በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዓይን ብርሃን ፀር የሆነው ግላኮማ

የዓይን ብርሃን ፀር የሆነው ግላኮማ

የዓይን ብርሃን ፀር የሆነው ግላኮማ

እስቲ ላንዳፍታ ዓይንህን በዚህ ዓረፍተ ነገር መጨረሻ ባለው ቃል ላይ አሳርፍ። ዓይንህን ከዚህ ቃል ላይ ሳትነቅል በዙሪያው፣ ማለትም በዚህ ገጽ ላይ ዓይኖችህ ከተተከሉበት ቃል በላይና በታች እንዲሁም ግራና ቀኝ ያሉት ቃላትና ፊደላት ይታዩሃል? የጨረፍታ እይታ በመባል የሚታወቀው እይታ በመኖሩ ምክንያት ሳይታዩህ እንደማይቀሩ ይታመናል። ይህ ችሎታ ከጎንህ በኩል ሾከክ እያለ የሚመጣን ሰው እንድታይ ያደርግሃል። የጨረፍታ እይታ በእግር በምትሄድበት ጊዜ በመሬት ላይ ካሉ የሚያደናቅፉ ነገሮች ገለል ብለህ እንድታልፍና ከግድግዳ ጋር እንዳትጋጭ ይረዳሃል። መኪና የምትነዳ ከሆነም አንድ እግረኛ የመንገዱን ጠርዝ ለቆ ሊገባብህ መሆኑን እንድታስተውል ይረዳሃል።

ይሁን እንጂ ይህን ገጽ በምታነብበት ጊዜ እንኳን ሳይታወቅህ የጨረፍታ እይታህ ቀስ በቀስ እየቀነሰ ሊሆን ይችላል። በዓለም ዙሪያ በግምት 66 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በጥቅሉ ግላኮማ ተብለው በሚጠሩ የዓይን በሽታ ዓይነቶች እየተጠቁ ነው። ከዚህ ቁጥር ውስጥ ከአምስት ሚሊዮን የሚበልጡት ጨርሶ የታወሩ በመሆናቸው ግላኮማ ለዓይነ ሥውርነት መንስኤ ከሆኑት ነገሮች መካከል የሦስተኝነትን ደረጃ ይይዛል። “ሆኖም በግላኮማ ላይ ያነጣጠሩ የትምህርት መርሐ ግብሮች በሚካሄዱባቸው ያደጉ አገሮች እንኳ ግላኮማ ካለባቸው ሰዎች ውስጥ ገሚሶቹ በሽታው ሳይታወቅላቸው ይቀራል” በማለት ዘ ላንሴት የተሰኘው የሕክምና መጽሔት ይናገራል።

በግላኮማ የመያዝ አጋጣሚ ያላቸው እነማን ናቸው? በሽታው ተለይቶ የሚታወቀውና ሕክምና ሊደረግለት የሚችለውስ እንዴት ነው?

ግላኮማ ምንድን ነው?

በመጀመሪያ ስለ ዓይናችን መረዳት ያለብን ጥቂት ነገር አለ። በአውስትራሊያው የግላኮማ ተቋም የተዘጋጀ ብሮሹር እንደሚገልጸው “ዓይናችን ቋሚ ቅርጹን የሚያገኘው ለስላሳ የሆኑ የዓይን ሕብረ ሕዋሳት ልክ እንደ መኪና ጎማ ወይም እንደ ፊኛ ‘ሲነፉ’ በሚያስከትሉት ግፊት ነው።” በዓይን ውስጥ በእንግሊዝኛ ሲሊያሪ ቦዲ የሚባል ቧንቧ ኤክዊየስ ሂዩመር የሚባል ፈሳሽ ከደም ሥር ወስዶ ወደ ዓይን ያስገባል። “ኤክዊየስ ሂዩመር በዓይን ውስጥ ለውስጥ እየተዘዋወረ የዓይንን ሕዋሳት መግቦ ሲያበቃ በፊት ዓይናችን ላይ የሚገኘውን ብርሃን አስተላላፊ ስስ መሸፈኛ (ኮርኒያ) እና ወደ ዓይናችን የሚገባውን ብርሃን መጠን የሚቆጣጠረውን የዓይናችን ክፍል (አይሪስ) በሚያገናኘው በእንግሊዝኛ ትራቤኩላር ሜሽዎርክ በሚባለው እርስ በርሳቸው የተጠላለፉ ማጥለያ መሳይ ማስተላለፊያዎች በሞሉበት አካል በኩል አድርጎ ወደ ደም ሥር ይመለሳል።”

