅሞች ከመጠን በላይ ተጋንነዋል” በማለት ተናግረዋል። በተመሳሳይም የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ማይክል አርጋይል በሺህ በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ለ11 ዓመታት ጥናት ካካሄዱ በኋላ “ከኅብረተሰቡ መሃል ከሁሉ በባሰ ሁኔታ ደስታ ያልነበራቸው ሰዎች ከትዳር ጓደኛቸው የተፋቱ ወይም የተለያዩ እንደሆኑ” ማወቅ ችለዋል። ይህ ለምን ሆነ?

ፍቺ አንዳንድ ችግሮችን ሊያስወግድልህ ቢችልም ታምቀው የቆዩና ብዙም ልትገታቸው የማትችላቸውን የሥነ ልቦና ቀውሶች ሊያስከትልብህ ይችላል። እንዲያውም ፍቺ በአብዛኛው ጭንቀትን እንደማይቀንስ ወይም አንድ ሰው ለራሱ ያለውን አክብሮት ከፍ እንደማያደርግለት በጥናት ተረጋግጧል።

“የተዋጣለት ትዳር” ባይኖርህም እንኳን ከትዳር ጓደኛህ ጋር አብረህ መቆየትህ ጥቅም አለው። እንዲህ ለማድረግ የቆረጡ ብዙ ሰዎች ደስታ ማግኘት ችለዋል። ፕሮፌሰር ዌት “በርካታ ችግሮች ቀስ በቀስ ይፈታሉ፤ ባልና ሚስቶችም ደስተኛ እየሆኑ ይመጣሉ” ብለዋል። አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ደግሞ “ከባድ ችግር” የነበረባቸው ነገር ግን ያልተፋቱ ባለ ትዳሮች ከ5 ዓመት በኋላ ከአሥሩ ስምንቱ “ትዳራቸው አስደሳች” ሊሆን ችሏል። ስለዚህ ስር የሰደዱ ችግሮች ቢኖሩባቸውም እንኳን ባልና ሚስት ለመፋታት ባይቻኮሉ የተሻለ ነው።

ጠቃሚ እርምጃዎች

ለመፋታት የሚያስቡ ሰዎች ከትዳራቸው የሚጠብቁት ነገር ተጨባጭነት ያለው መሆኑን ራሳቸውን መጠየቅ ይገባቸዋል። መገናኛ ብዙኃን ፍቅራዊ ግንኙነት በትልቅ ሠርግ እንደሚደመደምና ባለ ትዳሮቹ ያለ ምንም ችግር ሁልጊዜ በሰላምና በደስታ እንደሚኖሩ አስመስለው ያቀርባሉ። ከሠርጉ በኋላ ተስፋ ሲደረጉ የነበሩት ነገሮች ሳይፈጸሙ መቅረታቸው ብስጭት ያመጣል፤ ይህም ጠብ እንዲጫር ምክንያት ይሆናል። በትዳሩ ውስጥ ውጥረት እየነገሠ ሲመጣ አንዱ የሌላውን ስሜት ሊጎዳና ሊያቆስል ይችላል። በዚህም ሳቢያ ፍቅር ይጠወልግና ውሎ አድሮ በብስጭትና በጥላቻ ይተካል። እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ሰው የሚታየው ብቸኛ አማራጭ ፍቺ ሊሆን ይችላል።—ምሳሌ 13:12

አፍራሽ የሆኑ ስሜቶች አመለካከትህ ላይ ተጽዕኖ እንዲያደርጉብህ ከመፍቀድ ይልቅ ትዳራቸውን አክብደው ከሚመለከቱ ሰዎች ጋር ተቀራረብ። ክርስቲያኖች ‘እርስ በርሳቸው እንዲጽናኑና አንዱም ሌላውን እንዲያንጽ’ ተመክረዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:11) እውነት ነው፣ ሰላማዊ ትዳር የሌላቸው ሰዎች ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ማበረታቻ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል።

አምላካዊ ባሕርያት የሚያስገኙት ጥቅም

“ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ ጨዋነትንና ትዕግሥትን ልበሱ” በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ አጥብቆ አሳስቧል። (ቆላስይስ 3:12) አምላካዊ ባሕርያት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ባሉበት ጊዜ የጋብቻን አንድነት ጠብቆ ለማቆየት ያስችላሉ።

ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እርስ በርሳችሁ ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ።” (ቆላስይስ 3:13) በሚሺገን ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ክሪስቶፈር ፒተርሰን “ይቅር ባይነት ከደስታ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ባሕርይ ነው” ብለዋል።

ደግነት፣ አሳቢነትና ይቅር ባይነት “በፍጹም አንድነት የሚያስተሳስረውን ፍቅርን” እንድናዳብር ይረዱናል። (ቆላስይስ 3:14) በአንድ ወቅት ለትዳር ጓደኛህ ጥልቅ ፍቅር እንደነበረህ ምንም ጥርጥር የለውም። ያን ጊዜ የነበረህ የፍቅር ስሜት ዳግመኛ በውስጥህ እንዲያድግ ማድረግ ትችል ይሆን? ሁኔታህ ምንም ያህል የከፋ ቢሆን በርትተህ ታገል። ተስፋ አትቁረጥ። ሳይፋቱ መኖርና የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሥራ ላይ ማዋል ፈጽሞ ያላሰብከውን ትልቅ ደስታ ያስገኝልሃል። ለዚህ ብለህ የምታደርገው ጥረት የጋብቻ መሥራች የሆነውን ይሖዋ አምላክን ደስ እንደሚያሰኘው ምንም ጥርጥር የለውም።—ምሳሌ 15:20

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 ንጹሕ የሆነው ወገን ዝሙት የፈጸመውን የትዳር ጓደኛ ለመፍታት ወይም ላለመፍታት ቢመርጥ የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያን ጉባኤ ውሳኔውን ያከብርለታል። የመስከረም 1999 ንቁ! መጽሔት ከገጽ 5-9⁠ን ተመልከት።