ጥሩ አባት መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?
ጥሩ አባት መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?
እየተበላሸ ስለመጣው የቤተሰብ ሕይወት የሚገልጽ ኢኮኖሚስት መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ ሐተታውን ሲጀምር “ልጆች መውለድ ቀላል ነገር ሲሆን ጥሩ አባት መሆን ግን ቀላል ነገር አይደለም” የሚል ትኩረት የሚስብ አነጋገር ጠቅሷል።
በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ብዙ ከባድ ሥራዎች ይኑሩ እንጂ ይበልጥ ከባድና እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት ሥራዎች አንዱ ጥሩ አባት መሆን ነው። እያንዳንዱ አባት የቤተሰቡ ደኅንነትና ደስታ በእርሱ ላይ የተመካ በመሆኑ ጥሩ አባት ለመሆን መጣር ይኖርበታል።
ቀላል ያልሆነው ለምንድን ነው?
በአጭር አነጋገር ጥሩ አባት መሆን ቀላል ያልሆነው ወላጆችም ሆኑ ልጆች ፍጹም ባለመሆናቸው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ሐሳቡ ወደ ክፋት ያዘነበለ” እንደሆነ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 8:21) በዚህም የተነሳ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ “ገና እናቴም ስትፀንሰኝ ኀጢአተኛ ነኝ” ብሏል። (መዝሙር 51:5፤ ሮሜ 5:12) በወረስነው ኃጢአት ምክንያት መጥፎ ወደ ማድረግ የምናዘነብል መሆናችን ጥሩ አባት መሆንን አስቸጋሪ ከሚያደርጉት እንቅፋቶች አንዱ ብቻ ነው።
ይህ ዓለም ወይም ሥርዓት ደግሞ ሌላው ትልቅ እንቅፋት ነው። ለምን? መጽሐፍ ቅዱስ “መላው ዓለምም በክፉው ሥር እንደ ሆነ እናውቃለን” ይላል። ይህ ክፉ “ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው” እንደሆነ ተገልጿል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣንን “የዚህ ዓለም አምላክ” ሲል ይጠራዋል። ኢየሱስ ተከታዮቹን ልክ እርሱ እንዳደረገው ‘ከዚህ ዓለም እንዳይሆኑ’ መናገሩ ሊያስደንቅ አይገባም።—1 ዮሐንስ 5:19፤ ራእይ 12:9፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4፤ ዮሐንስ 17:16
ጥሩ አባት ለመሆን ቁልፉ አለፍጽምና መውረሳችንን፣ ሰይጣን ዲያብሎስ መኖሩንና ይህ ዓለም በእርሱ የሚተዳደር መሆኑን ሁልጊዜ መገንዘብ ነው። እነዚህ እንቅፋቶች እንዲሁ ሐሳብ የወለዳቸው ሳይሆኑ በእርግጥ ያሉ ነገሮች ናቸው። ይሁን እንጂ አንድ ሰው እነዚህን እንቅፋቶች አልፎ ጥሩ አባት ለመሆን የሚያስችለውን እውቀት ከየት ሊያገኝ ይችላል?
መለኮታዊ ምሳሌዎች
አንድ አባት እነዚህን እንቅፋቶች ለመወጣት የሚያስችለውን እርዳታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጣም ግሩም የሆኑ ምሳሌዎች እናገኛለን። ኢየሱስ ተከታዮቹ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ” ብለው እንዲጸልዩ ባስተማረበት ጊዜ ከሁሉ የሚበልጠው ምሳሌ ማን እንደሆነ አመልክቷል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰማዩ አባታችን ባሕርይ ሲገልጽ በቀላል አነጋገር ማቴዎስ 6:9, 10፤ 1 ዮሐንስ 4:8፤ ኤፌሶን 5:1, 2
“እግዚአብሔር ፍቅር ነው” ይላል። ታዲያ ይህ የፍቅር ምሳሌ አንድን ሰብዓዊ አባት ምን እንዲያደርግ ሊያነሳሳው ይገባል? ሐዋርያው ጳውሎስ “እግዚአብሔርን ምሰሉ” እንዲሁም “በፍቅር ተመላለሱ” ሲል ይመክራል።—አባት ከሆንክ አንድ ጊዜ አምላክ ልጁን ኢየሱስን አስመልክቶ ከተናገረው ነገር ምን ልትማር እንደምትችል ተመልከት። ማቴዎስ 3:17 ኢየሱስ በውኃ በተጠመቀበት ጊዜ የአምላክ ድምፅ ከሰማይ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ሲል እንደተሰማ ይገልጻል። ከዚህ ምን ልንማር እንችላለን?
