በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለማዊ ዝና የበለጠ ነገር

ከዓለማዊ ዝና የበለጠ ነገር

ከዓለማዊ ዝና የበለጠ ነገር

ቻርልስ ሲነትኮ እንደተናገረው

በ1957 በሳምንት አንድ ሺህ ዶላር እየተከፈለኝ ለ13 ሳምንታት በዩናይትድ ስቴትስ ነቫዳ፣ ላስ ቬጋስ ውስጥ እንድዘፍን ተጠየቅኩ፤ ከዚያ በኋላ ውጤቱ ታይቶ ኮንትራቱ ለ50 ሳምንታት ሊራዘምልኝ እንደሚችል ተነገረኝ። ይህ ደግሞ ተጨማሪ 50 ሺህ ዶላር ያስገኝልኛል፤ ገንዘቡ በዚያን ጊዜ በጣም ብዙ ነበር። ይህን በሚያክል ገንዘብ ለመደራደር እንዴት እንደበቃሁና ሥራውን ልሥራ አልሥራ የሚለውን ነገር ለመወሰን ለምን እንደከበደኝ ልግለጽላችሁ።

አባቴ ዩክሬናዊ ሲሆን በ1910 በምሥራቅ አውሮፓ ተወለደ። የአባቴ እናት ከባሏ ጋር ለመገናኘት በ1913 ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ስትሄድ እሱንም ይዛው ሄደች። አባቴ በ1935 አገባና ከአንድ ዓመት በኋላ በአምብሪጅ፣ ፔንስልቬኒያ ተወለድኩ። በዚያን ጊዜ ሁለት የአባቴ ታላላቅ ወንድሞች የይሖዋ ምሥክሮች ሆነው ነበር።

እኔና ሦስቱ ወንድሞቼ ልጆች እያለን ቤተሰባችን በፔንስልቬኒያ፣ ኒው ካስል ከተማ አቅራቢያ ይኖር ነበር፤ በዚያን ጊዜ እናታችን ለጥቂት ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ አጥንታ ነበር። ከወላጆቼ መሃል አንዳቸውም በወቅቱ የይሖዋ ምሥክር አልሆኑም፤ አባቴ ግን ወንድሞቹ ባሻቸው ነገር የማመን መብት እንዳላቸው ያምን ነበር። የአገር ፍቅር ስሜት እንዲኖረን አድርጎ ያሳደገን ቢሆንም ሰዎች ደስ ያሰኛቸውን ነገር ማምለክ ይችላሉ በማለት ለሌሎች መብት ይከራከር ነበር።

ዘፋኝነት ሙያዬ ሆነ

ወላጆቼ ለዘፈን የሚሆን ጥሩ ድምፅ እንዳለኝ ስለተገነዘቡ ይህን ችሎታዬን እንዳዳብር አቅማቸው የፈቀደላቸውን ያህል ይረዱኝ ነበር። የስድስት ወይም የሰባት ዓመት ልጅ ሳለሁ አባቴ የምሽት ጭፈራ ቤት ይዞኝ በመሄድ ባንኮኒ ላይ አቁሞ ጊታር እየመታሁ እንድዘፍን ያደርግ ነበር። ዘፈኑ አፍቃሪ እናት ያሏትን ባሕርያት የሚገልጽ ሲሆን ስሜት በሚነካ ግጥምና ሞቅ ባለ ሙዚቃ ይደመደማል። አብዛኛውን ጊዜ በቡና ቤቱ ውስጥ ያሉ ከልክ በላይ የጠጡ ሰዎች እያለቀሱ በአባቴ ባርኔጣ ውስጥ ገንዘብ ይጨምራሉ።