ትራቤኩላር ሜሽዎርክ በማንኛውም ምክንያት ከተዘጋ ወይም ከጠበበ በዓይናችን ውስጥ ያለው ግፊት ይጨምርና የኋላ ኋላ በዓይናችን በስተጀርባ ያሉ በቀላሉ የሚበሳሰኩ የነርቭ ክሮች ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል። ይህ ሁኔታ ሥር የሰደደ ቀላል ግላኮማ ወይም ክፍት ማዕዘን ግላኮማ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን 90 በመቶ ለሚሆኑት በግላኮማ ምክንያት ለሚመጡ የዓይን በሽታዎች መንስኤ ሆኖ ይጠቀሳል።

በእንግሊዝኛ ኢንትራኦኪዩላር ፕሬዠር ተብሎ የሚጠራው በዓይንህ ውስጥ ያለው ግፊት በቀን ውስጥ ሊለዋወጥ የሚችል ሲሆን የልብ ምትህን፣ የምትጠጣውን ፈሳሽ መጠንና የሰውነት አቋምህን ጨምሮ የተለያዩ ምክንያቶች ተጽዕኖ ሊያደርጉበት ይችላሉ። እነዚህ በተፈጥሮ በዓይን ግፊት ላይ የሚከሰቱ ለውጦች በዓይንህ ላይ ጉዳት አያስከትሉም። የጤነኛ ዓይን ግፊት ከሰው ወደ ሰው ስለሚለያይ በዓይንህ ላይ የሚደርስ ከፍተኛ ግፊት በራሱ ግላኮማ አለብህ ሊያሰኝ አይችልም። ሆኖም ከፍተኛ የዓይን ግፊት ግላኮማ ሊኖርብህ እንደሚችል ከሚጠቁሙት ምልክቶች አንዱ ነው።

እምብዛም የማያጋጥም የግላኮማ ዓይነት አጣዳፊ ወይም የማዕዘን መዘጋት የሚባለው ግላኮማ ሲሆን ይህም በኮርኒያና አይሪስ መካከል ያለው ማዕዘን ከወትሮው ጠባብ ሲሆን የሚያጋጥም ነው። ክፍት ማዕዘን ግላኮማ ከሚባለው በተቃራኒ ይኼኛው ዓይነት ግላኮማ በዓይን ላይ ድንገተኛ የሆነ የግፊት መጨመር የሚያስከትል ነው። የእይታ መደብዘዝንና ማስመለስን ጨምሮ ከባድ የዓይን ህመም ያስከትላል። ምልክቶቹ መታየት ከጀመሩ አንስቶ በሰዓታት ውስጥ ሕክምና ካልተገኘ አብዛኛውን ጊዜ መታወርን ያስከትላል። ሌላው ዓይነት ግላኮማ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ግላኮማ ተብሎ ይጠራል። ስሙ እንደሚያመለክተው ይኼኛው ዓይነት ግላኮማ በዓይን ላይ በሚወጡ ዕጢዎች፣ ካታራክት በሚባለው የዓይን ብርሃን መታገድ ችግር፣ በዓይን ላይ በሚደርሱ ጉዳቶች ወይም እነዚህን በመሳሰሉ ሌሎች ችግሮች ሳቢያ የሚመጣ ነው። የዘር ውርስ ግላኮማ በመባል በሚታወቀው በአራተኛው ዓይነት ግላኮማ የሚጠቁት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ናቸው። ይኼኛው ዓይነት ግላኮማ አብሮ የሚወለድ ወይም ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የሚጀምር ሲሆን ሕፃኑ የፈጠጠ ዓይን ያለው ከሆነና ብርሃን ለማየት የሚፈራ ከሆነ የዘር ውርስ ግላኮማ እንዳለበት አመላካች ነው።

የማየት ችሎታን የሚጎዳው እንዴት ነው?