በመጀመሪያ አንድ አባት በኩራት ‘ይህ ልጄ ነው ’ ወይም ‘ይህች ልጄ ነች ’ ሲል ልጁ ምን እንደሚሰማው ወይም እንደሚሰማት አስብ። ልጆች የወላጆቻቸውን ትኩረት፣ በተለይም አድናቆታቸውን ሲያገኙ ጥሩ ሆነው ያድጋሉ። የበለጠ እውቅናና አድናቆት ለማግኘት የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ይገፋፋሉ።
ሁለተኛ አምላክ “የምወደው” በማለት ስለ ኢየሱስ ምን እንደሚሰማው ገልጿል። ኢየሱስ ይህን የአባቱን የፍቅር መግለጫ ሲሰማ ልቡ በደስታ ሳይሞላ አልቀረም። ያንተም ልጆች በምትናገረው ነገርም ሆነ አብረሃቸው ጊዜ በማሳለፍ፣ ትኩረት በመስጠትና አሳቢነት በማሳየት እንደምትወዳቸው ስትገልጽላቸው ይበረታታሉ።
ሦስተኛ አምላክ ልጁን “በአንተ ደስ ይለኛል” ብሎታል። (ማርቆስ 1:11) ይህም አንድ አባት ለልጆቹ ሊያደርግላቸው ከሚገቡ አስፈላጊ ነገሮች አንዱ ነው። በልጆቹ ደስ እንደተሰኘ መግለጽ አለበት። እርግጥ ነው፣ ልጅ ደጋግሞ ጥፋት መሥራቱ አይቀርም። ሁላችንም እናጠፋለን። ይሁን እንጂ በአባትነትህ ልጆችህ በሚያደርጉት ወይም በሚናገሩት ጥሩ ነገር ደስ እንደተሰኘህ እንድትገልጽ የሚያስችሉህን አጋጣሚዎች ትፈልጋለህ?
ኢየሱስም ከአባቱ ጥሩ አድርጎ ተምሯል። ምድር ሳለ አባቱ ለምድራዊ ልጆቹ ያለውን ስሜት በቃልም ሆነ በተግባር አሳይቷል። (ዮሐንስ 14:9) ኢየሱስ ሥራ በበዛበትና በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ይገኝ በነበረበት ጊዜ ከልጆች ጋር ቁጭ ብሎ ተነጋግሯል። ደቀ መዛሙርቱን “ሕፃናት ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸው” ብሏል። (ማርቆስ 10:14) ታዲያ አባቶች የይሖዋ አምላክንና የልጁን ምሳሌ ሙሉ በሙሉ ትከተላላችሁ?
ጥሩ ምሳሌ መሆን እጅግ አስፈላጊ ነው
ለልጆቻችሁ ጥሩ ምሳሌ መሆን በጣም አስፈላጊ ነው። እናንተ ራሳችሁ የአምላክን ተግሣጽ የማትቀበሉና ሕይወታችሁም በእርሱ እንዲመራ የማታደርጉ ከሆነ ልጆቻችሁን “በጌታ ምክርና ተግሣጽ” ለማሳደግ የምታደርጉት ጥረት ምንም ውጤት አይኖረውም። (ኤፌሶን 6:4) ይሁን እንጂ ለልጆቻችሁ ተገቢውን እንክብካቤ እንድታደርጉ አምላክ የሰጠውን ትእዛዝ ለመፈጸም በምታደርጉት ጥረት የሚያጋጥማችሁን እንቅፋት በእርሱ እርዳታ መወጣት ትችላላችሁ።
በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ይኖር የነበረውንና የይሖዋ ምሥክር የሆነውን የቪክቶር ጉትሽሚትን ምሳሌ እንመልከት። ስለ እምነቱ ለሌሎች ሰዎች በመናገሩ በጥቅምት ወር 1957 የአሥር ዓመት እስራት ተፈረደበት። ሁለት
ትናንሽ ሴት ልጆቹንና ባለቤቱን ፖሊናን ለብቻቸው ትቶ ታሠረ። በእስር ቤት እንዳለ ለቤተሰቦቹ ደብዳቤ መጻፍ ቢፈቀድለትም ስለ አምላክም ሆነ ስለ ማንኛውም ሃይማኖታዊ ጉዳይ እንዳያነሳ ተከለከለ። እንዲህ ባለው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እያለም እንኳን ቪክቶር ጥሩ አባት ለመሆን ቆርጦ ተነሳ። ልጆቹን ስለ አምላክ ማስተማር በጣም አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝቧል። ታዲያ ምን አደረገ?ቪክቶር ታሪኩን ሲናገር “ያንግ ናቹራሊስት እና ኔቸር ከተባሉት የሶቪየት መጽሔቶች ጥሩ ማስተማሪያ አገኘሁ። በካርድ ላይ የእንስሳትና የሰዎች ሥዕል ከሳልኩ በኋላ ስለ ተፈጥሮ የሚገልጽ ታሪክ ወይም ተሞክሮ ጨምሬ እልክላቸው ነበር” ይላል።