ለመጀመሪያ ጊዜ የሬዲዮ ፕሮግራም ያቀረብኩት በ1945 ኒው ካስል በሚገኝ ደብልዩ ኬ ኤስ ቲ በተባለ የሬዲዮ ጣቢያ ሲሆን የአሜሪካንን የአገር ባህል ዘፈን እዘፍን ነበር። ቆየት ብሎም የሳምንቱን አሥር ምርጥ ዘፈኖች በሚያቀርብ ሳምንታዊ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ታዋቂ ስልቶችን ጭምር መዝፈን ጀመርኩ። በቴሌቪዥን ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረብኩት በ1950 ፖል ኋይትማን በሚያዘጋጀው ትርኢት ላይ ነበር። እሱ ያዘጋጀው የጆርጅ ገርሽዊን “ራፕሶዲ ኢን ብሉ” የተባለው ዘፈን እስከ አሁን ድረስ ተወዳጅ ነው። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ አባቴ ሥራዬን በስፋት ልሠራ እንደምችል ተስፋ በማድረግ በፔንስልቬኒያ ያለውን ቤታችንን ሸጠና ወደ ካሊፎርኒያ ግዛት ሎስ አንጀለስ ተዛወርን።

ለአባቴ ምሥጋና ይግባውና በእርሱ ብርታት ወዲያውኑ በፓሰዲና ሬዲዮ ጣቢያ የራሴን ሳምንታዊ ፕሮግራም፤ በሆሊዉድ ደግሞ ለግማሽ ሰዓት ያህል ሳምንታዊ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ማቅረብ ቻልኩ። በካፒተል ሪኮርድስ ድርጅት ውስጥ ቴድ ዴል የሚባል ሰው ከሚመራው ሀንድረድ ፒስ ከተባለ የሙዚቃ ቡድን ጋር ሙዚቃዎችን እቀዳ ነበር፤ በተጨማሪም ሲ ቢ ኤስ በተባለ የሬዲዮ ጣቢያ ውስጥ ሙዚቀኛ ሆንኩ። በ1955 በሰሜናዊ ካሊፎርኒያ በሚገኘው ታሆ ሐይቅ የሙዚቃ ትርኢት አዘጋጀሁ። እዚያ በነበርኩበት ጊዜ በሕይወቴ ውስጥ አንደኛ ደረጃ በምሰጠው ነገር ረገድ በአስደናቂ ሁኔታ የአመለካከት ለውጥ አደረግሁ።

ለሌሎች ነገሮች ቅድሚያ መስጠት ጀመርኩ

ከፔንስልቬኒያ ወደ ካሊፎርኒያ መኖሪያውን የቀየረው የአባቴ ታላቅ ወንድም ጆን ወደ ታሆ ሐይቅ ልሄድ አካባቢ “እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን” የሚል ርዕስ ያለውን መጽሐፍ ሰጥቶኝ ስለነበር ይዤው ወደዚያ ሄድኩ። * * የመጨረሻውን ትርኢት እኩለ ሌሊት ካለፈ በኋላ ጨረስን፤ ከዚያም ከመተኛቴ በፊት ትንሽ ዘና ለማለት መጽሐፉን ማንበብ ጀመርኩ። ለረጅም ጊዜ በአእምሮዬ ሲጉላሉ ለነበሩ ጥያቄዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ መልስ በማግኘቴ በጣም ተደሰትኩ።

ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በምሽት ጭፈራ ቤቶች ውስጥ ከሥራ በኋላ ከባልደረቦቼ ጋር እስኪነጋ ድረስ መወያየት ጀመርን። ከምንወያይባቸው ርዕሶች መካከል ከሞት በኋላ ሕይወት አለ? አምላክ መከራ ሲደርስብን ዝም ብሎ የሚመለከተው ለምንድን ነው? የሰው ልጅ ውሎ አድሮ ራሱንና ምድርን ያጠፋ ይሆን? የሚሉት ይገኙበታል። ከጥቂት ወራት በኋላ ማለትም ሐምሌ 9, 1955 በሎስ አንጀለስ፣ ሪግሊ ፊልድ ስታዲየም በተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ ይሖዋ አምላክን ለማገልገል መወሰኔን በጥምቀት አሳየሁ።

ይህ ከሆነ ከስድስት ወራት ገደማ በኋላ በ1955 የገና በዓል ዕለት ጠዋት ሄንሪ ረስል የተባለ የይሖዋ ምሥክር ጃክ መኮይ ወደተባለ በመዝናኛው የሥራ መስክ ወደተሰማራ ሰው እንድንሄድ ጋበዘኝ። ሄንሪ ራሱ ኤን ቢ ሲ በተባለ የቴሌቪዥን ጣቢያ ውስጥ የሙዚቃ ክፍል መሪ ነበር። ቤታቸው የደረስነው የገና ስጦታዎቻቸውን መክፈት ሲጀምሩ ቢሆንም ጃክ፣ ሚስቱና ሦስት ልጆቻቸው ቁጭ ብለው አዳመጡን። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጃክና ቤተሰቡ የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ።

