በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ቆሻሻን ለምግብነት

“ቆሻሻ ለወፎችና ለአጥቢ እንስሳት ምግብነት ጠቃሚ መሆኑ ያስገርማል” በማለት የሥነ ሕይወት ተመራማሪ የሆኑት ቪልፍሪት ሜየር ተናግረዋል። “በአንዳንድ ሥፍራዎች አንዳንድ የእንስሳት ዝርያዎችን በሕይወት እንዲቀጥሉ የሚያስችላቸው ቆሻሻ ነው።” ዴር ሽፒገል የተሰኘው የዜና መጽሔት እንደዘገበው በዓለም ዙሪያ በተደረገው ጥናት ወደ 70 የሚጠጉ የአእዋፍ ዝርያዎችና 50 የሚያህሉ አጥቢ እንስሳት የቤት ጥራጊ ቆሻሻ ይመገባሉ። በቆሻሻ መጣያ አካባቢዎች የሚኖሩ ሕያዋን ፍጥረታት ሕልውና እርስ በርስ የተቆራኘ ነው። ነፍሳት በመበስበስ ላይ ባለው ጥራጊ ውስጥ የሚፈጠረው ሙቀት ያፋፋቸዋል። ወፎችና ትንንሽ አጥቢ እንስሳት እነዚህን ነፍሳት የሚመገቡ ሲሆን እነሱ ራሳቸው ደግሞ በሌሎች ወፎችና አዳኝ እንስሳት ይታደናሉ። የሚገርመው ነገር በተፈጥሯቸው ሰው የሚፈሩ አንዳንድ ወፎችም እንኳን ጥራጊውን የሚጠቀጥቅ መኪና የሚያሰማው የሚያደነቁር ጩኸት፣ የሌሎች እንስሳትና የሰዎች በአካባቢው መኖር ምንም አያስፈራቸውም።

ግዙፍ ዘራፊዎች

በአውራ ጎዳና ላይ መንገደኞችን ጠብቀው የሚዘርፉት ሰዎች ብቻ ላይሆኑ ይችላሉ። ባንኮክ ፖስት እንደዘገበው ከሆነ ዝሆኖችም ዘረፋ ያካሂዳሉ። ከባንኮክ በስተ ምሥራቅ በሚገኘው ጫካ ያሉ የተራቡ ዝሆኖች ሸንኮራ የጫኑ የጭነት መኪናዎች የሚያልፉበትን መንገድ በመዝጋት የጫኑትን ሸንኮራ አገዳ ዘርፈዋል። አንግ ሉዌ ናይ የተሰኘው የዱር አራዊት መጠለያ 130 የሚያህሉ ዝሆኖች ማኖር የሚችል ቢሆንም ደረቁ የአየር ጠባይ የሚመገቡትን ሣር ቅጠል ስለቀነሰባቸው የተራቡት ዝሆኖች ምግብ ፍለጋ ከጫካው ለመውጣት ተገደዋል። የዱር አራዊቱ መጠለያ የበላይ ጠባቂ የሆኑት ዩ ሴናታም እንደተናገሩት አንዳንድ ዝሆኖች እርሻ ውስጥ ገብተው የዘረፉ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ የጭነት መኪና ሾፌሮች ለዝሆኖቹ በማዘን የሚጥሉላቸውን ሸንኮራ ይለቃቅማሉ።

ለእንስሳት የሚሰጥ አንቲባዮቲክ

የዓለም ጤና ድርጅት ላልታመሙ የርቢ እንስሳት ከመጠን ያለፈና አላስፈላጊ የሆነ አንቲባዮቲክ መስጠት ስላለው አደጋ ለረዥም ጊዜ ሲያስጠነቅቅ ቆይቷል። ኤቢሲ የተሰኘው የስፔይን ዕለታዊ ጋዜጣ ባሠፈረው መሠረት ብዙውን ጊዜ መድኃኒቶቹ “የርቢ እንስሳቱን በአጭር ጊዜ እንዲያፋፏቸው ሲባል” በእንስሳቱ መኖ ውስጥ ይጨመራሉ። በቅርቡ በዴንማርክ የተካሄደ ጥናት እንዳመለከተው አንቲባዮቲክ ሳይጠቀሙ እንስሳትን ማርባት አትራፊ ሊሆን ይችላል። ገበሬዎቹ ከእንስሳቱ መኖ ውስጥ አንቲባዮቲኩን ሲያስወግዱ የዶሮ ምርት አልቀነሰም፣ በዓሣማ ሥጋ ምርት ላይም ቢሆን የዋጋ ጭማሪ የታየው 1 በመቶ ብቻ ነበር። የዓለም የጤና ድርጅት የዴንማርክን ጅምር አድንቆ ሌሎች አገሮችም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ እያበረታታ ነው። ጋዜጣው እንደገለጸው በእንስሳት ምግብ ውስጥ አንቲባዮቲክ አለመጨመር “ለተጠቃሚው ኅብረተሰብ ጤንነትም ጠቃሚ ይሆናል።”