“ካርዶቹ እንደደረሱን ወዲያው ሥዕሎቹን ከመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳዮች ጋር እናዛምዳቸዋለን። ለምሳሌ ስለ ተፈጥሮ ውበት፣ ስለ ጫካዎች ወይም ስለ ወንዞች የሚያሳይ ሥዕል ሲደርሰን አምላክ ምድርን ገነት እንደሚያደርግ ስለሰጠን ተስፋ የሚናገረውን ኢሳይያስ 65ን አነብላቸዋለሁ” ትላለች ፖሊና።
የቪክቶር ልጅ የሆነችው ዩልያ “ከዚያ በኋላ እማማ አብራን ትጸልይና እናለቅሳለን። እነዚህ ሥዕሎች ለመልካም አስተዳደጋችን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል” ብላለች። በዚህ ምክንያት “ልጆቹ ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ለአምላክ ጠንካራ ፍቅር አደረባቸው” ትላለች ፖሊና። ባሁኑ ጊዜ ቤተሰቡ እንዴት ባለ ሁኔታ ላይ ይገኛል?
ቪክቶር እንዲህ ይላል:- “አሁን ልጆቼ ሁለቱም ክርስቲያን ሽማግሌዎችን አግብተዋል። ሁለቱም በመንፈሳዊ ጠንካራ የሆነ ቤተሰብ አላቸው። ልጆቻቸውም ይሖዋን በታማኝነት ያገለግላሉ።”
ጥሩ ምሳሌ መሆን ጥበበኛ መሆን ብቻ ሳይሆን ትልቅ ጥረትም ይጠይቃል። አባታቸው ምን ያህል ጥረት እያደረገ እንዳለ ሲመለከቱ የልጆች ልብ ይነካል። ለበርካታ ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆየ አንድ ልጅ ለአባቱ ያለውን አድናቆት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “አባዬ አንዳንድ ጊዜ በጣም ደክሞት ከሥራ ቢመጣም እንቅልፍ እያዳፋው እንኳ ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችንን ይመራልናል። ይህም የጥናቱን አስፈላጊነት እንድንገነዘብ አስችሎናል።”
በቃልም ሆነ በድርጊት መልካም አርዓያ መሆን ጥሩ አባት ለመሆን በጣም አስፈላጊ ነገር እንደሆነ ግልጽ ነው። አንተም “ልጅን የሚሄድበትን መንገድ አስተምረው፤ በሚሸመግልበት ጊዜ ከዚያ ፈቀቅ አይልም” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እውነት መሆኑን ለማየት ከፈለግህ እንዲሁ ማድረግ ያስፈልግሃል።—ምሳሌ 22:6
ስለዚህ መናገር ብቻውን በቂ እንደማይሆን አስታውስ። በጣም አስፈላጊ የሆነው የምታሳየው ምሳሌነት ነው። ሕፃናትን በማስተማር ሥራ የሰለጠኑ አንድ ካናዳዊ ባለሙያ “ልጆቻችን [እኛ የምንፈልገውን] ጠባይ እንዲያሳዩ ለማድረግ ከሁሉ የሚሻለው ዘዴ ተፈላጊውን ባሕርይ እኛ ራሳችን ማሳየት ነው” ሲሉ ጽፈዋል። በእርግጥም ልጆቻችሁ ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ትልቅ ግምት እንዲሰጡ ከፈለጋችሁ እናንተ ራሳችሁ እንዲህ ማድረጋችሁ አስፈላጊ ነው።
በቂ ጊዜ መድቡላቸው
ልጆች መልካም ምሳሌነታችሁን ማየት አለባቸው። ይህን እንዲያዩ ደግሞ ቅንጥብጣቢ ጊዜ ሳይሆን ረዘም ያለና በቂ ጊዜ ልትሰጧቸው ይገባል። “ዘመኑን በሚገባ ኤፌሶን 5:15, 16) እንደ እውነቱ ከሆነ ከልጆቻችሁ የሚበልጥባችሁ ምን ነገር ይኖራል? ቴሌቪዥን፣ መዝናኛ፣ ቆንጆ ቤት ወይስ ሥራ?