በዚሁ ጊዜ አካባቢ እናቴን ማስጠናት የጀመርኩ ሲሆን እርሷም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተቀብላ ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክር ሆነች። ከዚያም አቅኚ ማለትም የሙሉ ጊዜ የምሥራቹ ሰባኪ ሆና ማገልገል ጀመረች። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሦስቱ ወንድሞቼ የተጠመቁ ሲሆን ለተወሰነ ጊዜ በአቅኚነት አገልግሎት ተካፍለዋል። እኔም በሃያ ዓመቴ መስከረም 1956 አቅኚ ሆንኩ።

ሥራ መቀጠርን በተመለከተ ያደረግኳቸው ውሳኔዎች

የሥራ ወኪሌ የቅርብ ጓደኛ ጆርጅ መርፊ እኔን ይበልጥ ለማስተዋወቅ ፈለገ። ጆርጅ በ1930ዎቹ እና 40ዎቹ በበርካታ ፊልሞች ውስጥ ተውኗል። ጆርጅ ብዙ ሰዎችን ያውቅ ስለነበር በታኅሣሥ 1956 በኒው ዮርክ ከተማ ባለው ሲ ቢ ኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሚተላለፈው የጃኪ ግሊሰን ፕሮግራም ውስጥ መካፈል ጀመርኩ። ፕሮግራሙ ወደ 20,000,000 የሚገመቱ ሰዎች ይከታተሉት ስለነበር ሥራዬን ለማስተዋወቅ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጎልኛል። ኒው ዮርክ በነበርኩበት ጊዜ በብሩክሊን የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ጎበኘሁ።

በግሊሰን ፕሮግራም ውስጥ ከተካፈልኩ በኋላ ኤም ጂ ኤም ከተባለ የፊልም ኩባንያ ጋር የሰባት ዓመት ኮንትራት ተፈራረምኩ። በምዕራብ ዩናይትድ ስቴትስ ሕይወት ምን እንደሚመስል በሚተርከው ተከታታይ ፊልም ውስጥ ቋሚ ገጸ ባሕርይ ተሰጠኝ። ይሁን እንጂ የሥነ ምግባር ብልግናንና ሌሎች ክርስቲያናዊ ያልሆኑ ባሕርያትን የሚያበረታቱ እንደ ቁማርተኛና አደገኛ ተኳሽ ያሉ ገጸ ባሕርያትን ተላብሼ እጫወት ስለነበር ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሕሊናዬ ይረብሸኝ ጀመር። ስለዚህ ሥራዬን ለቀቅኩ። በመዝናኛው የሥራ መስክ የተሰማሩት ሰዎች ያበድኩ መሰላቸው።

መጀመሪያ ላይ የጠቀስኩት ብዙ ገንዘብ ተከፍሎኝ በላስ ቬጋስ ዝግጅት እንዳቀርብ የተጋበዝኩት በዚህ ወቅት ነበር። ሥራዬን መጀመር የነበረብኝ ተጓዥ የበላይ ተመልካቻችን በሚጎበኝበት ሳምንት ነበር። በዚያን ጊዜ ካልጀመርኩ ደግሞ ሥራውን ላጣ ነው። አባቴ ሠርቼ ብዙ ገንዘብ እንዳገኝ ይጠብቅ ስለነበር በጣም ግራ ተጋባሁ! እኔ ትልቅ ቦታ እንድደርስ ከፍተኛውን ሚና የተጫወተው እሱ በመሆኑ ልክሰው እንደሚገባ ተሰምቶኝ ነበር።

