በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተረሳው የጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም

የተረሳው የጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም

የተረሳው የጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም

ኒው ዚላንድ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

በቀላሉ ሊያዝ የሚችል፣ ለማንበብ የማያስቸግር ጽሕፈት ያለውና መጠኑ አነስተኛ የሆነ መጽሐፍ ቅዱስ አለህ? አዘገጃጀቱ የምትፈልገውን መረጃ በቀላሉ ለማግኘት የሚያስችል ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች የሰጠኸው ምላሽ አዎን የሚል ከሆነ በ1560 የታተመው የጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ ባለውለታህ ነው።

በዛሬው ጊዜ ስለ ጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያውቁት ጥቂቶች ናቸው። ሆኖም ይህ በዓይነቱ ልዩ የነበረ ትርጉም በዘመኑ በብዛት በመሸጥ አቻ አልነበረውም። የትርጉሙ ትክክለኛነትና አዘገጃጀቱ በዓይነቱ የመጀመሪያ መሆኑ በአንባቢዎች ዘንድ ተወዳጅ እንዲሆን አድርጎታል። እንግሊዛውያኑ የቲያትር ደራሲያን ሼክስፒር እና ማርሎው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶችን የሚጠቅሱት ከዚህ ትርጉም ነበር።

ይህ ተወዳጅ የ16ኛው መቶ ዘመን እንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ፈረንሳይኛ ቋንቋ በሚነገርባት የስዊስ ከተማ ጄኔቫ እንዴት ሊጻፍ ቻለ? ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ልዩ የሚያደርጉት ገጽታዎች ምንድን ናቸው? ጥቅም ላይ መዋሉን እንዲያቆም ያደረገው ነገር ምንድን ነው? ዛሬስ በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

አዳዲስ ገጽታዎች ያሉት መጽሐፍ ቅዱስ

የጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ አዘጋጆች፣ ሜሪ ቲዩዶር በ1553 ንግሥት በሆኑበት ወቅት በእንግሊዝ የነበረውን ሃይማኖታዊ ጭቆናና ሊከሰት የሚችለውን ግድያ በመፍራት የተሰደዱ ሰዎች ናቸው። እነዚህን ምሑራን የጄኔቫ ፕሮቴስታንቶች በደስታ ተቀበሏቸው። ጄኔቫ የሕትመት ኢንዱስትሪ ያደገባት ቦታ ስለነበረችና ነዋሪዎቿም መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ፍላጎት ስለነበራቸው መጽሐፍ ቅዱስን የመተርጎምና የማተም ሥራ በሰፊው ይካሄድባት ነበር።

በዊልያም ህዊቲንግኸም እና በረዳቶቹ የተተረጎመው የጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ በ1560 ታትሞ ወጣ። ብዙም ሳይቆይ እንግሊዝ ውስጥ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሱን በጉጉት ያነቡት ጀመር። ከዚያ ቀደም ከወጡት ትርጉሞች ይልቅ ለማንበብ ቀላል የነበረው ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ በሰፊው በሚሠራበት ጥቅሶችን በቁጥር በመከፋፈል ዘዴ የተዘጋጀ የመጀመሪያው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። እንዲሁም አንባቢዎች በቀላሉ የሚፈልጉትን ጥቅስ ለማግኘት እንዲችሉ በእያንዳንዱ ገጹ አናት ላይ ጥቂት ቁልፍ የሆኑ ቃላትን በርዕስ መልክ ይዟል። በተጨማሪም ተርጓሚዎቹ ደማቅ የሆኑትን ጥንታዊ የጎቲክ ፊደላት ከመጠቀም ይልቅ አዳዲስ የጽሑፍ ፊደላት በመቅረጽ ዛሬ ያሉት የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱሶች የተጻፉበትን የሚመስል የአጻጻፍ ስልት ተጠቅመዋል።

