አሻንጉሊት አልባ መዋዕለ ሕፃናት
አሻንጉሊት አልባ መዋዕለ ሕፃናት
ጀርመን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
አንድ ቀን ጠዋት ልጆች ወደ መዋዕለ ሕፃናቱ ሲገቡ በየክፍሎቹ ውስጥ ከወንበርና ከጠረጴዛ በስተቀር ምንም ነገር አልነበረም። አሻንጉሊቶቻቸውን ወይም መጫወቻዎቻቸውን ቢፈልጉ፣ ቢፈልጉ ሊያገኟቸው አልቻሉም። መጽሐፎች ወይም የእቃ እቃ ቤት ለመሥራት የሚያገለግሉ ነገሮችም አልነበሩም። ሌላው ቀርቶ ወረቀትና መቀስ እንኳን አልነበረም። ይህ ሁኔታ ለሦስት ወራት እንዲቀጥል ተደረገ። ከዚያስ ምን ሆነ?
ይህ መዋዕለ ሕፃናት በኦስትሪያ፣ በጀርመንና በስዊዘርላንድ ከአሻንጉሊት ነፃ የሆነ መዋዕለ ሕፃናት የሚባል በዓይነቱ ልዩ በሆነ አዲስ እቅድ ላይ ከሚካፈሉት ታዋቂ እየሆኑ ከመጡት ሕፃናት መዋያዎች አንዱ ነው። ነገሩ እንግዳ ሊመስል ቢችልም በአውሮፓ ኅብረት የሕክምና ባለሙያዎች በከፍተኛ ሁኔታ የተደነቀው ይህ እቅድ ዓላማው አጉል ልማዶችን አስቀድሞ መከላከል ነው። ሰዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ ጥሩ ማኅበራዊ ግንኙነት ካላቸው ለማንኛውም ዓይነት አጉል ልማድ የመገዛት አጋጣሚያቸው አነስተኛ እንደሚሆን ተመራማሪዎች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተገነዘቡ መጥተዋል። ይህም “በቀላሉ ከሰዎች ጋር የመግባባትና ሐሳብን የመግለጽ ችሎታን፣ አለመግባባቶችን በቀላሉ መፍታትን፣ ለፈጸሙት ነገር ኃላፊነት መውሰድን፣ እቅድ ማውጣትን፣ ችግሮችን ለይቶ ማወቅን፣ ከሌሎች እርዳታ መጠየቅን እንዲሁም ለአንድ ችግር መፍትሄ ማግኘትን” እንደሚጨምር አንድ ጋዜጣ ገልጿል። የዚህ እቅድ ደጋፊዎች እንዳሉት ከሆነ እንዲህ የመሳሰሉት ችሎታዎች በተቻለ መጠን ገና ከልጅነት መዳበር ይገባቸዋል፤ ለዚሁ ዓላማ ተብለው የተዘጋጁት እነዚህ ከአሻንጉሊት ነፃ የሆኑ ፕሮግራሞች የፈጠራ ችሎታንና በራስ መተማመንን ለማዳበር ይረዳሉ።
አሻንጉሊቶቹ ለሦስት ወር እንዲሰወሩ የተደረገው በደንብ ታስቦበት ሲሆን በጉዳዩ ላይ ከወላጆችም ሆነ ከልጆቹ ጋር ውይይት ተደርጓል። መጀመሪያ ላይ አንዳንድ ሕፃናት አሻንጉሊት ሳይኖራቸው እንዴት እንደሚሆኑ ግራ ገብቷቸው ነበር። ዘገባው እንደሚያሳየው “ለመጀመሪያዎቹ አራት ሳምንታት ልጆች ከሥርዓት ውጪ ሆነው የከረሙባቸው ሕፃናት መዋያዎች ነበሩ”፤ በመሆኑም እቅዱን የነደፉት አካላት በነገሩ ተስፋ ቆርጠው ነበር። ልጆቹ ግን ሁኔታውን መላመድና የፈጠራ ችሎታዎችን ማዳበር ችለዋል። የሚጫወቱባቸው አሻንጉሊቶች ስላልነበሯቸው እርስ በርስ ለመወያየት፣ አብረው እቅድ ለማውጣትና አብረው ለመጫወት ችለዋል፤ ይህም ማኅበራዊ ግንኙነታቸውንና የቋንቋ ችሎታቸውን ለማሻሻል ረድቷቸዋል። በአሻንጉሊቶቻቸው “ይደበቁ” የነበሩ አንዳንዶች አሁን ጓደኞችን ማፍራት ጀምረዋል። ወላጆችም ልጆቻቸው ያደረጓቸውን ጥሩ ለውጦች ማስተዋል ችለዋል። በሚጫወቱበት ጊዜ መልካም ምግባር ማሳየት እንደ ጀመሩና የፈጠራ ችሎታቸው ከበፊቱ እንደ ተሻለ ተናግረዋል።