ስለዚህ በ1920ዎቹ ዓመታት ሙዚቀኛና ኒው ዮርክ በሚገኘው ደብልዩ ቢ ቢ አር ሬዲዮ ጣቢያ ቫዮሊን የተባለ የሙዚቃ መሣሪያ ይጫወት ወደነበረው ሰብሳቢ የበላይ ተመልካቻችን ካርል ፓርክ ቀርቤ አማከርኩት። ይህን ሥራ ከሠራሁ ገንዘብ ሳይቸግረኝ ዕድሜ ልኬን በአቅኚነት ማገልገል እንደምችል ገለጽኩለት። “ምን ማድረግ እንዳለብህ ልወስንልህ አልችልም፤ ነገር ግን ውሳኔ ማድረግ እንድትችል እረዳሃለሁ” ሲል መለሰልኝ። ከዚያም እንዲህ ብሎ ጠየቀኝ:- “ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ሳምንት ጉባኤያችንን የሚጎበኝ ቢሆን ኖሮ ጉብኝቱን ጥለህ ትሄድ ነበር?” አክሎም “ኢየሱስ ምን እንድታደርግ የሚጠብቅብህ ይመስልሃል?” ሲል ጠየቀኝ።

ነገሩ በጣም ግልጽ ነው ስል አሰብኩ። ለአባቴ ላስ ቬጋስ ያገኘሁትን ሥራ እንደማልሠራ ስነግረው ሕይወቱን እንዳበላሸሁበት ገለጸልኝ። ያን ዕለት ምሽት ሊገድለኝ አስቦ ሽጉጡን ይዞ ይጠብቀኝ ነበር። ሆኖም በጣም በመጠጣቱ ምክንያት እንቅልፍ ወሰደው። ከዚያም ጋራዥ ውስጥ ራሱን በመኪና ጭስ አፍኖ ሊገድል ሞከረ። የአደጋ ጊዜ እርዳታ ሰጪዎችን ጠርቼ ሕይወቱ ሊተርፍ ቻለ።

አባቴ ግልፍተኛ ስለነበር አብዛኞቹ የጉባኤያችን አባላት ይፈሩት ነበር፤ የወረዳ የበላይ ተመልካቻችን ሬ ዳዌል ግን አልፈራውም። ወንድም ሬ አባቴን ሊጠይቀው በሄደ ጊዜ እኔ ስወለድ በሕይወት የመቆየቴ ነገር በጣም አጠራጣሪ እንደነበር በአጋጣሚ ነገረው። በዚያን ጊዜ አባቴ ከሞት ከተረፍኩ አምላክን እንዳገለግል እንደሚያደርግ ተስሎ ነበር። በዚህን ጊዜ ወንድም ሬ አምላክ ስዕለቴን እንድፈጽም ይጠብቅብኛል ብሎ አስቦ ያውቅ እንደሆነ አባቴን ጠየቀው። ጥያቄው አባቴን አስደነገጠው። ከዚያም ሬ “የአምላክ ልጅ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከተካፈለ የአንተስ ልጅ በዚህ መስክ ቢሰማራ ምን አለበት?” ሲል ጠየቀው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አባቴ ምርጫዬን ለማክበር ፈቃደኛ ሆነ።

በዚያው ሰሞን በጥር 1957 ሸርሊ ላርጅ አቅኚ ከሆነችው የአገልግሎት ጓደኛዋ ጋር ወዳጆቿን ለመጠየቅ ከካናዳ መጣች። እኔ፣ ሸርሊና የአገልግሎት ጓደኛዋ ከቤት ወደ ቤት በምናገለግልበት ጊዜ ከሸርሊ ጋር በደንብ ተቀራረብን። ብዙም ሳይቆይ ሆሊዉድ ውስጥ በሚገኝ ቦውል በሚባል አምፊቲያትር ውስጥ ከፐርል ቤይሊ ጋር በዘፈንኩበት ጊዜ ሸርሊን ይዣት ሄጄ ነበር።

በውሳኔዬ ጸናሁ

በመስከረም 1957 በአይዋ ግዛት በልዩ አቅኚነት እንዳገለግል ተመደብኩ። ለአባቴ በልዩ አቅኚነት ለማገልገል መወሰኔን ስነግረው ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ። ጠቃሚ ስለ ሆነው ነገር ያለኝ አዲስ አመለካከት ምንም ሊገባው አልቻለም። ወደ ሆሊዉድ በመኪና ሄጄ የነበሩኝን ውሎች ሁሉ ሰረዝኩ። ተዋውያቸው ከነበሩት ሰዎች አንዱ ታዋቂው የሙዚቃ ጓድና የመዘምራን ቡድን መሪ ፍሬድ ዋሪንግ ነበር። ውሌን ካፈረስኩ ዳግም ዘፋኝ ሆኜ ልሠራ እንደማልችል ነገረኝ። ስለዚህ የዘፋኝነት ሥራዬን የምተወው በይሖዋ አምላክ አገልግሎት የማደርገውን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ እንደሆነ ነገርኩት።