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአትሮንስ ላይ ለማንበብ ታስበው የተዘጋጁ የቀድሞ መጽሐፍ ቅዱሶች ለመያዝ የማይመቹና ትላልቅ ነበሩ። የጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ ግን መጠኑ ከበፊቱ በግማሽ ያህል የሚያንስ ለመያዝ ምቹ የሆነ መጽሐፍ ነበር። ይህ አነስተኛ መጠን ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ለግል ንባብና ጥናት የሚመች ብቻ ሳይሆን ዋጋውም ቀላል ነበር።

በትክክል ለመተርጎም የተደረገው ጥረት

የጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የመጀመሪያውን የዕብራይስጥ ጽሑፍ ለዛና መንፈስ ለማስተላለፍ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም በዘፀአት 6:3፤ 17:5 እና በመዝሙር 83:18 እንዲሁም በሌሎች ጥቂት ቦታዎች ላይ ይገኛል። ተርጓሚዎቹ አስፈላጊ ናቸው ብለው የጨመሯቸውን ቃላት ጋደል አድርገው የጻፏቸው ሲሆን የጥቅሱን ሰዋስዋዊ አገባብ ግልጽ ለማድረግ ሲባል የተጨመሩትን ቃላት ደግሞ በማዕዘናዊ ቅንፍ ውስጥ አስገብተዋቸዋል።

የጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በስኮትላንድ ወዲያው ሕጋዊ እውቅና አገኘ። በእንግሊዝ አገርም ቢሆን ብዙ ሰዎች ይጠቀሙበት ነበር፤ እንዲሁም በ1620 አሁን ዩናይትድ ስቴትስ ወደሚባለው ቦታ የተጓዙ እንግሊዛውያን ቅኝ ገዥዎች ይህን ትርጉም ይዘው እንደሄዱ ይገመታል። ይህ ትርጉም በጣም ርቃ የምትገኘውን ኒው ዚላንድን ጨምሮ ወደ ሌሎች የእንግሊዝ ቅኝ ግዛቶችም ተወስዷል። የኒው ዚላንድ ገዥ የነበረው ሰር ጆርጅ ግሬይ በ1845 ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በነበሩት የመጻሕፍት ስብስብ ላይ ጨምሮታል።

ውዝግብ የፈጠሩት የኅዳግ ማስታወሻዎች

የጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ ሰፊ ማብራሪያ መስጠቱ በአንባቢዎቹ ዘንድ ለረጅም ጊዜ ተወዳጅ እንደሆነ እንዲቆይ አስተዋጽኦ አድርጓል። ተርጓሚዎቹ እነዚህን ተጨማሪ ማብራሪያዎች የሰጡት መጽሐፍ ቅዱስ ‘አስቸጋሪ ቦታዎች’ ወይም ለመረዳት የሚከብዱ ክፍሎች እንዳሉት በማመናቸው ነው። የኅዳግ ማስታወሻዎችን መጻፍ በዚያን ጊዜ የተጀመረ ነገር አልነበረም። ቲንደል በ1534 ባሳተመው “አዲስ ኪዳን” ላይ ይህን ዘዴ ተጠቅሟል። የጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ የአንባቢውን ግንዛቤ ለማስፋት ከኅዳግ ማስታወሻዎች በተጨማሪ ሥዕሎችን፣ መግቢያዎችንና ካርታዎችን አካትቷል። መጽሐፉ የዘር ሐረጎችን የያዘ ሣጥን፣ ፍሬ ነገሮቹን የሚገልጽ ሐሳብና መጽሐፍ ቅዱስ በየዕለቱ እንዲነበብ የቀረበ ማበረታቻም ይዟል።

የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ባለ ሥልጣናት ትርጉሙ ድንቅ መሆኑን በግል ቢያምኑም የኅዳግ ማስታወሻዎቹ አጻጻፍ ከተለመደው ወጣ ያለ ነው በማለት በአደባባይ አወገዙት። በዚያን ጊዜ የካንተርበሪ ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ማቲው ፓርከር “ጠንቅ የሆኑ በርካታ ማስታወሻዎች” ሲሉ ጠርተዋቸዋል። ንጉሥ ጄምስ ቀዳማዊ እነዚህን የኅዳግ ማስታወሻዎች “በጣም አድሏዊነት ያላቸው፣ እውነትነት የሌላቸው፣ ሕዝባዊ ዓመጽ የሚያነሳሱ” ሲሉ ገልጸዋቸዋል። አንዳንዶቹ ማስታወሻዎች ነገሥታቱ የመግዛት “መለኮታዊ መብት” አላቸው የሚለውን ሐሳብ ስለሚቃወሙ እነዚህን የመሰሉ አስተያየቶች ቢሰጡ ምንም አያስደንቅም!

የጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅም ላይ መዋሉ ቀረ

ንጉሥ ጄምስ የጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ ከእንግሊዝ ጨርሶ እንዲጠፋ በማሰብ በ1604 አዲስ ትርጉም እንዲዘጋጅ ትእዛዝ ሰጡ። የሃይማኖት ታሪክ ጸሐፊ የሆኑት አለስተር መግራት እንደገለጹት “የኪንግ ጄምስ ትርጉም በአሥራ ሰባተኛው መቶ ዘመን ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት እንዳያገኝ ትልቁ መሰናክል የሆነበት ነገር የጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የነበረው ተወዳጅነት መቀጠሉ ነው።” የጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ ለበርካታ ዓመታት በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የነበረው ሲሆን በስኮትላንድ ሕጋዊ መጽሐፍ ቅዱስ ሆኖ ቆይቷል። እስከ 1644 ድረስ አዳዲስ እትሞች መውጣታቸውን ቀጥለው ነበር።

የብሪታንያና የባሕር ማዶ አገራት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር እንዲህ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል:- “በ1611 በታተመው በኪንግ ጄምስ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው ተርጓሚዎቹ . . . ከሌሎች እንግሊዝኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይልቅ የጄኔቫ [መጽሐፍ ቅዱስ] ተጽዕኖ አድርጎባቸዋል።” በጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ጥቅም ላይ የዋሉት አዳዲስ የአጻጻፍ ስልቶችና የተተረጎመበት መንገድ በኪንግ ጄምስ ትርጉም ላይ ተንጸባርቋል፤ መክብብ 12:1 እና ማቴዎስ 6:29 ለዚህ ግሩም ምሳሌ ናቸው።

ያሳደረው ዘላቂ ተጽዕኖ

የጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ ውሎ አድሮ በኦቶራይዝድ ትርጉም ወይም በኪንግ ጄምስ ትርጉም ቢተካም በሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ግምት ይሰጠዋል። ይህ ትርጉም አዳዲስ የአተረጓጎም ስልቶችንና የአቀራረብ ዘዴ ከማስተዋወቁም በተጨማሪ በተከታታይ እየተሻሻሉ ለወጡት የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱሶች እንደ ዋና መንደርደሪያ ሆኖ አገልግሏል። እንዲሁም የማንበብ አጋጣሚው ያልነበራቸው በርካታ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነቡና እንዲያጠኑ አበረታቷል።

የጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለኪንግ ጄምስ ትርጉም ጥርጊያ መንገድ ከመክፈቱም በላይ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በሥነ ጽሑፍ መስክ እንዲጠቀሱ ምክንያት ሆኗል። ስለዚህ የጄኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በበርካታ ሰዎች ዘንድ የተረሳ ቢሆንም እንኳን በታሪክ ውስጥ የራሱን አሻራ ትቷል።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ ስም የሚገኝበት ዘፀአት 6:3

[በገጽ 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በገጹ አናት ላይ የተጻፉ መግለጫዎች

ሥዕላዊ መግለጫ

የኅዳግ ማስታወሻዎች

[ምንጭ]

ፎቶዎቹ በሙሉ የተወሰዱት:- Courtesy American Bible Society

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ፎቶዎቹ በሙሉ የተወሰዱት:- Courtesy American Bible Society