በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለአረጋውያን ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

ለአረጋውያን ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ለአረጋውያን ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

በ2003 የበጋ ወቅት በተከሰተ ከ60 ዓመት ወዲህ በመላው አውሮፓ ታይቶ በማይታወቅ ኃይለኛ ሙቀት ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞቱ። ከሟቾቹ ውስጥ አብዛኞቹ አረጋውያን ነበሩ። አንዳንዶቹ አረጋውያን፣ ዘመዶቻቸው ለዕረፍት ሲሄዱ ቤት ውስጥ ብቻቸውን የቀሩ ነበሩ። ሌሎቹ ደግሞ የሆስፒታልና የአረጋውያን እንክብካቤ መስጫ ተቋማት ሠራተኞች በሥራ መብዛት የተነሳ ችላ ያሏቸው ወይም የረሷቸው እንደሆኑ ተዘግቧል። ለ ፓሪዚየን የተሰኘው ጋዜጣ በፓሪስ ብቻ 450 አስከሬኖች ፈላጊ እንዳልነበራቸው ዘግቧል። ጋዜጣው ባዶ ቤት ውስጥ ሞተው ስለተገኙ ማንነታቸው እንኳን ስላልታወቀ ሰዎች ሲናገር “አባቶቻችንን፣ እናቶቻችንንና አያቶቻችንን እስከመርሳት የደረስነው ምን ሆነን ነው?” በማለት ጥያቄ አቅርቧል።

ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆናቸው ሰዎች ቁጥር ከዚህ በፊት ታይቶ በማያውቅ መጠን በየወሩ በ795,000 እየጨመረ ባለበት በዚህ ዓለም የአረጋውያንን ፍላጎት ማሟላት በዛሬው ጊዜ ካሉት አሳሳቢ ጉዳዮች አንዱ ሆኗል። “በመላው ዓለም የአረጋውያን ቁጥር ከዚህ በፊት ታይቶ በማያውቅ ፍጥነት እየጨመረ ስለመጣ የዕድሜ መግፋት ስለሚያመጣቸው ተፈታታኝ ችግሮችና መብቶች አገሮች እንዴት ምላሽ እየሰጡ እንዳሉ ቅርብ ክትትል ማድረግ ያስፈልገናል” በማለት ናንሲ ጎርደን የተባሉት በዩናይትድ ስቴትስ የምጣኔ ሕዝብ ፕሮግራሞች ኤጀንሲ ረዳት ዳይሬክተር ተናግረዋል።

ፈጣሪያችንም ለአረጋውያን ትኩረት ይሰጣል። እንዲያውም ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ ለአረጋውያን ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን እንደሚገባ መመሪያ ይሰጠናል።

አረጋውያንን ማክበር

ለሙሴ የተሰጠው የአምላክ ሕግ አረጋውያን መከበር እንዳለባቸው ይገልጻል። ሕጉ “ዕድሜው ለገፋ ተነሥለት፤ ሽማግሌውን አክብር” በማለት ይናገራል። (ዘሌዋውያን 19:32) ታዛዥ የሆኑ የአምላክ አገልጋዮች (1) በዕድሜ ለገፋ ሰው አክብሮት ለማሳየት እና (2) አምላኪዎቹ ለአምላክ አክብሮታዊ ፍርሃት ያላቸው መሆኑን ለመግለጽ በአረጋዊው ፊት ‘እንዲነሡ’ ይጠበቅባቸው ነበር። በመሆኑም በዕድሜ የገፉ ሰዎች ክብር ሊሰጣቸው የሚገባ ከመሆኑም ሌላ በጣም አስፈላጊ እንደሆኑ ተደርገው መታየት ነበረባቸው።—ምሳሌ 16:31፤ 23:22

በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር ባይሆኑም ሕጉ የተመሠረተባቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች የይሖዋን አስተሳሰብና የላቀ ሥፍራ የሚሰጣቸውን ነገሮች ስለሚያሳዩ ይሖዋ ለአረጋውያን ከፍተኛ ግምት እንደሚሰጥ በግልጽ መረዳት ይቻላል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የክርስቲያን ጉባኤ አባላት እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሚገባ ተረድተው ነበር። ለዚህም በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኝ አንድ ዘገባ ማስረጃ ይሆናል። በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም ከነበሩት ክርስቲያኖች መካከል አንዳንድ ችግረኛ መበለቶች ይገኙ ነበር። ከእነርሱም መካከል በርካታ አረጋውያን እንደነበሩ አያጠራጥርም። ሐዋርያት ለአረጋውያን እንክብካቤ የመስጠቱን ጉዳይ የጉባኤው “ኀላፊነት” እንደሆነ አድርገው ስለተመለከቱት እነዚህ ሴቶች ዕለታዊ ምግብ በአግባቡ እንዲያገኙ ለማድረግ ሲሉ ሰባት “የተመሰከረላቸውን” ሰዎች ሾሙ።—የሐዋርያት ሥራ 6:1-7