ሚስተር ዋሪንግ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ስሰጠው በአክብሮት ካዳመጠኝ በኋላ በእርጋታ ያልጠበቅኩትን መልስ ሰጠኝ:- “የእኔ ልጅ ይህን የመሰለ ግሩም ሙያ በመተውህ በጣም አዝናለሁ፤ ሆኖም በሙዚቃ ሙያ ያሳለፍኩት ሕይወት ከሙዚቃ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ነገሮች እንዳሉ አስተምሮኛል። አምላክ የምታደርገውን ነገር ይባርክልህ።” መኪና እየነዳሁ ወደ ቤት ስመለስ ሕይወቴን ለይሖዋ አገልግሎት ለማዋል የሚያስችል ነፃነት በማግኘቴ ያነባሁት የደስታ እንባ እስከ አሁን ድረስ ትዝ ይለኛል።

“ምነው እምነት አጣህ?”

አቅኚ ከሆነው የአገልግሎት ጓደኛዬ ከጆው ትሪፍ ጋር በአይዋ ግዛት በምትገኘው ወደ 1,200 የሚጠጉ ነዋሪዎች ባሏት ስትሮውበሪ ፖይንት የምትባል ከተማ ማገልገል ጀመርኩ። ሸርሊ ልትጠይቀን በመጣችበት ጊዜ ስለ ጋብቻ ጉዳይ አንስተን ተነጋገርን። እኔም ሆንኩ እርሷ ተቀማጭ ገንዘብ አልነበረንም። ሠርቼ ያገኘሁትን ገንዘብ በሙሉ የሚቆጣጠረው አባቴ ነበር። ስለዚህ እንዲህ አልኳት:- “ላገባሽ እፈልግ ነበር፤ ግን እንዴት እንኖራለን? ለልዩ አቅኚ በወር የሚሰጠው የወጪ መሸፈኛ 40 ዶላር ብቻ ነው ያለኝ።” በተለመደ እርጋታዋ በግልጽ እንዲህ አለችኝ:- “ቻርልስ፤ ምነው እምነት አጣህ? ኢየሱስ መንግሥቱንና ጽድቁን ካስቀደምን የሚያስፈልገንን ሁሉ እንደሚጨምርልን ቃል ገብቷል።” (ማቴዎስ 6:33) ነገሩ በዚህ የተደመደመ ሲሆን ኅዳር 16, 1957 ተጋባን።

ከስትሮውበሪ ፖይንት ወጣ ብሎ የሚኖር አንድ መጽሐፍ ቅዱስን የማስጠናው ገበሬ የራሱ ይዞታ በሆነ ጫካ ውስጥ ወደ 8 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ከእንጨት የተሰራ ቤት ነበረው። ቤቱ ኤሌክትሪክም ሆነ የቧንቧ ውኃ እንዲሁም መጸዳጃ ቤት አልነበረውም። ከፈለግን ግን በነጻ መኖር እንችል ነበር። ኋላ ቀር በሆነ መንገድ የተሠራ ቤት ቢሆንም ሙሉ ቀን አገልግሎት ስለምንውል የሚያስፈልገን ማደሪያ ብቻ ነው ብለን ደመደምን።