ግላኮማ ሳይታወቅህ የአንድ ዓይንህን የማየት ችሎታ 90 በመቶ ሊቀንሰው ይችላል። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ሁላችንም በተፈጥሯችን ከዓይናችን በስተኋላ በኩል ምስል ተቀባይ በሆነው የዓይናችን ክፍል (ሬቲና) ላይ ብርሃን የማያስተላልፍ ሥፍራ አለን። የነርቭ አውታሮች ኦፕቲክ ነርቭ በመባል የሚታወቀውን ለመፍጠር የሚገናኙበት ይህ ሥፍራ ብርሃን የሚለዩ ሴሎች የሉበትም። ይሁን እንጂ አንጎልህ ዓይንህ ያረፈበትን ምስል ሽርፍራፊዎች “አገጣጥሞ” የማሳየት ችሎታ ስላለው በዓይንህ ላይ ያለው ብርሃን የማያስተላልፍ ክፍል መኖሩም እንኳን አይታወቅህም። ይኸው የአንጎል ችሎታም ነው ግላኮማን ሳይታወቅ ከፍተኛ ጉዳት እንዲያደርስ የሚያደርገው።

ዶክተር ኢቫን ጎልድበርግ የተባሉ የታወቁ የአውስትራሊያ የዓይን ሐኪም ለንቁ! ሲናገሩ “ግላኮማ ምንም ምልክት ስለማያሳይ መሠሪ ሌባ ነው። በሠፊው የሚታወቀው የግላኮማ ዓይነት ቀስ እያለ ሆኖም ያለማቋረጥ ስር እየሰደደ የሚመጣና ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ ዓይንን ከአንጎል ጋር የሚያገናኙትን የነርቭ አውታሮች የሚያበላሽ ነው። ዓይንህ እንባ እንባ የሚለው ይሁን አይሁን፣ ደረቅ ይሁን አይሁን ወይም ስታነብና ስትጽፍ በግልጽ ማየት የምትችል ሆንክ አልሆንክ፣ ለግላኮማ ምንም ልዩነት አያመጣም። በማየት ችሎታህ ላይ ምንም እንከን ሳይሰማህ በጣም ከባድ ግላኮማ ይኖርብህ ይሆናል።”

ግላኮማ መኖሩን መርምሮ ማግኘት

ክፋቱ ደግሞ ግላኮማን መርምሮ ለማግኘት የሚያስችል የተወሰነ ምርመራ አለመኖሩ ነው። የዓይን ስፔሻሊስቱ ቶኖሜትር የሚባል መሣሪያ በመጠቀም በዓይንህ ውስጥ ያለውን ፈሳሽ ግፊት በመፈተሽ ምርመራውን ይጀምር ይሆናል። ኮርኒያ የሚባለው የፊት ዓይንህ ስስ ሽፋን በቀስታ በቶኖሜትሩ እንዲሰፋ ይደረጋል። ይህን ለማከናወን የሚያስፈልገውን ኃይል በመመጠን በዓይንህ ውስጥ ያለውን ግፊት መጠን ይለካል። በተጨማሪም የዓይን ስፔሻሊስቱ ዓይንን ከአንጎል ጋር በሚያገናኘው የነርቭ አውታር ላይ ጉዳት የደረሰበትን ሕብረ ሕዋስ የሚያሳውቁ መሣሪያዎችን በመጠቀም የግላኮማ ምልክት መኖሩን ይመለከታል። ዶክተር ጎልድበርግ “በዓይን ኋላ ያሉት የነርቭ ክሮች ወይም የደም ሥሮች ቅርጽ እንደ ወትሮው መሆን አለመሆኑን እናያለን፣ ምክንያቱም ይህ ነርቮች ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን የሚጠቁም ሊሆን ይችላል” ይላሉ።

ግላኮማ መኖር አለመኖሩን ለማወቅ የሚያስችል ሌላ ምርመራም አለ። ዶክተር ጎልድበርግ “ሰውየው ብሩሕ በሆነ ክብ ጎድጓዳ ነገር ላይ እንዲመለከት ይደረግና በውስጡ በተለያዩ ሥፍራዎች ላይ ደመቅ ያለ ብርሃን እንዲበራ ይደረጋል። ሰውየው/ሴትየዋ ይበልጥ ደማቅ የሆነውን ትንሹን ነጭ ብርሃን ሲያይ/ስታይ ደወል ይጫናል/ትጫናለች” በማለት ያብራራሉ። ዓይኖችህ ከተተከሉበት ማዕከላዊ ሥፍራ ውጪ የሚበራውን ነጭ ብርሃን ማየት ካልቻልክ ግላኮማ እንዳለብህ ሊጠቁም ይችላል። ይህን አድካሚ የምርመራ ሂደት ሊያቃልሉ የሚችሉ አዳዲስ መሣሪያዎች በመሠራት ላይ ናቸው።

ግላኮማ ሊይዛቸው የሚችሉት እነማን ናቸው?