“ዕድሜው ለገፋ ተነሥለት” የሚለው መሠረታዊ ሥርዓት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም እንደሚሠራ ሐዋርያው ጳውሎስ ገልጿል። ለወጣቱ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች ለጢሞቴዎስ “አረጋዊውን ሰው እንደ አባትህ ቈጥረህ ምከረው እንጂ በኀይለ ቃል አትናገረው። . . . አሮጊቶችን እንደ እናቶች” በማለት ነግሮታል። (1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2) ወጣቱ ጢሞቴዎስ በአረጋውያን ክርስቲያኖች ላይ የተወሰነ ሥልጣን ቢኖረውም በዕድሜ የገፋን ሰው እንዳያንኳስስ ተነግሮታል። ከዚህ ይልቅ እሱን እንደ አባት በአክብሮት መለመን ነበረበት። በጉባኤው ውስጥ ለነበሩ በዕድሜ የገፉ ሴቶችም ተመሳሳይ አክብሮት እንዲያሳይ ተመክሯል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ይህን ምክር ሲሰጠው እግረ መንገዱን ሁሉም የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ‘በዕድሜ ለገፋ እንዲነሱ’ መምከሩ ነበር።

እርግጥ ነው፣ አምላክን የሚታዘዙ ሰዎች በዕድሜ የገፉትን በክብር ስለመያዝ ሕግ እንዲወጣላቸው አይፈልጉም። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰውን የዮሴፍን ታሪክ ተመልከቱ። ዮሴፍ 130 ዓመት የሆነውን አረጋዊ አባቱን በዘመኑ ብዙ አገሮችን አጥቅቶ ከነበረው ረሃብ ለማዳን ሲል እሱን ወደ ግብፅ ለማስመጣት አቅሙ የሚፈቅድለትን ሁሉ አድርጓል። ከሁለት አሥርተ ዓመታት በላይ የተለየውን አባቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያየው “ዐንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ለረጅም ጊዜ አለቀሰ።” (ዘፍጥረት 46:29) አረጋውያንን በርኅራኄና በጥልቅ አክብሮት ስለመያዝ ለእሥራኤላውያን ሕግ ከመሰጠቱ ከረዥም ጊዜ በፊት ዮሴፍ ለአባቱ እንዲህ ያለ ክብር በመስጠት የአምላክን አመለካከት አንጸባርቋል።

ኢየሱስም ምድር ላይ ባገለገለበት ወቅት ለአረጋውያን አሳቢነት አሳይቷል። ለሃይማኖታዊ ወጋቸው ሲሉ ያረጁ ወላጆቻቸውን ችላ ቢሉ ተጠያቂ እንደማይሆኑ የተሰማቸውን የሃይማኖት መሪዎች በጥብቅ አውግዟል። (ማቴዎስ 15:3-9) በተጨማሪም ኢየሱስ ለእናቱ ፍቅራዊ አሳቢነት አሳይቷል። በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ በከባድ ሥቃይ ላይ በነበረበት ወቅት በዕድሜ የገፋችው እናቱ በሚወደው ሐዋርያ በዮሐንስ አማካኝነት እንክብካቤ እንድታገኝ ሁኔታዎችን አመቻችቷል።—ዮሐንስ 19:26, 27

አምላክ ታማኞቹን ችላ አይልም

መዝሙራዊው “በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፤ ጉልበቴም ባለቀበት ጊዜ አትተወኝ” በማለት ጸልዮአል። (መዝሙር 71:9) አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹ በዕድሜ መግፋት ምክንያት ዋጋ እንደሌላቸው ቢሰማቸውም እንኳን እሱ ግን ‘አይጥላቸውም።’ መዝሙራዊው ይሖዋ እንደጣለው ሆኖ አልተሰማውም፤ ከዚህ ይልቅ እያረጀ በሄደ መጠን በፈጣሪው ላይ መታመን እንደሚያስፈልገው ተገንዝቧል። ይሖዋ በእሱ ለሚታመን ሰው በዕድሜ ዘመኑ በሙሉ ድጋፍ በመስጠት ወሮታ ይከፍላል። (መዝሙር 18:25) ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለው ድጋፍ የሚመጣው በመሰል ክርስቲያኖች አማካኝነት ነው።

እስካሁን እንደተመለከትነው አምላክን ማክበር የሚፈልጉ ሁሉ አረጋውያንንም ማክበር እንዳለባቸው ግልጽ ነው። በእርግጥም አረጋውያን በፈጣሪያችን ዓይን ውድ ናቸው። እኛም በአምሳሉ የተፈጠርን እንደመሆናችን መጠን ምንጊዜም አምላክ ‘ለሽበታሙ’ ያለውን አመለካከት የምናንጸባርቅ እንሁን።—መዝሙር 71:18

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያኖች አረጋውያንን በክብር ይይዛሉ