ውኃ የምቀዳው በአቅራቢያችን ካለ ምንጭ ሲሆን በምድጃ ላይ እንጨት በማንደድ ቤታችንን እናሞቃለን። ለንባብ የነጭ ጋዝ ብርሃን እንጠቀማለን፣ ሸርሊ ደግሞ በነጭ ጋዝ በሚሠራ ምድጃ ምግባችንን ታበስላለች። ገላችንን በአሮጌ ሳፋ ላይ እንታጠብ ነበር። ማታ ማታ የተኩላዎች ጩኸት ይሰማናል፤ አንድ ላይ በመሆናችንና ክርስቲያን አገልጋዮች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ አብረን ለማገልገል በመቻላችን እንደታደልን ይሰማን ነበር። በአሁኑ ጊዜ ብሩክሊን በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የሚሠሩት ቢል ማሌንፎንት እና ባለቤቱ ሳንድረ ወደ 100 ኪሎ ሜትር አካባቢ ርቃ በምትገኘው በዲኮረ፣ አይዋ ውስጥ ልዩ አቅኚዎች ሆነው አገልግለዋል። አልፎ አልፎ ወደ እኛ በመምጣት አብረውን በመስክ አገልግሎት ይካፈሉ ነበር። ከጊዜ በኋላ በስትሮውበሪ ፖይንት 25 ተሰብሳቢዎች ያሉት ትንሽ ጉባኤ ተመሠረተ።

ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆንኩ

በግንቦት 1960 በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት እንድናገለግል ግብዣ ቀረበልን። የመጀመሪያው ወረዳችን ኖርዝ ካሮላይና ሲሆን ይህ ወረዳ ራሌ፣ ግሪንስቦሮና ዱረም የተባሉ ከተሞችን እንዲሁም ሌሎች ትንንሽ የገጠር ከተሞችን ይጨምር ነበር። ኤሌክትሪክና አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የቤት ውስጥ መጸዳጃ ያላቸው ቤተሰቦች ጋር እናርፍ ስለነበር የኑሮ ሁኔታችን ተሻሻለ። በጣም ያሳስበን የነበረው ከቤት ውጪ መጸዳጃ የነበራቸው ወንድሞች ይሰጡን የነበረው ማስጠንቀቂያ ነው። ወደ መጸዳጃ ቤቱ ስንሄድ እባቦች በመንገዱ ላይ ስላሉ እንድንጠነቀቅ ይነግሩን ነበር!

በ1963 መጀመሪያ ላይ ፍሎሪዳ ውስጥ ወደሚገኝ አንድ ወረዳ ተዛወርን፤ በዚያ እያለሁ ለሞት የሚያደርስ የልብ ሕመም ገጠመኝ። ቦብ እና ጂኒ ማኪ የተባሉ የታምፓ ነዋሪዎች ባይረዱን ኖሮ ምናልባት ሞቼ ነበር። * እነርሱን ወደሚረዳቸው ሐኪም ወስደው በራሳቸው ወጪ አሳከሙኝ።

ቀድሞ አግኝቼው የነበረውን ሥልጠና ተጠቀምኩበት

በ1963 የበጋ ወራት በኒው ዮርክ ይደረግ ከነበረ የይሖዋ ምሥክሮች አውራጃ ስብሰባ ጋር የተያያዘ ሥራ እንድሠራ ተጋበዝኩ። የይሖዋ ምሥክሮች ቃል አቀባይ የነበረው ሚልተን ሄንሽል በሬዲዮ ቃለ ምልልስ ሊያደርግ ስለነበር አብሬው ሄድኩ፤ ቃለ ምልልሱን ያደረገለት ሌሪ ኪንግ ነበር። ሚስተር ኪንግ የቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ ፕሮግራም በማዘጋጀት ረገድ አሁንም በጣም የታወቀ ነው። ሰው አክባሪ የነበረ ከመሆኑም በላይ ከቃለ ምልልሱ በኋላ ለአንድ ሰዓት ያህል ሥራችንን በተመለከተ በርካታ ጥያቄዎችን ጠየቀን።

በዚያው የበጋ ወቅት፣ በኮሚኒስት ቻይና በሚስዮናዊነት ሲያገለግል የነበረውና ከእስር የተለቀቀው ሃሮልድ ኪንግ በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ በእንግድነት ተጋብዞ ነበር። አንድ ቀን ምሽት 700 ለሚጠጉ አድማጮች ተሞክሮዎቹንና ከአራት ዓመት በላይ ለብቻው ተገልሎ በእስር ያሳለፈው ጊዜ እምነቱን እንዴት እንዳጠነከረለት ገለጸ። በእስር ቤት እያለ በመጽሐፍ ቅዱስ እና በክርስቲያናዊ አገልግሎት ላይ ያተኮሩ ጭብጦች ያሏቸውን መዝሙሮች ደርሷል።