ፖል በ40ዎቹ ዓመታት ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የሚገኝ ጤናማ ሰው ነው። እንዲህ ይላል:- “መነጽር ለማስለወጥ ብዬ ዓይኔን ለመመርመር ወደ ዓይን ሐኪም ሄጄ ሳለ ከቤተሰቦቼ መካከል ግላኮማ የነበረበት ሰው እንዳለ ጠየቀኝ። እኔም ሳጠያይቅ የእናቴ ወንድምና እህት ግላኮማ እንደነበረባቸው ሰማሁ። ወደ ዓይን ስፔሻሊስት ተላክሁኝና ግላኮማ እንዳለብኝ ተረጋገጠ።” ዶክተር ጎልድበርግ እንደሚከተለው በማለት ያብራራሉ:- “እናትህ ወይም አባትህ ግላኮማ ከነበረባቸው አንተም በበሽታው የመያዝ አጋጣሚህ ከሦስት እስከ አምስት እጥፍ ይጨምራል። ግላኮማ ያለባቸው ወንድም ወይም እህት ካሉህ ደግሞ አንተም የመያዝ አጋጣሚህ ከአምስት እስከ ሰባት እጥፍ ይጨምራል።”

በዩናይትድ ስቴትስ የግላኮማ ተቋም ውስጥ የሚሠሩት ዶክተር ኬቪን ግሪኒጅ ለግላኮማ የሚያጋልጡ ሌሎች አጋጣሚዎችም እንዳሉ እንደሚከተለው በማለት ይናገራሉ:- “ዕድሜህ ከ45 ዓመት በላይ ከሆነና አፍሪካዊ ዝርያ ያለህ ከሆንክ ወይም ግላኮማ ያለበት ዘመድ ካለህ፣ ከርቀት የማየት ችግር ካለብህ፣ የስኳር በሽተኛ ከሆንክ፣ ቀደም ሲል በዓይንህ ላይ ጉዳት ደርሶብህ ከነበረ አሊያም ደግሞ ኮርቲሶን/ስቴሮይድ የሚባሉትን መድኃኒቶች አዘውትረህ የምትወስድ ከሆነ በየዓመቱ ዓይንህን መመርመር ይኖርብሃል።” ለግላኮማ የመጋለጥ አጋጣሚ የሌለህና ዕድሜህም ከ45 ዓመት በታች ብትሆንም እንኳን የግላኮማ ተቋሙ በየአራት ዓመቱ የግላኮማ ምርመራ እንድታደርግ ይመክራል። ዕድሜህ ከ45 ዓመት በላይ ከሆነ ደግሞ በየሁለት ዓመቱ ተመርመር።

ታከመው፣ እንዲሁም ተቆጣጠረው

ፖል ግላኮማውን በታከመበት ወቅት በቀን አንድ ጊዜ ዓይን ውስጥ የሚጨመር ልዩ የዓይን ጠብታ ታዝዞለታል። ፖል “ጠብታው በዓይኖቼ ውስጥ የሚፈጠረውን የኤክዊየስ ፈሳሽ መጠን ይቀንሳል” ሲል ተናግሯል። በተጨማሪም ፖል በዓይኑ ላይ በተፈጥሮ የእንባ መውጫ ባለበት ቦታ አካባቢ በሌዘር ጨረር አሥር ትንንሽ ቀዳዳዎች “በማስበሳት” ሕክምና አድርጎ ነበር። እንዲህ ይላል:- “በሌዘር ጨረሩ የመጀመሪያውን ዓይኔን በታከምኩበት ጊዜ በጣም ተጨንቄና ተደናግጬ ስለነበር ስቃዩ በጣም ተሰምቶኝ ነበር። ይሁን እንጂ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሁለተኛውን ዓይኔን በታከምኩበት ጊዜ ውጤቱን ስላወቅኩ አልተጨነቅሁም። ከበፊቱ በጣም በተሻለ መልኩ ዘና ብዬ ስለነበር ሐኪሙ ሳይታወቀኝ ሕክምናውን ጨረሰልኝ።” ፖል ያደረገው ሕክምና በዓይኑ ውስጥ ያለውን ግፊት ለመቆጣጠር ረድቶታል።