ዋጁ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በመከተል ከልጆቻችሁ ጋር ለመሆን ስትሉ የግድ አስፈላጊ ያልሆኑ ጉዳዮችን ተዉ። (አባቶች ልጆቻቸው ገና በለጋ ዕድሜ ላይ እያሉ አብረዋቸው በቂ ጊዜ የማያሳልፉ ከሆነ የኋላ ኋላ ለችግር መዳረጋቸው አይቀርም። በሥነ ምግባር ብልግና የተዘፈቁ ወይም መንፈሳዊነት የጎደለው አኗኗር መኖር የጀመሩ ልጆች ያሏቸው አባቶች በጣም ይቆጫቸዋል። ልጆቻቸው አባታቸው ከአጠገባቸው እንዳይለይና አስፈላጊውን እንክብካቤ እንዲያደርግላቸው ይፈልጉ በነበረበት ወቅት አብረዋቸው ሳይሆኑ በመቅረታቸው በጣም ይጸጸታሉ።
በሕይወት ውስጥ ስለምታደርጓቸው ምርጫዎች በጥንቃቄ ማሰብ የሚኖርባችሁ ልጆቻችሁ ገና ትናንሾች ሳሉ እንደሆነ አትዘንጉ። መጽሐፍ ቅዱስ ልጆች ለእናንተ በአደራ የተሰጡ “የእግዚአብሔር ስጦታ” እንደሆኑ ይናገራል። (መዝሙር 127:3) ስለዚህ ስለ ልጆቻችሁ በአምላክ ፊት ተጠያቂዎች እንደሆናችሁ አትርሱ።
እርዳታ ማግኘት ይቻላል
አንድ ጥሩ አባት ልጆቹን የሚጠቅም እርዳታ ለማግኘት ይጓጓል። ማኑሄ ሚስቱ ልጅ እንደምትወልድ አንድ መልአክ ከነገረው በኋላ “የሚወለደውን ልጅ እንዴት አድርገን ማሳደግ [እ]ንዳለብን እንዲያስተምረን ያ ወደ እኛ የላክኸው የእግዚአብሔር ሰው እንደ ገና እንዲመጣ ታደርግ ዘንድ እለምንሃለሁ” ሲል ወደ አምላክ ጸልዮአል። (መሳፍንት 13:8, 9) ማኑሄ እንደ ዛሬዎቹ ወላጆች ያስፈልገው የነበረው እርዳታ ምን ዓይነት ነበር? እስቲ እንመልከት።
በደቡብ አፍሪካ በኬፕ ታውን ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ብሬንት ቡርጎይን “አንድ ሰው ለልጁ ሊሰጥ ከሚችላቸው ታላላቅ ሥጦታዎች አንዱ በሕይወቱ የሚመራባቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ማስተማር ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ልጆች እንደነዚህ ያሉትን መሠረታዊ ሥርዓቶች መማራቸው አስፈላጊ መሆኑን ዴይሊ ዮሚዩሪ በተባለው የጃፓን ጋዜጣ ላይ ከወጣው ሪፖርት መገንዘብ ይቻላል። ይህ ሪፖርት “ከጃፓናውያን ልጆች መካከል 71 በመቶ የሚሆኑት ውሸት መጥፎ መሆኑን አባቶቻቸው ነግረዋቸው እንደማያውቁ [አንድ] ጥናት አመልክቷል” ይላል። ይህ የሚያሳዝን አይደለም?