በዚያ የማይረሳ ምሽት፣ የድምፅ አወጣጥ ሥልጠና ከወሰዱና በእውነት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ከቆዩት ኦድሪ ኖር፣ ካርል ክላይን እና ፍሬድ ፍራንዝ ከተባሉ ወንድሞች ጋር “ከቤት ወደ ቤት” የሚለውን መዝሙር ዘመርኩ፤ ከጊዜ በኋላ ይህ መዝሙር በይሖዋ ምሥክሮች የመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ ተካትቷል። በዚያን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ ይመራ የነበረው ናታን ኖር በቀጣዩ ሳምንት በያንኪ ስታዲየም በተካሄደው “የዘላለሙ ምሥራች” በተባለው ትልቅ ስብሰባ ላይ መዝሙሩን እንድዘምር ጠየቀኝና ዘመርኩ።

ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ ስሠራ ያገኘኋቸው ተሞክሮዎች

በቺካጎ፣ ኢሊኖይ እያገለገልን በነበርንበት ወቅት ሁለት የማይረሱ ነገሮች አጋጠሙን። የመጀመሪያው፣ በአንድ የወረዳ ስብሰባ ላይ ሸርሊ ለእርሷና ለእናቷ በ1940ዎቹ አጋማሽ ላይ በካናዳ እውነትን የመሠከረችላቸውን ቪረ ስቴዋርትን አገኘቻት። በዚያን ጊዜ የ11 ዓመት ልጅ የነበረችው ሸርሊ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች ስትሰማ በጣም ተደሰተች። ቪረን እንዲህ ብላ ጠይቃት ነበር:- “በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ መኖር የምችል ይመስልሻል?” ቪረም “ሸርሊ፤ የማትችይበት ምንም ምክንያት የለም” ስትል መለሰችላት። ሁለቱም እነዚህን ቃላት በትክክል ያስታውሷቸዋል። ከቪረ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ከተወያዮበት ዕለት አንስቶ ሸርሊ ይሖዋን ማገልገል እንዳለባት ተሰማት።

ሁለተኛው ደግሞ፣ አንድ የይሖዋ ምሥክር በ1958 የክረምት ወቅት ወደ 22.6 ኪሎ ግራም የሚመዝን ጆንያ ሙሉ ድንች በራችን ላይ ማግኘታችንን አስታውስ እንደሆነ ጠየቀኝ። በደምብ አስታውሳለሁ። አንድ ቀን ምሽት ንፋስ የቀላቀለ በረዶ ይዘንብ ስለነበር በሥቃይ ቤታችን ደረስን፤ ስንደርስ ድንቹን አገኘን! ማን እንዳመጣው ባናውቅም ላገኘነው ስንቅ ይሖዋን አመሰገንን። ከባድ የበረዶ ዝናብ ስለነበር ለአምስት ቀናት ያህል ከቤት መውጣት አልቻልንም፤ ነገር ግን ድንቹን እንደ ቂጣ በመጋገር፣ በመጥበስ፣ በመፍጨትና ሾርባ በመሥራት እየበላን ስንደሰት ቆየን! ሌላ ምግብ አልነበረንም። ይህ የይሖዋ ምሥክር እኛንም ሆነ የምንኖርበትን ቦታ አያውቅም ነበር፤ ሆኖም በአካባቢው ያሉ አቅኚዎች ችግር እንዳለባቸው ይሰማል። እነዚህ ወጣት አቅኚዎች የሚኖሩበትን ቦታ እንዲፈልግ ልቡ እንዳነሳሳው ነገረኝ። ገበሬዎቹ በአካባቢያቸው ስለሚኖሩ ሰዎች ሁሉን ነገር ያውቁ ስለነበር የእኛን ቤት ጠቆሙትና ድንቹን በበረዶ ውስጥ ተሸክሞ ይዞ መጣ።