በመሆኑም ፖል አዎንታዊ አመለካከት ሊኖረው ችሏል። እንዲህ ይላል:- “መጠነኛ ጉዳት የደረሰበት ምስል ተቀባዩ የዓይን ክፍል (ሬቲና) ብቻ ስለሆነና አሁንም ሙሉ የጨረፍታ እይታ ስላለኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ። የዓይን ጠብታዬን በየቀኑ ማድረግ ካስታወስኩ የጨረፍታ እይታዬ ሳይጓደል እንዳለ መቀጠል የሚችል ይመስለኛል።”

“መሠሪ ሌባ” ተብሎ የተገለጸው ግላኮማ እይታህን እየሰረቀብህ ነው? እስካሁን ከግላኮማ ነፃ መሆን አለመሆንህን ለማወቅ ምርመራ ያላደረግህ ከሆነና በተለይም ደግሞ ለግላኮማ የመጋለጥ አጋጣሚ ካላቸው ሰዎች መካከል ከሆንክ የግላኮማ ምርመራ እንዲያደርግልህ ሐኪምህን ብትጠይቅ ጥሩ ነው። ዶክተር ጎልድበርግ እንደሚሉት ከሆነ “በግላኮማ የሚመጣውን አብዛኛውን ጉዳት ቀደም ብሎ ተገቢ ሕክምና በማድረግ መከላከል ይቻላል።” አዎን፣ ግላኮማን መታከምና መቆጣጠር ትችላለህ!

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በግላኮማ የመያዝ አጋጣሚህ የሚጨምረው

● አፍሪካዊ ዝርያ ያለህ ከሆንክ

● ግላኮማ ያለበት የቅርብ ዘመድ ካለህ

● የስኳር በሽተኛ ከሆንክ

● ከርቀት የማየት ችግር ካለብህ

● ለሕክምና በሚታዘዙ አንዳንድ ቅባቶችና በአስም ስፕሬይ ውስጥ የሚገኙትን የኮርቲሶን/ስቴሮይድ ንጥረ ነገሮች አዘውትረህ ለረጅም ጊዜ የምትጠቀም ከሆነ

● ቀደም ሲል በዓይንህ ላይ ጉዳት ደርሶብህ ከነበረ

● ዕድሜህ ከ45 ዓመት በላይ ከሆነ

[ሥዕል]

አዘውትሮ መመርመር በማየት ችሎታ ላይ ከባድ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል ሊረዳ ይችላል

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ/ሥዕሎች]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ክፍት ማዕዘን ግላኮማ

ኮርኒያ

አይሪስ

ሌንስ

ሬቲና

ኦፕቲክ ዲስክ ወይም ብርሃን የማያስተላልፍ ሥፍራ የሚገኘው የነርቭ ክሮች ኦፕቲክ ነርቭን ለመፍጠር በሚገናኙበት ቦታ ላይ ነው

ኦፕቲክ ነርቭ ለአንጎል ምስል ያቀብላል

ሲሊያሪ ቦዲ ፈሳሹ የሚዘጋጅበት ቦታ ነው

1 ኤክዊየስ ሂዩመር ሌንስን፣ አይሪስንና የኮርኒያን የውስጠኛ ክፍል የሚመግብ የጠራ ፈሳሽ ነው። ይህ ፈሳሽ የዓይንን የውጭ ክፍል ከሚያጥበው ከእንባ የተለየ ነው

2 ትራቤኩላር ሜሽዎርክ ፈሳሹን ያስወጣል

3 ትራቤኩላር ሜሽዎርክ ከተዘጋ ወይም ከጠበበ በዓይናችን ውስጥ ያለው ግፊት ይጨምራል

4 በዓይን ውስጥ ያለው ግፊት ከጨመረ ከዓይን በስተጀርባ የሚገኙት በቀላሉ የሚበሳሰኩ የነርቭ ክሮች ጉዳት ይደርስባቸዋል፤ ይህም ግላኮማ ወይም የዓይን መድከም ያስከትላል

[በገጽ 27 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ኦፕቲክ ዲስክ

የምታየው ምስል

ትክክለኛ እይታ

መጀመሪያ ደረጃ ላይ ያለ ግላኮማ

የተባባሰ ግላኮማ

[ምንጭ]

የኦፕቲክ ዲስክ ፎቶዎች:- Courtesy Atlas of Ophthalmology