ታዲያ ለሕይወት መመሪያ የሚሆኑ አስተማማኝ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሊሰጠን የሚችለው ማነው? ልክ እንደ ማኑሄ እንዲህ ያለውን መመሪያ ማግኘት የምንችለው ከአምላክ ነው። አምላክ እርዳታ እንድናገኝ ሲል ውድ ልጁን ኢየሱስን አስተማሪ አድርጎ ልኮልናል። ባሁኑ ጊዜ፣ ኢየሱስ ባስተማራቸው ትምህርቶች ላይ የሚያተኩረው ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ የተባለው (እንግሊዝኛ) መጽሐፍ በብዙ ቋንቋዎች የተዘጋጀ በመሆኑ ልጆቻችሁን ለማስተማር ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ።
ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ የተባለው መጽሐፍ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረቱ የሕይወት መመሪያዎችን የሚገልጽ ከመሆኑም በላይ በጽሑፍ የሠፈሩትን ሐሳቦች ቀጥተኛ ጥያቄዎች ባሏቸው ከ160 የሚበልጡ ሥዕላዊ መግለጫዎች ግልጽ አድርጎ ያሳያል። ለምሳሌ በዚህ መጽሔት ገጽ 32 ላይ የወጣው ሥዕል “መዋሸት የሌለብን ለምንድን ነው?” በሚለው በ22ኛው ምዕራፍ ውስጥ ይገኛል። ይህ ሥዕል በሚገኝበት ገጽ ላይ የሠፈረው ጽሑፍ “አንድ ልጅ ለአባቱ ኳሱን ወደ ቤት የመታሁት እኔ አይደለሁም ይል ይሆናል። ግን መትቶት ከነበረስ? አልመታሁም ቢል ስህተት ይሆናል?” ይላል።
ከዚህም ሌላ “ታዛዥነት ከጉዳት ይጠብቅሃል፣” “ፈተናዎችን መቋቋም አለብን፣” “ስለ ደግነት የተሰጠ ትምህርት፣” “ሌባ እንዳትሆን ተጠንቀቅ፣” “ሁሉም ዓይነት ግብዣዎች አምላክን ያስደስታሉ?፣” “አምላክን ማስደሰት የሚቻለው እንዴት ነው?” እንዲሁም “መሥራት የሚኖርብን ለምንድን ነው?” የሚሉትን ጨምሮ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በሚገኙ 48 ምዕራፎች ግሩም ትምህርቶች ተካትተዋል።
የመጽሐፉ መቅድም እንዲህ በማለት ይደመድማል:- “በተለይ ልጆች የጥበብ ሁሉ ምንጭ ወደሆነው ወደ ሰማዩ አባታችን ወደ ይሖዋ አምላክ መመራት ይኖርባቸዋል። ታላቁ አስተማሪ ኢየሱስም ሁልጊዜ ያደርግ የነበረው ይህንኑ ነበር። ይህ መጽሐፍ አንተንም ሆነ ቤተሰብህን ሕይወታችሁን ይሖዋን በሚያስደስትና የዘላለም ሕይወት በሚያስገኝ መንገድ እንድትቀርጹ እንደሚረዳችሁ ከልባችን ተስፋ እናደርጋለን።” *
በእርግጥም ጥሩ አባት መሆን ለልጆች ጥሩ ምሳሌ መተውን፣ አብሮ ብዙ ጊዜ ማሳለፍንና አምላክ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከገለጻቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ መርዳትን እንደሚያካትት ግልጽ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.35 የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰቦችን ለመርዳት ካዘጋጅዋቸው መጻሕፍት መካከል የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ፣ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች እንዲሁም ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባሉት መጻሕፍት ይገኛሉ።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቪክቶር ጉትሽሚት በእስር ቤት የነበረ ቢሆንም ጥሩ አባት መሆን ችሏል
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ቪክቶር በእምነቱ ምክንያት ታሥሮ በነበረበት ወቅት ልጆቹን ለማስተማር እነዚህን ሥዕሎች ስሏል
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቪክቶር ልጆች በ1965
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አባቶች ልጆቻቸውን በማስተማር ረገድ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይገባቸዋል