በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከመጠን በላይ መጠጣት ምን ስሕተት አለው?

ከመጠን በላይ መጠጣት ምን ስሕተት አለው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

ከመጠን በላይ መጠጣት ምን ስሕተት አለው?

“ከጓደኛዬ ጋር ለሰዓታት ስንጠጣ የቆየን ቢሆንም ከሌሊቱ 7:00 ላይ ከግብዣው ቦታ ስንወጣ ሁለታችንም በጠርሙስ ውስኪ ይዘን ነበር። ከያዝነው ውስኪ እየተጎነጨን ወደ ቤታችን ማዝገም ጀመርን። ከዚያ ቀጥሎ ትዝ የሚለኝ ጎህ መቅደዱ ነው፤ በተሳሳተ አቅጣጫ ስንጓዝ እንደነበረ ያወቅሁት በዚህ ጊዜ ነበር። የምንሄደው በዋናው አውራ ጎዳና ላይ ስለነበር የሚያልፉ መኪኖች ሳይገጩን መትረፋችንም ተዓምር ነው።”—ክሌይ *

ከመጠን በላይ መጠጣት፣ ለመስከር ብሎ መጠጣት የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ዩ ኤስ ናሽናል ኢንስቲትዩት ኦን አልኮሆል አቢዩዝ ኤንድ አልኮሆሊዝም የተባለው ድርጅት ደግሞ ከመጠን በላይ መጠጣት የሚለው አገላለጽ “ለወንዶች አምስት ብርጭቆ ወይም ከዚያ በላይ ለሴቶች ደግሞ አራት ብርጭቆ ወይም ከዚያ በላይ አከታትሎ መጠጣትን” እንደሚያመለክት ገልጿል።

በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ የጤና ባለሞያዎች ከመጠን በላይ መጠጣት “ዋነኛው የሕዝብ ጤና ጠንቅ” እንደሆነ ይናገራሉ። በእንግሊዝ፣ በስኮትላንድና በዌልስ በሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ የተካሄደ ጥናት እንደሚያሳየው “13 እና 14 ዓመት ከሆናቸው ልጆች መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት በአንድ ጊዜ ቢያንስ አምስት ብርጭቆ የአልኮል መጠጥ እንደጠጡ ተናግረዋል።” በጥናቱ ከተካፈሉት የ15 እና 16 ዓመት ልጆች መካከል ግማሽ ያህሉም ተመሳሳይ ነገር ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከ5 የኮሌጅ ተማሪዎች መካከል 2ቱ ጥናቱ ከመካሄዱ በፊት በነበሩት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ቢያንስ አንድ ጊዜ ከመጠን በላይ ጠጥተዋል። የዩናይትድ ስቴትስ የጤና ክፍል ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው “ዕድሜያቸው ከ12 እስከ 20 ዓመት ከሚደርሱ ወጣቶች መካከል 10.4 ሚሊዮን የሚያህሉት የአልኮል መጠጥ እንደሚወስዱ ተናግረዋል። ከእነዚህ ውስጥ 5.1 ሚሊዮን የሚሆኑት ከመጠን በላይ የመጠጣት ልማድ ያላቸው ሲሆን በአንድ ወር ውስጥ ቢያንስ አምስት ጊዜ ከመጠን በላይ እንደጠጡ የገለጹ 2.3 ሚሊዮን የሚያህሉ ኃይለኛ ጠጪዎችም በዚህ አኃዝ ውስጥ ይካተታሉ።” በአውስትራሊያ የተካሄደ ጥናት እንደሚያሳየው በዚያች አገር ከወንዶች ይልቅ ወጣት ሴቶች ከመጠን በላይ የመጠጣት ልማድ ያላቸው ከመሆኑም በላይ በአንድ ጊዜ ከ13 እስከ 30 ብርጭቆ መጠጥ ሊጠጡ ይችላሉ!

ወጣቶች አብዛኛውን ጊዜ እንደዚህ የሚያደርጉት በእኩዮቻቸው ግፊት ነው። ካሮል ፋልኮቭስኪ የተባሉ ተመራማሪ እንዲህ ብለዋል:- “ድፍረት የሚታይባቸው አዳዲስ የመጠጥ ጨዋታዎች እየተበራከቱ መጥተዋል፤ ወጣቶች ጥንብዝ ብለው እስኪሰክሩ ድረስ ለመጠጣት በማሰብ የቡድን ጨዋታዎች ያዘጋጃሉ። ለአብነት ያህል፣ በአንዳንዶቹ ጨዋታዎች ላይ ተጫዋቾቹ በሙሉ አንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ወይም የቡድን ውይይት እስኪያበቃ ድረስ ባለው የተወሰነ ጊዜ ውስጥ አንድ መለኪያ ደረቅ አልኮል እንዲጠጡ ይጠበቅባቸዋል።”

ከመጠን በላይ መጠጣት የሚያስከትላቸው አደጋዎች

ምንም እንኳ አንዳንዶች ከመጠን በላይ መጠጣትን እንደ ጨዋታ ቢመለከቱትም ይህ በጣም አደገኛ ጨዋታ ነው! አልኮል ከመጠን በላይ መውሰድ አንጎላችን ኦክስጂን እንዲያጣ ስለሚያደርገው በሰውነታችን ውስጥ የሚካሄዱት ጠቃሚ ተግባራት ሊቋረጡ ይችላሉ። ማስመለስ፣ ራስን መሳትና ዝግተኛ ወይም ቁርጥ ቁርጥ የሚል አተነፋፈስ የዚህ ምልክት ናቸው። አንዳንድ ጊዜም ሞት ሊከተል ይችላል። ኪም የተባለች አንዲት የ17 ዓመት ወጣት መጠጥ እንደ ውኃ በሚቀዳበት ግብዣ ላይ በተገኘችበት ወቅት ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከተመረቀች ከአንድ ወር አይበልጥም ነበር። በግብዣው ላይ 17 ብርጭቆ አልኮል ከጠጣች በኋላ ራሷን ስለሳተች ታላቅ እህቷ መጥታ ወደ ቤት ወሰደቻት፤ በማግስቱ እናቷ ስትመለከታት ሕይወቷ አልፏል።

ከልክ በላይ መጠጣት ሁልጊዜ ለሞት የሚዳርግ ባይሆንም ለጤና እክል ግን ያጋልጣል። የአእምሮ ሕክምና ባለሞያ የሆኑት ጄሮም ሌቪን እንዲህ ብለዋል:- “አልኮል በማንኛውም የሰውነታችሁ ክፍል ላይ ከባድ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። በተለይ ግን የአልኮል መጠጥን አላግባብ መውሰድ የነርቭ ሥርዓትን ያቃውሳል እንዲሁም ጉበትና ልብን ይጎዳል።” ዲስከቨር በተሰኘ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ እንዲህ ይላል:- “ወጣቶች ከመጠን በላይ ሲጠጡ ራሳቸውን ለአደጋ እንደሚያጋልጡ አዳዲስ ጥናቶች ያሳያሉ። አእምሯቸው በሃያዎቹ ዕድሜም እድገት ማድረጉን ስለሚቀጥል በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ እያሉ ከመጠን በላይ የሚጠጡ ወጣቶች የማሰብ ችሎታቸውን እያዳከሙት ሊሆን ይችላል።” ከልክ በላይ አልኮል መውሰድ ከብጉር መብዛት፣ ያለ ዕድሜ ከሚመጣ የቆዳ መሸብሸብ፣ ክብደት ከመጨመር፣ ከውስጥ አካላት መጎዳት፣ መጠጥ ሳይቀምሱ ምንም ነገር መሥራት ካለመቻል እንዲሁም ከዕፅ ሱሰኝነት ጋር እንደሚያያዝም ተገልጿል።

ከመጠን በላይ መጠጣት የሚያስከትላቸው ሌሎች ችግሮችም አሉ። መስከር ለጥቃት ያጋልጣል። አካላዊ ጥቃት ሊሰነዘርባችሁ አልፎ ተርፎም ተገድዳችሁ ልትደፈሩ ትችላላችሁ። ከዚህም በላይ ባልጠጣችሁበት ወቅት ፈጽሞ የማታስቧቸውን ነገሮች በማድረግ ከቁጥጥር ውጭ ሆናችሁ በሌሎች ላይ አደጋ ልታደርሱ ትችላላችሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ከልክ በላይ ከጠጣህ “ዐይኖችህ እንግዳ ነገር ያያሉ፤ አእምሮህም ይቀባዥራል” በማለት ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 23:33) ከልክ በላይ መጠጣት ከሚያስከትላቸው አሳዛኝ ውጤቶች መካከል ከሌሎች ጋር ያለን ወዳጅነት መበላሸት፣ በትምህርት ቤት ወይም በመሥሪያ ቤት ጥራት ያለው ሥራ ማከናወን አለመቻል፣ ወንጀል መፈጸምና ድህነት ይገኙበታል። *ምሳሌ 23:21

እንድትጠጡ የሚደረግባችሁ ግፊት

ከመጠን በላይ መጠጣት ለእነዚህ ሁሉ አደጋዎች ቢያጋልጥም ብዙ አገሮች የአልኮል መጠጥን በሰፊው የሚያስተዋውቁ ከመሆኑም በላይ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። እንዲያውም በቴሌቪዥን ፕሮግራሞች የሚቀርቡና በመጽሔቶች ላይ የሚወጡ ማስታወቂያዎች የአልኮል መጠጥን በጣም ተወዳጅ ነገር አድርገው ይገልጹታል። ይሁን እንጂ ወጣቶች በአብዛኛው ከመጠን በላይ የሚጠጡት በእኩዮቻቸው ግፊት ነው።

በአውስትራሊያ የአልኮል መጠጥን አስመልክቶ በተካሄደ ጥናት ላይ ጥያቄ ከቀረበላቸው ወጣቶች መካከል 36 በመቶ የሚሆኑት የሚጠጡበት ዋነኛ ምክንያት “በማኅበራዊ ዝግጅቶች ላይ ከሌሎች ጋር ለመመሳሰል” እንደሆነ ገልጸዋል። ለወትሮው ዓይናፋር የነበረ ወጣት ትርምስምስ ባለ “የቢራ ግብዣ” ላይ ጓደኞቹ በላይ በላዩ እንዲጠጣ ሲገፋፉት የግብዣው ዋና ተዋናይ ሆኖ ሊገኝ ይችላል። ኬቲ እንዲህ ባለው ግብዣ ላይ ከመጠን በላይ በመጠጣቷ ወደ ቤቷ ስትወሰድ ራሷን ስታ ነበር። “ጓደኛዋ” የሆነ አንድ ወጣት “ያዢ እንጂ ኬቲ፣ አሁን እኮ አንቺ ትልቅ ልጅ ነሽ። በአንድ ትንፋሽ ጭልጥ አድርገሽ መጠጣት መልመድ አለብሽ” በማለት እንድትጠጣ አደፋፍሯት ነበር።

ከመጠን በላይ መጠጣት አደገኛ መሆኑን የሚጠቁሙ አሳማኝ ምክንያቶች ቢኖሩም ወጣቶች ለመደሰትና እኩዮቻቸውን ለመምሰል ያላቸው ጉጉት ስለሚያይል ይህ ልማድ አሁንም በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ ነው።

ውሳኔህ ምንድን ነው?

አሁን የሚነሳው ጥያቄ መጠጥን በተመለከተ ውሳኔህ ምንድን ነው? የሚል ይሆናል። እኩዮችህ ያደረጉትን ሁሉ ታደርጋለህ? መጽሐፍ ቅዱስ በሮሜ 6:16 ላይ የሚሰጠውን “ራሳችሁን እንደ ባሪያ አድርጋችሁ ስታቀርቡ፣ ለምትታዘዙት ለእርሱ፣ . . . ባሮች እንደሆናችሁ አታውቁምን?” የሚለውን ማስጠንቀቂያ አስታውስ። እኩዮችህ እያንዳንዱን እንቅስቃሴህን እንዲቆጣጠሩ ከፈቀድክላቸው የእነርሱ ባሪያ ትሆናለህ። መጽሐፍ ቅዱስ ሌሎችን ከመከተል ይልቅ የራስህን ውሳኔ እንድታደርግ ያበረታታሃል። (ምሳሌ 1:4) ከዚህም በላይ ከባድ ስሕተት ከመሥራት ሊጠብቅህ የሚችል ምክር ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስ አልኮልን አስመልክቶ የሚሰጠውን ሐሳብ ተመልከት።

መጽሐፍ ቅዱስ አልኮል መጠጣትንም ሆነ መዝናናትን አያወግዝም። ሆኖም ከመጠን በላይ መጠጣት አደጋ እንዳለው ያስጠነቅቃል። ምሳሌ 20:1 እንዲህ ይላል:- “የወይን ጠጅ ፌዘኛ፣ ብርቱ መጠጥም ጠበኛ ያደርጋል፤ በእነዚህ የሳተ ሁሉ ጠቢብ አይደለም።” በእርግጥም የአልኮል መጠጥ አንድን ሰው ፌዘኛና ጠበኛ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል። መጠጥ ጊዜያዊ ደስታ ሊያስገኝልህ እንደሚችል አይካድም፤ ሆኖም ከመጠን በላይ መጠጣት አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ጉዳት ስለሚያስከትል መጠጥ “እንደ እባብ ይነድፋል” ተብሏል።—ምሳሌ 23:32

ልብ ሊባል የሚገባው ሌላው ነገር ደግሞ በብዙ አገሮች ውስጥ የአልኮል መጠጥ መውሰድ የሚቻልበት የዕድሜ ገደብ መኖሩ ነው። ክርስቲያኖች እንደዚህ ያለውን ሕግ ይታዘዛሉ። (ቲቶ 3:1) ይህ ሕግ የወጣው አንተን ከአደጋ ለመጠበቅ ነው።

ከሁሉ በላይ ደግሞ ከመጠን በላይ መጠጣት የሚያስከትለውን መንፈሳዊ ጉዳት ማስተዋል ያስፈልጋል። ይሖዋ አምላክ አልኮል ከመጠን በላይ በመውሰድ በተበላሸ አእምሮ ሳይሆን “በፍጹም ሐሳብህ” እንድታገለግለው ይፈልጋል። (ማቴዎስ 22:37) የአምላክ ቃል ‘ስካርን’ ብቻ ሳይሆን ‘ያለ ልክ መጠጣትንም’ ያወግዛል። (1 ጴጥሮስ 4:3) በመሆኑም ከመጠን በላይ መጠጣት ከፈጣሪያችን ፈቃድ ጋር ይጋጫል። እንደዚህ ያለው ልማድ አንድ ሰው ከአምላክ ጋር የቀረበ ዝምድና እንዳይመሠርት እንቅፋት ሊሆንበት ይችላል።

ከመጠን በላይ የመጠጣት ልማድ ካለህ ምን ማድረግ ትችላለህ? ከወላጆችህ ወይም ከጎለመሱ ክርስቲያኖች ጋር በመነጋገር እርዳታ ለማግኘት ሞክር። * ወደ ይሖዋ አምላክ በመጸለይ እንዲረዳህ ለምነው። አምላክ “በሚደርስብን መከራ ሁሉ የቅርብ ረዳታችን ነው።” (መዝሙር 46:1) አብዛኛውን ጊዜ ወጣቶች ከመጠን በላይ እንዲጠጡና ያለ ዕድሜያቸው መጠጥ እንዲጀምሩ ግፊት የሚያደርጉባቸው እኩዮቻቸው ስለሆኑ በጓደኛም ሆነ በመዝናኛ ምርጫህ ረገድ ከፍተኛ ለውጥ ማድረግ ያስፈልግህ ይሆናል። እንደዚህ ያለ ለውጥ ማድረግ ቀላል ላይሆን ይችላል፤ ሆኖም በይሖዋ እርዳታ ይሳካልሃል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.11 በዩናይትድ ስቴትስ የተካሄደ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው “ከመጠን በላይ የሚጠጡ ተማሪዎች ክፍል ሳይገቡ የመቅረት፣ የትምህርት ቤት ሥራቸውን ዘግይቶ የማስረከብ፣ የመጎዳት እና በንብረት ላይ ጉዳት የማድረስ አጋጣሚያቸው ከሌሎች ተማሪዎች በስምንት እጥፍ ይበልጣል።”

^ አን.21 አንዳንድ ጊዜ የሕክምና ባለሞያ እርዳታ ያስፈልግ ይሆናል።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ከመጠን በላይ መጠጣት የሚያስከትለውን መዘዝ የሚያሳዩ አኃዞች

ከዚህ ቀጥሎ የቀረበው አኃዛዊ መረጃ ከመጠን በላይ መጠጣት በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኙ የኮሌጅ ተማሪዎች ላይ ያስከተለውን አሳዛኝ ውጤት የሚያሳይ ነው:-

ሞት:- በየዓመቱ ከ18 እስከ 24 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 1,400 የኮሌጅ ተማሪዎች ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ ሌሎች ሳያውቁ ባደረሱባቸው ጉዳትና በመኪና አደጋ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጣሉ

ጉዳት:- ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 24 ዓመት የሚሆኑ 500,000 ተማሪዎች ሰክረው እያለ ጉዳት ይደርስባቸዋል

ጥቃት:- ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 24 ዓመት የሆነ ከ600,000 በላይ ተማሪዎች በሰከረ ተማሪ ጥቃት ይሰነዘርባቸዋል

ወሲባዊ በደል:- ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 24 ዓመት የሆነ ከ70,000 የሚበልጡ ተማሪዎች በስካር መንፈስ የወሲብ ጥቃት ይደርስባቸዋል ወይም በጓደኛቸው ተገድደው ይደፈራሉ

[ምንጭ]

ምንጭ:- ዩ ኤስ ናሽናል ኢንስቲትዩት ኦን አልኮሆል አቢዩዝ ኤንድ አልኮሆሊዝም

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እኩዮችህ ከመጠን በላይ እንድትጠጣ ይገፋፉህ ይሆናል