አታላይ የቼዝ ተጫዋቾች

“ብዙ የቼዝ ተጫዋቾች የጨዋታውን ደንብ ዘወትር አያከብሩም” በማለት ፍራንክፈርተር አልገማይነ ጻይቱንግ ዘግቧል። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን አንዱን ታዋቂ የቼዝ ተጫዋች ያሸነፈ አንድ አማተር ተጫዋች ነው። ይሁን እንጂ በኋላ በሌላ ክፍል ውስጥ ኮምፒውተር እየተጠቀመ ካለ ሌላ የቼዝ ተጫዋች ጋር የሚገናኝበት ማይክሮፎን፣ የጆሮ ማዳመጫና ካሜራ በረዥም ፀጉሩ ውስጥ ደብቆ ማስገባቱ ተደረሰበት። ሌሎችም ወደ መጸዳጃ ቤት ሄደው በሩን ከዘጉ በኋላ እጅ ላይ የምትያዝ አነስተኛ ኮምፒውተር አውጥተው ቀጣዩን እንቅስቃሴያቸውን እንደሚያሰሉ ታውቋል። በኢንተርኔት የሚጫወቱ የቼዝ ተጫዋቾችም ሊያታልሉ ይችላሉ። አንዳንዶች በኮምፒውተራቸው ላይ ባለ የቼዝ ፕሮግራም እየተጠቀሙ በኢንተርኔት ውድድር ይሳተፋሉ። በሌላ አጋጣሚም ተጫዋቾች ሁለት ስም ተጠቅመው ከራሳቸው ጋር በመወዳደር አንዱ ሁልጊዜ እንዲሸነፍና ሌላው ደግሞ ሁልጊዜ እንዲያሸንፍ ያደረጉ አሉ። “ብዙዎቹ የሚያታልሉት ለገንዘብ ሽልማቱ አይደለም” በማለት ጋዜጣው ይናገራል። “ሁሉንም ለማለት ይቻላል እንዲያታልሉ የሚያነሳሳቸው ስግብግብነት ሳይሆን በውሸትም ቢሆን አሸናፊ የመባል ከንቱ ምኞት ነው።”

የወጣት ጥፋተኝነት ይህን ያህል የተበራከተው ለምንድን ነው?

ወንጀለኛ ልጆች እንዲበራከቱ ያደረገው ዋና ምክንያት በየፊናቸው የሚውሉ ቤተሰቦች አኗኗር እንደሆነ በመስኩ የተሠማሩ ባለሙያዎች ያምናሉ። ዊኬንድ ዊትነስ የተሰኘው የደቡብ አፍሪካ ጋዜጣ እንዳመለከተው ከእነዚህ ልጆች ውስጥ አብዛኞቹ የወጡት ከተፋቱ ወላጆች ወይም “በሥራ ተወጥረው ስለሚውሉ ለልጆቻቸው እንክብካቤ ለማድረግ ከሚደክማቸው አሊያም በጥድፊያ የተሞላ ኑሮ ከሚኖሩ” ወላጆች ነው። ወንጀልን የሚያጠኑት ደቡብ አፍሪካዊቷ የትምህርት ሥነ ልቦና ባለሙያ ኢርማ ላቡስካግኒ እንደሚሉት ከሆነ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ብዙዎቹ ወጣቶች “ቤተሰብ” የሚባለውን ነገር ምንነት እንኳን ስለማያውቁ “ፍቅርና ተቀባይነት ለማግኘት ይጓጓሉ።” በመሆኑም እንደዚህ ያሉት ልጆች ፍቅርና ተቀባይነት የሚያገኙበትን የእኔ የሚሉት ቦታ ፍለጋ ሲባዝኑ የወንጀለኛ ዱርዬዎች ሲሳይ ይሆናሉ። የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ሲሴሊያ ጃንሰን እንደተናገሩት ወላጆች “የራሳቸውን ሥልጣን፣ ስኬትና ሀብት በማሳደድ ስለሚጠመዱ በቤተሰባቸው አባላት ሕይወት ውስጥ ምን እየደረሰ እንዳለ አያውቁም።” ላቡስካግኒና ጃንሰን “ወደ ድሮው የቤተሰብ አኗኗር እንድንመለስ” ምክራቸውን ይለግሳሉ በማለት ጋዜጣው ይናገራል። ጋዜጣው በማጠቃለል “ጤናማና ደስተኛ የሆነ የቀድሞው ዓይነት ቤተሰብ ምንም ምትክ አይገኝለትም” ይላል።

በቻይና የተከሰተው የመኪና ማቆሚያ እጥረት

በቻይና የታየው ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የግል መኪና እንዲኖራቸው አስችሏል። ይህ ግን የመኪና ማቆሚያ ቦታ እጦት አስከትሏል። ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ የተገነቡ በርካታ መኖሪያ ቤቶች የመኪና ማቆሚያ ቦታ የላቸውም። ለዚህም ምክንያቱ ቤቶቹ በተሠሩበት ወቅት መኪና የነበራቸው ሰዎች ቁጥር በጣም ጥቂት መሆኑ ነው። ከበርካታ ዓመታት በፊት በተቋቋሙ የመኖሪያ ሠፈሮች ውስጥ የሚገኙት መንገዶች ጠባብና ጠመዝማዛ በመሆናቸው መንገድ ዳር መኪና ማቆም ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው። በአሁኑ ጊዜ “ቤጂንግ ውስጥ ያሉት የመኪናዎች ብዛት ከ2 ሚሊዮን የበለጠ ሲሆን የመኪና ማቆሚያ ቦታ ግን 600,000 ብቻ ነው” ሲል ቻይና ቱዴይ ዘግቧል። በመላ አገሪቱ ሕጋዊ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ያላቸው 20 በመቶ የሚያህሉ የመኪና ባለ ንብረቶች ብቻ ናቸው። የመኪናዎች ቁጥር ማደጉን የሚያመላክተው ሌላው ነገር የነዳጅ ፍጆታ መጨመር ሲሆን “ቻይና በነዳጅ ፍጆታ በዓለም ሁለተኛ በመሆን በቅርቡ የጃፓንን ቦታ እንደምትይዝ ይጠበቃል” ሲል ቻይና ቱዴይ ዘግቧል።

ገዳይ ርዕደ መሬቶች በ2003

“የዩናይትድ ስቴትስ የምድር ጥናት ተቋም እንዳመለከተው 2003 ያበቃው ከ1990 ወዲህ ታይተው የማያውቁ እንዲያውም በ2002 ከደረሱት ርዕደ መሬቶች 25 ጊዜ እጥፍ የበለጠ ገዳይ የሆኑ ርዕደ መሬቶችን በማስተናገድ ነው” በማለት ከተቋሙ የወጣ አንድ ዘገባ ይገልጻል። “በ2002 በዓለም ዙሪያ በደረሱ ርዕደ መሬቶች 1711 ሰዎች ሲሞቱ” ባለፈው ዓመት ግን 43,819 ሰዎች አልቀዋል። ከእነዚህ ሟቾች ውስጥ 41,000 የሚሆኑት ያለቁት ታኅሣሥ 26, 2003 በኢራን ውስጥ በባም ከተማ መጠኑ በሬክተር መለኪያ 6.6 የሆነ የመሬት መናወጥ በደረሰ ጊዜ ነበር። “ታላቅ” ርዕደ መሬት ለመባል የበቃው በጣም አሰቃቂው ርዕደ መሬት መስከረም 25, 2003 የጃፓኗን ሆካይዶ የመታው ነበር። መጠኑ በሬክተር መለኪያ 8.3 የደረሰ ነበር። በዘገባው መሠረት “የዩናይትድ ስቴትስ የምድር ጥናት ተቋም በየቀኑ ወደ 50 የሚጠጉ ርዕደ መሬቶች ይመዘግባል። . . . በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ በአማካይ መጠናቸው በሬክተር መለኪያ ከ7.0 እስከ 7.9 የሚደርስ 18 ርዕደ መሬቶችና በሬክተር መለኪያ 8.0 ወይም ከዚያ በላይ የሚደርስ አንድ ታላቅ የመሬት መናወጥ ይከሰታሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ርዕደ መሬቶች የሚደርሱ ሲሆን ብዙ ርዕደ መሬቶች ግን በጣም ሩቅ በሆኑ ቦታዎች የሚከሰቱ በመሆናቸው፣ አለዚያም መጠናቸው በጣም አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት ሳይደረስባቸው ይቀራሉ።”