ባደረግኩት ምርጫ ደስተኛ ነኝ

በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ለ33 ዓመታት ካገለገልኩ በኋላ ጤንነቴ ክፉኛ ስለተቃወሰ በ1993 የጉብኝት ሥራዬን ለማቆም ተገደድኩ። ሸርሊ እና እኔ አቅማችን የፈቀደውን ያህል እያገለገልን እስከ አሁን ድረስ ልዩ አቅኚዎች ነን። ከአሁን በኋላ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ ለማገልገል የሚያስችል ጥንካሬ የሌለኝ መሆኑ ቢያሳዝነኝም የነበረኝን ጉልበት ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት በማዋሌ ደስ ይለኛል።

ሦስቱ ወንድሞቼ የተለያዩ ምርጫዎችን አድርገዋል። እያንዳንዳቸው ውሎ አድሮ ቁሳዊ ሀብት ማሳደድን መርጠዋል፤ አንዳቸው እንኳን በዛሬው ጊዜ ይሖዋን እያገለገሉ አይደለም። አባቴ በ1958 የተጠመቀ ሲሆን እሱና እናቴ ብዙ ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁና ራሳቸውን ወስነው እንዲጠመቁ ረድተዋል። ሁለቱም በ1999 ሞቱ። ዓለማዊ ዝናንና ሀብትን ላለማሳደድ ያደረግሁት ውሳኔ አባቴ እንዲሁም እርሱና እናቴ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ያካፈሏቸው ሰዎች የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲኖራቸው ምክንያት ሆኗል። ‘በመጀመሪያ ያደረግኩትን ምርጫ ሳላደርግ ቀርቼ ቢሆን ኖሮ ይሖዋን ማገልገሌን እቀጥል ነበር?’ እያልኩ ብዙ ጊዜ ራሴን እጠይቃለሁ።

ተጓዥ የበላይ ተመልካችነቴን ካቆምኩ ከአምስት ዓመታት ገደማ በኋላ ጤናዬ እየተስተካከለ በመምጣቱ አገልግሎቴን ማስፋት ችያለሁ። አሁን በካሊፎርኒያ በሚገኘው ዴዘርት ሆት ስፕሪንግስ ጉባኤ ውስጥ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች ሆኜ አገለግላለሁ። እንዲሁም ተተኪ የወረዳ የበላይ ተመልካች የመሆን፣ በፍርድ ኮሚቴ ውስጥ የማገልገልና በአቅኚዎች አገልግሎት ትምህርት ቤት ውስጥ የማስተማር መብት አግኝቻለሁ።

እስከ አሁን ድረስ ሸርሊ የቅርብ ወዳጄ ነች። እርሷን የመሰለ ወዳጅ ስላለኝ በጣም እደሰታለሁ። አዘውትረን የሚያነቃቁ መንፈሳዊ ጭውውቶችን እናደርጋለን፤ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ላይ የተመሠረቱ ጭውውቶችን በማድረግ እንደሰታለን። ሸርሊ ከዛሬ 47 ዓመታት በፊት በእርጋታ ያቀረበችልኝን “ቻርልስ፤ ምነው እምነት አጣህ?” የሚለውን ጥያቄ አሁን ድረስ በአድናቆት አስታውሰዋለሁ። ወጣት የሆኑ ክርስቲያን ባልና ሚስቶች ይህን ጥያቄ እርስ በርሳቸው ቢጠያየቁ ምን ያህሎቹ እኛ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያገኘነውን ደስታና በረከት ሊያገኙ እንደሚችሉ ይታየኛል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.11 ጆን ሲነትኮ በ1996 በ92 ዓመቱ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ታማኝ የይሖዋ ምሥክር ነበር።

^ አን.11 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ። አሁን ግን መታተም አቁሟል።

^ አን.32 የየካቲት 22, 1975 ንቁ! (እንግሊዝኛ) መጽሔት ከገጽ 12-16 ላይ ቦብ ማኪ ከአካል ጉዳተኝነት ጋር ያደረገውን ትግል የተመለከተ ተሞክሮ ይዞ ወጥቷል።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አጎቴ ጆን በ1935 በተጠመቀበት ዓመት

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከእንጨት የተሠራው ቤታችን

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆቼ እስከ ዕለተ ሞታቸው ታማኝነታቸውን ጠብቀዋል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዛሬው ጊዜ ከሸርሊ ጋር